Ethiopian Ministry of Peace

የኢፌዴሪ ሰላም ሚኒስቴር

ሰኞ ጥቅምት 24 ቀን 2012 ዓ.ም. (November 4, 2019)

ሰሞኑን በአገራችን ግጭቶች መከሰታችው ይታወቃል። በዚህ ክስተት የሰላም ሚኒስቴር የበላይ አመራሮችና ሠራተኞች ሕይወታቸውን ላጡ ዜጎቻችን የተሰማንን ጥልቅ ኀዘን እየገለጽን፤ ለቤተሰቦቻቸው መፅናናትን እንመኛለን።

የሰላም እሴቶቻችንን ለማጎልበት ከሚሠሩ ሥራዎች ጎን ለጎን ሚኒስቴር መሥሪያ ቤታችን ከፌዴራል የፀጥታና ደኅንነት እንዲሁም በየደረጃው ከሚገኙ የፀጥታ መዋቅሮች ጋር ቅንጅት በመፍጠር በግጭቱ ተሳትፎ የነበራቸውን ተጠርጣሪዎች በሕግ ቁጥጥር ሥር የማዋል ሥራ እየተሠራ ይገኛል። ከዚህ በተጨማሪም ከሃይማኖት አባቶች፣ ከአባገዳዎች፣ ከአገር ሽማግሌዎች፣ ከወጣቶች፣ ከሴቶችና ችግሩ ከተፈጠረባቸው አካባቢ ያሉ የአመራር አካላት ጋር ግንኙነት በመፍጠር ግጭቱ የብሔርና የሃይማኖት መልክ ይዞ እንዳይስፋፋ ለማድረግ ተችሏል።

ከብሔራዊ አደጋ ሥጋትና ሥራ አመራር ኮሚሽንና ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የተውጣጡ ግብረኃይሎችን ግጭቱ በተከሰተባቸው አካባቢዎች በመላክ፤ በአደጋው ተጎጂ ለኾኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች 878 ኩንታል የምግብ አቅርቦት፣ 712 ካርቶን ብስኩት እንዲሁም ምግብ ነክ ያልኾኑ 10280 የቤት ቁሳቁሶችን ተደራሽ ማድረግ ተችሏል። ግጭቱ እንዳይባባስና የተጀመረው ሥራ ውጤታማ እንዲኾን የድርሻቸውን የተወጡና አዎንታዊ አስተዋጽኦ ያበረከቱ የሰላም ባለቤት የኾኑትን ዜጎቻችንን ልናመሰግን እንወዳለን።

ስለሰላም መሥራትና በሕዝባችን መካከል መተማመን እንዲኖር መጣር ተገቢና ያሉንን የሐሳብ ልዩነቶች ወይም አለመግባባቶች በጠረጴዛ ዙሪያና በሕግ ማዕቀፍ ሥር መፍታት አስፈላጊ ነው። በመኾኑም በአገራችን የተካሔደው ለውጥ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታው የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ በውል በመገንዘብ በማጥፋት ማትረፍ ስለማይቻል፤ ሁሉም የአገራችን ሕዝቦች የሰላም ጉዳይ የእኔ ጉዳይ ነው በማለት ለአገሪቱ ሰላም መስፈን የበኩላችሁን አስተዋጽኦ በማበርከት አገራዊ ግዴታችሁን እንድትወጡ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።

የሰላም ባለቤት እርስዎ ነዎት!
የኢፌዴሪ ሰላም ሚኒስቴር

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ