የዓድዋ ድልና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪካዊ ድርሻና ውለታ

ፍቅር ለይኩን ከደቡብ አፍሪካ

የዓድዋ ድልን በማስመልከት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ን በስንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ በማኅበረ ቅዱሳን የምርምርና የጥናት ማእከል ድሉን አስመልክቶ ቤተ ክርስቲያኒቱ የነበራትን ሚና ለማዘከር በአዲስ አበባ በብሔራዊ ሙዚየም የተደረገውን ውይይት ዜና በደጀ ሰላም ማንበቤ በውስጤ አንድ ስሜት አጫረብኝ፤ እናም ስለ ድሉና ቤተ ክርስቲያናችን ስለነበራት ታላቅ ድርሻና ወለታ ጭምር ጥቂት ለመጨመር አስብኩና ብዕሬን አነሳሁ።

 

በዚህ በደቡብ አፍሪካ በዩኒቨርስቲ ቆይታዬ የዓድዋ ድል ለጥቁር ህዝቦች የነጻነት ትግል የነበረውን ፋይዳ በማስመልከት ባለፈው ዓመት አንዲት አጠር ያለች ጥናታዊ ጹሁፍ በዩኒቨርስቲው አቅርቤ ነበር። በዚህ ጹሁፍም በተለይ ለደቡብ አፍሪካ የጸረ ቅኝ ግዛትና የጸረ አፓርታይድ ትግል የዓድዋ ድል፣ የረጅሙ ዘመን የኢትዮጵያ የስልጣኔ የነጻነት ታሪክና የህዝቦቿ አይበገሬነት በአጭሩ ለመዳሰስ በሞከረው ጹሁፌ ለዚህ ነጻነትና ስልጣኔ እንዲሁም የህዝቦች አንድነት ሰፊ ድርሻ የነበራት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንን የተጫወተችወን ሚና በዚህ ጹሁፌ በአጭሩ ለክፍል ጓደኞቼና ለትምህርት ክፍሉ ምሁራን ፕሮፌስሮች ለመግለጽ ሞክሬ ነበር።

 

ከጽሁፌ በኃላ ባደረግነው ውይይት በሙሉ ማለት ይቻላል ደቡብ አፍሪካውያንም ሆኑ ከሌላ ሀገራት የመጡ ተማሪዎች (International Students) ስለ ዓድዋ ድል የሚያውቁትም ሆነ የሰሙትም ነገር እንደሌለ ነው የነገሩኝ፤ ባንጻሩ ስለ ኢትዮጵያ የሚያውቁት ነገር ቢኖር የጦርነትና የረሃብ ምድር ብቻ መሆኗን ሲገልጹልኝ ውስጤን ቁጭትና እልህ እያንገበገበው ስለ ሀገራችን የረጅም ዘመን የስልጣኔና የነጻነት ታሪክ በተመለከተ በተለያየ ጊዜ ያደረጉላቸው ገለጻ ብዙዎችን የክፍል ጓደኞቸን ቢያንስ ለሀገራችን ያላቸውን ምስል በመጠኑም ቢሆን እንዲያስተካክሉ እንደረዳቸው ተገንዝቤያለሁ።

 

በተለይም ደግሞ እጅግ ተወዳጅ በሆነውና ተደናቂነትን ባተረፈው የታላቁን የነጻነት አርበኛ የኔልሰን ማንዴላን የ 27 ዓመታት መራር ግን የነጻነትን ጣፍጭ ፍሬ ለማጣጣም የበቁበትን የራሳቸውንና የህዝባቸውን የነጻነት ተጋድሎ በሚተርከው በራሳቸው እጅ በተጻፈው Long Walk to Freedom በተባለው መጽሃፋቸው የሀገራችንን የኢትዮጵያ አኩሪ ስም ደጋግሞ መንሳት ብቻ ሳይሆን ለጥቁር ህዝብ የአይበገሬነትና የነጻነት ፍልሚያ የኢትዮጵያ የረጅም ዘመን የነጻነት ተጋድሎ ታሪክ ለርጅሙ የነጻነት ተጋድሎቸው የወኔ ስንቅ ሆኗቸው እንደነበረ በመጽሃፋቸው የሰጡት ምስክርነት ብዙዎች ደቡብ አፍሪካውያን ተማሪዎችንና ከሌላ ዓለም ጭምር የመጡትን ተማሪዎች ስለ ኢትዮጵያችንና ስለ ታልቁ የዓድዋ ድል በክፍላችን ውስጥ በብዙ እንድንወያይ ያደረገን ነበር፤ በተለይም ደግሞ የአፍሪካንና የመላውን ጥቁር ህዝቦች የነጻነትና የፖለቲካ ትግል ጥሎ ያለፈውን ድማቅ አሻራና ቅርስ በምንነጋገርበት የትምህርት ክፈለ ጊዜ የሀገራችን ስም ደግሞ ደጋግሞ በትምህርት ክፍሉ ፕሮፌስር ይነሳ ስለነበር ኢትዮጵያንና የዓድዋ ድልን አስመልክቶ ለምናደርገው ውይይት ጥሩ መንሻ ሆኖኝ ነበር።

 

ታላቁ የነጻነት አርበኛ ኔልስን ማንዴላ በዚሁ በራሳቸው በተጻፈ የሕይወት ታሪካቸው መጽሃፍ ስለ ኢትዮጵያ ያላቸውን ክብርና ኩራት እንዲህ በማለት ነው የገለጹት፦

“Ethiopia always has a special place in my imagination and the prospect of visiting Ethiopia attracted me more strongly than a trip to France, England and America combined. I felt I would be visiting my own genesis, unearthing the roots of what made me an African.”1

 

ዛሬ ምንም እንኳ ታሪክን በሚገባ ባልተረዱና ባልመረመሩ ሰዎች ዘንድ ስለ ኢትዮጵውያንና ስለ ኢትዮጵያ በኅሊናቸው ሁልጊዜም የሚመጣው ምስል የረሃብና የጦርነት ቢሆንም የሀገራችንን የረጅም ዘመን የስልጣኔና የነጻነት ተጋድሎ በሚያውቁ ሰዎች መካከል ኢትዮጵያዊነት ታላቅ ክብር ያለው የነጻነትና የስልጣኔ ምልክት ነው። ይህን እውነታ በተለያዩ አጋጣሚዎች ካገኘኃቸው የውጭ ሀገር ሰዎች ልረዳ ችያለሁ፤ በተቃራኒው ግን አሁን አሁን እያስፈራኝ ያለሁ ታሪኩንና ማንነቱን የጣለ፣ ለሀገሩ ታሪክና ለአባቶቹ የነጻነት ተጋድሎ ቁብ የማይሰጥ "የራሱን አያውቅ የሰው ናፋቂ" ትውልድ እየተፈጠረ መምጣቱ የትውልዳችን ሌላው እንቆቅልሽ ነው። በዚህ በደጀ ሰላም ጽሁፍ እንደተዘገበው ሌሎችም እንደታዘቡት ከዓድዋ ድል በዓል ይልቅ በብዙ ድምቀትና ሽር ጉድ ተከብሮ ያለፈው የቫሌንታይን ቀን መሆኑ ብዙዎችን አስገርሞ አልፏል።

 

በዚህ ጉዳይ ላይ ብዙ መነጋገርና መወያየት እንዳለብን ይሰማኛል በተጨማሪም ወጣቱ ትውልድ ለሀገሩ ታሪክ፣ ለአባቶቹ አኩሪ የነጻነት ተጋድሎ ሊኖረው የሚገባውን ብሔራዊ ስሜት ጠብቆ እንዲቆይ ለማድረግ ከማኅበራዊና ባህላዊ ተቋማት ባሻገር እንደ ማኅበረ ቅዱሳን ያሉ የወጣት ማኅበራት የሞራል ውድቀትና የማንነት ቀውስ (Identity Crisis) የተጋረጠበትን ትውልድ ካለበት የምእራቡ ዓለም ስነ ልቦናዊ ጫና መላቀቅ እንዲችል ሀገራዊ ብሔራዊ ፋይዳ ባላቸው እንደ ዓድዋና ሌሎች የቤተ ክርስቲያኒቱን ተሳትፎና መንፈሳዊ ተጋድሎ በሚዘክርበት በዓላት ጭምር አሁን እንደተደረገው ይሄን ዓይነት መድረክ በማዘጋጀት ወጣቱን ትውልድ በሀገሩ ታሪክ የሚኮራ፣ ስብዓዊና መንፈሳዊ ህይወቱ የጎለበተ፣ ለሀገሩና ለህዝቡ ፍቅርና ክብር ያለው ትውልድ የመፍጠር ኃላፊነትን ማኅበረ ቅዱሳንና ለሎች ማኅበራትም ጭምር ኃላፊነት መውሰድ ያለባቸው ይመስለኛል። ልክ በጥምቀት በዓል ወጣቱ አካባቢውን በማጽዳት፣ ለእምነታቸው፣ ለመንፈሳዊና ቁሳዊ ባህሎቻቸውና እሴቶቻቸው ያላቸውን አክብሮት የገለጹበት የአንድነት መንፈስ ተጠናክሮ እንዲቀጥል እንደ ማኅበረ ቅዱሳን ያሉ ወጣቱን ሊያሳትፉ የሚችሉ ማኅበራት በተቀናጀ መልኩ ሊንቀሳቀሱ ይገባል።

 

እንዲሁም እነዚህ ወጣቶች በዓሉ በሰላም፣ በደስታና በፍቅር እንዲከበር የተጫወቱት ሚና ለቤተ ክርስቲያኒቱ ብቻ ሳይሆን በበዓሉ ምክንያት የሚመጡ በርካታ የውጭ ሀገራት ቱሪስቶች በዓሉን ያለምንም ስጋት ማክበር መቻላቸው ሀገሪቱ በእነዚህ ቱሪስቶች ምክንያት የምታገኘውን የውጭ ምንዛሪ ጭምር ከጊዜ ወደ ጊዜ ከፍ እንዲያደርግ የሚችል ክብርና ዋጋ ሊሰጠው የሚገባ ሀገራዊ ተሳትፎ ጭምር ነው። ወደ ተነሳሁበት ዋና የጽሁፈ ጭብጥ ለመለስና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤ/ን በዓድዋ ድል የነበራትን ጉልህ ድርሻ በመጠኑም ቢሆን ለመዳሰስ የሞከርኩበትንና በደጀ ሰላም ከተነሱት ሐሳቦች በተጨማሪ ከላይ በጠቀስኩት ጥናታዊ ጽሁፌ ስለ ዓድዋ ድልና የቤተ ክርስቲያናችን ድርሻና ታሪካዊ ውለታ አንዳንድ ሐሳቦች ለመጨመር እፈልጋለሁ።

 

በተለይ ለዓድዋው ጦርነት ድል ከፍተኛውን የጦር አዝማችነት ሃላፊነት የወሰዱት አፄ ምኒልክ ህዝቡን በማደራጀትና አንድ አድርጎ በመምራት በኩል ቤተ ክርስቲያን ልትጫወት የምትችለውን ታላቅ ሚና አስቀድመው የተረዱ ስለነበረ ለዘመቻቸው እቅድም ሆነ በኃላም ለአንጸባራቂ ድላቸው ግንባር ቀደሙን ሚና የተጫወተችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ንን በተጻጻፏቸው ደብዳቤዎችም ሆነ ከውጭ ሀገራት ነገስታትና ባለስልጣናት ጋር ባደረጓቸው የመልእክት ልውውጦች ቤተ ክርስቲያኒቱ የነበራትን ታላቅ ሚና ከመግለጽ ወደ ኃላ አላሉም ነበር። የኢጣልያ ወረራ የማይቀር ብቻ ሳይሆን በፍጥነት እየገፋ መምጣቱን የተገነዘቡት አፄ ምኒልክ ለህዝባቸው ያስተላለፉትን አዋጅ ፕሮፌስር ክንፈ አብርሃም፦ Adowa and Its Inspiration on Decolonisation Pan-Africanism and the Struggle of the Black People በተባለ መጽሃፋቸው እንዲህ ገልጸውታል፦

"When the aims of the Italians became obvious by 1984, a nation-wide revulsion against white men arose. It was said that “one recovers from the bite of a black snake, but never from white snake.” Menelik exploited such primordialism in his mobilization proclamation of 1984, which was also calculated to strengthen the religious solidarity of the Ethiopian Orthodox Church in the face of the Roman Catholicism.”2

 

የዓድዋ ድል የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የመላው ጥቁር ህዝቦች ታሪክ መሆኑ የታወጀው ከድሉ ማግስት በኃላ የሚወጡ ጋዜጦች ሁሉ ለዘመናት የቆየውን የነጭ የበላይነትና የቅኝ አገዛዝ ኢፍትሃዊ የሆነ መብት ትልቅ ጥያቄ ውስጥ ያሰገባ ነበር፤ በአፍሪካ፣ በካረቢያንና በአሜሪካ ያሉ ጥቁር ህዝቦች አንገታቸውን ቀና አድርገው እንዲሄዱ ያስቻለና ለነጻነታቸው እንዲነሱ የማንቂያ ደዎል ነበር የዓድዋ አንጸባራቂ ድል፣ በአሜሪካ የጥቁሮች መብት ትግል ትልቅ ስምና ዝና ያለው ማርከስ ጋርቬይና ተከታዮቹ ዘንድ የዓድዋ ድልና የኢትዮጵያ የረጅም ዘመን ስልጣኔና የነጻነት ተጋድሎ ታሪክ በፈጠረባቸው ስሜት የተነሳ የአፍሪካ ብሔራዊ መዝሙር በሚል በደረሱት ግጥማቸው ውስጥ ኢትዮጵያዊነትና የዓድዋ ድል እንዲህ ተገልጿል፦

"Ethiopia, the tyrant is falling,

Who smote thee upon thy knees?

And the children are lustily calling

From over distant seas.

Jehovah, the Great One has heard us,

Has noted our sighs and our tears,

With His Spirit of Love has stirred us

To be one through the coming years."3

 

የዓድዋን ድል በማስመልከት የጻፉና የዘገቡ ጥቁሮች ብቻ ሳይሆኑ አውሮፓውያን ጭምር ናቸው፤ ከዚህ ድል በኃላም የአውሮፓ ኃያላን ሀገራትም ሆኑ አሜሪካ ለአጼ ምኒልክ የእንኳን ደስ አለዎት መልእክትና የዲፕሎማሲ ግንኙነት ጥያቄ በማቅረብ ሀገራችን በዓለም አቀፍ ደረጃ ሉዓላዊትና ነጻ ሀገር (Sovereign State) መሆኗን መመስከር ችለዋል።

 

የዓድዋ ድል ለብዙ የአፍሪካና የካረቢያን እንዲሁም የአሜሪካ ጥቁር ህዝቦች በጫንቃቸው ላይ የተጫነባቸውን ከባድ የባረነት ቀንበር ለማላቀቅ የወኔ ስንቅ ሆናቸው ትግላቸውን ሲያቀጣጥሉ፤ ለዚህ ድል ግንባ ቀደም ሚና የተጫወተችውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤ/ንን ድርሻ በማሰብ ሳይወዱ በግድ እንዲቀበሉት የተገደዱትን የአውሮፓውያኑን እምነት ጭምር ከነሱ በማስወገድ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ መሆናቸውን ለመግለጽ በአፍሪካና በአሜሪካ ብዙ አብያተ ከርስቲያናት አብሲኒያ ቤ/ን፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤ/ን በሚል ስያሜ ቤተ እምነታቸውን በመሰይም ለኢትዮጵያና ለቤተ ክርስቲያኒቷ ያላቸውን ክብርና አጋረነት ጭምር ገልጸዋል፤ በዚህ በደቡብ አፍሪካ ያሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክሰ እምነት ተከታዮች የኃላ ዘመን የእምነት ነጻነት ተጋድሎ ታሪክ ውሉ የሚመዘዘው ከዚሁ ከዓድዋ አንጸባራቂ ድል ነው። አሜሪካዊው የማኅበረሰብ ሳይንስ ጥናት (Sociology) ፕሮፌስር የሆኑት ዶናልድ ሌቪን ስለ ዓድዋ ድል በጻፉት የጥናት ወረቀታቸው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ከዓድዋ ድል በኃላ በመላው በጥቁር ዓለምና በደቡብ አፍሪካ ከፍ ብላ የታየችበትን የታሪክ እውነት እንዲህ አስቀምጠውታል፤

 

"for a number of colonized African countries, the Ethiopian victory at Adowa symbolized and signalled the possibility of future emancipation. Hence Black South African of the Ethiopian Church came to identify with the Christian Kingdom in the Horn, a connection that leads South African leaders to write to Menelik for help in caring for the Christian communities of Egypt and the Sudan."4

 

በአፓርታይድ የዘረኛ መንግስት ህሊናቸው ክፉኛ የቆሰሉ ደቡብ አፍሪካውያን በተለይም ደግሞ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤ/ን ስር ያሉ የእድሜ ባለጸጎችን ለማነጋገር እንደሞከርኩት ለዘመናት ሲናፍቁት የነበረውን ወደ እናት ቤተ ክርስቲያናቸው ወደ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ን ጋር ግንኙነት ለመፍጠር የከፈሉት ዋጋ እጅግ ከባድ ነው፤ በዚህ ትግል ውስጥ ብዙ ደቡብ አፍሪካውያን አባቶችና እናቶች የህይወት መስዋእትነት ጭምር ከፍለዋል፤ የእነዚህን አባቶች መራር ትግልና መስዋእትነት በዚህ አጭር ጹሁፍ ለመግለጽ የሚሞከር አይደለም፤ በሌላ ተመሳሳይ ጹሁፍ ልመለስበት እችል ይሆናል፤ በተለይም ደግሞ ከወጣትነታቸው ጀምረው እስካሁን እስከ እርጅናቸው እድሜያቸው በዚህ በደቡብ አፍሪካ በሚገኘው በደቡብና በምእራብ አፍሪካ ሀገር ስብከት የጆሀንስበርግ ጽርሐ ጽዮን መድኃኒዓለም ካቴድራል ውስጥ በማገልገል ላይ የሚገኙት ቄስ ደሊዛ ቫሊዛ የቀደሙ አባቶቻቸው ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤ/ን ጋር ለመገናኝት የከፈሉትን መስዋእትነትና እልህ አስጨራሽ ታሪክ ሲተርኩ መስማት ልብን በሃዘን፣ በቁጭት፣ በእልህ ስሜት የሚንጥ እንዲሁም ልዩ የሆነ የሀገር ፍቅርንና ክብርን የሚያጭር ነው፤ ምናልባት እግዚአብሔር ቢፈቅድ የኚህን ደቡብ አፍሪካዊ ካህን የታሪክ ምስክርነትና ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነታቸው ሲሉ በተለያየ ጊዜ በህይወታቸው ጭምር የተጋረጠባቸውን የሞት አደጋ ያለፉበትን አስደናቂ የእምነት ተጋድሎ በሌላ ጽሁፈ ለማቅረብ እሞክራለሁ።

 

የዓድዋ ድል የመላው ጥቁር ህዝብ ብቻ ሳይሆን የመላው ነጻነት አፍቃሪ ህዝብ ድል ነው፤ ለዚህ ለሰው ልጆች ነጻነት ለተከፈለ ዋጋ ትልቅ ድርሻ ያላት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ከርስቲይን ደግማ ደጋግማ መነሳትና መመስገን ይገባታል፤ የማኅበረ ቅዱሳን የምርምርና የጥናት ማእከልም ይሄን ታሪካዊ ቀን በዚህ መልኩ ለመዘክር መፍቀዱ ይበል የሚያሰኝና ወደ ፊትም በብሔራዊ ደረጃ ጭምር ተጠናክሮ መቀጠል የሚችልበትን ቅድመ ሁኔታ ማመቻቸት እንዳለበት ለማሳሰብ እወዳለሁ። በዘላለማዊ ፍቅሩ ለወደደን ለዘመናት ከተጫነን የሰይጣን የሞትና የሲኦል የባርነት ቀንበር ነጻ ላወጣን ለጌታችንና ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ክብር ምስጋና ይሁንለት! ሀገራችንን በነጻነት፣ በሰላምና በአንድነት ይጠብቅልን!

የአባቶቻችን አምላክ እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ!

ሰላም! ሻሎም!

1 Nelson Rolihlahla Mandela, Long Walk to Freedom, 1994, Great Britain, p. 349.

2 Authors View K. Abraham, The Battle of Adowa and Significance to Pan-Africanism, Volume 4, p. 11-21. No. 24, March 1996.

3 Kinfe Abraham, The Missing Millions: Why and How Africa is Underdeveloped? New Jersey: The Red Sea Press, 1995, p. 52 Politics of Black Nationalism, op ct., p. 104.

4 Donald N. Levine, The Battle of Adowa as ‘historic event’,

http://memebers.stripod.com/~Abyssinia/Ethiopia/Adwa.htm  


በፍቅር ለይኩን ከደቡብ አፍሪካ

This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ