ኢትዮጵያና ደቡብ አፍሪካ በዲሞክራሲ ገጽታ (ከፕ/ር ዓለማየሁ ገ/ማርያም)
ፕሮፌሠር ዓለማየሁ ገ/ማርያም
ኢትዮጵያና ደቡብ አፍሪካን ከሚለይዋቸው ገጽታዎች ዋነኛው በዲሞክራሲ ግንባታ ረገድ እየተጓዙበት ያለው መንገድ ነው። በደቡብ አፍሪካ የዲሞክራሲ መገለጫ የሆነው የህዝብ መንግሥት፣ በህዝብ የተመረጠ መንግሥትና ለህዝብ የሚሠራ መንግሥት የመኖሩ ጉዳይ ነው። (Government of the people by people and for the people) በኢትዮጵያ ያለው የአገዛዝ ሥርዓት መገለጫ ግን የዲሞክራሲ ገጽታ አለው ለማለት ይከብዳል። ምክንያቱም ከዲሞክራሲ መገለጫው ይልቅ ጥቂት ግለሰቦች በሥልጣን ላይ የሚቆዩበትና የህዝብን ሀብት እንደፈለጉ የሚያደርጉበት ሁኔታ የበለጠ ይጐላልና።
በደቡብ አፍሪካ በቅርቡ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት የነበሩት ታቦ ኤምቤኪ ማንኛውም አፍሪካዊ መሪ የማያደርገውን ነገር ሲያደርጉ አይተናል፣ ሰምተናል። በክብርና በሠላማዊ መንገድ ሥልጣናቸውን በፍቃዳቸው ማስረከባቸው፣ በአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስ ኤ.ኤን.ሲ. ፓርቲ ከሥልጣን ይውረዱ ጥያቄ አለማንገራገራቸው ትልቅ ትምህርት ሆኖ አልፏል። ፓርቲያቸው ከሥልጣን እንዲወርዱ ሲጠይቃቸው ያለ ምንም ማንገራገር ያለምንም ቅሬታ፣ ያለ ምንም ወከባ፣ ምንም ማብራሪያ ሳይጠይቁ ለጥያቄው ተገዢ መሆናቸውን ያስታወቁት በጥቂት ቃላት ነበር።
ከሥልጣን የመልቀቃቸው ጉዳይ ሕገመንግሥታዊ ሥርዓትን ተከትሎ በሠላማዊ መንገድ እንዲከናወን ከፍተኛ ጥንቃቄ አድርገዋል። በስንብት ንግግራቸው የደቡብ አፍሪካን ህዝብ “እንዳገለግላችሁ ስለመረጣችሁኝና ዕድሉን ስለሰጣችሁኝ አመሠግናለሁ!” ብለዋል። የኤ.ኤን.ሲ. ዋና ፀሐፊ ግዌዲ ማንታሼ “በህዝቡ ላይ ሽብርና ሥጋት ሳይፈጠር፣ ከፓርቲው የቀረበላቸውን የሥልጣን ይልቀቁ ጥያቄ በፓርላሜንታዊ ሥርዓት በመቀበላቸው ሊደነቁ ይገባል …” ሲሉ ነው ኤምቤኪን ያሞካሹዋቸው። እኛስ ይህን ሊያደርግ የሚችል ፓርቲና ባለሥልጣን አለን ወይ? ነው ጥያቄው።
ከአንድ አፍሪካዊ መሪ ይህን መሰል ውሳኔ ማድመጥ ከባድ ሊሆን ይችላል። ኤምቤኪ ወደ ሥልጣን ሲመጡ ትልቅ ስም የነበራቸውን ኔልሰን ማንዴላን ተክተው ከመምጣታቸው አንፃር፣ ሀገሪቱን መምራት ሊከብዳቸው እንደሚችል ቢነገርም እርሳቸው ግን ለዘጠኝ ዓመት ተኩል ያህል ሀገራቸውን በብቃት መርተዋል። ኤምቤኪ ታሪክ ሠርተው ሲያልፉ ተተኪያቸው ግን ከፊታቸው ትልቅ ፈተና ይጠብቀቸዋል። የሥልጣን ዘመናቸው ሊጠናቀቅ ስድስት ወራት ሲቀራቸው ባልተጠበቀ ሁኔታ በፈቃዳቸው ሥልጣን የለቀቁት ታቦ ኤምቤኪ፣ ከኤ.ኤን.ሲ. ጋር ጥብቅ ቁርኝት አላቸው። አባታቸው ጐቫን እ.ኤ.አ. በ1960 ከኔልሰን ማንዴላ ጋር በጥምር ክስ ቀርቦባቸው የነበሩ ሲሆን፣ በሮቢን ደሴት ሩብ ክፍለ ዘመን በእስር አሳልፈዋል። ኤምቤኪ በደቡብ አፍሪካ ብቻ ሳይሆን በመላው አፍሪካ ታሪክ ትልልቅ ሥራዎች ሠርተዋል። የሩዋንዳውን፣ የቡሩንዲውን፣ የኮትዲቭዋሩንና የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጐን የሠላም ስምምነቶች በዋነኛነት የሸመገሉ ሲሆን፣ በቅርቡ በዚምባቡዌ ለተፈጠረው ፖለቲካዊ ቀውስ ፖለቲካዊ መፍትሔ ያሳደሩ ተሰሚነት ያላቸው መሪ ነበሩ። ይሁን እንጂ በሀገሪቱ ያለው የፖለቲካ ሥርዓት የፓርቲ የበላይነት እንጂ የግለሰብ የበላይነት የሚታይበት ባለመሆኑ ታቦ ኤምቤኪ ከኤ.ኤን.ሲ. የቀረበላቸው የሥልጣን ይልቀቁ ጥያቄ ተቀብለው የአፍሪካ የጀግኖች ጀግና በመሆን ዓለምን ጉድ አሰኝተዋል።
በደቡብ አፍሪካ የዳኝነት ነፃነትም ተከብሯል፤ በቀድሞ የሀገሪቱ ምክትል ፕሬዝዳንትና የኤ.ኤን.ሲ. ፕሬዝዳንት ጃኮብ ዙማ ላይ የሙስና ክስ ቀርቦ፣ ክሱን ሲመለከት የነበረው ፍርድ ቤት ከፕሬዝዳንቱ ጽሕፈት ቤት በኩል ተጽዕኖ ሲደረግበት እንደነበር አስታውቋል። ይህም ዙማ ከክሱ ነፃ ሲሆኑ በኤ.ኤን.ሲ. ውስጥ የውዝግብ መነሻ ሆኖ ፕሬዝዳንት ታቦ ኤምቤኪ ከሥልጣን እንዲወርዱ ምክንያት የሆናቸው ጉዳይ ነው። በዚህ የተነሳ ፓርቲያቸው ያቀረበላቸውን ጥያቄ ተቀብለው በአምባገነንነት ጥላ ስር ሆና ዓመታትን ለገፋችው አፍሪካ የዲሞክራሲ ብርሃን ፈንጥቀው አልፈዋል።
የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት መለያው የዜጐች ተሣትፎ፣ በሥርዓቱ ውስጥ የሚኖራቸው ውክልና፣ ተጠያቂነት፣ ግልጽነት፣ የሕግ የበላይነት መስፈንና ሁሉን አቀፍነት ነው። በደቡብ አፍሪካም ዲሞክራሲ ፍሬ ሊያፈራ የቻለባቸውን ጉዳዮች በአራት ነጥቦች ማስቀመጥ ይቻላል።
አንደኛ፦ ራዕይ ያላቸው መሪዎች ብቸኛ ዓላማቸው አድርገው የተንቀሳቀሱት ህዝቡን አንድ ማድረግ መሆኑ፤
ሁለተኛ፦ በመድብለ ፓርቲ ሥርዓት ውስጥ ራሱን እያረመ የሚጓዝ ፓርቲ መኖሩ፤
ሦስተኛ፦ ነፃና ገለልተኛ የፍትህ ሥርዓት መኖሩና የሕግ የበላይነትን ለማስፈን የሚያስችል ሥራ የህዝብ አመኔታ ያለው መሆኑ እና
አራተኛ፦ ተጠያቂነትን ለማስፈን የሚያስችል ነፃ ፕሬስ የመኖሩ ጉዳይ ነው።
ደቡብ አፍሪካ በአፖርታይድ ሥርዓት የተጨቆነች ሀገር ብትሆንም ባሏት ባለራዕይ መሪዎቿ፣ በአፍሪካ ተጠቃሽ ሀገር ለመሆን ችላለች። ኔልሰን ማንዴላ፣ አልበር ሊቱሊ፣ ጐቫን ኤምቤኪ፣ ዋልተር ሲሱሉ፣ አልበርቲና ሲሱሉ፣ ኦሊቭር ታምቦ፣ ዊኒ ማንዴላ፣ ሊቀጳጳስ ዴዝሞንድ ቱቱ፣ ስቲቭ ቢኮ እና ሌሎችንም መሪዎች መጥቀስ ይቻላል። እነዚህ መሪዎች ለመርህና ለእኩልነት ታግለዋል። በሀገሪቱ ጂኦግራፊያዊ ትስስር ለማምጣት ተንቀሳቅሰዋል። የሊቀጳጳስ ዴዝሞንድ ቱቱ የእውነትና እርቅ አፈላላጊ ኰሚሽን በአፓርታይድ ዘመን (እ.ኤ.አ. ከ1960-1994) የተፈፀሙ ወንጀሎችና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በማጣራት ኃላፊነት ያለባቸው እንዲጠየቁ፣ ምሕረት ማግኘት ያለባቸው እንዲማሩ፣ መካስ ያለባቸውም እንዲካሱ አድርጓል።
በደቡብ አፍሪካ ጠንካራ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት ተመሥርቷል። በአሁኑ ወቅት ከ20 በላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚንቀሳቀሱ ሲሆን፣ እ.ኤ.አ. በ2004 በተካሄደው ምርጫ፣ ዲሞክራቲክ አሊያንስ የተባለው ፓርቲ 12 በመቶ፣ የኢንካታ ነፃነት ፓርቲ ደግሞ 7 በመቶ ድምፅ አግኝተዋል። የፍትህ ሥርዓቱም ቢሆን በፍትሃዊነቱ የሚጠቀስ ሲሆን፣ ሕግ በመተርጐምና በማስፈፀም እንዲሁም ሕገመንግሥቱ እንዲከበር በማድረግ በኩል፣ የዳኝነት አካሉ ያለው ሚና ከፍተኛ ነው። ከፍተኛ የማኅበረሰብ ተቀባይነትና የዳኝነት ነፃነት ያላቸው ፍርድ ቤቶቹ ከፓርቲዎችና ከፖለቲካ አመራሮች ነፃ የሚሆኑበት ተቋማዊ ነፃነትም አላቸው። የሀገሪቱ ፕሬዝዳንትም ሆነ ፓርላማው ፍርድ ቤቶችን እንደፈለገ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የብሔር አልያም የኃይማኖት ዓላማ ማስፈጸሚያ ሊያደርግ የሚችልበት ምንም ክፍተት የለም። በጃኮብ ዙማ ላይ ቀርቦ የነበረው የሙስና ክስ፣ በዞማና በታቦ ኤምቤኪ መካከል ባለ የፉክክር መንፈስ ላይ የተመሰረተ ሲሆን፣ ዳኛው ክሪስ ኒኮልስን የዙማን ክስ ውድቅ አድርገው በነፃ ሲያሰናብቷቸው፣ በጉዳዩ ላይ ፖለቲካዊ ጣልቃ ገብነት መኖሩን መናገራቸውና የፍትህ ሚኒስትሩ በጉዳዩ ጣልቃ መግባታቸው፣ የፍ/ቤቶች የዳኝነት ነፃነት አደጋ እንደተጋረጠበት በማስታወቃቸው ነው ገዢው ኤ.ኤን.ሲ. ፓርቲ አፋጣኝ እርምጃ የወሰደው። ይህ ደግሞ ማንኛውም ወገን በዳኝነት ነፃነት ውስጥ ጣልቃ ሲገባ ዝም ማለት እንደሌለበት ያሳያል ብለዋል ዳኛው። ለተቀረው የአህጉሪቱ ክፍል የሚያስተላልፈውም በደቡብ አፍሪካ ነፃ የዳኝነት አካል መኖሩንና አስመሳይ ችሎት አለመኖሩን ነው።
የደቡብ አፍሪካንና የኢትዮጵያን ፖለቲካ የአገዛዝ ሥርዓቱ ዲሞክራሲያዊነት ይለያቸዋል። ከዚህ ባለፈ ደቡብ አፍሪካውያን በብሔር ላይ የተመሠረተ ፖለቲካን በማስወገድ፣ አንድ ሀገር መመሥረት ሲችሉ፣ የኢትዮጵያ መሪዎች ግን ሀገሪቱ ያላትን ብሔሮች እንደልዩነት ምንጭ በመውሰድ የብሔሮች ፌደራል ሥርዓት (Ethnic Federalism) መመሥረታቸው የመከፋፈል መንስዔ ሆኗል። በደቡብ አፍሪካ የተለያዩ ብሔሮች ቢኖሩም፣ አንድነታቸው የጠነከረ ነው፤ በኢትዮጵያ ግን (Ethnic Federalism) የልዩነት ምንጭ ከመሆን አልፎ የጥቂት ግለሰቦች መበልፀጊያና የወንጀለኞች መደበቂያ፣ የነፃ ፕሬስ ማፈኛ እየሆነ ነው። በሚያስገርም ሁኔታ የደቡብ አፍሪካ ነፃ ፕሬሶች ያላቸው ነፃነት የምዕራባውያን ነፃ ፕሬሶች ካላቸው ነፃነት አይተናነስም። እንቅስቃሴያቸው በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የሚታወቅ ሲሆን፣ ማንም አካል ጣልቃ የማይገባባቸው ፍርድ ቤቶች እንቅስቃሴያቸውን አያስተጓጉሉም። በኢትዮጵያ የዳኝነት ሥርዓት ብቻ ሳይሆን የዲሞክራሲ ሥርዓቱ በእንጭጭ ደረጃ ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ የሀገሪቱ የፖለቲካ መሪዎች ጅምሩን ዲሞክራሲ የማሳደግ፣ መልካም አስተዳደር እየተሠራ መሆኑን ይናገራሉ። በገጠር ኢኮኖሚያዊ ዕድገት መመዝገቡን፣ ተፎካካሪ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት መመሥረቱንና ንቁ የሲቪክ ማኅበረሰብ መመሥረቱን በመግለጽ ህዝቡን ለመስበክ ጥረት ቢያደርጉም ያለው እውነታ ከዚህ የተለየ ነው። በመስከረም መጀመሪያ ላይ በሐዋሳ ከተማ የተካሄደው 7ኛው የኢህአዲግ ጉባዔ እንኳ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ለ7ኛ ጊዜ የግንባሩ ሊቀመንበር አድርጐ በመምረጥ ፓርቲው የአንድ ሰው ፓርቲ መሆኑን አሳይቶናል።
ግንባሩ የነበረውን እንጂ አዲስ አመለካከት ይዞ ለመቀጠል ዝግጁ አለመሆኑንም በመረጣቸው ነባር ሥራ አስፈፃሚዎች ብዛት ማወቅ ይቻላል። ፓርቲው በቀጣይ ሁለት ዓመታትም ዓላማውን ለማስተዋወቅ ሥልጠና በመስጠት በህዝብ ዘንድ ተዓማኒነት ለማግኘት እንደሚጥር ቢገልጽም፤ ሥልጠናው በታማኝ የፖርቲው አባላት ዘንድ ብቻ ተወስኖ እንደሚቀር መገመት አያዳግትም። በኢትዮጵያ እየተመሠረተ ያለው የፓርቲ ታማኞች ሥርዓት (Patronage System) ነውና።
በ(Patronage System) ኢህአዴግ ሥራ በመስጠትና ጥቅማ ጥቅሞችን በመቸር ድጋፍ ለማግኘት፣ የፓርቲ አባላቱንም ለማብዛት ጥረት እያደረገ መሆኑ ይታወቃል። ይህም የፓርቲ ታማኞች በህዝብ ገንዘብ የበለጠ እንዲበለጽጉ በማድረግ የስታሊን ዓይነት የፓርቲ ሥርዓት ለመመሥረት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ያሳያል። ያለፈው የሶቭየቱ የስታሊን ሥርዓት ከአጠቃላዩ ህዝብ እስከ 10 በመቶ የሚደርሰውን ህዝብ ተጠቃሚ ያደረገ ሲሆን፣ ኢህአዴግም አካሄዱ ቢያንስ 4.5 ሚሊየን አባላቱን ወይም ከአጠቃላዩ ህዝብ ከ5 በመቶ የማያንሰውን ተጠቃሚ ለማድረግ ማለሙን መረዳት ይቻላል። ከውጭ በማስመጣት በሥራ ቦታዎች የተሻለ ጥቅምና ደረጃ በማግኘት፣ በትምህርትና በቤቶች ጥቅማ ጥቅም ተጠቃሚ በመሆን፣ የንግድ ዕድል በማመቻቸትና … የበለጠ ተጠቃሚ እየሆኑ ያሉት የፓርቲው አባላት መሆናቸውም የሚያሳየው ይህንኑ ነው። በአጠቃላይ በኢትዮጵያ በሕግ የበላይነት የሚመራና የዜጐችን መብት የሚያስከብር ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ምኞት እንጂ እውን አልሆነም። አሁን እየተከናወነ ያለውም በህዝብ ፍላጐት ላይ የተመሠረተ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለማጨናገፍ እንጂ ለዘላቄታው መመሥረት የሚያስችል ነው ለማለት ይከብዳል።
ፕሮፌሠር አለማየሁ ገብረማርያም ሳን በርናርዲኖ በሚገኘው የካሊፎርኒያ ስቴት ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የፖለቲካ ሣይንስ መምህር ናቸው።
ማስታወሻ፦ ፕ/ር አለማየሁ ገ/ማርያም “The Strange Career of Democracy in Africa” በሚል ርዕስ በእንግሊዝኛ ያቀረቡትን ጽሑፍ ለአማርኛ አንባቢዎች ይደርስ ዘንድ ወደ አማርኛ በመተርጎም የቀረበ ነው።
- ኢትዮጵያ ዛሬ



