ፕሮፌሠር ዓለማየሁ ገ/ማርያም

ባለፈው ሣምንት የኢትዮጵያን ውስጣዊ የፀጥታ ሁኔታ ማዘመን “Moderenizing Internal Security In Ethiopia” የሚል ይፋዊ ሪፖርት ተሰራጭቶ ነበር። ሪፖርቱ በጡረተኛው የብሪታኒያ ኮሎኔል ሚካኤል ዲዋር ሰኔ ወር 2000 ዓ.ም. ላይ የተዘጋጀ ሲሆን ቅኝቱ፣ ግኝቱና የመፍትሔ ሃሳቡ ስኬትን በሚያሳይ መልኩ የተቀመጠ ነው። ለፖለቲካና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶችም ምክር ይሰጣል። ኮሎኔል ዲዋር እንደሚገልፁት በጥናቱ ላይ በለንደን የኢትዮጵያ አምባሣደርና በኢትዮጵያ የቀድሞ የብሪታኒያ አምባሳደርን ጨምሮ በርካታ ባለሙያዎች ከግንቦት 2007 እ.ኤ.አ. ጀምሮ መሳተፋቸውን ይጠቅሳል።

 

የኢህአዴግ ባለሥልጣን አቶ ተፈራ ዋልዋ ጥር 2 ቀን 2008 እ.ኤ.አ. በተላከ ደብዳቤ ኮሎኔል ዲዋር የጥናቱን የመጀመሪያ ዳሰሳ እንዲያጠናቅቁና ዘመናዊ የፀጥታ ኃይል እንዴት መፍጠር፣ የኢትዮጵያን ህዝብና መንግሥት የሚያውክ የማኅበረሰብ አለመረጋጋት (civil unrest) ከመፈጠሩ በፊት መመከት የሚቻልበትን ስትራቴጂ የተካተተበት የመፍትሔ ሃሳብ እንዲላክላቸው እንዲሁም የፀጥታ ኃይሎች ማሠልጠን በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ሃሳብ እንዲሰጡ በደብዳቤ ጠይቀው ነበር። የኮሎኔሉ ሪፖርት ግን ይፋ የተደረገው ከታሰበው በተቃራኒ ነበር። ኮሎኔሉ እንዳሉት የፀጥታን ሁኔታ በአሁኑ ወቅት ከሰብዓዊ መብት አጠባበቅ ነጥሎ መመልከት አይቻልም። ኅብረ ብሔራዊና የዘመናት ባህልና መቻቻል በነገሰበትና በርካታ ቋንቋዎች በሚነገርበት ሀገር ስለሰብዓዊ መብት ኮንቬንሽኖች ማስተማር ፈታኝ መሆኑንም ነው የጠቀሱት።

 

ይሁንና አምነስቲ ኢንተርናሽናል የሶማሌን ሁኔታ በቅርበት ሳይመለከትና በቂ እውቀት ሳይኖረው ያወጣው መግለጫ አፍራሽነት አለው ብለዋል። ኮሎኔሉ እንደገለፁት በሶማሊያ የተፈጠረው ቀውስ ከሰብዓዊ መብት ጥሰት ጋር አይያያዝም፤ ወይም ከኢትዮጵያ ወታደሮች ጋርም አይገናኝም። እንዲያውም የኢትዮጵያ መንግሥት የሰብዓዊ መብትን የተመለከቱ ፕሮግራሞች በመዘርጋቱ ሊመሰገን እንደሚገባ ጠቅሰዋል። የመፍትሔ ሃሳብ ያሉትንም በሁለት ደረጃዎች አስቀምጠዋል። አንደኛው የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ መክፈት ሲሆን፤ ሁለተኛው ሁከት በሚታይባቸው አካባቢዎች የሎጂስቲክና ቴክኒካዊ ድጋፍ መስጠት የሚሉት ናቸው። የፕሮፓጋንዳ ዘመቻው ምዕራባውያን ብዙኀን መገናኛዎች የአምነስቲ ኢንተርናሽናል መግለጫን ለማስተካከል በፀረ ፕሮፓጋንዳነቱ የሚያገለግል ሲሆን፣ በሰብዓዊ መብት አያያዝ የታዩትን መሻሻሎችና አወንታዊ ለውጦች ሊያካትት ይገባል።

 

ኮሎኔል ዲዋር እ.ኤ.አ. ከ2005 ጀምሮ ሦስት ፀረ-መንግሥት ግርግሮች የተካሄዱ መሆናቸውን በመጥቀስ በአሁኑ ወቅት ግን ሁኔታዎች መልካም ናቸው ይላሉ። የፀጥታ ኃይሉም የብረት ቆብ፣ የዓይን መከለያ፣ የእግር መሸፈኛና ሌሎች ቁልፍ የተሟሉለት ሲሆን፤ መሠረታዊ የፀጥታ ኃይል ቁሶችም የተሟሉ እንደሆኑ ያምናሉ። ይህም ለተወሰኑ ዓመታት ያለችግር ሊቆይ እንደሚችል ይጠቅሳሉ። ይሁን እንጂ አድማ በታኝ ፖሊሶች (Riot Police) ሥልጠና ከወሰዱ በኋላ ያለሥራ ከመቀመጣቸው በላይ ሁከት እስኪፈጠር ድረስ ብቻ ጊዜያቸውን በከንቱ ያሳልፋሉ። ስለሆነም አድማ በታኞቹ ተጨማሪ ኃላፊነት ተሰጥቷቸው ረብሻ በማይኖርበት ጊዜ ሌላኛውን ተግባራቸውን እንዲያከናውኑ ቢደረግ የሚል የመፍትሔ ሃሳብ አስቀምጠዋል።

 

የኢትዮጵያ ፖሊስ ኮሌጅን የጎበኙት ኮሎኔል ዲዋር የኮሌጁ እንቅስቃሴና የውስጥ ድርጅት አለመሟላት እንዳስገረማቸው በሪፖርቱ አስፈረዋል። ይሁን እንጂ ኃላፊዎች በቂ አለመሆናቸውን፣ በሥልጠና በኩል መሻሻል አለመታየቱን፣ የመማሪያ ክፍሎች ባዶ መሆናቸውን ጠቅሰዋል። ከኮሌጁ ዳይሬክተር ጀነራል ጋር ለ3 ሰዓታት ባደረጉት ውይይትም ፖሊስ ያልታጠቁ ሠላማዊ ሰዎችን መግደሉ በህዝብ ዘንድ መጥፎ ምስል መቅረፁን እንደነገሯቸው ሲጠቅሱ፤ ከዚህ ጋር በተያያዘ ከ97ቱ ረብሻ ጋር በተያያዘ 237 የፖሊስ አባላት ከሥራ እንደታገዱ ተገልፆላቸዋል።

 

ኮሎኔል ዲዋር በአዲስ አበባ የአንድ እስር ቤትን የውስጥ ይዘት ተመልክተው ፍርሃት እንደነገሰባቸው እንዲህ ሲሉ ነው የገለፁት። “እስረኞቹ ወዳሉበት ቅጥር ግቢ እንድገባ ጠየቅኩ፤ ይህ ሰፊ ስፍራ ያካለለው ግቢ መጠነኛ መጠለያዎች አሉት። ቅጥሩ የታጠረ፣ የመመልከቻ ማማ ያለበት፣ የታጠቀ ሰው ቁጥጥር የሚያደርግበት ሲሆን፤ በውስጡ ከ70 እስከ 80 ሰዎች ምቹ ባልሆነ ሁኔታ ተፋፍነው ይኖራሉ። ሰዎቹ የሚተኙበት በቂ ስፍራ የላቸውም፤ ክፍሉም በቂ ብርሃን የለውም፤ እዚያው ስለሚፀዳዱም የሚሰነፍጥ ሽታ አለ፤ በቅጥሩ ውስጥ የውሃም ሆነ የንጽኅና መጠበቂያ አገልግሎት እንደሌለ ያስታውቃል። በሴቶች እስር ቤት በኩል ግን መለስተኛ የቆሻሻ ማጠራቀሚያ አለች። ይሁን እንጂ የአካባቢውን ሁኔታ ለማሻሻል ማንም ምንም የወሰደው እርምጃ የለም። እስረኞቹ በዚያ ያሉት በአብዛኛው በጥቃቅን ወንጀሎች ነው። በተለይ በስርቆት አንዳንዶቹ ለወራት የቆዩ ሲሆን፣ አንድ የ12 ወይም 13 ዓመት ወይም ከ15 የማይዘል መሃከላቸው ይገኛል። አንዱን ፖሊስ ስጠይቀው ግን የታሳሪዎች ዝቅተኛ ዕድሜ 18 ሌላው ደግሞ 15 ዓመት መሆኑን ነግረውኛል።

 

ኮሎኔል ዲዋር የእስረኞች አያያዝ ሁኔታ ሰብዓዊነት ያልተላበሰ በመሆኑ ፌደራል ፖሊስን ለሰብዓዊ መብት ወትዋቾች ትችት ሊያጋልጠው እንደሚችል በማጠቃለያቸው አስፍረዋል። “ስለሆነም መንግሥት በኢትዮጵያ ማረሚያ ቤቶች ውስጥ ያለውን የእስረኞች አያያዝ በማሻሻል ምርመራ (ፍተሻ) ማድረግ ይኖርበታል። የኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት፣ ሚኒስትሮችና የፖሊስ መኮንኖች እኔ ያየሁት እስር ቤት ሊያዩ ይገባል” ብለዋል።

 

ሁከት በኢትዮጵያ

 

በኢትዮጵያ የወንጀለኛ ሕግ እንደሰፈረው ሁከት የሚባለው አንድ ሰው በገዛ ፈቃዱ ሕገወጥ የሆነ ተግባር በግልም ሆነ በቡድን ሲፈፅም፣ በንብረትና በሰዎች ላይ ጉዳት ሲያደርስ ነው፤ ቅጣቱም ቀላል እስራት ነው። ሁከት በህዝብ ሠላምና ፀጥታ ላይ የሚፈፀም ሕገወጥ ተግባር ነው። ይሁን እንጂ የኢፌዲሪ ሕገመንግሥት አንቀጽ 30 የመሰብሰብ፣ የመቃወም እና አቤቱታ የማሰማት መብት የሰጠ በመሆኑ ህዝብ ለፈለገው ዓላማ መሰብሰብ ተፈቅዶለታል። በ1997 ሰኔ ወርና በ1998 ኅዳር ወር ግን የመለስ ዜናዊ ታማኝ ወታደሮች ባልታጠቁ ሰዎች ላይ ሁከት ፈጣሪዎች በሚል የጥቃት እሩምታ ከፍተዋል። በወቅቱ የተቋቋመው አጣሪ ኮሚሽንም ፖሊስ 193 ሰዎችን መግደሉንና 763 ሰዎች ማቁሰሉን አረጋግጧል። ሰባት አድማ በታኝ ፖሊሶችም ተገድለዋል። በቃሊቲ ማረሚያ ቤትም ኅዳር 1998 ላይ 1500 ጥይት ተተኩሶ ሁከት ፈጥረዋል የተባሉ 65 እስረኞች ተገድለዋል። ኮሚሽኑ 30,000 ሰዎች ተይዘው ስለመታሰራቸው መረጃዎች አግኝቷል። በማጠቃለያውም ሁከት ፈጣሪ ተብለው የተገደሉት ሰዎች መሣሪያ ያልታጠቁ እንደነበር፤ ፖሊስ ተቃውሞ የወጡትን ለመበተን፤ ሕጋዊ ያልሆነና ከመጠን ያለፈ ኃይል መጠቀሙን አጋልጧል። በወቅቱ (በ1997 እና 98 ግርግር) ንብረት መውደሙን፣ በመግለፅ ሚዲያዎች አንዳንድ ተቃዋሚዎች የጦር መሣሪያ ይዘው እንደነበር ቢገልፁም፤ ማንኛውም የተቃውሞ ሰልፍ የወጣ የጦር መሣሪያ አለመያዙን፣ አድማ በታኞችም አድማውን ለመበተን ሳይሆን አልመው ደረትና ጭንቅላት ሲመቱ ስለነበር ሕግ ተጥሷል። የመንግሥት ጦርም ከመጠን ያለፈ ኃይል ተጠቅሟል።

 

የኮሚሽኑ ሰብሳቢ ዳኛ ፍሬሕይወት ሳሙኤል በሰጡት አስተያየት በርካታ ሰዎች በዘፈቀደ ከሕግ ውጪ ተገድለዋል። አዛውንቶች በመኖሪያ ቤታቸው ሲገደሉ ሕፃናትም ሲጫወቱ የጥቃት ሰለባ ሆነዋል ብለዋል።

 

የኮሚሽኑ አባል የነበሩት ሺህ ኤልያስ ሬድማን ግን በጭካኔ የተቃዋሚ ሰልፈኞች ዓላማ መንግሥትን መገልበጥ ስለሆነ እርምጃው ተገቢ ነው ብለው ድጋፋቸውን ሰጥተዋል።

 

የዲዋር ሪፖርት

 

የኮሎኔል ዲዋር ሪፖርት መንግሥት ስለመሠረታዊ የሰብዓዊ መብት አጠባበቅ ያለው ዕውቀት ዝቅተኛ መሆኑን ያሳያል። የሰብዓዊ መብት ሠላማዊ ሰልፍ ማድረግን፣ መቃወምን፣ በአደባባይ መሰብሰብን ብሎም እንደ ማህተመ ጋንዲ አንድን ነገር አላደርግም ብሎ አለመታዘዝን ያካትታል።

 

ጋንዲ ህዝባዊ ያለመታዘዝ አመጽ (ሠላማዊ አመጽ) በብሪታኒያ ላይ እንደ አንድ ሠላማዊ የመቃወሚያ ስልት ተጠቅሞበታል። መንግሥት ሕግ የማያከብርና ሙሰኛ ሲሆን፣ ዜጎች አለመታዘዝ ኃይማኖታዊ ግዴታቸው ነው ብለው ነበር።

 

በርካታ የአፍሪካ ሀገሮች ነፃነታቸውን የተቀዳጁት በሠላማዊ መንገድ ሳይሆን በህዝባዊ አመጽ ነው። ኔልሰን ማንዴላ፣ ሊቀ ጳጳስ ዴዝሞንድ ቱቱና ስቲቭ ቢክ አፓርታይድን ለመቃወም ያቀነቀኑት ስለ ሠላማዊ አመጽ ነው። የአሜሪካ የሰብዓዊ መብቶች ንቅናቄ መሪ ዶክተር ማርቲን ሎተር ኪንግም ፍልስፍናው የተመሠረተው በጋንዲ ሠላማዊ አመጽ (ያለመታዘዝ አመጽ) ላይ ነበር።

 

ዲዋር ያቀረቡት ሪፖርት ላይ የሰፈረው ግን ከዚህ የተለየ ነው። አድማ በታኞች አድማ ለመበተን መምታት ወይም መተኮስ በዘመናዊ የሥልጠና ዘዴ ተጠቅሞ አመጽን ከመቆጣጠር ይልቅ ቅድሚያ የሚሰጠው መሆን እንዳለበት ያስቀምጣሉ። ለነገሩ እርሳቸውም በ1970ዎቹ በአየርላንድ ህዝባዊ አመጽን ለማዳፈን ተሰማርተው ነበር፤ የአሁኑ ተሞክሯቸው የተቀረፀውም በዚሁ ላይ ነው። ኮሎኔሉ የፃፉት መጽሐፍ "War in the streets: The story of urban combat for Calais to khafic" በከተማ ህዝባዊ አመጽን ለማስቆም መወሰድ ስላለባቸው እርምጃዎች ይዘረዝራል። ይሁን እንጂ ስለኢትዮጵያ የፃፉት እውነታን የያዘና ያልተበረዘ ነው። እንደተመለከቱት አስፍረዋል።

 

አምነስቲ ኢንተርናሽናል በ2008 ሪፖርቱ በኢትዮጵያ ማረሚያ ቤቶች የፖለቲካ እስረኞች አያያዝ የከፋ መሆኑን ጠቅሷል። በዚያ ያልተፈረደባቸው ተጠርጣሪዎች እንዳሉ፣ የተፋፈገና ንፅህናውን ያልጠበቀ መሆኑን አስፍረዋል። በ2006 ደግሞ ማረሚያ ቤቶች ውስጥ ሕፃናት ታራሚዎች እንደሚገኙ፣ በሰው የተጨናነቁ፣ ውስጣቸው ጥሩ አለመሆኑንና ሕክምና አለመኖሩን ጠቅሶ ነበር።

 

ለማረሚያ ቤት ማሻሻያ በጀት እንደማይያዝ፣ ፖሊስ በእስር ቤቶች አካላዊ ጥቃት እንደሚፈፅምና ባለሥልጣናትም አንዳንዴ ሕፃናትን ከአዋቂዎች ጋር እንደሚያስሩ ገልጧል።

 

ኮሎኔል ዲዋር ከምርጫ 97 በኋላ በተከሰተው ጭፍጨፋ 237 የፖሊስ አባላት ከሥራ እንደተባረሩ ተገልፆላቸው ነበር። ገዥው ፓርቲ የአድማ በታኝ አባላት ሕገወጥ ተግባር አልፈፀሙም ሲል ሲያስተባብል ቆይቷል፤ ዲዋር ግን በጭፍጨፋው ተጠያቂ ሊሆኑ የሚገባቸው በትንሹ 275 ፖሊሶች መሆናቸውን ይጠቅሳሉ። በመሆኑም እነዚህ ተጠርጣሪ የፖሊስ አባላት በአስቸኳይ ለፍርድ መቅረብ ይኖርባቸዋል።

 

በኬንያ ከወራት በፊት የተካሄደውን ምርጫ ተከትሎ የተከሰተውን ሁከት የሚያጣራ በፍትህ ሚኒስትሩ ፊሊፕ ዋኪ የሚመራ አንድ ኮሚሽን ተቋቁሞ ነበር። ኮሚሽኑ ከማጣራቱ በኋላ በሁከቱ የተሳተፉ ሰዎችን ጉዳይ የሚመረምርና ውሳኔ የሚሰጥ ልዩ ፍ/ቤት እንዲቋቋም ሃሳብ አቅርቦ ነበር። ከዚህ ጋር አያይዞም የተጠርጣሪዎችን ዝርዝር ለዓለም አቀፍ የጦር ወንጀለኞች ችሎት አቅርቧል። ለፍትህ፣ ለሰብዓዊ መብትና ለሕግ የበላይነት የቆሙ ኢትዮጵያውያንም ምርጫ 97ን ተከትሎ በተፈፀመው ምርጫ የተሳተፉ የፖሊስ አባላት ለዓለም አቀፍ የጦር ወንጀለኞች ችሎት ማቅረብ ይኖርባቸዋል።

 

በኢትዮጵያ ባለፉት 17 ዓመታት ሁከት እየነገሰ መጥቷል። ከህዝቧ ሲሶው ለረሃብ ተጋልጧል፤ ግሽበትም በኢትዮጵያ ታሪክ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል። ማጋነን አይሁን እንጂ ኢትዮጵያዊያን ወደ ሀገር ቤት የሚልኩት ገንዘብ እየቀረ መንግሥትም እየተንሳፈፈ ነው። የሶማሊያ ጦርነትም የሀገሪቱን ውስን ሀብት እያሟጠጠ፣ ወጣት ልጆቿን መስዋዕት እያደረገ ሀገሪቱን ለሁከት እያጋለጠ ነው።


 

ፕሮፌሠር አለማየሁ ገብረማርያም ሳን በርናርዲኖ በሚገኘው የካሊፎርኒያ ስቴት ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የፖለቲካ ሣይንስ መምህር ናቸው።

 

ማስታወሻ ፕ/ር አለማየሁ ገ/ማርያም “Quiet riot in Ethiopia” በሚል ርዕስ በእንግሊዝኛ ያቀረቡትን ጽሑፍ ለአማርኛ አንባቢዎች ይደርስ ዘንድ ወደ አማርኛ በመተርጎም የቀረበ ነው።

- ኢትዮጵያ ዛሬ

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ