በተሳሳተ አስተሳሰብ ከመወደድ ትክክለኛ ሆኖ መጠላት (ከኤርምያስ ጋሹ)
ከኤርምያስ ጋሹ (የኢዴአፓ መድህን ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል)
(“የኢዴአፓ "ልጓም ለቅቆ ቼቼ"” በሚል ርዕስ በቃልኪዳን አምባቸው ለቀረበው ጽሑፍ የተሰጠ ምላሽ)
ቃልኪዳን አምባቸው የተባሉ ፀሐፊ “የኢዴአፓ "ልጓም ለቅቆ ቼቼ"” በሚል የጻፉትን በአግራሞት አነበብኩ። ስለኢዴአፓ መድህንም ሆነ በአጠቃላይ ስለኢትዮጵያ ፖለቲካ ጉዳዮች በእንዲህ ዓይነት ጽሑፍ እንካ ሠላንቲያ የመሰጣጠት ፍላጐት የለኝም። በኢዴአፓ መድህን ውስጥም እንዲህ ዓይነት ጽሑፎችን እየተከታተሉ ላለማስተባበል በቂ ምክንያት አለን።
ኢዴአፓ መድህንም ሆነ እኔ በግሌ፣ በኢዴአፓ መድህን ፓለቲካ ውስጥም ባለኝ ተሳትፎ፣ በየዕለቱ ከምንጋፈጣቸው ችግሮቻችን አንደኛው፣ እንዲህ ዓይነት ጽሑፎች በኅብረተሰቡ ውስጥ የሚፈጥሩት የተምታታ ግንዛቤ መሆኑ አልቀረም። እንዲህ ዓይነት ጽሑፎች መልዕክት በራሱ ዘላቂነት ባይኖረውም ዘላቂነት ያላቸውን ምክንያቶች በመፍጠር፣ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ለምንፈልገው ምክንያታዊነትና እውነተኝነት እንቅፋት እየሆነ ነው። ስለዚህ በዚያ ጽሑፍ፣ ፀሐፊው ካነሷቸው አንዳንድ ጉዳዮችን መነሻ በማድረግ፣ የኢዴአፓ ፖለቲካን ከመከላከል በተጨማሪ የፀሐፊው መንፈስ የሚፈቅድ ከሆነ የራሴን የግል ግንዛቤዬን በማካፈል ከፀሐፊው ጋር መሟገት አንዳንድ ነጥቦችን ለማጥራት ሊጠቅም ይችላል።
የፀሐፊው መንፈስ የሚፈቅድ ከሆነ ማለቴ ግልጽ ሊሆን ይገባል። ፀሐፊው ጽሑፉን የጻፉት ባነሷቸው ጉዳዮች ላይ የኢዴአፓ መድህን አስተሳሰብ ስህተት መሆኑን በርግጠኝነት አውቀውና አምነው ነው ወይስ ባለፉት ዓመታት በኢዴአፓ መድህን ላይ ሲዥጐደጐድ የነበረውን አሉባልታ መነሻ ያደረገ ማጥላላት መቀጠላቸው ነው? ጽሑፉን ባነበብኩ ጊዜ የፀሐፊው መነሻ ሃሳብ፣ ከሁለቱ የቱ እንደሆነ የገባኝ ቢሆንም ከእሳቸው በላይ ሊገባኝ አይችልም። እንደዚሁም ፀሐፊው ስለእኔ ሃሳብ ሊኖራቸው የሚችለው አስተያየት በእሳቸው ግንዛቤ የሚወሰን ነው። የእሳቸው ግንዛቤ መነሻ ያደረገው፣ በዚያ ጥላቻ መንፈስ በጣም ግልጽ የሆነው አንዳንዱን እውነታ ኢዴአፓ ስላለው ብቻ ለመቃወም ከሆነ በጣም አስቸጋሪ ነው። ስለዚህ የእኔን ጽሑፍ በሚያነቡበት ጊዜ ፀሐፊው በሃሳብነቱ ድክመትና ብቃት መዝነው ብቻ እንዲያነቡልኝ በአክብሮት መጠየቅ የግድ ሊሆንብኝ ነው። እንደዚሁም ጽሑፉ ስሜታዊ ሳያደርገኝ አልቀረም፤ ስለዚህ ለአንዳንድ አገላለጾች አንባቢያንም ጭምር ከወዲሁ ይቅርታ መጠየቅ አለብኝ።
ፀሐፊው በጽሑፋቸው መግቢያ ላይ “ለፖለቲካ ንቃተ ኅሊና መፈጠር ገንቢ ሚና ከተጫወቱ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ ኢዴአፓ መድህን በዋናነት ተጠቃሽ ነው” ካሉ በኋላ በግንቦቱ ምርጫ ሂደት ፓርቲያችን የተጫወተውን ገንቢ ሚና ጠቅሰው፣ በአሁኑ ወቅትም “በተሣትፎ የሚያምን ፓርቲ ስለመሆኑ ተመስክሮለታል” ብለዋል። ይህንን ያሉት ወረድ ብለው “ኢዴአፓ መድህን ሌሎችም ሊነሱ የሚችሉ ጠንካራ ጐኖችና በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ያሳደረው አዎንታዊ ተፅዕኖ ቢኖርም …” ብለው አሉታዊ ወዳሉዋቸው ነጥቦች ከመሸጋገራቸው በፊት ነው። ስለዚህ ፓርቲያችን ለፖለቲካ ንቃተ ኅሊና መፈጠር ገንቢ ሚናን መጫወቱንና በተሳትፎ ፖለቲካ የሚያምን ስለመሆኑ እንደተመሰከረለት አረጋግጠዋል ማለት ነው።
ይህ ምስክርነት ለፖርቲያችን ብቻ ሳይሆን ለእኔ በግሌም አበረታች ነው። ባለፉት ወራት በኢዴአፓ መድህን ላይ ተጽፈው የነበሩ አንዳንድ መሰል ጽሑፎች እንዲሁ በጅምላ የሚያወግዙን ነበሩ። ፀሐፊው በጐ አስተዋጿችንም ጭምር በመጥቀስ ከዚያ የጅምላ ጥላቻ አስተሳሰብ ራሳቸውን ለይተው አንድ እርምጃ ወደፊት የተራመዱ መሆናቸውን አሳይተዋል። ይሁንና ፀሐፊውን ለዚህ ገንቢ ለሆነው አስተዋጽዖ ለኢዴአፓ መድህን እየተከፈለለት ያለውን ውለታ በቅን ልቦና እንዲያሰላስሉ እጠይቃለሁ። ከጽሑፋቸው እንደተረዳሁት ፀሐፊው በተሳትፎ ፖለቲካ ትክክለኛነት ላይ እምነት አላቸው፤ ይህ ከሆነና በርግጥም የኢትዮጵያን ወቅታዊ ፖለቲካን በአግባቡ የሚከታተሉ ከሆኑ፣ ይኽ እሳቸው የሚያምኑት የኢዴአፓ መድህን ተሳትፎ ፖለቲካ መርኅና አተገባበር በሌሎች ዘንድ ምን እያስባለ እንደሆነ በስፋት ሳይሰሙ እንዳልቀሩ ተስፋ አደርጋለሁ። ዛሬ ስለኢዴአፓ መድህን “አሉታዊ” ብለው ስላሰቧቸው ጉዳዮች በእንዲህ መልክ መፃፍ ተገቢም ነው። ነገር ግን ሌላው ቢቀር ፀሐፊው ከሚያምኑበት የተሳትፎ ፖለቲካችን ትክክለኛነት አንፃር፣ የሌሎችን ስህተት አንስተው ስለ የኢዴአፓ መድህን ትክክለኛነት ጽፈው ቢሆን ኖሮ ምንኛ ደስ ባለኝ።
ይህንን ያልኩት ስለኢዴአፓ-መድህን “ስህተት” መጻፉቸውን ዝቅ ለማድረግ አይደለም። ሁለት ምክንያቶች አሉኝ። አንደኛው ኢዴአፓ-መድህን አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲ የራሱ ውስጣዊ ድክመቶች ችግሮች ቢኖሩትም፣ የሌሎች አመለካከትና አስተሳሰብ ደካማነት ጭምር ተጠቂ ስለመሆኑ ብዙ ማስረጃዎችን ማቅረብ የምንችል መሆኑን ለማረጋገጥ ነው። ሁለተኛው ምክንያቴ የተቺዎቻችን የፖለቲካ ግንዛቤ ደረጃ ብቻም ሳይሆን የሞራል ብቃትና ፍትሃዊነታቸውንም የምንመዝን መሆናችንን ለማሳየት ነው። አሁን ተቃዋሚ ፓርቲዎች በሚገኙበት ተጨባጭ ሁኔታ ኢዴአፓ እራሱን ብቻ ሳይሆን የሌሎችንም ድክመት እንዲሁም በሀገራችን ፖለቲካ ውስጥ አሻሚ በሆኑ በርካታ ጉዳዮች አንጻር ሰፋ ያለ ጊዜ ወስዶ እያደረገ ያለው ግምገማ መልካም አሳቢነትና በጐነት የነገሠበት ቢሆን ኖሮ እገዛ ሊቸረው በተገባ ነበር።
የፀሐፊው ዋነኛ መልዕክት ኢዴአፓ ከግንቦቱ የ1997 ዓ.ም. ምርጫ በኋላ በሀገራችን ለተከሰተው ችግር፣ የህዝቡም መሳሳት ድርሻ አለበት ማለቱ ትክክለኛ እንዳይደለ ማሳየት መሆኑ ይታያል። ለፀሐፊው ይህ ዋነኛ “ልጓም መልቀቅን” ነው። ፀሐፊው ኢዴአፓ በአሁኑ ወቅት ህዝቡ ስለተቃውሞ ፖለቲካ ተስፋ ቆርጧል ማለቱን በመጥቀስ፤ “ህዝብ የትና መቼ በምንስ መልኩ ለኢዴአፓ ተስፋ መቁረጡን እንዳሳወቀው የሚታወቅ ነገር የለም” በማለት ይሳለቃሉ። በዚህ ነጥብ ላይ ለኢዴአፓ አስተሳሰብ አቻ የሚሆነው ክርክር ህዝቡ ተስፋ እንዳልቆረጠ ማሳየት መሆኑ ግልጽ ነው። ለመሆኑ ስለህዝቡ ተስፋ መቁረጥ ህዝቡ “ተስፋ ቆርጫለሁ” ብሎ ካልነገረው በቀር ኢዴአፓ ሊያውቅ አይችልም? ባለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት ህዝቡ ስለተቃውሞ ትግል ተስፋ ያጣ መሆኑን በመተንተን በየጋዜጦች ላይ ሲጽፉ የነበሩ በርካቶች ናቸው። ሰዎች ሁሉ ይህንን ሲሉ የነበሩት ህዝቡ “ተስፋ ቆርጫለሁ” ብሎ እየነገራቸው ነው? የጥያቄው ምንጭ ጥራዝ ነጠቅነት መሆኑን መረዳት ይቻላል።
ፀሐፊው “ኢዴአፓ ህዝቡን ተሳስቷል የሚለው ማነው? በምንስ መሥፈርት ነው?” ብለው ጠይቀዋል። እነኚህ ሁለቱ ጥያቄዎች መሠረታዊ ልዩነት ያላቸውን ሁለት ነጥቦችን በአንድነት አጣምረው የያዙ ናቸው። በዚህ ጉዳይ ፀሐፊው ኢዴአፓን መተቸት የፈለጉበትን መነሻ አጣርተው ያላወቁ መሆናቸውን ለማሳየት እነኚህን ሁለት ነጥቦችን ለያይተን እንመልከት። አንደኛው የጽሑፋቸው ሃሳብ በመርኅ ደረጃ ህዝብን ተሳስቷል ማለትን የሚቃወም ሆኖ እየታየ፤ በሌላ በኩል ኢዴአፓ ይህን ለማለት ያለውን ብቃትና ስለተጠቀመበት መሥፈርት ይጠይቃሉ። የእሳቸው እምነት በፖለቲካ ክስተቶች ሂደት የመጨረሻው ውጤት ህዝብንም ጭምር ከስህተት ላይ ሊጥል አይችልም ከሆነ ዋናው ተቃውሞ መሆን ያለበት ከዚህ ሃሳብ ጋር ነው። ሃሳባቸው የዚህ ተቃራኒ ከሆነ ክርክራቸው መቆም ያለበት በኢዴአፓ ዙሪያ ላይ ብቻ ነው።
“ኢዴአፓ ህዝብን ተሳስተሃል የሚለው ማነው?” ብለው ሲጠይቁ ችግራቸው ኢዴአፓ ህዝብን ተሳስቷል ለማለት ያለው ብቃት ይመስላል። ስለህዝቡ መሳሳት ለመናገር ኢዴአፓ ያለውን ብቃት በተመለከተ ያነሱት ጥያቄ ሲታይ በጽሑፋቸው መግቢያ ላይ ካነሱት ሃሳብ ጋር ይጋጫል። ኢዴአፓ በሀገራችን ፖለቲካ አዎንታዊ ሚና የተጫወተ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ መሆኑን ካመኑ እንዲህ ዓይነቱ ፓርቲ ስለሚታገልለት ህዝብ ፖለቲካዊ ንቃተ ህሊና እና ፖለቲካዊ ባህሪ በመገምገም፣ ከእነዚህ ስለሚመነጩ ችግሮች በግልጽ አቋም ለመውሰድ የሚገባ መሆኑ ለምን ያከራክራል? ከምርጫው በኋላ በህዝቡ ውስጥ ስለታየው አዎንታዊ ስላልነበረው ነገር ባለፉት ዓመታት በተለያዩ መልኮች ሲገለጽ አልነበረም? ይህም ኢዴአፓ ስላለው ብቻ ተብሎ ተቃውሞ ሊቀርብበት ይገባልን?
እዚህ ላይ የህዝቡን መሳሳት ድርሻ ለመለካት ኢዴአፓ ስለተጠቀመበት መሥፈርት ለመነጋገር በመጀመሪያ ፀሐፊው የህዝብ መሳሳት በመርኅ ደረጃ የሚቀበሉ መሆናቸው ግልጽ ስላልሆነ አስቸጋሪ ነው፤ አላስፈላጊ ሥራም ይሆናል። ህዝቡ ማነው? ብለውም ጠይቀዋል። ለዚህ ጥያቄ ምላሽ መስጠት የሚያስፈልግ አይመስለኝም።
ፀሐፊውን ለመርዳት የተሻለ የሚሆነው በፖለቲካ ሂደት በብዙ ምክንያቶች ህዝብ የስህተት ባለድርሻ ሊሆን እንደሚችል ብዙም ክርክር የሚያስፈልገው ነጥብ አለመሆኑን መግለጽ በቂ ነው። ህዝብ ስንል የብዙ ሰዎች ስብስብ ቢሆንም ቃሉ የሚገልጸው ከስብስብነቱ በላይ የስብስብነቱ ውጤት ነው። እያንዳንዱ ሰው የህዝብ አካል ነው፤ እያንዳንዱ ሰው በተፈጥሮው ሊሳሳት የሚችል ሆኖ መፈጠሩ የማያከራከር እስከሆነ ድረስ “ብዙ ሰዎች በአንድነት ሲሆኑ ሊሳሳቱ አይችሉም” የሚል ክርክር ሊቀርብ አይችልም። በፖለቲካ ሂደት ህዝብንም ጭምር እንዲሳሳት ስለሚያደርጉ ነገሮች ስናነሳ የአንድን ሀገር ህዝብ በሙሉ ማለታችን ሊሆን አይችልም፤ ፖለቲካ በህዝብ ውስጥ የቡድን ፍላጐት መገለጫ ነውና።
በአንድ የፖለቲካ አቋም፣ ህዝብ የሚኖረው አመለካከት በህዝቡ ውስጥ የበላይነትን ለማግኘት ከሚታገሉ የተለያዩ ቡድኖች እንቅስቃሴ ጋር የተያያዘ ነው። አንዳንድ ሃሳቦች በህዝቡ ውስጥ የበላይነት የሚያገኙት ትክክለኛ ስለሆኑ ብቻ አይደለም። ትክክለኛም ቢሆኑ የመጨረሻ ውጤታቸውን ህዝብ ሁሉ የሚወስነው አይሆንም፤ ልማትና ሠላም የህዝብ ቋሚ ፍላጐቶች ናቸው። እነዚህን መነሻ ያደረጉ ፖለቲካዊ አስተሳሰቦች በህዝብ ዘንድ ተቀባይነት የሚያገኙ ቢሆንም ልማትና ሠላም ስለሚመጣበት ወይም የህዝብ ፍላጐትና ምኞት እውን ስለሚሆንበት መንገድ የመወሰኑ ሥራ የጥቂት ልህቃን ሥራ መሆኑ ግልጽ ነው። ከግንቦቱ ምርጫ በኋላ በቅንጅቱ ውስጥ ይህን በመወሰን ረገድ የተሠሩት ስህተትና ጥፋት ብዙዎቹን አሳስቷል። ይህን ስህተትና ጥፋት ዛሬ የማያከራክር ቢሆንም ብዙዎች ከዚህ አንፃር ችግሩን ተረድተው ተገቢ አቋም ለመውሰድ እየቻሉ አለመሆኑ ይታያል።
በሌላ በኩል በየትኛውም ሀገር ተጨባጭ ሁኔታ፣ የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ስኬት ከህዝብ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ባህሪይ ጋር በጥብቅ የተሳሰረ ነው። ከዚህ አንጻር የህዝብን ብቃትና ሚና በተመለከተ የኢትዮጵያ ህዝብ ቀርቶ፣ የአሜሪካ ህዝብም ቢሆን ከዚህ አንጻር የራሱ ችግር አለበት። በግንቦቱ ምርጫ ሂደት ህዝቡ ችግር አልነበረበትም የሚሉ ከሆነ ፀሐፊው ይህንን በግልጽ በማብራራት በኢዴአፓ አስተሳሰብ ላይ ተቃውሞ ማቅረብ ነበረባቸው። ችግር አለ ከተባለም ለሁላችንም የሚጠቅመው ችግሩን በግልጽ ለይቶ እንዳይደገም ለማድረግ የመፍትሔ አቅጣጫ ማስቀመጥ ነው። ይህ ደግሞ ከፀሐፊው አቅም በላይ የሆነ ሥራ መሆኑን መገመት ይቻላል።
የኢዴአፓ ዓላማም ይህ መሆኑን መመስከር እችላለሁ። ለኔ ጠቃሚ የሚመስለኝ ይህ ነው፤ ለምን እንዲህ ተባለ የሚለው አስተሳሰብ በምንም መሥፈርት ቢሆን ትክክለኝነት ሊኖረው አይችልም። ብዙ ጊዜ በኢዴአፓ ላይ የሚነሱ ተቃውሞዎች፣ ፓርቲው በቀደሙ ሃሳቦች መነሻነት የመሪነት ሚና ለመጫወት የሚያደርገው ሙከራ፣ በሌሎች ዘንድ ከሚፈጥረው ብዥታ ነው። በርግጥ አንዳንዶች በተለመደው “ለእኔ ካልሆነ ለአንተም አይሳካ” ዓይነት አስተሳሰብ መነሻነት ኢዴአፓን በምቀኝነት ተነሳስተው ሲቃወሙና ሲታገሉ ማየትን ለምደናል።
ወደ ነበርንበት እንመለስና ሁለት ነገሮችን ላንሣ። ዛሬ ኢዴአፓ መድህን የሚባለው ፓርቲ ገና ኢዴአፓ ተብሎ ሲመሠረት ኢዴአፓ-መድህን ሠላማዊ የትግል ስልትን የተቃውሞ ትግሉ ብቸኛው ስልት መሆን አለበት በማለቱ ምን ተብሎ ነበር? ወያኔ/ኢህአዲግን ከወንበሩ ሊያሽቀነጥር እየገሠገሠ ያለውን የትጥቅ ትግል ለማደናቀፍ የተወጠነ ተንኮል አልተባለምን? በ1992 ዓ.ም. በተደረገው ምርጫ ሂደት፣ ፓርቲው በአንድ የክርክር መድረክ በመሳተፉ የወያኔ/ኢህአዴግን የማስመሰያ ዲሞክራሲ የሚሠራ አልተባለምን? ፀሐፊው በዚያ ሰሞን የተጻፉ ጋዜጦች ርዕሰ አንቀጾችንም ጭምር ለማየት ጊዜ እንደሚኖራቸው ተስፋ አደርጋለሁ።
የኢዴአፓ መድህን አስተሳሰብ ምን ያህል ትክክል እንደ ነበር ማረጋገጫው በወቅቱ የኢዴአፓን የሠላማዊ ትግል ስልት አቋም “ወያኔነት” ያሉ ሁሉ በኋላ በዚህ የትግል ስልት አራማጅነት፣ ኢዴአፓን ጭምር የቀደሙ መስለው መታየታቸው ነው። ኢዴአፓ በሌሎች ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዘንድ የሚታየውን ፀረ ዲሞክራሲያዊነት ባህሪና የፓለቲካ ደካማነትን መተቸት የጀመረው ገና ከጅምሩ ነው። ይህ ያስፈለገበት ዋነኛው ምክንያት ኢዴአፓ ከሌሎች ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች አንፃር ራሱን ለማሳየት ያለው ጉጉት ሳይሆን፤ በኢትዮጵያ ከዲሞክራሲያዊ ሥርዓት መረጋገጥ አንጻር ያሉ ችግሮች ዳር ድንበራቸው የት ድረስ እንደሆነ በኅብረተሰቡ ውስጥ “የፖለቲካ ንቃተ ኅሊና ለመፍጠር” ነው። የኢህአዴግ ፀረ ዲሞክራሲያዊነት ለተቃዋሚዎች የዲሞክሪሲያዊነት ሽልማት ሆኖ ራሳቸውን የሚደብቁበት ካባ እንዲሆን ይፈለጋልን?
ፀሐፊው “ለኢዴአፓ-መድህን አንገብጋቢው ጉዳይ እሱ ራሱ ጠንካራ ተቃዋሚ ሆኖ ያለመገኘቱ ወይንስ የሌሎች ተቃዋሚዎች ጠንካራ አለመሆናቸው?” ሲሉ ጠይቀዋል። ለኢዴአፓ-መድህን የሌሎች ተቃዋሚዎች አለመጠናከር ከራሱ ጠንካራ አለመሆን የበለጠ አንገብጋቢ ሊሆን ባይችልም ለኢትዮጵያ ዲሞክራሲ ጥያቄ ግን ከኢዴአፓ-መድህን መጠናከር ያላነሰ አንገብጋቢ ጉዳይ ነው።
በዚህ ጉዳይ ላይ ፀሐፊው ኢዴአፓን “ልጓም የለቀቀ” ማለት የፈለጉት ኢዴአፓ ጠንካራ ተቃዋሚ እያለ ማየት ተስኖት “የለም” ስላለ ነው? ወይስ ለምን አልክ? ማለታቸው ነው? ይህ ባለፉት ዓመታት ሁሉም ሲለው የነበረው እና አሁንም እየተባለ ያለ ነገር አይደለም እንዴ? በእውነት በኢትዮጵያ ውስጥ የጠንካራ ተቃዋሚ አለመኖር መጠያየቅና መመራመር የሚያስፈልገው ነገር ነውን? ፀሐፊው በመቀጠል “ሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎች ባለመጠናከራቸው የኢዴአፓ ጠንካራ ተቃዋሚ ሆኖ እንዳይወጣ ይታሰባል?” ብለው ጠይቀዋል። ሌሎች ተቃዋሚ ፖለቲካዎች ባለመጠናከራቸው መታሰብ የሚገባውን ያልተረዳ ሰው ለምን ባልገባው ነገር ላይ እንደሚከራከር ለእኔ ግልጽ አይደለም። ኢዴአፓ ብቻ ሳይሆን ሌሎች ተቃዋሚዎችም ባለመጠናከራቸው መታሰብ የሚገባው ሁሉም ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጠንካራ ሊሆኑ ያለመቻላቸው መሠረት ምን እንደሆነ ነው። ስለሌሎች ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ኢዴአፓ እያደረገ ያለው ግምገማ ዓላማ ይህን በተመለከተ አንደኛ፡- በኅብረተሰቡ ውስጥ የ”ፖለቲካ ንቃተ ሕሊና” ለመፍጠር ሲሆን ሁለተኛው፡- ችግሩን በግልፅ አውቆ ለመታገል ነው።
ፀሐፊው “ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጠንካራ ለመሆን ባለመቻላቸው ኢዴአፓን ለምን ተቆጨ ብሎ ክርክር መግጠም አይቻል ይሆናል” ይላሉ። ለምንድነው የማይቻለው? ይቻላል! ቢያንስ ቢያንስ ኢዴአፓ-መድህን ለፖለቲካ ንቃተ ኅሊና መፈጠር ገንቢ ሚና ከተጫወቱ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥን አንዱ መሆኑና ዛሬም በተሣትፎ የሚያምን ፓርቲ ስለመሆኑ የቀረበው ምስክርነት በቂ ምክንያት ሊሆን አይችልም? እርግጥ ነው ፀሐፊው ከቆሙበት መነሻ አንፃር ብቻ ለሚመለከት ሰው አይችልም ይባል ይሆናል።
ፀሐፊው “… አጠቃላይ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ያላቸውን ጥንካሬና ድክመት በመለካትም ሆነ በመተንተን የተጠመደው ውይይት የኢዴአፓ-መድህን ጥንካሬና ድክመት ለይቶ ፓርቲው እንደ ፓርቲ ስላለበት ደረጃ አባላቱ ሊደረስበት የሚገባውን የጠራ ግንዛቤና አቋም ሠርጐ እንዳይቀር ሥጋት ያሳድራል” ብለዋል። በአንድ በኩል ያደረባቸው ስጋት ተገቢ ነው፤ በሌላ በኩል ስለኢትዮጵያ ወቅታዊ ፖለቲካ ጉዳዮች ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ በመገምገም የወደፊቱን የትግል አቅጣጫ መሆን ስላለበት ለመወሰን አድካሚ ሥራ እየሠራ ያለው ፓርቲ የራሱን ድክመትና ጥንካሬ የመገምገም አስፈላጊነትን ያጣል ብሎ ከማሰብ የመነጨ ከሆነ ይህ ከተራ ንቀት የመነጨ ሥጋት ነው። ፀሐፊው ኢዴአፓ የራሱን ውስጣዊ ድክመት አብራርቶ በመፈተሽ፣ ችግሩ ምን እንደሆነ ለማየት የሚፈራበት ምክንያት ይኖራል ብለው ከአሰቡ በእርግጥ ኢዴአፓን በተመለከተ ጥብቅ በሆነ የአስተሳሰብ ስብራት ውስጥ አሉ ማለት ነው።
በ1998 ዓ.ም. ኢዴአፓ የራሱን ችግር በመፈተሽና የነበረውን አካሄድ በመገምገም ብዙ ጊዜ አጥፍቷል። በዚያ ወቅት የዚያ ዓይነት ግመገማ በየጊዜው ሊደረግ የሚገባ መሆኑንም አስቀምጧል። የኢትዮጵያን ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታና የፓርቲውን አቋም አመራሩ በየጊዜው ይመራመራል። ፀሐፊው ስለ እውነተኛ መረጃ አስፈላጊነት ትጋት የሚሰማቸው ቢሆኑ ኖሮ ይህንኑ በቀላሉ ማረጋገጥ በቻሉ ነበር። በአሁኑ ወቅት በመወያያነት ከተያዙ በርካታ አጀንዳዎች እኩሌታው ራሱን ኢዴአፓን የሚመለከት መሆኑ አስቀድሞ በመረጃ መረቦች ተሠራጭቷል። በውይይቱ ማጠቃለያ ላይም ፓርቲው ምን ደረጃ ላይ እንዳለና ድክመቱን ለይቶ ወደ ጥንካሬ ለመለወጥ የደረሰበትን ድምዳሜ ግልፅ ያደርጋል። የድምዳሜ አስተያየት ከመስጠት በፊት ቢያንስ ቢያንስ እየሆነ ያለው ነገር እስከሚጠናቀቅ ጠብቆ ሂደቱ ከተጠናቀቀ በኋላ መሆን የሚገባው አለመሆኑን አይቶ መክሰስ አዋቂነት ነው። ፀሐፊው ይህ የኢዴአፓ-መድህን ግምገማ ውጤቱ ምን ሊሆን እንደሚችል ሥጋት ያደረባቸው ይመስላል።
ፀሐፊው “ኢዴአፓ ህዝቡን ከመለካት ለምን ህዝቡ ውስጥ ያለውን ተቀባይነት ለመለካት እንዳልደፈረ የጠራ አቋም መያዝ አለበት” ብለዋል። በአሁኑ ወቅት በህዝቡ ውስጥ ስለኢዴአፓ- መድህን ያለው አስተሳሰብና የፓርቲያችን ተቀባይነት ደረጃ ከማንም በላይ ኢዴአፓን ሊያሳስበው የሚገባው ጉዳይ ነው። በመጀመሪያ ፀሐፊው ኢዴአፓ በህዝቡ ውስጥ ስላለው ስለራሱ ተቀባይነት ለመለካት የሚሠራ መሆኑን ወይም አለመሆኑን አላረጋገጡም። ሁለተኛ ኢዴአፓ በህዝቡ ውስጥ ያለውን ተቀባይነት ከፍ ያለና ዝቅ ያለ መሆን ፓርቲው የህዝቡን ሁኔታ እንዳይገመግም የሚያደርግ ሊሆን ይችላል እንዴ?
በአሁኑ ወቅት በህዝቡ ውስጥ ስለኢዴአፓ መድህን ግልጽ የሆነው አሉታዊ ሁኔታ የተፈጠረው ከግንቦቱ ምርጫ በኋላ ከቅንጅት ጋር በተያያዘ ነው። ቅንጅትና ኢዴአፓን በተለያዩ ጉዳዮች ቀደም ሲል የጋራ አቋም የነበራቸው ወገኖችም፣ ኢዴአፓ ባነሳቸው ችግሮች አስገዳጅነት አብሮ መሆን አቅቷቸው። ዛሬ አንዱ ስለሌላው ተጠያቂነት እያወሩ ናቸው። የኢዴአፓ ችግር እነኚህን ችግሮች አስቀድሞ አይቶ አቋም መውሰዱ ነው። የወሰደው አቋም በወቅቱ ለብዙዎች የቅንጅት ውስጣዊ ሁኔታን ስላልተረዱ እና ለአንዳንዶች የእነሱን ደካማነት ያጋለጠ በመሆኑ በኢዴአፓ ላይ ባለፉት ሁለት እና ሦስት ዓመታት ይህ ቀረሽ የማይባል የጥላቻ ቅስቀሳ ሲካሄድ ቆይቷል። ነገር ግን ጊዜ ያረጋገጠውና ዛሬ ማንም ሊክደው የማይችለው እውነታ የኢዴአፓ አቋሞች ትክክል እንደነበሩ ነው። የኢዴአፓን ከቅንጅት መነጠልን ያስከተለው ከወደኋላ ውሎ አድሮ ግልጽ ሆኖ የወጣው የቅንጅት ፖለቲካዊ ተፈጥሮ ነው። ኢዴአፓ የዚህ ሰለባ ነው። አንዳንዶች እንደሚሉት የቅንጅትን መፍረስ ያስከተለው የኢዴአፓ ከቅንጅት መነጠል ሳይሆን፤ የኢዴአፓ ከቅንጅት መነጠል የቅንጅት መፍረስ ውጤት ነው። በእነዚህና በሌሎች ጉዳዮች ሁሉ ኢዴአፓ በተሳሳተ መንገድ ርካሽ ተወዳጅነትን ከማትረፍ ይልቅ ትክክለኛ ሆኖ መጠላትን ለምዷል።
ይህ አካሄዱ የኢዴአፓን ችግር ብቻ ሳይሆን የሌሎች ድክመት ጭምር የሚያሳይ በመሆኑ የኢትዮጵያን ፖለቲካ ችግሮች በደንብ ለማወቅ ጠቃሚ ነው። ኢዴአፓ በህዝቡ ውስጥ ያለውን ተቀባይነት ደረጃ በመለካት እና በማወቅ ባለፉት ዓመታት ይህንን ለመለወጥ ምን ማድረግ እንዳለበት አጥብቆ ሲያጠና ቆይቷል። ዋናው ጉዳይ ይህ ለምን ሆነ የሚለው ጥያቄ ነው? ከቅንጅት ጋር በተያያዘ ከግንቦት ምርጫ በኋላ ኢዴአፓ-መድህን በወሰዳቸው አቋሞች በአንድም ጉዳይ የኢዴአፓ መድህንን መሳሳት ማረጋገጥ አይቻልም። ስህተቱ አቋሞቹ የተሳሳቱ መሆናቸው ሳይሆን የተወሰዱበት አስቸጋሪ ሁኔታ ነው። ይህን ዛሬ ጊዜው እየተናገረ ካለው በላይ መናገር አስፈላጊ አይደለም።



