ጠ/ሚ ኃይለማርያም ደሳለኝ PM Hailemariam Desalegnግርማ ካሳ
በሕገ መንግሥቱ መሰረት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥና የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሰብሳቢ ናቸው። የጦር ኃይሎች ኤታ ማጆር ሹምን፣ ተቀዳሚ ጠቅላይ ሚኒስትርን፣ የሚኒስቴር ካቢኔዎችን፣ የፌደራል ፖሊስ አዛዦችን ... የመሾምና የመሻር ሙሉ ሥልጣን አላቸው። ፓርላማውን በትነው አዲስ ምርጫ መጥራትም ይችላሉ። ፓርላማው በፈለገ ጊዜ ጠቅላይ ሚኒስትሩን አውርዶ፣ ሌላ መሾም ይችላል። ጠቅላይ ሚኒስትሩም ተጠሪነታቸው ለፓርላማው ብቻ ነው።

የፓርላማ አባላት፣ በፓርቲያቸው ለእጩነት ቢቀርቡም፣ በሕዝብ የተመረጡ፣ ተጠሪነታቸው ለፓርቲው አመራር አባላት ሳይሆን፣ ለመረጣቸው ሕዝብ ብቻ ነው። በፓርላማው ካሉ 547 መቀመጫዎች ደግሞ፣ የህወሓት አባል የሆኑት 38ቱ ብቻ ናቸው (6.9 በመቶ ብቻ)።

የአቶ መለስን ሕልፈት ተከትሎ፣ በሕጉ መሰረት፣ ፓርላማው አዲስ ጠቅላይ ሚኒስቴር እስኪመርጥ፣ በወቅቱ ምክትል ጠ/ሚ ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ አክቲንግ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ወዲያውኑ መቀጠል ነበረባቸው። ነገር ግን የህወሓት ሰዎች (አንዳንዶቹ የፓርላማ አባል እንኳን ያልሆኑ) "ኢሕአዴግ እንደ ፓርቲ ሳይወስን፣ አቶ ኃይለማርያምን አክቲንግ ጠ/ሚ ማድረግ አይችልም" ብለው አቶ ኃይለማርያም በምክትል ጠ/ሚኒስትርነት እንዲቀጥሉ አደረጉ። በሕገ መንግሥቱ፣ ጠቅላይ ሚኒስትርን የሚሾሙት፣ የፓርላማ አባላት እንጂ፣ የፓርቲዎች ፖሊት ቢሮ አለመሆኑ እየታወቀ፣ ህወሓቶች በዚህ ሁኔታ፣ ለስድስት ወራት አቶ ኃይለማርያም ጠ/ሚ እንዳይሆኑ፣ ማከላከላቸው የሚያሳየው፣ ሕገ መንግሥቱን በአፍጢሙ እንደገለበጡት ነው።

ከስድስት ወራት በኋላ፣ ህወሓት፣ አቶ ኃይለማርያም ጠ/ሚ እንዲሆኑ እያቅማማ ለጊዜው ተስማማ። ነገር ግን በአቶ ኃይለማርያም አንገት ላይ ማነቆ ታሰረላቸው። ሦስት ምክትል ጠ/ሚ እንዲሾሙ ተደረገ። አቶ ደመቀ መኮንን፣ አቶ ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል እና አቶ ሙክታር ከድር።

አቶ ደብረጽዮን እንደ ቴሌ ያሉትን መስሪያ ቤቶች ከመቆጣጠራቸው በተጨማሪ፣ የኢኮኖሚክና የፋይናንስ ዘርፉም በርሳቸው ስር እንዲሆን ተደረገ። በስልክ፣ በኢንተርኔት የምንነጋገረውን ሁሉ አቶ ደብረጽዮን ያዳምጣሉ። ባንኮችን፣ ቀረጥን የሀገር ውስጥና የውጭ ንግድን የማዕድን እና የመብራት አገልግሎትን በሙሉ የሚቆጣጠሩትና የሚመሩት እኝሁ ህወሓቱ አቶ ደብረጽዮን ናቸው።

ከትምህርት፣ ከጤና፣ ከቱሪዝም ከመሳሰሉ ጋር የሚገናኙ መስሪያ ቤቶች ብቻ፣ ለአቶ ሙክታርና ለአቶ ደመቀ ተሰጡ። መከላከያ፣ ውጭ ጉዳይና ደህንነት መስሪያ ቤቶች በአቶ ኃይለማርያም ስር እንዲቆዩ ቢደረግም፣ ከታች ይቆጣጠሯቸው ዘንድ፣ አቶ ቴዎድሮስ አዳኖም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው ተሾሙ። ጀነራል ሳሞራ የነሱ የጦር ኃይሎች የኤታማዦር ሹም፣ አቶ ጌታቸው ደግሞ የደህንነት ቢሮ ኃላፊ ሆነው እንዲቀጥሉ ተደረገ። ሁሉም ህወሓቶች!!!!

"ዝም ብላችሁ ነው የምትደክሙት" ተብለን ነበር። እኛ ግን "አይ፣ አቶ ኃይለማርያም በሂደት ነገሮችን ያስተካክላሉ። ጊዜ ይሰጣቸው። ኢሕአዴግ ውስጥ ጥሩ ልብ ያላቸው ብዙ አሉ" እያልን ተከራከርን። በዚህ አቋማችንም በተቃዋሚ ወገን ባሉት ተተቸን። "ወያኔ ናቸው" እስከመባልም ደረስን። 94% በመቶ የሚሆኑት ህወሓት ያልሆኑ የፓርላማ አባላትም፣ ሕገ መንግሥታዊ መብታቸውን ተጠቅመው፣ ጡንቻቸውን በማሳየት በህወሓቶች፣ ውስጥ ውስጡን የሚሰራውን ፀረ-ዴሞክራሲያዊ፣ ፀረ-እኩልነትና ፀረ-ሕዝብ ተግባራትን ሊያስቆሙ የሚችሉበት ሁኔታ ሊኖር እንደሚችልም አሰብን።

ነገር ግን እንዳሰብነውና እንደገመትነው አልሆነም። ኦሕዴድ፣ የደቡብ ህዝቦች፣ የነአዲሱ ለገሰ የአማራው ድርጅት አባላትና መሪዎች፣ በሚያስገርምና በሚያሳፍር ሁኔታ ለሕዝብ ጥቅም ከመቆም፣ ውሻ ለባላቤቱን እንደሚታዘዘው፣ የጥቂት ህወሓት ባለሥልጣናት ታዛዦችና ባርያዎች መሆናቸውን ቀጠሉ።

በሳዑዲ ወገኖቻችን ላይ በተከሰተው ግፍ ዙሪያ "ተማጽኖ ለጠ/ሚ ኃይለማርያም" በሚል ርዕስ፣ ጠ/ሚኒስትሩ ሕዝቡን እንደ አንድ ሕዝብ እንዲያስተባብሩና ከተቃዋሚዎች ጋር በመሆን፣ ገለልተኛ የስደተኞች ኮሚሽን እንዲያቋቁሙ ጠይቀን ነበር። ነገር ግን፣ ዶ/ር ቴዎድሮስ አዳኖምን፣ ቁልፍ ሚና ሲጫወቱ በየሚዲያው ስንመለከት፣ አቶ ኃይለማርያም ድራሻቸውን አጠፉ። (በነገራችን ላይ ዶ/ር ቴዎድሮስ የህወሓት አመራር ሆነው በህወሓት ድርጅታቸው የሚደረገውን ግፍ እያዩ ዝም ማለታቸው፣ ወይንም የግፉ አካል መሆናቸው እንደተጠበቀና ወደፊት በስፋት የምንነጋገርበት ሆኖ፣ በስደተኖች ዙሪያ እየሰሩ ያሉት ግን ማለፊያ ነው።)

"በዚህ ብሔራዊ ውርደትና ቁስል ወቅት፣ ሕዝብ ከርሳቸው መስማት ሲፈልግ፣ አቶ ኃይለማርያም መሰወራቸው ተገቢ አይደለም። ዛሬ ብቅ ብለው ይሆን?" ብዬ በስማቸው ጉግል ሳደርግና ድረ ገጾችን ሳካልል፣ ያላዳመጥኩት፣ ከአንድ ወር በፊት ገደማ፣ በፀረ-ሽብርተኝነት ሕግ ዙሪያ፣ በእንግሊዘኛ የሰጡትን ቃለምልልስ አገኘሁ። ሊንኩን ነካ አድርጌ ቪድዮውን ማየትና ማዳመጥ ጀመርኩ። ዘገነነኝ። ሰውዬው "የአገር መሪ ነኝ፤ መጽሐፍ ቅዱስ አነባለሁ፤ እጸልያለሁ ..." ይላሉ። ግን በዚህ ቃለምልልስ የሰማሁት የአንድ ዱርዬና ጀብደኛ ቃለምልልስን ነው። አዘንኩ። አፈርኩ። አቶ ኃይለማርያም ሕሊናቸውን፣ ወይንም "አነባለሁ" የሚሉትን መጽሐፍ ቅዱስ የሚያዳምጡ ሳይሆን፣ ሙሉ ለሙሉ የህወሓትን ጥቅም የሚያስጠብቁ፣ ትግሪኛ የማይናገሩ "ህወሓት" መሆናቸው ገባኝ።

"አንዳንዶች ህወሓቶች አጥረዋቸው እያስገደዷቸው ነው" ሊሉ ይችላሉ። እኔ ግን አልስማም። የሚናገሩትን ተገደው ሳይሆን የሚናገሩት፤ በስሜት ጠረጴዛ እየደበደቡና አምነውበት መሆኑን ነው ከንግግራቸው የምንረዳው። ይቅርታ ይደረግለኝና፤ ለእኝህ ሰው የነበረኝ ከበሬታ ፍጹም ተሟጣል። እኝህ ሰው የመጡበትን ብሔረሰብ ያሰደቡ፣ የእግዚብሔርን ስም ያሰደቡ፣ ስለርሳቸው ጥሩ ሲናገሩና ሲጽፉ የነበሩትን "ደጋፊዎቻቸውን" ያሳፋሩ የማይረቡ ሰው ናቸው።

በቃለምልልሱ፣ አቶ ኃይለማርያም ስለ ቦምብ ያወራሉ። እስክንድር ነጋ፣ አንዱዋለም አራጌ፣ ርዮት ዓለሙ፣ በቀለ ገርባ እንዲሁም በፖለቲካ አቋማቸው ምክንያት ሽብርተኞች ተብለው የሚማቅቁ ወገኖቻችን፣ ጀግኖቻችን እንጂ ሽብርተኞች አይደሉም። በአንድ ሰው ላይ አንዲት ጠጠር አልወረወሩም። በቤታቸው የተገኘ ፈንጂ፣ የተገኘ የራዲዮ ኮሚኒኬሽን መሳሪያዎችና ሚስጥራዊ ሰነዶች የሉም። የቀረበባቸው የተጨበጠ ማስረጃ የለም። በዚህም ምክንያት የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ፣ አቶ አማረ አሞኜም "ሽብርተኞች አይደሉም" ብለው ሊፈቷቸውም ነበር። ህወሓቶች "መለስ አደገኛ ያላቸውን መፍታት የለብንም። እዚያው ቃሊቲ ይበስብሱ" በማለት አቶ አማረን፣ በሌላ ዳኛ ለውጠው፣ ፍርደ ገምድል ውሳኔ አስወሰኑ እንጂ። የእነ እስክንድር ወንጀል፣ ሕዝብና ሀገርን መውደዳቸው፣ እውነት፣ ፍትህና እኩልነትን መስበካቸው ነው።



አቶ ኃይለማርያም፣ የ"ህወሓት" መሪ ሆነው እቅጩኝ ነግረውናል። ደንፍተውብናል። "የሕሊና እስረኞች አይፈቱም። የሕግ ሥርዓት፣ መልካም አስተዳደር አይኖርም። የትግራይ ሕዝብን ሳይቀር እያሰቃዩ ካሉ፣ ከጥቂት የህወሓት አመራሮች፣ ከነስብሃት ነጋ ፍቃድ ውጭ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ፍቃድ የለውም። እነርሱ የሚሉትን ተቀብሎ፣ ተሰለፍ ሲሉት በነቂስ እየተሰለፈ፣ ከቤትህ እንዳትወጣ ሲሉት ቤቱ እየተቀመጠ፣ ከወጣም ደግሞ እየተደበደበ፣ ተናገር የሚሉትን እየተናገረ፣ ተናገር ያልተባለውን ከተናገረ እየታሰረ፤ ምረጥ የተባለውን እየመረጠ፣ ምረጥ ከተባለው ውጭ ከመረጠ ደግሞ ድምፁ እየተሻረ፣ የባርነት ኑሮ ይቀጥላል" ነው እያሉን ያሉት።

እንግዲህ አብዛኞቻችን በእርቅና በሰላም በንግግር እናምናለን። በገዢ ፓርቲ ዘንድ በማንኛውም ጊዜ ለእርቅና ለሰላም ዝግጁነት ከታየ እሰየው ነው የምንለው። ነገር ግን ከአቶ ኃይለማያም ጸያፍ ንግግር እንደሰማነው፣ ህወሓት ከሕዝብ ፍላጎት ተቃራኒ የሆነ መንገድ የመረጠ ይመስላል። በመሆኑም፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ የራሱን ዕድል በራሱ ለመወሰን መዘጋጀት ይጠበቅበታል። 90 ሚሊዮን የሚሆን ሕዝብ፣ እፍኝ በሚያህሉ ጥቂቶች፣ ታስሮና መብቱ ተረግጦ መቀጠል የለበትም። የዓለም አቀፍ ሕግ በሚፈቅደው መሰረት፣ ሰላማዊ የእምቢተኝነት ዘመቻ በተቀናበረ መንገድ መደረግ አለበት። በውጭ እና በሀገር ውስጥ የምንኖር ኢትዮጵያዊያን ሁሉ፣ በቤታችን ፀሎት ከማድረግ ጀምሮ፣ የድርሻችንን ለመወጣት መነሳት አለብን። ነፃነታችችን፣ መብታችንን እና ክብራችን ማስመለስ ይኖርብናል።

ስለሰላም፣ ስለእርቅ፣ ስለፍቅርና ስለብሔራዊ መግባባት ስናወራ፣ በዚያኛው ወገን እርቅን የሚፈልግ የሠለጠነ ቡድን አለ ብለን እንጂ፣ ፈርተን፣ ባርነትንና ዘረኝነት አሜን ብለን ተቀብለን አይደለም። የሰው ልጅ እግዚአብሔር ሲፈጥረው በነፃነት ነው። የሰው ልጅ ያለ ነፃነቱ ሰው አይደለም።


ግርማ ካሳ
This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.
ኖቬምበር 25 ቀን 2013

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ