በሽብርተንነት ስም የህዝብ መብቶችን ማፈን ይቁም!
ቅዱስ ዮሃንስ
ፀረ -ሽብርተኝነት ለአምባገነኖች ሁለት ጥቅም ያስገኝላቸዋል። አንደኛ በፀረ- ሽብርተኝነት ስም ከምዕራባውያን ኃያላን ጎን በአጋርነት በመቆማቸው በጥሬ ገንዘብም ሆነ በዓይነት (ለምሳሌ በመሣሪያ፣ በፖለቲካ ድጋፍ) ዳጎስ ያለ ጥቅም ያገኛሉ።
ሁለተኛ ሽብርተኝነትን በመዋጋት ስም የሚያወጡት ሕግ የውስጥ የሥልጣን ተቀናቃኞቻቸውን ለማጥቃት የሚያስችላቸውን ሕጋዊ ሽፋን ይሰጣቸዋል። ስለዚህ ነው ፀረ -ሽብርተኝነት ለአምባገነኖች ከሰማይ የወረደ የተቀናቃኝ ማጥቂያ መሣሪያ ነው የሚባለው። ይህንን ያልኩበት አብይ ጉዳይ ዛሬ ሀገራችንንና ህዝቧን እያስጨነቀ ያለው የወያኔ አገዛዝ የፀረ ሽብርተኝነት ሕግን ከለላ በማድረግ በሰላማዊ ህዝብ ላይ እያደረሰ ያለው የመብት ረገጣ፤ እጅግ የከፋ ደረጃ በመድረሱ ነው።
በሰላማዊ ትግል ዴሞክራሲያዊ የመንግሥት ለውጥ ለማምጣት የሚታገሉ ሰላማዊ ዜጎችን አግባብ ባልሆነና ባልተጨበጠ ክስና ውንጀላ ማሰር፣ አፍኖ መሰወር፣ ንብረትን ማውደምና መውረስ እንዲሁም የአደባባይ ግድያ ባለፉት 22 የወያኔ የአገዛዝ ዘመናት የተለመዱ ተግባሮች ሆነው ቆይተዋል። አሁን ደግሞ ይህ አምባገነናዊና ኢፍትሀዊ ተግባር በሕግ ሽፋን ተጠናክሮ ቀጥሏል።
ለገዥው ሥርዓት የአፈናና የጥርነፋ መዋቅር ተባባሪ ያልሆኑና ለመብታቸው መከበር የሚታገሉ ዜጎች በአሸባሪነት ስም በጅምላ እየታፈሱና እየታሰሩ ይገኛሉ። ታፍነው የተወሰዱና ያሉበት ቦታ የማይታወቀውም ጥቂቶች አይደሉም። ባለፉት ጥቂት ዓመታት ብቻ በሺህዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በሽብርተኝነት ተወንጅለው ታስረዋል። ሰብዓዊ መብታቸውም በማንአለብኝነት እየተረገጠ ይገኛል። ከነዚህ ንፁኀን ዜጎች ውስጥ ብዙዎቹ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ አባላቶች፤ የእምነት መሪዎችና ለሞያቸው ታማኝ የሆኑ ጋዜጠኞች መሆናቸውን ስናይ ደግሞ ዘመቻው በሀገራችን ተጠናክሮ የህዝብን የሥልጣን ባለቤትነት ለማረጋገጥ የሚደረገውን ሰላማዊ ትግል ለመጨፍለቅና ህዝብን ከትክክለኛ መረጃ አርቆና አፍኖ ለመግዛት ታስቦበትና ሆነ ተብሎ የተያዘ ስልት መሆኑን ግልፅ ነው።
በሽብርትኝነት ያለመከሰስ መብቱን በጠብመንጃ ያስከበረው ወያኔ ግን ሰላማዊውን ህዝብ በተለያዩ መንገዶች እያሸበረ የሥልጣን ቆይታውን ለማርዘም ሌት ተቀን እየሰራ ይገኛል። ዜጐችን በማፈናቀል፤ በእምነት ውስጥ ጣልቃ በመግባትና የኢትዮጵያን ህዝብ በዘር፣ በጎሣ፣ በኃይማኖት በመከፋፈል እያፋጀ የሽብር ሴራውን እየፈፀመ ይገኛል። ሰላማዊ ዜጋውን፣ አርሶ አደሩን፣ አርብቶ አደሩን በልማት ስም ተወልዶ ካደገበት እትብቱ ከተቀበረበት ሀገር እያፈናቀለ ለስደት እየዳረገው ይገኛል። ለዚህም የሽብር ሴራው ሰለባ የሆኑት፤ የሚበሉት፤ የሚጠጡት እና በመጠለያ እጦት በየአደባባዩ ሰፍረው የድረሱልኝ ጥሪ እያሰሙ ከሚገኙት ውስጥ የአማራ ብሔረሰብ ወገኖቻችን ይገኙበታል።
እነዚህ ወገኖቻችን ከሀገሪቱ አራቱም ማዕዘናት እየተፈናቀሉና እየተዋከቡ ይገኛሉ። ማፈናቀለ አልበቃ ያለው የወያኔ የሽብር መረብ ወደ እምነት ቦታዎችም በመዛመት ዋልድባን እና የተለያዩ የኃይማኖት ቦታዎችን በማፈራረስ በዓለም ደረጃ እውቅና እና አድናቆት የተሰጣቸውን የሀገሪቱን የኃይማኖት፤ የታሪክ ቅርሶች በማውደም፤ ኢትዮጵያውያን በቀደምትነት በምንታወቅበት እምነታችን ላይ አደጋ በመፍጠር፤ አዋራጅ ድርጊቶችን በንቀት እና በጥላቻ እየፈፀሙ ይገኛሉ።
ከእምነት ቦታዎች ባሻገር በዓለም ደረጃ እውቅናን ካገኙት ታሪካዊ ቦታዎች ውስጥ ተጠቃሹ የታችኛው አዋሽ እና ኦሞ ሸለቆዎች አንዱ ነው። ይህ ታሪካዊ ቦታ ያራዊቶች እና የተለያዩ ደኖች ስብስብ ያለበት ሰፊ የሀገራችን ቅርስ የነበረው ሲሆን፤ ዛሬ ላይ ግን ወያኔዎች በልማት ስም ለውጭ ባለሀብቶች አስረክበውት ድብዛው እየጠፋ ነው።
አምባገነኑ ወያኔ የእስልምና ኃይማኖት ተከታይ ኢትዮጵያውያን ያነሱትን የመብት ጥያቄ ወደ ጎን በመተው በእኔ አውቅላችኋለሁ እብሪት የተሞላ አስተሳሰብ በማፈን ንፁኀኑን ሙስሊም እየገደሉ ብሎም በሽብርተኝነት በመወንጀል እያሰቃዩት ይገኛሉ። ሙስሊሙ ሕብረተሰብ የተቃውሞ ድምፁን ያሰማበትን ዓላማ ምንድነው? ችግሩስ ከምን የመነጨ ነው? ብሎ እልባት ከመስጠት ይልቅ ጥያቄአቸውን በማንቋሸሽ እና በማጥላላት በጠብመንጃ አፈሙዝ የሚመልሱት ይመስል ህዝበ ሙስሊሙን ለከፋ መከራና ስቃይ ዳርገውታል። ለዚህ ድርጊታቸው ደግሞ ሚስጥሩ ንፁኀኑ ህዝበ ሙስሊም ላይ የሐሰት ታርጋ በመለጠፍ አሸባሪነትንና አክራሪነትን እየተዋጋሁ ነው በሚል የማስመሰልና የማታለል ሥራው የምዕራባውያን ሀገራትንና የአሜሪካ ቀልብ ለመሳብና እርዳታ ለማጋበስ ነው። ቢያውቁት ግን ይህ ድርጊታቸው አውሬ እንጅ ሰው አለመሆናቸውን ቁልጭ አድርጐ ያሳያል። ለገንዘብ ሲባል ሰውን ያክል ፍጡር መግደል፤ ማሰርና ማሰቃየት ከአንድ ሰው የሆነ ሰብዓዊ ፍጡር አይጠበቅምና።
ሌላው ወያኔዎች 22 ዓመታት በጠብመንጃ ሥልጣን ላይ ከወጡበት ጊዜ አንስቶ ሲጠነስሱት የነበረው ሽብር የኢትዮጵያን ህዝብ በዘር፣ በጎሣ፣ በኃይማኖት በመከፋፈልና በማፋጀት የኢትዮጵያን ህልውና አንድነትን፣ ማንነትን በማናወጥ፤ የሥልጣን ዕድሜያቸውን ማርዘም ነው። ይህ ሥራቸው ከምን ጊዜውም በላይ በአሁኑ ሰዓት እያፋፋሙትና፤ ሰላማዊውን ህዝብ በዘር፣ በጎሣ፣ በኃይማኖት በማጋጨት የሽብር ሴራቸውን እያስፋፉ ይገኛሉ። ዳሩ ግን ለወያኔዎች ህዝብን መከፋፈል የሚበጅ ቢመስላቸውም የዚህ የሽብር ድራማቸው ተጠቂዎች ግን በፍፁም ልንሆን አልቻልንም፤ ወደፊትም ልንሆን አንችልምም። ምክንያቱም መቻቻል እና በፍቅር አብሮ መኖር መለያ ባህላችንን በፍፁም ይህ ሰይጣናዊ ድርጊታቸው ሊያመክነው ስለማይችል ነው። ይህንን አንድነታችንን፤ ፍቅራችንን የመቻቻል ባህላችንን የበለጠ በማጎልበት፤ ባህላችንን፣ አንድነታችንን፣ ኃይማኖታችንን እየተፈታተነን ያለው የወያኔን የሽብር ስልት በማክሸፍ፤ ለበለጠ ድል እስክንበቃ ትግላችንን ማጠናከር ይኖርብናል።
በመጨረሻም የወያኔ ባለሥልጣናት በፈረጠመ አምባገነናዊ ክንድ ህዝብን በማሸበርና በማፈን የሥልጣን ዘመንን ለማራዘም መሞከር፤ አወዳደቅን ማክፋት መሆኑን ካለፉት አምባገነናዊ ሥርዓቶች ሊማሩ ይገባል! አሁንም በድጋሚ ወያኔዎች ጠንቅቀው ሊያውቁት የሚገባ እውነት የኢትዮጵያ ህዝብ ሽብርተኝነትን በጽናትና በቁርጠኝነት ይቃወማል፤ ያወግዛልም። በፀረ-ሽብርተኝነት ሽፋን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን እየጣሰ ያለውን የወያኔ አገዛዝንም በተመሳሳይ ጽናትና ቁርጠኝነት ይቃወማል፤ ይታገላልም!!!
ድል ለጭቁኑ የኢትዮጵያ ህዝብ!
ያለዎትን አስተያየት በፀሐፊው አድራሻ: This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ይላኩ።



