መልስ ለልጅ ተክሌ "ለነገሩ ለብርቱካንም ለእኛም መታሰሯ ይበጀናል" ፀሐፊ
ገራዶ
የልጅ ተክሌን ጽሑፍ እንደ ወትሮው ሁሉ ዛሬም አነበብኩት። እንደ ወትሮው ሁሉ ዛሬም ተቃወምኩት። በጽሑፉ ውስጥ እንደ ወትሮው ሁሉ ስሜት ከምክንያት ልቆ አየሁበት። ብዙ የመጻፊያ ሰዓት ስለሌለኝ ጽሑፌን ያለመግቢያና ሀተታ በመደምደሚያ ብቻ አጠር አድርጌ እቋጫለሁ።
ጠቅለል አድርጌ ሳየው፣ ልጅ ተክሌ “ብርቱካን ብትፈታ የመታገያ አጀንዳ እናጣለን” ይላል። ልክ አጀንዳችን ሁሉ ብርቱካን ትመስል። ልክ ሌሎች ሁሉ መብቶቻችን ተከብረውልን ብርቱካን ብቻ በመታሰሩዋ የምንጮህ ይመስል። እኛ ብርቱካን ትፈታ ስንል ብርቱካን የምትወክለውን "ነፃነት" ይፈታ ማለታችን ነው። ነፃነታችን ከብርቱካን ጋር አብሮ ታስሮአል ማለታችን ነው። ነገር ግን ብርቱካን ብትፈታ ነፃነታችን አብሮ አይፈታም። ነፃነታችን ከብርቱካን መፈታትም በኋላ ታስሮ ይቆያል። ነፃነታችን ከግለሰቦች እስርና መፈታት ጋር የተያያዘ አይደለም። የነፃነት ትግል ጥልቅ ትርጉም ያለው ነው። ነፃነት ማለት እንደ ዜጋ እኩል መታየት ማለት ነው። ነፃነት ማለት የጥቂቶች የበላይነት የብዙዎች የበታችነት ሥርዓት ፍጻሜ ማለት ነው። ነፃነት ማለት ነፃ ማሰብ፣ በነፃነት መናገር፣ በነፃነት መሰብሰብ ማለት ነው። ነፃነት ማለት የሰውን ልጅ ሰው የሚያደርገው ማለት ነው።
ነፃነት ከግለሰቦች እስር ጋር የተያያዘ አለመሆኑ በቅንጅት እስረኞች መፈታትና መታሰር ታይቷል። የነፃነት አርበኞቹ እነዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ሲታሰሩ ትግሉ ቀጠለ፣ ሲፈቱም ትግሉ ቀጠለ። አርበኝት ብርቱካን ስትታሰር ትግሉ ቀጠለ፣ ስትፈታም ይቀጥላል። ብርቱካን ስትፈታ የምንታገልበት የለንም ማለት የትግሉን ምንነት አለመረዳት ነው። ልጅ ተክሌ ሠላማዊ ሰልፍ ፊት የሚታየውና ብርቱካን ትፈታ እያለ የሚጮኸው አሁን ባለው የነፃነት እውቀቱ ነው። ልጅ ተክሌ ብርቱካን ስትፈታ ትግሉን ያቆማል ማለት ነው። ሠላማዊ ሰልፍ አይወጣም ማለት ነው። በቃ ለእሱ የነፃነት ትግል ከብርቱካን መፈታት ጋር ያቆማል ማለት ነው።
አይ ልጅ ተክሌና ትግል!
ገራዶ



