ገ/ኢ ጎርፉ

ትንሽ ተቆጥቼ፣ ብዕርሬን አንስቼ ጫፉን

አሿሿልሁት፣ ስለቱን አየሁት እንደ ጦር

ተመዝዞ፣ በጣቶች ተይዞ፣ የደራሲ

ምርኩዝ፣ የዕድሜ ልክ ጉዞ፣ ቀለም

አልነበረኝ፣ ፈለግሁኝ፣ ፈለግሁኝ!

ከጭንቅላቴ ውስጥ፣ ከአንጐሌ ጠቀስሁኝ …

 

ረቂቅ ፍልስፍና፣ ጥልቅ ምርምር፣

ወረቀት አልቀረኝ እንደ ሳር ክምር

ጻፍሁኝ! ጻፍሁኝ! ጻፍሁኝ! ምንም ሳላስቀር!

 

አንጐል ነጫጭባ፣ አይደምቅም ቀለሙ፣

አንብቦ የገባው የለም በዓለሙ…

 

ከዚያም ሌላ ዘዴ እያሰብኩ ሳሰላ፣

ተመራመርኩና አገኘሁኝ መላ፣

ጫካ ተደብቄ በቅጠል ከለላ፣

በውድቅት ሌሊት ማንም ሰው ሳያይ፣

ብዕሬን አቅንቼ በደረቴ ላይ

ልቤንን ወጋሁት፣ ደሜን አጠጣሁት፣

ብዕሬም ደም ጠብቶ ወጣ እንደ ግስላ

ከዚያም ስለ ስሜት፣ ጻፈ ሰለ ፍቅር

መንፈሳዊውና ስለ ስጋ ግብር

 

ጻፈ! ጻፈ! ጻፈ! አንድም ሳያስቀር…

ሰው ግን ደሙን ፈርቶ ይጠየፍ ነበር።

 

ይህ ዘዴም አልሠራም፣ ታድያ ምን ይሻላል?

ስለ ሰዎች ችግር መጻፉ ይቀላል?

ብየ ሳሰላስል፣ ሳወጣ፣ ሳወርድ

መታኝ ብዙ ፀሐይ፣ መታኝ ብዙ ብርድ፣

ዳግም ደረቴ ላይ ብዕሬን ወግቼ

ከሐሞት ከረጢት ቀለም አጠጥቼ

እንዲያው የሰው ልጆች ኑሯቸው መራራ

ብዙ ፍዳ ሲያዩ ለቁራሽ እንጀራ

እያልኩ የዓለም ስቃይ ስቆጥር፣ መከራ…

 

እውነት አልፈለጉም ስዎች ግን ፍጹም

የሚሰማኝ ጠፋ፣ አንድ እንኳን የለም!

 

ከዚያም ያ ደራሲ ልምከርህ አለና

ሰገራ ቤት ሄዶ እዳሪ ወጣና

ብዕሩን ጠቀስ አድርጎ ቢለቀልቀው

ሰው ሁሉ ወደደው፣ ሁሉ አደነቀው

ዓለሙን በሞላ አነቃነቀው…

ከዚያም ስማ ብሎ ምስጢር ሲያስረዳኝ

“ጥልቅ አትመራመር፣ ውስጥ አትግባ!” አለኝ

“የኑሮን መከራ፣ ጥላቻ፣ ፍቅር

ሐቁን አታፍረጥርጥ፣ በረቂቅ ምስጢር”

 

“የአንገት ላይ-ላዩን ይወደዋል ሰው

ቡልሺት! ብልሽት! አድርገህ እንዲሁ ተወው።”

ገ/ኢ. ጐርፉ

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ