ከጠፍር አንቀልባ እስከ “ሬሳ ቅምባ”
ጉዶሊያስ
በወጉ መራመድ መዳሕ ሳይጀምሩ፣
ጡጦና ጡት እንኳ መለየት ሳይችሉ፣ በጀርባ እየኖሩ፣
ተንኮል የሚጠቡ፣ ደባ ‘ሚሸርቡ፤ አያሌዎች ናቸው፤ አሉ በሰፈሩ፣ አሉ በየ አገሩ።
ለጥፋት ተጸንሰው፣ ለጥፋት ተወልደው፣ በጥፋት ያደጉ፣
የእናት መከራዎች፤ ደስታን የሚነጥቁ፣ ሕልምን የሚዘጉ፣
ከአስር አንድ አይጠፉም የሰላም ጥላሸት በዓለም የወረጉ።
የድሃ ብሶቱ፣ የአኗኗሩ ዘይቤ፤ የጎጆው ምስጢሩ፣
ደንታ የሌላቸው፤ በድሃ አጥንት ላይ መሰረት የጣሉ፣ እግዜር የማይፈሩ፣
እንደ አሸንፈልተዋል፤ አሉ በሰፈሩ፤ አሉ በሃገሩ።
ለሃገር ምንነት፣ የእምነት መሰረቱ፣
ለነጴጥሮስ ሐውልት፤ ለታሪክ ውበቱ፣
ለገዳማት ክብር፤ ለበረከት ቤቱ፣
ደንታ የሌላቸው፣ ትርጉሙ ትውፊቱ፣
ሰላም የሚነሱ፣ ሕይወት የሚነጥቁ፣
የዘመን ኩብኩባ፤ የሃገር መዥገሮች፤ ታሪክ የሚንቁ፣
ትውልድን ከትውልድ እንደቅል ሚያጋጩ፣
በቋንቋ፣ በቀለም፣ በጎሳ ልዩነት መርዝን የሚረጩ፣
መናበብ፣ መግባባት፣ መተሳሰብ ቀርቶ፣
በቀዬ፣ በጎራ፣ እድገቱ ልማቱ ማንቁርቱ ተዘግቶ፣
እንደ ተልባ ስፍር ወኔያችን የሃገር፣
ተሸርሽሮ እንዲወርድ ዘዴ በመቀየር፣
እያደናገሩ፤ እያወናበዱ ከተማና ገጠር፣
የድሃውን ጉልበት ይመጠምጡታል እንደ ጉያ መዥገር።
አመል ብሎባቸው መቅበጥ በድሃ እምባ፣
ከጠፍር አንቀልባ እስከ “ሬሳ ቅምባ”።
ጉዶሊያስ
Godolias: Wednesday, January 23, 2013



