ነጋ ደሞ ሥራ ልግባ!

ወለላዬ

(በፒ.ዲ.ኤፍ. አስነብበኝ)

ሰዓት ልቆጥር ጊዜ ላምጥ

ልሽከረከር በሃሳብ ማጥ

በማይለቀኝ በዛ አዙሪት

ስንገላታ ልውልበት

ላይመሽልኝ ዛሬም ጠባ

ልሂድ ደሞ ሥራ ልግባ!

 

እንዳይበርደኝ የደረብኩት

በለጥ ይላል ከኔ ክብደት

ይሄም አንሷል ለበረዶ

ተቆልሏል ዛሬም ወርዶ

ልብሴና እኔን ተሸክሜ

ስንቀሳቀስ ስሄድ ቆሜ

የሚጎተት የድሮ ሱቅ

እመስላለሁ አቤት ሳስቅ

 

አለቃዬ ተኮሳትራ

በኔ ሳይሆን በሷው ሥራ

ሠላም ስላት እንዳላየች

ገፋ አድርጋኝ ታልፈኛለች

ሥራው ደሞ ተርመጥምጦ

ሲጠብቀኝ ዓይን አፍጦ

ትቼው ልሄድ አስብና

መለስ ስል እንደገና

ያቺ እናቴ የሀገር ቤቷ

ጠባቂዬ በፀሎቷ

እህቴና ያ ወንድሜ

እህል ሲያጡ እኔ ቆሜ

ያሳደገን እኛን ለፍቶ

አባታችን ፊቴ መጥቶ

ድቅን ሲል ሁሉን ትቼ

ከሥራው ጋር ተስማምቼ

እውላለሁ ምን ይደረግ

ሳፀዳና ስጠራርግ

 

ምን ብሠራ ብዙም ባገኝ

እርካታና ደስታም የለኝ

ወይ ለነሱ አላሳለፍኩ

ወይ ገንዘቤን በቅጥ አልያዝኩ

ጠዋት ማታ ደፋ ቀና

ሲሆንብኝ ሁሉ መና

 

ሀገሬ ላይ ቤት ሠርቼ

ያቺ ጩኒን ቶሎ አምጥቼ

ሁለታችን በርብርብ

አጠራቅመን ይዘን ገንዘብ

ከዚህ ሀገር ቶሎ ልሂድ

እኖራለሁ በትንሽ ንግድ

ወይ አርፌ ትዳር ልያዝ

ይሻል እንደሁ መተጋገዝ

ብዬ እያልኩኝ ሳሰላስል

ከሥራ ጋር ስብሰለሰል

አንዱን ስይዝ አንዱን ስጥል

በአካሌ በመንፈሴ

ተሽመድምጄ ደክማ ነፍሴ

ዛል ብሎ አከላቴ

አዘግማለሁ ወደ ቤቴ

መቼም አያልቅ የኔ ፍርጃ

ደግሞ አለብኝ ያ ደረጃ

እንደምንም ከሱ አልፌ

ከዕዳ ፖስታ ተቃቅፌ

እወድቃለሁ ተሸንፌ

 

እንደገና በሃሳብ ማጥ

ተዘፍቄ ልርመጠመጥ

በማይለቀኝ በዛ አዙሪት

ስንገላታ ልውልበት

ላይመሽልኝ ዛሬም ጠባ

ልሂድ ደሞ ሥራ ልግባ!


ወለላዬ ከስዊድን

This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ