ግጥም በያይነቱ (ዘውገ ፋንታ)
ግጥም በያይነቱ
ዘውገ ፋንታ (This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.)
ፀሐፊዎች ሁሉ፣
ተሰብስበው መጡ፤
ደራሲዎች ሊሉ፣
ጠፍቷል መላ ቅጡ፣
ግጥምን ተራ አሉ፣
ለነሱ ቢያጡ፣
ለኛ ስም አወጡ።
ቦታ አጣ ቂሉ፤
ሲገባ ጥሬው፣
ሁሉም ጠፉ በሉ፣
የበሰሉት አብረው፣
የተቆሉት አረው።
የሚይዘው አጥቶ፣
አቁማዳ ጎተራ፣
ፈሷል በሉ ሸሽቶ፣
ጥሬውም በተራ፣
ማጎሪያውን ፈርቶ።
ነጋዴው ካፈራ፣
ድርሻየን አደራ!
ከቶ በምን ልግጠም፣
ሁሉን እንዲገባ፣
የቱን ቃል ልጠቀም፣
እንዳይሆን ገለባ።
ደራሲ አልባል፣
ፀሐፊ ነኝና፣
ገጣሚ እንዳልል፣
አዝማሪ ሆንኩና።
ጠፋና ሰፋሪ፣
መጣ አሉ ዝንጀሮ፣
አጥቶ አብራሪ፣
ምርቱ ጠፋ አድሮ፣
በላው ወራሪ፣
ወይ እኛ ዘንድሮ።
ሰው ሁሉ ተሳክሮ፣
በብርዝ በቅራሪ፣
ጦጣውም አብሮ፣
ገባ አሉ ወራሪ።
ፀሐፊዎች ሁሉ፣
አልያችሁ ዙሬ፣
ደራሲ ነው አሉ፣
እሱ አንድ ፍሬ፣
ይመስክር ብዕሬ።
ስም የለው ገጣሚ፣
እንደእንግሊዝ ቃላት፣
ለእኛ ተስማሚ፣
ቀኝ ነው በሉት፣
እንደእነሱ ፖየት።
ገጣሚ ምን ይባል፣
ዘምሮ ቢበላ፣
አደራ አልባል፣
እሱ ላሊበላ!
እናቱ ትውለደው፣
ይሄ ሰው ከሞተ፣
ሄደ በሉ ጀግናው፣
ሌላው ሰነበተ፣
እንደው እያቃተ።
ገደሉት አትበሉ፣
ይኖራል ሸፍቶ፣
ይመጣል በሉ፣
ወራሪን ተክቶ።
ተረግዟል ይወለድ፤
የሚሄድ በሰማይ፣
እንደ ዝናብ ይውረድ፣
ሊጥል በራሱ ላይ፣
ጠርጎልን ይውሰድ።
አይወለድ ዳግም፣
በቁሙ የሞተው፣
ለወገን አይሆንም፣
አገሩን የካደው።
ቢረጨው አይበቅል፣
ቢተክለው አይደግ፣
ቢጠብሱት ይቃጠል፣
እሳት ላይ ይማገድ።
እንግዲህ አልገጥምም፣
አኳያ የለኝም።
ከቶ አልቀኝም፣
ተርጓሚ የለኝም።
በቃ አልዘምርም፣
ተቀባይ የለኝም።
በቅቶኛል አልጮህም፣
ዜማ ነው አልልም።
ሳይወስደኝ አልተኛም
ሳልሞትም አላርፍም።
ፀሐይን አላፍርም፣
እንቅልፍን አልፈራም።
ስጓዝ ቢጨልምም፣
ካልነጋ አልልም።
ቆሜአለሁ አልተኛም፣
ብጋደም አልፈራም።
እውር ነው አይበሉኝ፣
አላይም አልልም፣
ጠንቋይ እንዳይሉኝ፣
አርቄ አላስብም።
ዘውገ ፋንታ (This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.)
ታህሳስ 2003 ዓ.ም.



