ፍቅር ግን ከሌለህ ... (ጌታቸው አበራ)
ፍቅር ግን ከሌለህ ...
(ለመለስ ዜናዊ እና ለጭፍን ደጋፊዎቹ)
ጌታቸው አበራ (መስከረም 2003 ዓ.ም. / ሴፕቴምበር 2010)
. . . ምንስ ብትኳኳል፣ “ቅንድብህ” ቢያስንቅም፣
ጭንቅላትህ አብጦ በ”ዕውቀት” ቢፈነዳም፣
መጽሐፉ እንደሚለው ...፣
ምንስ ዋጋ አለው?
ፍቅር ግን ከሌለህ፣
የከንቱ ከንቱ ነህ!
እንኳንስ ባንተነት ...
ክፋትን ተሞልተህ፣ ትዕቢትን አዝለህ፣
ቂም ጥላቻ ቋጥረህ፣ ባሰት ባህር ዋኝተህ፣
ንቀትን ተላብሰህ፣ የሰው ልጅ መብት ገፈህ፣
የህዝብ ድምፅ ሰርቀህ፣ ያገር ክብር አዋርደህ፣
ያማሩ አበቦችን ህጻናትን ቀጥፈህ፣
የስንት እናቶችን ሕይወት አጨልመህ፣
ንጹኀን ዜጎችን በወህኒ አጉረህ፣
ባምባ-ገነንነት አገር አሸብረህ ...፤
… ደንቁረህ ይቅርና ...
በመላዕክት ልሳን ብትናገር እንኳ፣
ትንቢትም ቢኖርህ ምስጢር እሚፈታ፣
ተራሮች እሚንድ እምነት ብትገነባ፣
ስጋህንም ክደህ ከሳት ብትገባ ...፣
አልታደልክም እንጅ፤
ይህን ሁሉ ጥበብ ብትታደል እንኳ ...፣
ፍቅር ግን ከሌለህ፣ …የለውም እርባና!
ጌታቸው አበራ
መስከረም 2003 ዓ.ም.
(ሴፕቴምበር 2010)
ይህቺን ግጥም የጫርኳት፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ላይ በመመርኮዝ ነው (ቆሮ 1 ምዕ 13 ቁ 1-3)።
ታላቁንና ክቡሩን ያገር ጉዳይ ትተው፣ “የእንግሊዘኛ ሰዋሰው ችሎታውን” እያደነቁ፣ “ፐ! -መለስ! ...” እያሉ ለሚነሆልሉ ጭፍን ደጋፊዎቹ ...፣ ትዕቢት ከወረሰው፣ ንቀት ከጨረሰው ...፣ ፍቅር ግን ከሌለው፣ “ይህን ሠራ ...” ብለው ለሚመጻደቁ፣ ቢሰራላቸው እንኳን፣ ፍቅር ግን ከሌለው፣ ምንም ዋጋ እንደሌለው ቢረዱ፣ በዚህ ጥቅስ አማካኝነት ለማስታወስ ነው።



