“ጊዜ ዱሮ ቀረ!”

ዳግማዊ ዳዊት

ሰው ተስፋው ሲቀጭጭ - ነገ ሲያስጨንቀው

ዛሬ መከራውን - ግፉን ሲያስቆጥረው

“ጊዜ ትናንት ቀረ! ጊዜ ዱሮ ቀረ!“ - ይሆናል ምስጋናው።

 

ጊዜ ተስፋ ዳምኖ - የሚዘንብ ሲመስል

ሰው ዛሬ እየከፋው - ይታያል ፈገግ ሲል።

 

ታዲያ ማነው እርሱ - ተስፋን የሚዘራ

በዛሬ የሚተኩስ - የሰው ባላጋራ

ምድር ነው ወይስ ሰው - የተስፋ ጠላቱ

ሰው ነው ወይ እርጉሙ - ወይንስ ምድሪቱ?

 

እምቅ ሀብት ሳይኖራት - ጃፓን ስትበለጥግ

ቻይና እልፍ ህዝቦቿን - አልብሳና አጉርሳ - በፍጥነት ስታድግ

አሜሪካ ኃያል ስትሆን- በአራት ዘመን

የሐበሻ ምድር በችግር ሲታመስ - ሲተላለቅ ወገን

ሀገርም ቢኖረው - መንግሥትም ቢኖረው - ሦስት ሽ ዘመን

ማሞገስ መኮነን - ሰውን ወይስ ጊዜን - ወይንስ ምድሪቱን?

 

ሐበሻ ሐገር ኖሮት - በታሪክ ላይ ሲጣፍ

አውሮጳ ያን ጊዜ - አልወረደም ከዛፍ

ካሌብ ምድረ-ዐረብን - አፍሪካን ሲያስገብር

የአሜሪካ ምድር - አልተቀኘም ነበር

ጉድም እንደ ጅራት - ከኋላ ነውና

ሐበሻ ሲዋረድ - እያየን ነው ገና።

 

እናም “ዱሮ ቀረ!” የሚባለው ጊዜ

ነውረኛ ንግግር - ሲገፋም አባዜ

አካፋን አካፋ - የምንል ከሆነ

ሰው ነው እንጅ ክፉ - ጊዜ ምን በደለ?

 

ትናንት ከሚባለው ትናንት ጀምሮ

ምነው አላቆመም - የሐበሻ ሮሮ

ሲያሳድደው ያለው - ከቦረና አስመራ

ከሃርጌሳ አንስቶ - ሴቲቱ-ሁመራ

ለህዝቡ ጦርነት - ሆኖበታል ሥራ።

 

ጊዜም እንደወተት - ሲገፋ ሲገፋ

ከትናንት የሚሻል - ዛሬ እሚባል ጠፋ።

 

ሰው ተስፋው ሲቀጭጭ - ነገ ሲያስጨንቀው

ዛሬ መከራውን - ግፉን ሲያስቆጥረው

“ጊዜ ትናንት ቀረ! ጊዜ ዱሮ ቀረ!“ - ይሆናል ምስጋናው።


ዳግማዊ ዳዊት

መስከረም 2003 ዓ.ም.

This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ