ሺ ዓመት

This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

ሰከንድ ደቂቃ ሰዓቱ ተቆጥሮ

ቀን ሣምንታት ወራትን ጨምሮ

ሚሊኒየም ሄደ ዓመታት ደምሮ

 

ስንቶቹ ነገሡ ወይ ንጉሥ ተባሉ

ከዘመን ዘመኑን እየተካፈሉ

 

ጥጋብ ደስታ ነበር እገሌ ሲነግሥ

በጦርነት በልቂት ሌላው ሲታወስ

እርጥብ ነው ዘመኑ ቀና ነበር ኮቴው

ያማ ደረቅ ጊዜ አካካጅ ዘመን ነው

 

ጭቆና ተጠልቶ ሽፍታነት ሲኖር

ያም ዘመን በስሙ ተጠርቶ ነበር

 

ኃይማኖት አጥንቶ ለኃይማኖት ተገዝቶ

ሁሉም ያልፋል ያለም በየዘመን ታየቶ

 

ደግ ክፉም ፍጡር በየዘመን ገብቶ

ዘሩን ሲያስተላልፍ በየፊናው ዘምቶ

 

መውደቅ መነሳቱ መወለድ ማለፉ

ዕድሜ የሚለካበት በየድርጊት ዘርፉ

መቁጠሪያ ነበረ ዘመን መለኪያው

የየዝንባሌው የየአምልኮቱ ጅምር መነሻው

 

በሽታ እንኳን ባቅሙ ስም እየፈረጀ

በዕድሜ ሳይወሰን ድንገት እያጃጀ

እሱም ጊዜያቶቹን ዘመን እያወጀ

ብቅ ሲል ታድሶ ሲከርም እያረጀ

እስኪገኝ ፈውሱ የሰውን ዘር ፈጀ

 

ዘመነ ስደትም የፍጡር ሀገር ሰፍቶ

ቀየ ያስጥል ጀመር ጥበቡን ዘርግቶ

በዘመድ በትዳር በዲቪ በሥራ

በጉብኝት ይሁን በሃጅና ኡምራ

በሥራ በትምህርት በሥልጠናም ስም

ያገር ፍቅር ስሜት ተብሎ አፈርቃም

 

ዘመኑ አሳይቷል ሀገሮች ተባዝተው

እርስ በርስ ሲፋጩ ዘር ጎሣ አበጃጅተው

በትምክህት መኖር ቅንነት አፍርሶ

በእበልጣለሁ ጎራ እራሱን ኮፍሶ

ይበልጣል ያለማ ጥቅሙን አገናዝቦ

ሲዋሃድ አይተናል አንድነቱ አብቦ

 

አላፊና መጭን በወጉ ለክቶ

ቁም ነገር ቢሠራ ሰው ተረጋግቶ

በኖረበት ዘመን በየፊናው ተግቶ

በሠላም በፍቅር በኩልነት ጠንቶ

ጥበቡማ ቢኖር ልኩን ብንሰፍር

እድገታችን በውል ፈር ይይዝ ነበር

 

ጊዜ የሰጠው ሰው ዘመን እዘዝ ያለው

ለራሱ እንደሚወድ ባያስብም ስለ ሰው

ቀና ቢሾምበት ቅን የሚያስተጋባ

ሹምም ባያበዛ የግፍ ባልደረባ

ጥቅሙን ብቻ የሚያይ ተንኮል አረብርቦ

ታዛዥም ሰው ባይንቅ ቅናትን ደርቦ

 

ባዎንታም አሉታም ለሚገኝ ድል

በቅን መንፈሥ የመቀበል ባህል

ቢዳብር ቢስፋፋ በየዘርፉ እርምጃ

ሐቅ ግልፅ ቢሆን ያለምንም ምልጃ

ለማሻሻል እንጂ ሳይሆን ለመናናቅ

ማሸነፍ መሸነፍ ያለ እንደሆን ልናቅ

 

ላለፈ ምስጋና ቢሰጠው ቅድሚያ

መጭን ብናደርገው ጉድለት ማሻሻያ

ምሳር ከማብዛቱ ያለፈን ለመጉዳት

ያለውን ሥርዓት ብንጠርብ በብልሃት

 

ሁሉም ቢከፈለው ልክ እንደልፋቱ

 

የዘመን መሰላል መውጪያ መውረጃው

ያራምደን ነበረ በቅን ብንይዘው

ሁሉም በየመልኩ አያያዥ ሰንሰለት

እንዳለው ተፈጥሮ ሁሉም ተገንዝቦት

ጣፍጦ የተሠራ የዘመን መሠረት

ልክ እንደ ቅመሙ ቢመጣጠንለት

 

በመከባበሩ በመደጋገፉ በመተሳሰቡ

ለሁሉ የሚያመች አራማጅ ቢክቡ

ያለፈን በፀፀት መጭን በቂም በቀል

ከመቀበል ይልቅ በይቅርታ ቢቀል

 

ለትውልድ የሚያልፍን ዘላቂ ግብር

በጥናት ወይ በንድፍ ውጥን ማስመር

ቢበላሽ ይበላሸ ባይሆንም ይቅር

ብሎ አያዘልቅ ጉዞን አለ መጀመር

 

ሁሉም የየአቅሙን ቢያካፍል ቢያዋጣ

በቅን ለመሰለፍ ቢሞክር ቢቃጣ

ስም የሚያሰጥ ድርጊት ተዝካር የሚሆን

ያታደል ይሆናል መጥሪያ ለዘመን

 

ግልፅ እንደመስታወት አሽሙር ያልሸፈነው

የውይይት መድረክ ንቃት ያነፀረው

አፈንጥቆ የሚያሳይ የእውቀትን ጮራ

ሁሉን እንደየዕድሜው በቅድ ያሰማራ

ቢዳረስ ላገሬው ለትውልድ ቢዘራ

ያ ዘመን መልካሙ ተብሎ እስኪጠራ

 

የሰው ልጅ አንጎልም መጥቆ በጣም ነቅቶ

ቴክኖሎጂ ረቆ ማወቅ ማሳወቁ ብሩህ ሆኖ ጎልቶ

ጠቅሞ መጠቀምን ማፈስ ማጨድ ዘርቶ

በጎሣና በዘር ከሚደክም አንጎል ነፃነት አራቁቶ

 

ምልክት ያለበት መጠሪያው ያማረ

ራሱን ባዎንታ መልኩ ያዘከረ

ህዝብንና ሀገርን ከሕመም ያሻረ

ስምና ሞገስን የሰጠ የቸረ

 

ቢሆን መጭው ዘመን ፀጋ ያለበሰ

ሌላ ዕልፍ ዘመን ሀገር ያስሞገሰ

ባንኖርም ልናኖር ታሪክ ተመዝግቦ

ለመጭው አክባሪ ሺ ዓመትን አስቦ


This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ