አረንጓዴ ሰው

ዳግማዊ ዳዊት (ጥቅምት 2002 ዓ.ም.) This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

“ህዝባችን ተሰብሰብ - ለሰበሩ ዜና

ባለፀጋው ጻድቅ - መሆኑ ይሰማ

ይኸ ባለፀጋ - ይኸ ያገሬ ሰው

ይኸ ባለሆቴል - ይኸ ወርቅ አንጣሪው

የሥራ ዕድል ፈጥሮ - ልቤን አስደሰተው”

 

ብሎ ጋዜጠኛው - ፅፎ አነበብኩና

ስለዚህ ባለሀብት - ሃሴት አረግሁና

እኔም የበኩሌን - ለገስኩት ምስጋና

 

“አንደበት ይከፈት - ጆሮዎች ያዳምጡ

ለዚህ ባላፀጋ - ሽልማቶች ይምጡ

በል እግዜሩም ስማ - ፅድቅ ተለውጧል

ከዛሬ መነኩሴ - ባላፀጋ በልጧል

“ፀሐይ ትቁምለት - ትዘግይ ጨረቃ

ይኸ ባለፀጋ - እስኪል ድረስ በቃ

እስከሚበዛለት - ሀብቱ እስከሚስፋፋ

ሌሊቱም ቀን ይሁን - ብርሃን አይጥፋ።”

 

ብዬ ምስጋናየን - ሳዥጎደጉደው

ይኸ የአጎቴ ልጅ - የተበሳጨው

ከእኔ የተለየ - ሚስጥር ያውቅ ኖሮ

እንዲህ ሲል ነገረኝ - ሃሳቡን ቀምሮ።

 

“ለተራበ ማብላት - ለታረዘ ማልበስ

ታማሚ ማጽናናት - ለችግርም መድረስ

መጾም መፀለዩ - ቅንነት ማሰቡ

መች ሆኖ ተገኘ - የዛሬ ሰው ግቡ!

 

“ከደሃ ቀምቶ - ከደካማ ዘርፎ

ቢሞላ ቢተርፍም - ከመጠንም ተርፎ

ወርቅና አልማዝ ይዞ - ነዳጅ አስቆፍሮ

ሆኖ መገኘት ነው - ካለመጠን ከብሮ

ሰውን ሰው ያሰኘው - የለየው ዘንድሮ።

 

“የሰው ልጅ ሲፈጠር - በጌታዬ አምሳያ

ነበረ ለታላቅ - ለክብር ማሳያ

ዛሬ የሰው ልጆች - ወረቀትን ፈጥረው

ቁጥር ጽፈውበት - አንድ ሁለት ብለው

አረንጓዴ ቀለም - ቅርጻ ቅርጹን ስለው

ከራሳቸው በላይ - ለብር ክብር ሰጥተው

መኖር ጀምረዋል - ከሱ በታች ሆነው።

 

“መልኩን ሳፈላልግ - ጠይም ወይም ቀዩን

ቀረና የእርሱነት - መምሰል አምሳያውን

ንዋየ ፀሎቱ - ገንዘብ ሆኖ አምላኩ

አረንጓዴ ሆኗል - ባለፀጋው መልኩ።

 

“አንተን መሳይ መንጋ - እናንት ኋላ ቀሮች

ጠይምና ጥቁር-ቀይ … የምትሉ ሰዎች

የሰው ልጅ ውበቱ - የሚያምር ቁመናው

አረንጓዴ ሆኗል - የእርሱ ሁለመናው።

 

“ገንዘቡ ዳኛ ነው - ፖሊስም ጠበቃ

ኃይሉ ልክ የሌለው - ተቆጥሮ አያበቃ

ፍትህና ክብር - ገዥ በገንዘቡ

ይኸ ባለፀጋ - ባለ ወርቅ ቅቡ

ሕጻን ሴት ያገባው - ሕፃን እቁባቱ

የሰው ሚስት የቀማው - አድርጎት መብቱ

ሁሉ ሰው ጌታዬ - ብሎ የሚጠራው

እርሱን የሚያደንቅ - ጋሸ ጋዜጠኛው።”

 

ብሎ ተናገረ - ይኽ የአጎቴ ልጅ

ስለ አረንጓዴው ሰው - ለሁሉ እንደማይበጅ።

 

ትናንት ህጻን ሆኘ - ሳድግ በሰፈሬ

የሰው ልጅ መጠሪያው - ልዩ ነው ከዛሬ

አይደለ በልብሱ - በፀጋ በሀብቱ

አይደል በቁመናው - ተክለ-ሰውነቱ

አይደል በትምህርቱ - በዕውቀት ሊቅነቱ

ሰው በሰውነቱ - ሲለካ የማውቀው

ፍፁም ልዩ ነበር - ዛሬ ከምናየው።

 

አንገቱን ለፍትህ - አንደበቱ ለእውነት

ውሸትን የጠላ - ግፍን የሚጋፈጥ

ከክፉዎች ሸንጎ - ፈጽሞ የራቀ

አንቱ የተባለ - በሀገር የታወቀ

ነበር የሰው መልኩ - ለእውነት መቆሙ

ትናንት የምናውቀው - የሰው ልጅ መልካሙ

ዛሬ ተለየና - ውበት ተቀይሮ

ዓይናችን የሚያየው - ብር ሆነ ዘንድሮ።

 

እስኪመለስ ድረስ - ዓይንም ወደ ድሮው

ስንናፍቅ ከዋልን - ገንዘብን እንደሰው

እውነትም ይዛባል - ፍትህ ይሰወራል

ገንዘብ የሀገር ዳኛ - ጠበቃ ይሆናል

 

አንተ ጋዜጠኛ - አንተ ወሬ አቀባይ

እስኪ እንደ አጎቴ ልጅ - አንተም እውነቱን እይ

ያ ባለፀጋ ሰው - በዓለም የከበረ

እውነቱን አሰማን - ማን እንደነበረ?


ዳግማዊ ዳዊት

ጥቅምት 2002 ዓ.ም.

This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ