ሳላገባት ፈታኝ (ዳግማዊ ዳዊት)
ሳላገባት ፈታኝ
ዳግማዊ ዳዊት - መስከረም 2002 ዓ.ም. This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.
ጅሉ ማንነቴ - ጉድ አድርጎኝ ሄዶ
ልቤ ይጨነቃል - የጠላኝን ወዶ።
የትውልድ አሻራ - ሰፊው ስድስት ኪሎ
ምነዋ ጠበብከኝ - ሲጨንቀኝ ዘንድሮ?
ልቤ ተስፋ አይቆርጥ - አላስቀምጥ ቢለኝ
ካለችበት ልሄድ - ወሰንኩ ተነሳሁኝ
ምሽት አንድ ሰዓት - ከክፍሌ ወጥቸ
ማየት ፈለግሁና - ካለችበት ሄጀ
ጫማየን ተጫማሁ - ተበጠረ ጠጉሬ
ምን አለ ቢቀናኝ - ብትለመን ፍቅሬ።
…
ከመኝታ ክፍሌ - በጥድፊያ ወጥቸ
የሴቶችን ሕንፃ - አሻግሬ አይቸ
ድንገት ቆማ ባያት - ብዬ በማሰቤ
በግ ተራን ፈተሽኩት - ሁሉንም ቀርቤ።
ራስ መኮንንን - አዳራሹን ሳልፈው
ያዩኝ ያክል ሆኖ - የሙት መንፈሣቸው
አስታውሶኝ መጸለይ - አንዴ ቆም አልኩና
ጀመርኩኝ ጸሎቴን - አምላኬን ልመና
ፈጣሪ እንዲሰማ ውስጧን እንዲያዘጋጅ
እኔና እርሷነቷ - ሆነን የልብ ወዳጅ።
ጸሎቴን ፈጽሜ - ብዬ ዓለም … ወዓለም
“አሜን!” አልኩኝና - ገባሁኝ አዘግም
ወረድኩ ወደ በሩ - ታጠፍኩ ወደ ግራ
ልቤ እሷን ፍለጋ - ዓይኔ ተሰማራ
ኬነዲ በሩ ላይ - ከነሣራ ጋራ
አየኋት ቅድስቴን - ቆማ ስታወራ።
ፈራ ተባ እያልኩኝ - ወደዚያው አምርቸ
ሠላምታ አቀረብኩኝ - እጆቸን ዘርግቸ
ሣራ “ሠላም” ብላ - እጇን ስትሰድልኝ
ጨበጥኩት ቀኝ እጇን - ጠጋ ስትልልኝ
እጀን መለስኩና - ስፈልግ ቀኝ እጇን
ቅድስት “ሃይ!” ሳትለኝ - አዞረችው ፊቷን።
ብቻችን ሆነን - እኔና ቅድስቴ
እንድንነጋገር - ሆነና ምኞቴ
ይቅርታ ጠየኳት - ሣራ እንድትለየን
ለእኔና ለቅድስት - ዕድል እንድትሰጠን።
“ሠላም” አልኳት ውዴን - መልሷን ባገኝ ብየ
ዓይኖቿን በዓይኖቸ - ለምኘ አባብየ።
“ተቀልዷል” አለች - ጉንጮቿ እየቀሉ
ምን ነካው ብላ ነው - ፍቅሯን ያላመሉ።
“ምንድን ነው ችግሩ” - ብየ ብጠይቃት
ለካስ የእኔው ጉድ ነው - እርሷን ያበሳጫት
ዘመኑ ሆነና - የቡድን ጨዋታ
ከሌሎች ሴቶች ጋር - መቃለዴን አይታ
የሚወዳት ዓይኔ - ሌላ ሴት አየና
የግል ጣፋጭ ፍቅሯ - የቡድን ሆነና
ጣዕሙን ማጣቷ ነው - ያበሳጫት ለካ
የእኔም ማንነቴ - በቡድን ተለካ፡
“እውነተኛ ፍቅር - አብሮ የሚያረጀው
በግል ነው እንጅ - መቸ በቡድን ነው”
ብላ ስትቆጣኝ - ዓይኖቿ እንባ ቋጥረው
እለምናት ገባሁ - ጥፋቴን አይቸው።
“ቅድስት የእኔ እመቤት - የልቤ ፀሐይ
ባክሽ ተለመኝ - መጨነቄን እይ
ልክ እንደ ድሯችን - እንደ ዓምና ታቻምና
አንድ እንሁን ውዴ - ደግመን እንደገና።”
እጇን አወናጭፋ - በድርጊቴም አዝና
ትናገር ቀጠለች - ደግማ በጥሞና
“እኔን በእኔነቴ - ቅድስት በመሆኔ
ብታከብር ብትወደኝ - ደስ ባለኝ እኔ
ከሌላው ተምረህ - የአንተ ያልሆነውን
ምን ብለህ ሞከርከው - ማፍቀሩን በቡድን
ፍቅሬ የግሌ ነው - የግል መብቴ
ከዚያ ነው እሚጀመር - የእኔ ማንነቴ
ይህን ስለረገጥህ - መቧደንን ወደህ
በቃኸኝ ከእንግዲህ - በል እኔም ልቅርብህ።”
ብላ ተለየችኝ - ጨክና ቅድስቴ
አስከፍቷት ኖሮ - አዲሱ እኔነቴ
ኬነዲ በር ላይ - ባለሁበት ጥላኝ
ቅድስቴ ተጓዘች - ሳላገባት ፈታኝ።
መታሳቢያነቱ፣
በኤች.አይ.ቪ. ኤድስ (HIV - AIDS) ሕይወታቸውን ላጡ፣ … እልባት ያላገኙት የቡድንና የግለሰብ መብቶች መልክ ይዘው ትርጉም ያለው ጉዞ በሀገራችን እንዲጀመር ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ለሚታገሉ ሁሉ ይሁንልኝ።
ዳግማዊ ዳዊት
መስከረም 2002 ዓ.ም.
This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.



