ምሕረት ዘገዬ (ከአዲስ አበባ)

Ginbot 20
የግምቦት 20 የሙዚቃ ምርጫ። (ምስል ቅንብር፣ ኢዛ)

ይህ በዓል የማን እንደሆነ አሁን ገና በደምብ ገባኝ! “ኢሕአዲግ” የሚባለው የሕወሓት መሀል-አገራዊ የሠርክ መጠሪያም የለየለት ቅጥፈት መሆኑን በዛሬዋ አጋጣሚ ይበልጥ ተገነዘብኩ።

አለቃየ አንድ አጣዳፊ ሥራ አዞኝ ከጧት ጀምሬ የተደፋሁ አሁን ድረስ አለሁ - ከቀኑ 11 ሰዓት፣ ዛሬ ግንቦት 22 ዕለተ ቅ. ዑራኤል 2009ዓ.ም ነው። ፍሪጅ ውስጥ ገብቶ እየተከበረ ያለው የግምቦት 20 የወያኔ በዓል በየቦታው ፍሪዳ እየተጣለ አጨብጫቢዎቹንና አባላቱን ሆዳቸውን በሥጋና በአልኮል እየቀበተተ አሁን ድረስ ቀጥሏል፤ ከዘረፋና ከሰሜናዊ አቅጣጫ ጉዞ የተረፈው የአገር ሀብት በነቀዝ የወያኔ አጋፋሪዎችና ጀሌዎች እየረተመልህ ነው ወገኔ። ይህን ማስታወሻ የምጽፍላችሁ በቅርቤ በዚህች ቅጽበት እየተከበረ ከሚገኝ የግንቦት 20 በዓል ላይ ተመርኩዤ ነው። ዘፈኑ እንደጉድ ይቀልጣል፤ ጩኸቱም እንደጅራፍ ይኖጋል። እውነትም ሶዶምና ገሞራ አዲስ አበባ ገብታለች ያስብላል፤ ሚሊዮኖች የሚልሱትን የሚቀምሱትን አጥተው በርሀብ አለንጋ ይገረፋሉ - እዚህ መቀሌ ላይ - ማለቴ አዲስ አበባ ላይ ደግሞ በጮቤ ረገጣ ዓለም ታልፋለች፤ በጭቁኖች ገንዘብ ዳንኪራ ይረገጣል - ምን ለማምጣት? ብለህ ጠይቅ - መናገር ሳያስፈልግ ዕድሜ ከሰጠን በቅርቡ አብረን የምናየው ይሆናል። ይህ ጥጋብ እነዚህን ተምቾችና አልቅቶች በቁም ሲዖል ካላወረደ ምላሴ ጥቁር አይደለም ማለት ነው። ለነገሩ ለዚህ አልተነሳሁምና …። አሃ! ሃሜታየን በብዕር እየከተብኩ መሆኔን በቴሌፓዚ የርቀት መገናኛ ተረዱ መሰለኝ ገና አሁን የይሁኔ በላይን “ነይማ ነይማ” የሚለውን ከፈቱ። …

ለዘፈን ግድ ኖሮኝ አይደለም። የማንም ይከፈት አይከፈት ግድ አይሰጠኝም፤ ጊዜውም ሆነ አጠቃላይ ዘመኑ የጸሎት፣ የምህላና የዋይታ እንጂ የዘፈንና የዳንኪራ እንዳልሆነ ጠንቅቄ የማውቅ ዜጋ ነኝ። ዕድሜየም ልምዴና ተሞክሮየም በተለይ በአሁኑ ሰዓት ለዘፈን ተጨናቂ እንድሆን አያደርጉኝም። ትዝብቴን ለመተንፈስ ብቻ ነው። እንጂ ከስቃይ በስተቀር ጥጋብን የማይችሉት ወያኔዎች አገርን ከተቆጣጠሩበት ጊዜ ጀምሮ በተለይ ሌሊት ሌሊት ሆስፒታል አይሉ ትምህርት ቤት፣ ሠፈር ውስጥ አይሉ የአምልኮት ሥፍራ ለመዝናናትም ሆነ ለመረበሽ ምቹ በሆነው የጋራ የትግርኛ ምታችን (rythm) በአሥረሽ ምቺው አገር ምድሩን እንደሚረብሹ ማንም ያውቃል፤ “ችለናቸውማል”። “ወደሽን ቆማጢት” አሉ? ... ሆ! ኧረ ማን ነው በማን ግዛት ተቆጭ ገልማጩ?

በአጠገቤ የሚካሄደው የወያኔ በዓል የተጀመረው ምሣ ሰዓት አካባቢ ነው። ከዚያን ሰዓት ጀምሮ የሚከፈተው ዘፈን ከ90 በመቶው በላይ ትግርኛ ነው - ሆን ብዬ እየተከታተልኩና በግብዝነታቸውም በሣቅ እየተንፈረፈርኩ ስለነበር የምለው ነገር እውነት ነው - ኩነኔውን ለኔ ጥላችሁ እንደ አንደኛ ደረጃ እውነት ውሰዱት ከፈለጋችሁ። … አሁን ደግሞ ለስንተኛ ጊዜ እንደሆነ አላውቅም “እምበር ተጋዳላይ” እየተዘፈነ ነው። የቀጥታ ሥርጭት ላይ ነው ያለሁት - በጽሑፍ። ዛራቸው ተነስቶ እየደለቁ ነው። ድንኳኑ የጠበባቸው ይመስላል። አጠገቤ ደግሞ አንድ የቢሮ ተጋሪ የቴዲን “ኢትዮጵያ” ከፈተብኝ። በ”እምበር ተጋዳላይ”ና በ“ኢትዮጵያ” መሀል እየተረበሽኩ ነው የምጽፍላችሁ። ለነገሩ ስበጠበጥ የኖርኩትና ብርቅዬውን ዕድሜየን ያገባደድኩትም በነዚህ የሳይቤሪያና የካልሃሪ ዓይነት ኑባሬያት ነው። መሀል ላይመጡ እኛን እንዳራራቁና እንዳፋጁ ይኖራሉ።

አልፎ አልፎ - ምናልባት ከአንድ ሰዓት በኋላ አንድ የጉራግኛ ወይም የኦሮምኛ ዘፈን ለማስመሰል ይመስለኛል ጣል ያደርጋሉ - የአማርኛ ዘፈን ሃሊዮት ኮሜት ሆናለች፤ ከስንት አንዴ አንዲት ውዳቂ ዘፈን - ከፖለቲካዊ አንድምታዋ አንጻር ተመርጣ - ታሽታና ተፈትላ ትቀርብና ለአፍታ ትዘፈናለች - ያኔ ታዲያ ቱባዎቹ ወያኔዎች ግምባራቸውን እንዴት እንደሚኮሰኩሱት ይታየኛል - አምሃርኛን በመጠየፍ ስሜት። ያ የከፈቱት የሌላ ጎሣ ዘፈን በቅጡ ሳይጠናቀቅ ወዲያውኑ ትግርኛውን ይለጥቃሉ። በዚህች ተራ ነገር፣ በየቤታቸው ከፍተው ሊዘሉበትና ሊፈርጡበት በሚችሉበት ትንሽ ነገር እንኳን ትዝብትን አይፈሩም፤ ሀፍረትም በጭራሽ አይሰማቸውም። ዳንኪራው ላይ እንኳን በዚህን አጋጣሚ እንድንጨፍር የምንችለውን ዘፈን በጋራ መናገሻ ከተማችን ውስጥ ቢከፍቱልንስ? ማለቴ ለጋበዟቸው ሰዎች ቢከፍቱላቸውስ? ትግሬዎች በሚበዙበት ቦታ ደግሞ ትግርኛ ብቻ ይሁን። በዚህም በደል?... በየትምህርት ቤቱ ሚኒ ሚዲያ ሳይቀር ግዳጅ የተጣለባቸው ይመስል ሁሉም የሚደልቀው በአብዛኛው ትግርኛ ነው - ሰርኩላር ተላልፎ ይሆን እንዴ ግን? የወያኔ ነገር ምን ይታወቃል! የየሆቴልና የምሽት ክበቡንማ ተውት (ሰዎች እንደሚነግሩኝ ነው ታዲያ - የት አየህ እዳትሉኝ)። ሰዎች ደግሞ የጭፈራ ሥልቱን እንኳን በቅጡ ሳያውቁት ለማስመሰልና ውዳሤ ከንቱን ለማትረፍ በየዳንስ ቤቱና በየድግሱ በትግርኛ ዘፈን ወንከር ወንከር ይላሉ። በሠርጎችማ ትግርኛን ያላዘፈነ ሠርጉ በወያኔ ፌዴራል ይበተናል የተባለ ይመስል አብዛኛው ዲጄ በአማራና ኦሮሞ ሠርግ ሣይቀር ካለትግርኛ አይከፍትም - ይቅርታ - መከፈቱ አይደለም የኔ ችግር - ለማስመሰልና አጉል ተወዳጅነትን ለማግኘት የሚደረገው ሩጫ ነው የሚያስገርመኝ። ባጭሩ አገራችን በአስመሳዮችና በሆዳሞች ተሞልታለች። አፉና ልቡ የሚለያየው ዜጋ በዝቷል። ትግሬነት ደግሞ በምኞትም ሆነ በስለት አይገኝም።

እርግጥ ነው አዲስ አበባ መቀሌን እንደምትመስል ሳይሆን አሁን አሁን መቀሌን እንደሆነች መገንዘብ አያዳግትም፤ አብዛኛው ደህና ነዋሪ ትግራዋይ ነው። አብዛኛው ዘመናዊ ተሸከርካሪ የትግሬ ነው። አብዛኛው ሕንፃና የንግድ ተቋም የትግሬ ነው። በርግጥም በዚህ ዘመን ትግሬ መሆን እጅግ ያስቀናል። ህግን መሬት ላይ እያንደባለለ የሚረጋግጥ ሰው ብታይ ባለህ ተወራረድ - ያ ሰው ትግሬ ነው። ትግሬ ሆንክ ማለት ኢትዮጵያን የግል ንብረትህ ለማድረግ ትልቅ ሊቼንሳ ነው ባጭሩ። ብዙው ትግሬ የመንግሥትን ሀብትና ንብረት ብቻ ሣይሆን ተራ ዜጎችን - እኛን - ሳይቀር በባለቤትነት የያዘና እንዳሻው የሚያደርግ ይመስለዋል፤ የንግግሩ ቃናና አድራጎቱ ሁሉ ሲታይ ከዚህ ስሜት የመነጨና በአልጠግባይነት ሥጋዊ ፍትወትም የተቃኘ ነው። ወያኔ ሲጠግብና ሥልጣን ሲይዝ ምን ተዓምር ሊያሳይ እንደሚችል እንግዲህ ላለፉት 26 ዓመታት አየን። እውነትህን ነው ቴዴ “እጄን አላነሳም እኔስ ከቀሚሷ፤ እናት እኮ ነች ተስፋ አልቆርጥም በርሷ” ይላል አጠገቤ የተከፈተው ቴዲ። የወያኔዎች ጥጋብ ግን ሁልጊዜ ይገርመኛል። ዕድሜ ሲጨምር እየሰከነ ሳይሆን እያሸተና እየጎመራ የሚሄድ ልዩ ጥጋብና ዕብሪት።

ልብ አድርጉ! አዲስ አበባ ውስጥ መቼም በተጋባዥነትም ይሁን በሠራተኝነት ከትግሬ ቁጥር እምብዝም የማይተናነስ የሌላ ብሔርና ዘውግ ተወላጅ አይጠፋም። ለነሱ ግን ሁሉም ትግሬ ነው የሚመስላቸው። የጠገበ ሰው ሁሉም ሰው የጠገበ እንደሚመስለው።

አንድ ጨዋታ ልንገራችሁና ወደሥራየ ልግባ፤ ከኔ የትውልድ ቀየ ከቅምብቢት አንድ ልጅ ዐይኑን ይታመምና አዲስ አበባ ለህክምና ይመጣል። ዶክተሩ የልጁን ዐይኖች አወጣና አጸዳድቶ ሊያስገባ ጠረጴዛው ላይ እንዳስቀመጣቸው ዕቃ ለማምጣት ዘወር ሲል የሆስፒታሉ ድመት እነዚያን ዐይኖች ቅርጥፍ አድርጎ ይበላቸዋል። ዶክተሩ ይናደዳል። የሚያደርገው ቢጠፋው የድመቱን ዐይኖች ያወጣና ለልጁ ገጥሞ ከአንድ ወር በኋላ ለ”ቼክአፕ” እንዲመለስ በማዘዝ ወደመጣበት ያሰናብተዋል።

ልጁ ቅምብቢት ይመጣል። አትታዘቡኝና እኔም ነበርኩ። ዘመድ አዝማድ ተሰብስበን “እሰይ! ድፋባቸው የኛ ልጅ! በደምብ ታክመህ መጣህ አይደል?...” እያልን ከብበን እንጠይቀው ያዝን። ከዚያም እኔ እሆን ሌላ ሰው - ጊዜው ራቀና ዘነጋሁት - “ለመሆኑ እዚህ አካባቢ እነማንና እነማን እንታይሃለን” ብለን ስንጠይቀው ዐይኖቹን እያጉረጠረጠ “ድመት! የሚታየኝ ሁሉ ድመት ነው!” አይል መሰላችሁ? ሁላችንም ደነገጥን። የሆነ የውስጥ አካሉን አበላሽተውበት ከሰውነት ተራም እንዳወጡት ገመትን።

አዎ፣ ወያኔዎች የሚታያቸው አንድ ነገር ብቻ ነው - ያም ትግሬና ትግሬነት ብቻ። ከመነሻው አባታቸው ሰይጣን የገጠመላቸው ሶፍትዌር ትግራይነትና ትግሬነትን ብቻ ነው - የአፍሪካ ቀንድ ጽዮናዊነት፤ እጅግ አደገኛ ዘረመላዊ ደዌ - ካላስቀበረ የማይለቅ የዘረኝነት ልክፍት። ከዚህ እልፍ ሊሉ አይችሉም - ቢያልፉ ደግሞ እውነታቸውንም ነው መዘዙ suicide የመፈጸም ያህል ነው - በየትኛው ምልዓታቸውና ደግ ሥራቸው በዴሞክራሲያዊ መንገድ ተወዳድረው የኢትዮጵያን ሕዝብ ልብ ሊያሸንፉ እንደሚችሉ ይታያችሁ። እናም ያላቸው ብቸኛ አማራጭ በጀመሩት የሊቀ ሣጥናኤል ሰፊ መንገድ ተጉዘው የቀረቻቸውን አጭር ግን አሣር የበዛባት ዕድሜ መጨረስ ነው - የሚያሳዝነው አመክሮና የፍርድ አስተያየት በሌለው ሁኔታ ስንብታቸው እስከወዲያኛው መሆኑ ነው - የሠሩት ሥራ ሰማይና ምድር ሊታገሱት ከሚችሉት በላይ ግዙፍ ነውና የሚወርድባቸውም ታሪክ የሚያውቀው ተራ ቅጣት ሳይሆን የክቱ ስሑል ነበልባላዊ መቅሰፍት እንደሚሆን የታሪክን ድርሣናት ባያነብም ተንተርሶ የተኛ በቀላሉ ይረዳዋል - ባይገርማችሁ እነሱም ጭምር! በበኩሌ እኔ በሚገባ አውቃለሁ፤ የተሰወጠችብኝ (የተሰወረችብኝ) የጊዜዋ ነገር ናት። …

ኢንተርኔት በመዘጋቱ ዛሬ መላክ አልቻልኩም። በሁሉም አቅጣጫ ዘጋግተው እንደሰሜን ኮሪያ ሕዝብ ትልቅ በረት ውስጥ አጉረው ያሰቃዩናል። … እንደሰማሁት በ10ኛና 12ኛ ክፍሎች ብሔራዊ ፈተና ምክንያት ኢንተርኔት ተዘግቷል አሉ። ከዓለም የምንገናኘው ከሣምንት በኋላ መሆኑ ነው - ያውም ያኔም ከለቀቁልን። እንዲህ እየተሆነ አገርን መምራት የትም ታይቶ አያውቅም። ጋጣ ውስጥ የታሰርኩ በግ ወይ ፍየል የሆንኩ ያህል ይሰማኛል። በውጭ አገር ያለ እንዴት የታደለ ነው! (ከነችግሩም ቢሆን)። 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ