ተሾመ ገብረሥላሴ በማዕደ-ኪን እንደጻፈው

ወለላዬ እንደገጠመው

(Read on PDF)

ሙዚቃ ተሰርቶ ተደግሶ ሲቀርብ፣

መሆን የለበትም ምንጊዜም ግብረገብ።

ሰው መርዳት መደገፍ የሚባል ሰበካ፣

በዘፈን ሲገለጽ ልብም አያረካ

ከሰው ቤት እንጀራ አልጫ መረቁ፣

እስከ የኔ ድሃ ስንኝ መፈልቀቁ

ካረዳ በስተቀር በሀብታም ለማቄም፣

ለአርባ ዓመታት ያህል አልሰጠንም ጥቅም

ደግና ንጹኅ ሰው ይጠቃል በማለት፣

እራስን ነፃ አርጎ ሌላውን በማማት

ፍረዱኝ በሚል ቃል ዘፈን የሚዘጋ፣

አይቀርም መጣሉ በስሜት አደጋ

አሸናፊነቱን ሊያሳይ የሚለፋም፣

ቢኖርም አንዳንዴ አልፎ አልፎ ባይጠፋም፣

መሰረት የያዘ ተስፋን አይሰንቅም

በዚህ በጨለማ የሰው ተራ ክፍተት፣

ጥበብ ጥበብ የሚል በመጠኑ የሚሸት፣

የጠራ ሙዚቃ አልተቻለም ማግኘት

የጥበብ ተፈጥሮ ብስራት እና ተስፋ፣

መሆኑ የገባው ያሳየ በይፋ፣

ተራርቆም ቢገኝ አንዳንዴም ባይጠፋ

እሱም ጅማሪውን ሥራውን እረስቶ፣

ያን ይዞ ያን ለቆ አንዱን ከአንዱ አምታቶ፣

ቁጭ ይላል በኋላ ጥበብን አብክቶ

መዚቃ በጥቅል በግዙፉ ሲታይ፣

መሆን ነበረበት የወጣለት ነብይ

ሲመረን ሲከፋን ሆድ ሲብሰን ደርሶ፣

ያንን አጸዳድቶ ከአዕምሮ ደምስሶ

የነገን ብሩህ ቤት አመቻችቶ ከፍቶ፣

ማኖር ነበረበት ውብ ምንጣፍ ዘርግቶ

ከዚህ ንቃቃታም ተራራ ባሻገር፣

አለ ጥሩ ሜዳ እያለ ቢናገር፣

በልባችን ተስፋ ባሳደረ ነበር

አለዛ ቢዘፍን እኛም ብናዳምጥ፣

ጣሙ መሆኑ ነው ጨው እንደሌለው ወጥ

በጨለማ ድባብ ተውጠን እንዳለን፣

መስማት የለብንም ያንኑ በዘፈን

አንተ በጨለማ መኖርክን የማታውቅ፣

እንዲለን አንሻም ዝም ብሎ እንዲራቀቅ

እኛን የሚርበን ፍቅርና ተስፋ፣

መሆኑን ይረዳ በሌላው አይልፋ

እኛን ለማስለቀስ ዜማ ጥሩ ግጥም፣

ሙዚቃ መሣሪያ ጭራሽ አንፈልግም

እናውቅበታለን ከሱ በላይ ማልቀስ፣

አያርገው ድራማ የኛን እምባ ማፍሰስ

ለዕንባችን መጥረጊያ ይልቅስ መሐረብ፣

ይሻለን ነበረ አዘጋጅቶ ቢቀርብ

ያንጀት ለቅሶአችንን ከኛ ከሚቀማ፣

ባፍንጫችን ይውጣ ይቅር የሱ ዜማ

 

ገባኝ ገባኝ የሚል የሞራልም ምክር፣

አንፈልግም እኛ አያጠቅመንም ይቅር

እራሳችን ገዝተን ዘፈን ማጫወቻ፣

ሞራል ባቁማዳ ምክር በስልቻ፣

አንፈልግም ጭራሽ ሸምተን መቀርቀብ፣

ማስተማር ይቅርበት ዘፋኙ ግብረገብ

በዚህ ባሁን ጊዜ በሠለጠነ ዓለም፣

ሞራል አስተማሪ ማንም አይፈልግም

ያውም ድርቅ ያለ ከቻቻ ሰባኪ፣

አይሆንም ጨርሶ የመንፈስ ጥም አርኪ

ከዚህ ወጣ ብሎ መንገዱን ካቀና፣

ሞራልን ለመስበክ አጣፍጦ ለኅሊና

የተለየ ብቃት ያስፈልገዋል ትጥቅ፣

በስነ-ልቦና አለበት መራቀቅ

አዝኔብሻለሁ ልቤ አይስቅልሽም፣

የሚልም አባባል የትም አያደርስም

እንደውም ባዶውን ግጥም አልባ ዜማ፣

በፀጥታ ቦታ አንዳንዴ ሲሰማ፣

አለምንም ስብከት ቻቻታ ሁካታ፣

አንሳፎ ሲወስዳት ነፍስን በደስታ

ምነው ይሄን ዜማ እንደሰማን ብንቀር፣

እያልን እያልን ግጥም በመደርደር

የማይረባ ዘፋኝ ያንን ደስታ ነጥቆ፣

ድንገት ሲወስድብን ከአዕምሮ ፈልቅቆ

 

ከመጠኑ በልጦ እጅግ ንዴታችን፣

አይቀርም ያንን ሰው ያንሳው ማለታችን

ይሄ ሲደርስብን ግጥምና ዜማ፣

የሙዚቃ ሰዎች ተዋዶ እንዲስማማ

አልቻሉም ጨርሶ አንሷቸዋል ብቃት፣

ብሎ ለመናገር አግኝተናል ድፍረት

ታዲያ እንዴት ሆኖ ነው ጥበብ የሚታነጽ፣

ግጥምና ዜማ እንዲህ ፈጥረው አመጽ

ቀጣይ ልጆቻችን የሚመጣው ትውልድ፣

ያገሩን ሙዚቃ ሲሰማ ቢናደድ

አዬ! የዋህ ዘፋኝ እያለም ቢሳለቅ፣

ልንለው አንችልም ከኛ ዘፈን ታረቅ

ሙዚቀኛው ሁሉ እንግዲህ በግዜ፣

መላቀቅ አለበት ከያዘው አባዜ።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ