Ethiopia Zare's weekly news digest, week 24th, 2012 Ethiopian calendar

ከየካቲት 9 - 15 ቀን 2012 ዓ.ም. የሳምንቱን አንኳር ወሬዎች በጨረፍታ

የዓመቱ ሃያ አራተኛ ሳምንት አንኳር ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ክንውኖች

ኢዛ (ከየካቲት 9 - 15 ቀን 2012 ዓ.ም.)፦ ባሳለፍነው ሳምንት ከፖለቲካው አንፃር በርከት ያሉ አዳዲስና መነጋገሪያ የኾኑ ጉዳዮች የተስተዋሉበት ነበር ማለት ይቻላል። በተለይ ከሕወሓት 45ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል ጋር ተያይዞ የወጣው መግለጫና የሕወሓት ሊቀመንበር ያደረጉት ዛቻ አዘል መልእክቶች ከሰሞኑ በአነጋጋሪነታቸው ከሚጠቀሱ ጉዳዮች አንዱ ነው። የአማራ ክልል አስቸኳይ ጉባዔና የጨፌ ኦሮሚያ መደበኛ ስብሰባዎችም ያሳለፉዋቸውን ውሳኔዎች እንዲሁም አዳዲስ ሹመቶች ከለውጡ ወዲህ የአመራሮች ሹምሽር በተደጋጋሚ መስተዋሉን ያመላከተ ሆኗል። በአማራ የክልል አስቸኳይ ጉባዔ ላይ ነበር የክልሉ አመራሮች ወደ ፌደራል ይሔዳሉ መባል ብዙ ያሟገተበት ኾኖ አልፏል።

የምርጫ ቦርድ ለስድስት ፓርቲዎች እውቅና መሥጠቱና ወደ ምርጫው የሚገቡ ፓርቲዎች ቀስ በቀስ እየተለዩ መኾናቸውን ያመላከተ ነው የሚል አስተያየት እየተሠጠ ባለበት ወቅት፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች መድረክ በአብላጫ ድምፅ ምርጫው መደረግ የለበትም የሚል ውሣኔ ማስተላለፉም በሳምንቱ ብዥታ ከፈጠሩ፤ እንዲሁም ቀጣዩ ምርጫ ምን ሊሆን ነው የሚል ጥያቄ ያስነሣ ኾኗል። የህዳሴ ግድብና ከዚሁ ጋር እየተደረገ ባለው ድርድር ዙሪያ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀምሮ ሌሎች ባለሥልጣናትና ባለድርሻ አካላት ለምክር ተቀምጠው የነበረው በዚሁ ሳምንት ነው። በሳምንቱ መጨረሻ ላይ ደግሞ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሰየመ ልዑክ ወደ ካይሮ ተጉዞ፤ ከግብጹ ፕሬዝዳንት አብዱል ፈታ አልሲሲ ጋር ስለመምከራቸው ተገልጿል። ከዶ/ር ዐቢይ የተላከ መልእክት ለፕሬዝዳንት አልሲሲ አቅርበዋል።

ስላሳለፍነው ሳምንት የተለያዩ ክንውኖች ከተነሣ የሳምንቱን ቀናት በሙሉ ሊባል በሚችል ደረጃ በኦሮሚያ ክልል፣ በአፋር፣ በደቡብና በሱማልያ የተለያዩ ከተሞች ብልጽግናንና የዶክተር ዐቢይን በመደገፍ የተካሔዱ ሰላማዊ ሰልፎች ይጠቀሳሉ። በየከተሞቹ በሺዎች የሚቆጠሩ ሠልፈኞች ብልጽግናና ዶክተር ዐቢይን ደግፎ መውጣት የአገሪቱን የፖለቲካ ሒደት አዲስ ምስል እየሠጠው ነው።

የእነዚህ ሰልፎች መካሔድ የምርጫ ቅስቀሳ ነው የሚል ትችት ያሰነዘረ ቢኾንም፤ በየከተማው በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ብልጽግና ፓርቲን የሚያወድሱ መፈክሮች የታዩበት ሲሆን፤ በለገጣፎ ለገዳዲ ከተማ ሰልፍ ላይ ደግሞ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚና ፖለቲካ ውስጥ ስማቸው የሚጠቀሰው የዛሬው አዛውንት አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ተኝተው ያስተላለፉት መልእክትም የብዙዎችን ቀልብ የሳበ ነበር።

አዲስና እንግዳ ከኾኑ የሳምንቱ ዜናዎች ውስጥ የትግራይ ብልጽግና ፓርቲ መመሥረቱ መገለጹና ጠቅላይ ሚኒስትሩም ከትግራይ ተወላጆች የብልጽግና ፓርቲ አባላት ጋር መወያየታቸው፤ የትግራይ ብልጽግና ፓርቲ የካቲት 11 ቀን አስመልክቶ መግለጫ ማውጣቱ፤ ብልጽግና በትግራይ ክልል እንደ አንድ ተፎካካሪ የሚቀርብ ስለመኾኑን ያመላከተበት ነው። ከወቅታዊው የአገሪቱ የፖለቲካ ሁኔታ ይህ ሁኔታ አዲስ ክስተት በመኾን የተሰማ ዜና ሆኗል። የትግራይ ብልጽግና ፓርቲ አስተባባሪ በመኾን እየሠሩ ያሉት የቀድሞ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ሥራ አስፈፃሚና የአሁኑ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር አብርሃም በላይ መኾናቸው የታወቀበት ነው። ከትግራይ የብልጽግና ፓርቲ ጋር ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተወያዩበት ወቅት እንደገለጹትም ከለውጡ ወዲህ የታሰሩ በሕግ አግባብ እንዲለቀቁ አቅጣጫ መሠጠቱን ጠቁመዋል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የኢትዮጵያ ጉብኝት፣ የኮሮና ቫይረስ የቁጥጥር ተግባሩ ጠንከር እያለ ነው ቢባልም ሥጋቱ ተጥሏል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ በቻይና የሚማሩ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ወላጆች፤ መንግሥት ወደ አገራቸው ይመለሱላቸው ዘንድ በአደባባይ አቤት ያሉበትም ሳምንት ነው። በቻይና የሚገኙ ተማሪዎችም ከዚያው ኾነው ችግር ላይ እንደኾኑ ገልጸዋል። መንግሥት ደግሞ እስከ 200 ዶላር እየቆረጥኩላቸው ነው ብሏል። ይህንኑ ጥያቄያቸውን ከዚህ ቀደም ያቀረቡ ቢኾንም በድጋሚ ጥያቄ አቅርበዋል። ሌላው ዜና ኦፌኮና የአቶ ጃዋር መሐመድ ዜግነት በተለከተ ምርጫ ቦርድ ጠይቆ የነበረው ማብራሪያ ምላሽ ያገኘበት ሳምንት ነው። ምርጫ ቦርድም በዚሁ ምላሽ ላይ ተመሥርቶ ኦፌኮን በድጋሚ ማብራሪያ ጠይቋል።

በሳምንቱ ወደመጨረሻ አካባቢ የተሰማው የቡራዩ ከተማ አስተዳደር የጸጥታ ዘርፍ ኃላፊ በታጣቂዎች መገደል ጉዳይ፤ ከለውጡ ወዲህ ከቡራዩ አካባቢ እየተሰሙ ያሉት ተደጋጋሚ ጥቃቶች ጉዳይ ምስጢሩ ምን ይሆን? የሚል ጥያቄ እያስነሳ ነበር። የጥቃት አድራሾቹና ተጠርጣሪዎቹ መያዛቸው ተገልጿል። ከዚህም ሌላ የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን የሳምንቱ መጨረሻ ላይ ጥቃቱን የሰነዘረው ኦነግ ሸኔ መኾኑን ገልጿል። የሳምንቱ መጨረሻ ደግሞ አዲስ አበባን በምሽት ያደመቀ በተለያዩ ምልከታዎች በዚህ ደረጃ እስከ ዛሬ ያልተሰናዳ ነው የተባለው የቴዲ አፍሮ ኮንሰርት ተካሒዷል።

ከቢዝነስ አንፃር ሰሞኑን የጸደቀውን የኤክሳይዝ ታክስ አዋጅ መሠረት ያደረገው የዋጋ ለውጥ በቀዳሚነት ሊጠቀስ ይችላል። የኤክሳይዝ ታክስ በእጅጉ ከማረካቸው የአልኮል መጠጦች፣ የለስላሳ መጠጦችና እንደ ሲጋራ ያሉ ምርቶች ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ተደርጐባቸው መከፋፈል መጀመራቸው፤ የችርቻሮ ዋጋቸውንም ሰቅሎታል። የቀድሞው የኦሮሚያ ፕሬዝዳንትና ሚኒስትር አቶ ጁነዲን ሳዶ ባንክ ለማቋቋም መነሣታቸው ሌላው ወቅታዊ የቢዝነስ ዜና ነው። ሦስቱ የመንግሥት የፋይናንስ ተቋማት በግማሽ ዓመቱ ከ10.7 ቢሊዮን ብር ማትረፋቸው የተነገረውም በዚህ ሳምንት ሲሆን፣ ኢትዮጵያ በስድስት ወር ውስጥ ከ37 ቢሊዮን ብር በላይ ብድርና እርዳታ ስለማግኘትዋም የሰማንበት ሳምንት ነው። በእነዚህና ሌሎች የተስተናገዱበት ሳምንታዊ ዜናዎች ውስጥ በተወሰኑት ላይ ተጨማሪ መረጃዎች የታከሉበትን ዘገባ የኢትዮጵያ ዛሬ ዝግጅት ክፍል እንደሚከተለው ቀርቧል።

ሕወሓትና ያልተቀየረው አቋሙ

የሕወሓት 45ኛ ዓመት በመቀሌ በድምቀት ተከብሯል። ከበዓሉ ዋዜማ ጀምሮ በክልሉ ከተሞች በተለያዩ ዝግጅቶች ሲከበር የነበረ ሲሆን፣ የማጠቃለያ በዓሉ በመቀሌ ስቴዲየም ተካሒዷል።

ወታደራዊ ትርዒቶችን ጨምሮ በተለያዩ በዓሉን ያደምቃሉ በተባሉ እንቅስቃሴዎች የታጀበው የዚህ በዓል መሰናዶ ላይ የሕወሓት ሊቀመንበር ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ረዥም ንግግር ያደረጉበት ነበር።

የዶክተር ደብረጽዮን ንግግር የብዙዎችን ትኩረት ስቦ የነበረው፤ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ያስተላለፉት መልእክት ሲሆን፤ የኃላፊነት ጊዜያቸው እየተጠናቀቀ መኾኑን ጠቅሰው በትግራይ ላይ በመሪዎች ደረጃ የጥላቻና የፀረ ሕዝብ ንግግሮችን በይፋ እንዲኮንኑ መጠየቃቸው ነበር። በትግራይ ላይ የሚካሔደውን ጥላቻ ካልተወገደ ትግራይ ራስዋን የቻለች አገር መኾንዋን እንዲወስኑ ለፓርላማ አባላቱ ጥሪ አስተላልፈዋል። ትግራይን ለማንበርከክ መንግሥት እየሠራ ነው ብለዋል።

ዶክተር ደብረጽዮን በኢትዮ-ኤርትራ ጉዳይም በንግግራቸው ያካተቱ ሲሆን፣ በኤርትራና በትግራይ ሕዝብ መካከል ያለውን ግንኙነት በማስታወስ፤ ለኤርትራ ወታደሮች ጭምር በራችን ክፍት ነው በማለት ያደረጉት ንግግር፤ ብዙዎችን ግር ያሰኘ ከመኾኑም በላይ የሕወሓትን አቅጣጫ ለማወቅ ግራ ያጋባ እንዲኾን አድርጎታል።

ከለውጡ ወዲህ ሕወሓት የያዘውን አቋም በሚያጠናክር መልኩ የለውጡን ኃይል የኮነኑበት ንግግራቸው እንዲያውም ኢትዮጵያ እጅግ አደገኛ ሁኔታ ላይ ስለመኾንዋ በተለያየ መልኩ ጠቅሰዋል። እንዲህ ዐይነት ይዘት ያላቸው የዶክተር ደብረጽዮን ንግግርን ተከትሎ የተለያዩ አስተያየቶች የተሠጡ ሲሆን፤ ሕወሓት ማስፈራራት ይዟል ከሚሉ አስተያየቶች ጀምሮ፤ የበዓሉ አከባበር የሕወሓትን መጨረሻ የሚያሳይ ነው በማለት የገለጹም አሉ። ትግራይን ለመገንጠል ያላቸውን ፍላጐት ሕዝቡ ላይ ለመጫን ያሳዩበት ነው በማለት አስተያየት የሠጡ ያሉ ሲሆን፤ እንደ ዶ/ር አረጋዊ በርሔ ያሉ የፖለቲካ ሰዎች ደግሞ፤ ትግራይ አትገነጠልም ከፈለገ ደብረጽዮን ይገንጠል በማለት የዶ/ር ደብረጽዮንን ንግግር የተቃወሙበትን አስተያየት በመሰንዘር ሕወሓት ለመለወጥ የማይሻ ቡድን ነው በማለት ተችተዋል። (ኢዛ)

የአማራ ክልል ሹምሽርና የነባር አመራሮች ማረፊያ

የአማራ ክልላዊ መንግሥት አስቸኳይ ስብሰባ የተካሔደው በዚህ ሳምንት እንደነበር ይታወሳል። ይህ አስቸኳይ ስብሰባ ሹምሽር የተካሔደበት ሲሆን፤ የክልሉ ከፍተኛ የተባሉ ባለሥልጣናት ወደ ፌዴራል እንዲዛወሩ ስለመደረጉ የተነገረበትም ነበር። የሰሞኑ ሹመትና ዝውውር ግን ክርክር አስነስቶ ነበር።

ማክሰኞ የካቲት 10 ቀን 2012 ዓ.ም. በተካሔደው በዚሁ አስቸኳይ ስብሰባ የክልሉ ከፍተኛ የሚባሉ ባለሥልጣናት መዛወራቸውን አስመልክቶ የስብሰባው ተሳታፊዎች “ለክልሉ ሊሠሩ የሚችሉ አመራሮች ወደ ፌዴራል መሔድ የለባቸውም” የሚል ተቃውሞ አዘል አስተያየት በመሰንዘር ክርክር የተፈጠረበት ነበር።

ይህ ነባሮቹን አመራሮች ለሚተኩት አዲስ አመራሮች ላይ የተሠጠው ድምፅ አሰጣጥ ላይ ድምፀ ተአቅቦ ያደረጉ ተሳታፊዎች በዛ ብሎ እንዲታይ ምክንያት እንደነበር ለመታዘብ ተችሏል። ኾኖም የአብዛኛው ሹመት በአብላጫ ድምፅ ጸድቋል። በተለይ የክልሉን ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ለመሰየም በተደረገው የድምፅ አሰጣጥ፤ አብላጫው ተሳታፊዎች ሹመቱ እንዲጸድቅ የድምፅ የሰጡ ቢሆንም፤ 44 የሚኾኑ የጉባዔው አባላት ድምፀ ተአቅቦ ማድረጋቸው ሹምሽሩን በተመለከተ የነበረውን ልዩነት ያመለከተ ኾኖ ተገኝቷል። “በዚህ ወቅት ከፍተኛ የክልሉ አመራሮች ከክልሉ ኃላፊት መለቀቅ የለባቸውም” ማለታቸውን ተከትሎ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሠጥተዋል። እርምጃው የድርጅታቸው ውሳኔ መኾኑን ለምክር ቤቱ አባላት አሳውቀዋል።

በተሠጠው ውሳኔ መሠረትም ወደ ፌዴራል ለከፍተኛ ኃላፊነት እንደሚሔዱ ተገልጾ ከክልል ኃላፊነታቸው የለቀቁት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ኾነው ሲያገለግሉ የቆዩት አቶ ላቀ አድገህ አንዱ ናቸው። በሰሞኑ ሹመት እርሳቸውን ተክተው ምክትል ርዕሰ መስተዳድር በመኾን የተሾሙት ደግሞ ዶ/ር ፋንታ ማንደፍሮ ናቸው። ሌላው ወደ ፌዴራል ይዛወራሉ ተብለው የክልለ ኃላፊነታቸውን የለቀቁት አቶ ዮሐንስ ቧያለው ናቸው። አቶ ዮሐንስ ቧያለው እስከ የሳምንታቱ የመጀመሪያ ድረስ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ የብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ በመኾን እያገለገሉ ነበር። በአማራ ክልል የብልጽግና ፓርቲ (በቀድሞው አዴፓ) ውስጥ ጠንከር ያለ አቋም ያላቸው መኾናቸው የሚነገርላቸው አቶ ዮሐንስ፤ በብዙዎች ዘንድ ቀጣዩ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ይኾናሉ በሚል ይነገርላቸው ነበር።

አቶ ዮሐንስ በፌዴራል የሚሠጣቸው ኃላፊነት እስካሁን ይፋ ባይኾንም፤ እርሳቸውን ከኃላፊነት ቦታ የተረከቡት አቶ አገኘው እንግዳ ኾነዋል። አቶ አገኘሁ የክልሉ የሰላምና ደኅንነት ኃላፊ የነበሩ ሲሆን፤ በአዲሱ ሹመታቸው በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ኾነዋል። በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ የነበሩት አቶ መላኩ አለበል ደግሞ ከዚህ ሰሞናዊ ሹምሽር በፊት ፌዴራል የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር መኾናቸው አይዘነጋም። ወደ ፌዴራል እንደሚዛወሩ ተነግሮ ከክልል ኃላፊነታቸው የለቀቁት ሌላው የከተማና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ የነበሩት አቶ ፋንታ ደጀን ናቸው። አቶ ፋንታ በዚሁ ሳምንት የኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ሚኒስትር ደኤታ ኾነው ተሹመዋል።

የክልሉ ሰላምና የሕዝብ ደኅንነት ቢሮ ኃላፊ እንደኾኑ ደግሞ አቶ ሲሳይ ዳምጤ የተሾሙ ሲሆን፤ እርሳቸው ደግሞ አቶ አገኘሁን በመተካት የሚሠሩ ይኾናል። በዚህ የኃላፊነት ቦታ አዲስ ተሿሚ ሲመደብ ለአራተኛ ጊዜ ነው።

ከዚህም ሌላ ዶ/ር ሙሉነሽ አበበ፣ ዶክተር ሰይድ ኑሩ፣ አቶ ተፈራ ወንድማገኝ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊና የኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪና የኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ ኾነው የተሾሙ ሲሆን፤ አብዛኛው የኃላፊነት ቦታ በተደጋጋሚ ኃላፊዎች የተሸጋሸጉበትና የተቀያየሩበት ነው። (ኢዛ)

ጨፌ ኦሮሚያ ሹምሽርና አቶ ሽመልስ የክልሉ ሰባተኛ ርዕሰ መስተዳድር መኾን

ጨፌ ኦሮሚያ ሰሞኑን ባካሔደው መደበኛ ስብሰባው የተለያዩ ሹመቶችና አዋጆችን በማጽደቅ ሲጠናቀቅ፤ ሹመታቸውን ካጸደቀላቸው መካከል አንዱ አቶ ሽመልስ አብዲሳ ናቸው። አቶ ሽመልስ እስካሁን ምክትል ርዕሰ መስተዳድር በሚል ሲሠሩ የቆዩ ሲሆን፤ በሰሞኑ ሹመት ግን አቶ ሽመልስ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኾነው እንዲሠሩ ተሹመው ቃለ መሃላ ፈጽመዋል።

አቶ ሽመልስ አብዲሳ ርዕሰ መስተዳድር ኾነው እንዲያገለግሉ ጨፌው በሙሉ ድምፅ ሹመቱን ማጽደቁ ታውቋል። ይህም አቶ ሽመልስ የክልሉ ሰባተኛ ርዕሰ መስተዳድር መኾናቸውን ያመላከተ ነው።

እስካሁን ክልሉን በርዕሰ መስተዳድርነት ያገለገሉት፡- አቶ አባዱላ ገመዳ፣ አቶ ሐሰን ዓሊ፣ አቶ ጁነዲነ ሳዶ፣ አቶ ዓለማየሁ አቶምሳ፣ አቶ ሙክታር ከድር፣ አቶ ለማ መገርሳ ናቸው።

ከአቶ ሽመልስ ሹመት ባሻገር ጨፌው ሹመታቸውን ያጸደቀላቸው ሌሎች ተሿሚዎች ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪ፣ አቶ ፍቃዱ ተሰማ የክልሉ መንግሥት ተጠሪ፣ አቶ አዲሱ አረጋ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ጉዳዮች ዘርፍ አስተባባሪ፣ አቶ ጀማል ከድር ገልገዶ የክልሉ ከተማ ልማትና ቤቶች ልማት አስተዳደር ኃላፊ ኾነዋል።

አቶ ጌታቸው ባልቻ ደግሞ የክልሉ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ፣ አቶ ጂብሪል መሐመድ ሮባ የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ፣ አቶ ቦጋለ ፈለቀ የኦሮሚያ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ በመኾን እንዲያገለግሉ ተሹመዋል። አቶ ካሳሁን ጎፌ የኦሮሚያ ገቢዎች ባለሥልጣን ኃላፊ፣ አቶ ዳንኤል አሰፋ የኦሮሚያ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ፣ አቶ ከበደ ደሲሳ የኦሮሚያ የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ፣ አቶ ተሾመ ግርማ የኦሮሚያ ክልል ፀረ ሙስናና ሥነ ምግባር ኮሚሽን ኮሚሽነር፣ ኾነው መሾማቸው ታውቋል።

አባጎራ የኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት በመኾን እንዲያገለግሉ የተሾሙት ደግሞ አቶ ጋዚል አባሲመል ናቸው። አቶ ጉዮ ዋሪዮ የኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ኾነው ተሾመዋል። ጨፌው ከዚህ ባለፈም ለዞንና ለወረዳ የቀረቡ የ65 ዳኞችን ሹመትም ያጸደቀ መኾኑም ታውቋል። በዚህ ሹመት ውስጥ ከተካተቱት ውስጥ ብዙዎች ከለውጡ ወዲህ የኃላፊነት ቦታቸውን በመቀያየር የቆዩ ናቸው። በዚህ ሳምንት ከተሾሙት ውስጥ አንዳንዶቹ ልክ የአማራ ክልል ምክር ቤት እንዳደረገው የኃላፊነት ሽግሽግ ያደረገበት ሲሆን፤ የተወሰኑ አዳዲስ ሹመቶች የተሠጡበት ነው። (ኢዛ)

ምርጫ ቦርድ፣ ኦፌኮ፣ አቶ ጃዋርና የተወሳሰበው የዜግነት ጉዳይ

በአክቲቪስትነቱ ይታወቅ የነበረው አቶ ጃዋር መሐመድ በለውጡ ማግስት ሠጥቷቸው ከነበሩ ቃለምልልሶች ውስጥ በአንዱ ላይ፤ በፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ የመግባት ፍላጐት የሌለው ስለመኾኑ መግለጹ ይታወሳል። በዚህ አቋሙ ከቆየ በኋላ መንግሥት ሲያደርግለት የነበረውን ጥበቃ ሊያነሳብኝ ነው በሚል ያስተላለፈውን መልእክት ተከትሎ በተፈጠረው ግርግር ማግስት፤ በፖለቲካ ውስጥ ገብቶ ራሱን እጩ ተወዳደሪ ማድረግ እንደሚሻ ገለጸ። ይህን የአቋም ለውጡን ካሳወቀ በኋላ የሚፈልገውን ፖለቲካ ለማራመድ ምርጫው ያደረገው ኦፌኮን ነበር። በፕሮፌሰር መረራ የመራው ኦፌኮን ስለመምረጡ አስታወቀ። ፕሮፌሰር መረራም አቶ ጃዋር ፓርቲያቸውን መቀላቀሉንና በአባልነት መዝገብ ላይ መስፈሩ ሰበር ዜና ኾኖ ተነገረ። ይህ ዜና ከተሰማ በኋላ ግን በብዙዎች ዘንድ ቀድሞ እንደ ጥያቄ የተነሣው አቶ ጃዋር የያዘው ፓስፖርት የአሜሪካ ዜግነት ያለው መኾኑን በመግለጽ፤ ኦፌኮ የውጭ ዜግነት ያለውን ግለሰብ በአባልነት መቀበሉ ሕግ የሚጋፋ አይደለም ወይ? የሚል ነበር።

ይህ ጥያቄ ያለ ምክንያት የቀረበ ሳይሆን በአገሪቱ የምርጫ ሕግ መሠረት የውጭ ዜግነት ያላቸው ሰዎችን የፓርቲ አባል ማድረግ እንደማይቻል ስለሚደነግግ ነው። ጥያቄው ሲገፋ ፕሮፌሰር መረራ አቶ ጃዋር ኢትዮጵያዊ መኾኑን የሚያረጋግጥልን መረጃ ስላቀረበ ተቀብለነዋል ብለው እስከ መግለጽ ደርሰዋል።

ይህ ጉዳይ ግን የመነጋገሪያ አጀንዳ ከመኾን አልፎ ወደ ምርጫ ቦርድ ድረስ ሔደ። ጉዳዩ የምርጫ ቦርድ ከመድረሱ ቀደም ብሎ ደግሞ ኦፌኮ ለአባላቱ የሚሠጠውን መታወቂያ ለአቶ ጃዋርም በመሥጠት፤ በመታወቂያው ላይ ዜግነት በሚለው ስፍራ “ኢትዮጵያዊ” የሚል መታወቂያ ሠጠ ተባለ። ይህ የኦፌኮ እርምጃ ነገሩን ይበልጥ በጥያቄ እንዲወሳሰብና አቶ ጃዋር ዜግነቱን ስለመቀየሩ ምን ማረጋገጫ አግኝቶ ነው የሚል ሌላ ጥያቄ አስነሳ። ይህ ጥያቄ አቶ ጃዋር አሜሪካዊነቱን ትቶ ኢትዮጵያዊ መኾኑን የሚያረጋግጥ መረጃ ሳይዝ በአባልነት ተቀብሎት ከኾነ ድርጊቱ በሕጉ መሠረት ለፓርቲውም ሕልውና አደጋ በመኾኑ ነው።

እንዲህ ባለመንገድ ብዙ ምልልሶች የተደረጉት የአቶ ጃዋር ጉዳይ ምርጫ ቦርድ ያገባኛል ብሎ ማብራሪያ ጠየቀ። ለኦፌኮም ጻፈ፤ አቶ ጃዋርም ኢትዮጵያ ዜግነቱ እንዲመለስላት ጥያቄ ማቅረቡን፣ ዜግነቱን መልሶ ለማግኘት በሕግ የተጠቀሰውን ሒደት ባሟላ መልኩ ማቅረቡንና ይህም ዜግነቱ እንደተመለሰ የሚያረጋግጥለት መኾኑን በመግለጽ አስታወቀ። ይህ መልስ ለኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ቀረበ። ነገር ግን ይህ ሁኔታ ሕጋዊ መኾኑን ለማረጋገጥ ምርጫ ቦርድ የዜግነት አመላለስ ሒደቱ ከሕግ አግባብ ምን እንደኾነ ማብራሪያ ይሠጠው ዘንድ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከተውን የኢሜግሬሽን ዜግነትና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲን በደብዳቤ ጠየቀ

ይህ ማብራሪያ እስከ የካቲት 9 ቀን 2012 ዓ.ም. እንዲደርሰውም አሳስቦ እንደነበረ አይዘነጋም። በዚሁ መሠረት ኤጀንሲው ምርጫ ቦርድ ባስቀመጠው በመጨረሻ የቀነ ገደብ ዕለት ምላሽ ሠጥቷል። በዚሁ መሠረት ኤጀንሲው ትውልደ ኢትዮጵያውያን የኢትዮጵያ ዜግነታቸው እንዲመለስላቸው ካመለከቱ ዜግነታቸው ያለ ኤጀንሲው ውሳኔ ወዲያው ያገኛሉ ወይስ አያገኙም የሚለውን የምርጫ ቦርድ ጥያቄ ሦስት ነገሮች መሟላት እንዳለበት ይገልጻል።

ይህም ለኤጀንሲው ማመልከቻ ማቅረብ፣ መደበኛ ኑሯቸውን በኢትዮጵያ ውስጥ ስለማድረጋቸው ማረጋገጫ ማቅረብና በሕግ አግኝተውት የነበረውን የሌላ አገር ዜግነት ስለመመለሳቸው ማረጋገጫ ማቅረብ የሚኖርባቸው መኾኑን ነው።

እነዚህ የተዘረዘሩት አስፈላጊ መስፈርቶች በተዘረዘረው መልኩ ማስረጃዎች ሲቀርቡ የዜግነት ኮሚቴው የቀረበውን ማመለከቻና ማረጋገጫ አጣርቶ የውሳኔ ሐሳብ ለኤጀንሲው እንዲቀርብ ይጠበቃል በማለትም ኤጀንሲው ለምርጫ ቦርድ በጻፈው ደብዳቤ ገልጿል።

አያይዞም በዜግነት ኮሚቴው የቀረበውን የውሳኔ ሐሳብ በኤጀንሲው ሲያጸድቅ ለአመልካቹ ኢትዮጵያዊ መኾኑን የሚያሳይ የዜግነት መታወቂያ ወረቀት የሚሠጠው መኾኑን በመግለጽ ሕጋዊ ሒደቱን የተመለከተ ማብራሪያ ሠጥቷል።

ይህ የኤጀንሲው ማብራሪያ ምርጫ ቦርድ እንደገና ኦፌኮን ማብሪሪያ እንዲጠይቅ ያስገደደው መኾኑን ለማወቅ ተችሏል።

እንዲህ መኾኑ ኦፌኮ አቶ ጃዋርን በአባልነት የመዘገበው ከኤጀንሲው አቶ ጃዋር ኢትዮጵያዊነታቸውን መልሰው ማግኘታቸውን የሚያረጋግጥ መረጃ ባልያዘበት ሁኔታ መኾኑን ሊያሳይ የሚችል በመኾኑ፤ ጉዳዩን ውስብስብ ያደርገዋል ተብሎ ተገምቷል። በቀጣይ ምን ዐይነት እርምጃ ይወሰዳል የሚለው ከአንድ ሳምንት በኋላ ኦፌኮ በጉዳዩ ላይ በሚሠጠው ማብራሪያ ላይ የተመሠረተ እንደሚኾንም ይጠበቃል። (ኢዛ)

የፖለቲካ ድርጅቶች የጋራ ምክር ቤት መጭው ምርጫ መደረግ የለበትም የሚለውን አቋሙን ያጸናበት መግለጫ

74 የፖለቲካ ድርጅቶችን የያዘው “የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት” ቀጣዩ አገራዊ ምርጫ መካሔድ የለበትም ከሚል ድምዳሜ ላይ መድረሱንና ይህንንም “ምርጫው መካሔድ የለበትም” የሚለውን አመለካከት በአብላጫ ድምፅ ማጽደቁን በይፋ አሳውቋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ምክር ቤት አመራሮች በሠጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፤ ምርጫው ይካሔድ አይካሔድ የሚለውን ጉዳይ በአጀንዳ በመያዝ የጋራ ምክር ቤቱ አባላት ውይይት ካደረጉ በኋላ፤ አብላጫው የምክር ቤቱ አባላት “ምርጫው አይካሔድ” በሚል ድምፅ እንደሠጡ የምክር ቤቱ አመራሮች በሠጡት መግለጫ ገልጸዋል።

ምክር ቤቱ በጉዳዩ ላይ ሠጡ በተባለው ድምፅ፤ ስድስቱ ምርጫው “መካሔድ አለበት” ሲሉ፤ አምስቱ ደግሞ ድምፀ ተአቅቦ አድርገዋል። 41 ፓርቲዎች ግን ምርጫው “መካሔድ የለበትም” ብለው ድምፅ ሠጥተዋል። በዚህ የጋራ ምክር ቤት ውስጥ በርካታ አባላት አላቸው ተብለው የሚነገርላቸው ብልጽግና፣ ኢዜማ፣ ኦነግና ሌሎችም በስም የሚታወቁ ፓርቲዎች ያሉበት እንደኾነ ይታወቃል።

የጋራ ምክር ቤቱ ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው የአገር ጉዳይ መቅደም አለበት ከሚል አመለካከት ነው። በአሁኑ ወቅት አገሪቱ ያለችበት ሁኔታ ምርጫ ለማካሔድ የሚያስችል ደረጃ ላይ ባለመኾኑ፤ መንግሥት ወይም ገዥው ፓርቲ ሳይቀር ሊደርስባቸው ያልቻሉ አካባቢዎች ያሉ በመኾኑ፤ እንዲህ ባለው ድባብ ውስጥ ኾኖ ምርጫ ማካሔድ አይቻልም በሚል ነው። ይህንንም አብዛኛው የጋራ ምክር ቤቱ አባላት ምርጫው “መካሔድ የለበትም” የሚል አቋም እንዲይዙና የዘንድሮው ምርጫ በዚህ ሁኔታ መደረግ አይኖርበትም የሚል ግንዛቤ በመያዙ ስለመኾኑ የተደረሰበትን ውሳኔ ያሳወቁት የጋራ ምክር ቤቱ አመራሮች ገልጸዋል።

ይሁንና ይህ ውሳኔ በአዲሱ የምርጫ ሕግ ብዙዎቹ ፓርቲዎች ወደ ምርጫ ለመግባት ያስፈልጋል የተባለውን መስፈርት ሊያሟሉ የማይችሉ በመኾኑ፤ ምርጫው እንዳይካሔድ የመፈለጋቸው ምክንያት ነው የሚል አስተያየት የተሠጠበት ቢኾንም፤ የጋራ ምክር ቤቱ ደግሞ ዋናው ምክንያት ምርጫ ለማድረግ የሚያስችል ሁኔታ ስለሌለ ነው ይላል። የጋራ ምክር ቤቱ አባላት እንዲህ ያለ ውሳኔ ላይ ከደረሱ፤ በቀጣይ ሊሆን የሚችለው ነገር የብዙዎች ጥያቄ መኾኑ አልቀረም። በአንፃሩ ግን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባስቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ ምርጫውን ለማካሔድ ዝግጅቶች ማድረጉን ቀጥሏል። (ኢዛ)

ለብልጽግናና ለዶክተር ዐቢይ የተደረጉ የድጋፍ ሰልፎች

በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ ከተሞች ለብልጽግና ፓርቲና ለዶክተር ዐቢይ አሕመድ ድጋፍ ለመሥጠት የሚካሔዱ ሰላማዊ ሰልፎች በዚህም ሳምንት ቀጥለዋል።

ብልጽግናንና ዶክተር ዐቢይን ለመደገፍ የመጀመሪያው ሰልፍ በጅማ የተጀመረ ሲሆን፣ ከዚያ በኋላ በተለያዩ የኦሮሚያ ክልሎች ተካሒዷል። በሱማሌ፣ በአፋርና በደቡብ ክልልም ተከናውኗል። እስካሁን አጋሮ፣ ምዕራብ ሐረርጌና በሌሎችም ከተሞች መካሔዳቸው የሚታወስ ሲሆን፣ ከዚያ በኋላ በባሌ ሮቢ፣ በምዕራብ ሐረርጌ ባቢሌ፣ ምሥራቅ ሐረርጌ ምዕራብ ሸዋ፣ ለገጣፎ ለገዳዲ፣ መቱና ሌሎች ከተሞች ይኸው የድጋፍ ሰልፍ ተካሒዷል። ቅዳሜ የካቲት 14 እና እሑድ የካቲት 15 ተመሳሳይ ሰልፎች በአዳማ፣ በአምቦ፣ በዱከም፣ በደብረዘይትና በመሳሰሉት ከተሞች ቀጥሎ ውሏል።

እሁድ የካቲት 15 ቀን በአምቦ በተደረገው የድጋፍ ሰልፍ ላይ በተሳተፈው ሕዝብ መሐል ቦምብ ተወርውሮ 29 ሰዎች የመቁሰል አደጋ የደረሰባቸው ሲሆን፣ 28ቱ በዕለቱ የሕክምና እርዳታ አግኝተው ወደየቤታቸው መሸኘታቸው ተገልጿል። አንዱ ግለሰብ ግን በአምቦ ሆስፒታል ሕክምና እየተከታተለ መኾኑን የዕለቱ ዕለት (እሁድ) ማምሻውን የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አራርሳ መርደሳ ገልጸዋል። ኮሚሽነሩ በሠጡት መግለጫ 6 ተጠርጣሪዎች መያዛቸውንና ጉዳቱን ያደረሰው አካል “ኦነግ ሸኔ” እንደኾነ አስታውቀዋል።

ከአምቦ ከተማ በተጨማሪ በገለምሶ ከተማም ለዶክተር ዐቢይና ለብልጽግና ድጋፍ ሰልፍ ላይ በነበሩ ሰዎች ላይ በቡድን የኾኑ ሰዎች ተቃውሞ ለማሰማት ባደረጉት ሙከራ ግጭት መፈጠሩም ታውቋል።
ዶክተር ዐቢይን በሚያወድሱና ብልጽግና ፓርቲን የሚደግፉ መልእክቶችን የያዙ መፈክሮችን በመያዝ በተደረጉት ትዕይንተ ሕዝቦች በሺዎች የሚቆጠሩ የየከተማው ነዋሪዎች የተገኙበት ሲሆን፤ ከአምቦና ከገለምሶ ከተሞች በስተቀር ሰላማዊ ሰልፉ በሰላም የተካሔደበትና በሰላማዊ መንገድ መጠናቀቃቸው ታውቋል።

በተለያዩ ከተሞች ውስጥ ከተደረጉ ሰልፎች አንዱ የኾነው የሐዋሳው ሰልፍ ላይ ሰልፉ የተደረገበት ዓላማ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይን፣ መላውን የለውጥ አመራርና ብልጽግና ፓርቲን ለማበረታታት ያለመ ስለመኾኑ ተገልጿል።

በአጭር ጊዜ በየዘርፉ አንፀባራቂ ድሎችን እያስመዘገበ የሚገኘው የለውጥና የብልጽግና ጉዞ በተለያዩ ኃይሎች እንዳይደናቀፍ ተግቶ መጠበቅ፣ ከብልጽግና ፓርቲና ከዶክተር ዐቢይ አሕመድ ጎን መቆም እንደሚያስፈልግ የተገለጸበት ነው ተብሏል።

እንዲህ ያለው የድጋፍ ሰልፍ ወቅታዊውን የአገሪቱን የፖለቲካ ሒደት ይቀይራል የሚል አስተያየት የተሠጠ ሲሆን፤ በሌላ ወገን ግን የምርጫ ቅስቀሳ መስሏል የሚልም ትችት የሰነዘሩ አሉ። ተቃዋሚዎች ድጋፍ አላቸው በተባሉ ከተሞችም ሳይቀር ነዋሪዎች “ለዚህች አገር ብልጽግና ምርጫችን ነው!” በማለት ሰልፍ እየወጡ መኾኑም እየታየ ነው። ይሁን እንጂ የድጋፍ ሰልፉ ከሰሞኑ ሰልፎች መካከል ለገጣፎ ለገዳዲ ከተማ በተካሔደው የድጋፍ ሰልፍ ላይ ታዋቂው የኢኮኖሚ ባለሙያና በፖለቲካ ተሳትፏቸውም የሚታወቁት አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ተገኝተዋል።

ዶክተር ዐቢይ መደገፍ ያለበት ስለመኾኑ በቦታው ለነበሩ ሚዲያዎች በሠጡት ቃለምልልስ ገልጸዋል። ማንንም ደግፈው ወጥተው እንደማያውቁና ለዶ/ር ዐቢይ ድጋፍ ግን በዚያ ሰልፍ ላይ መገኘታቸውን ተናግረዋል። አቶ ቡልቻ በፖለቲካ ተሳትፏቸው ኦፌኮ የሚል መጠሪያ ያለውን ፓርቲ በመመሥረትና በመምራት እንዲሁም የፓርላማ ተመራጭ በመኾን ማገልገላቸው ይታወሳል። የአቶ ቡልቻ አስተያየት በተሰማ በሰዓታት ልዩነት ከስልጤ ዞን ተወካዮች ጋር ውይይት ሲያደርጉ የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ እዚያው ውይይት ላይ አቶ ቡልቻን አመስግነዋል።

አቶ ቡልቻ ኦፌኮ ዛሬ በፕሮፌሰር መረራ ጉዲናና በአቶ በቀለ ገርባ የሚመራ መኾኑ ይታወቃል። እነዚህ የድጋፍ ሰልፎችን ተከትሎ ዶ/ር ዐቢይ ሰሞኑን ለተደረገው የድጋፍ ሰልፍ ምስጋና አስተላልፈዋል። (ኢዛ)

የትግራይ ብልጽግና ፓርቲ እና ቀጣዩ ጉዞ

ከሰሞኑ አነጋጋሪ ከነበሩ ዜናዎች አንዱ የትግራይ ክልል የብልጽግና ፓርቲ እየተደራጀ ስለመኾኑ መሰማቱ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድም በሕወሓት ምሥረታ ዋዜማ ላይ ከትግራይ ብልጽግና ፓርቲ አባላት ጋር መወያየታቸው ተገልጿል።

እስካሁን በትግራይ ክልል የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ስለመኖሩ ባይገለጽም ባሳለፍነው ሳምንት ግን ይፋ ተደርጓል። በትግራይ ክልል የብልጽግና ፓርቲን የሚወክል ይኸው የትግራይ ቅርንጫፍ የብልጽግና አባላት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ውይይት ማድረጋቸውንና በዚህ ውይይት ላይ ከአባላቱ የተለያዩ ጥያቄዎች ቀርበው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምላሽ ስለመሥጠታቸው ተገልጿል።

ዶ/ር ዐቢይ ከትግራይ ብልጽግና ፓርቲ አባላት ጋር ባደረጉት ውይይት ላይ፤ “ትግራይ ላይ ጫና ይደረጋል” የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸው፤ ይህ ፈጽሞ ሊሆን የማይችልና ያልኾነ መኾኑንም የሚያመላክት ማብራሪያ ሠጥተዋል። ከለውጡ ወዲህ የታሰሩ ሰዎችን በተመለከተ በሕግ አግባብ ሊለቀቁ የሚችሉትበት እድል መኖሩን የጠቆሙ ሲሆን፤ ይህም ለዓቃቤ ሕግ አቅጣጫ መሠጠቱን ጠቅሰዋል። (ኢዛ)

ሸገር ባንክና ጁነዲን ሳዶ

ከፋይናንስና ቢዝነስ አንፃር ሊጠቀስ የሚችለው ሰሞናዊው ክንውን የቀድሞ የኦሕዴድና የኢሕአዴግ ከፍተኛ አመራርና የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ፕሬዝዳንት፣ እንዲሁም ሦስት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችን በሚኒስትርነት የመሩት አቶ ጁነዲን ሳዶ ማልያ ቀይረው ሸገር ባንክ በሚል የሚጠራ አዲስ ባንክ ለመመሥረት ብቅ ማለታቸው ነው።

ከለውጡ ቀደም ባሉ ጊዜያት ከሥልጣን ተነስተው ለስደት ተዳርገው የነበሩት አቶ ጁነዲን፤ ከለውጡ ወዲህ ወደ አገር የመመለስ እድል ካገኙ በኋላ ኑሮዋቸውን አዲስ አበባ አድርገዋል።

በፖለቲካው ረገድ አሁን ያላቸው ተሳትፎ ባይታወቅም፤ ወደ ቢዝነሱ ያደሉ ስለመኾናቸው ከሰሞኑ ይፋ የኾነው የሸገር ባንክ ምሥረታ አመላክቷል። አቶ ጁነዲን የዚህ ባንክ ዋነኛ አደራጅ ኾነው የተሰየሙ ሲሆን፣ ባንኩን ለማደራጀት ከተሰባሰቡ 150 ከሚኾኑት ቀዳሚ አደራጆች አንዱ ብቻ ሳይኾኑ፤ አደራጅ ኮሚቴውንም የሚመሩት እርሳቸው ናቸው። ከዚህ አንፃር ፖለቲካው በቃኝ ያሉ ይመስላል።

ሸገር ባንክን ለመመሥረትና በይፋ አክሲዮን ሽያጭ መጀመራቸው የተገለጸው በዚህ ሳምንት ሲሆን፣ ባንኩን በተለየ አገልግሎት ሥራ ለማስጀመር መታሰቡም ተገልጿል። የአክሲዮን ሽያጩ በዚህ ሳምንት የተጀመረ ሲሆን፤ በምሥረታ ላይ ለሚገኘው ሸገር ባንክ የሚያስፈልገውን ካፒታል ለማሰባሰብ አንድ አክሲዮን በአንድ ሺሕ ብር ዋጋ የሚሸጥ መኾኑ ታውቋል። በኢትዮጵያ ሕግ መሠረት አንድ ባንክ ለማቋቋም የተከፈለ 500 ሚሊዮን ብር ያስፈልጋል። አንድ ባለአክሲዮን ከ10 አክሲዮን ጀምሮ በመግዛት የባንክ ባለቤት መኾን እንደሚቻል ተገልጿል። የአክሲዮን ሽያጩም እስከ 2012 መጠናቀቂያ ድረስ ይካሔደል። (ኢዛ)

ሦስቱ የመንግሥት የፋይናንስ ተቋማትና የ10.7 ቢሊዮን ብር ትርፋቸው

በመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲ ሥር የሚገኙት የኢትዮጵያ ልማት ባንክ፣ የኢትዮጵያ መድን ድርጅትና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፤ በ2012 ዓ.ም. የመጀመሪያው ግማሽ ዓመት ከቀረጥ በፊት 10.7 ቢሊዮን ብር አተረፉ። እነዚህ ሦስት የመንግሥት የፋይናንስ ድርጅቶች በግማሽ ዓመቱ ለማግኘት አቅደው የነበረው የትርፍ መጠን 9.67 ቢሊዮን ብር እንደነበር የሚያስታውሰው መረጃ፤ አፈፃፀም ሲታይ ከእቅዳቸው በላይ ማትረፋቸውን ነው ብሏል።

እንደ ኤጀንሲው መረጃ ድርጅቶቹ ይህንን ትርፍ ሊያገኙ የቻሉት የባንክና የመድን አገልግሎቶች በመሥጠት በሩብ ዓመቱ ብር 34.35 ቢሊዮን ገቢ ለማግኘት አቅደው፤ ብር 36.64 ቢሊዮን ወይም የእቅዳቸውን 107 በመቶ ማግኘት በመቻላቸው መኾኑን ይገልጻል።

በግማሽ ዓመቱ ውስጥ ሦስቱ የፋይናንስ ተቋማት ካገኙት የ10.71 ቢሊዮን ብር ትርፍ ውስጥ 9.33 ቢሊዮን ብር ወይም ከተገኘው ጠቅላላ ትርፍ ወይም 87 በመቶ ያህል ድርሻ የያዘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ነው።

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ደግሞ በግማሽ ዓመቱ ከኪሳራ ወጥቶ በአጠቃላይ በስድስት ወር 951.60 ብር ማትረፍ ችሏል። ይህም የእቅዱን 483 በመቶ ሊያሳካ መቻሉን ኤጀንሲው አስታውቋል። ልማት ባንክ ከአንድ ዓመት በፊት የተበላሸ የብድር መጠኑ ከ40 በመቶ በላይ መኾኑንና ኪሣራ ውስጥ መገኘቱ መገለጹ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ደግሞ በመንፈቅ ዓመቱ ብር 427.89 ሚሊዮን ወይም የእቅዱን 101 ማሳካት ስለመቻሉ ይኸው የኤጀንሲው መረጃ ያሳያል። (ኢዛ)

በግማሽ ዓመት ከ39 ቢሊዮን ብር በላይ ብድርና እርዳታ ተገኘ

ከሳምንቱ ኢኮኖሚ ጉዳዮች ውስጥ በቀዳሚነት ሊጠቀስ የሚችለው ገንዘብ ሚኒስቴር ብድርና እርዳታን በተመለከተ በስድስት ወር የተገኘውን ያሳወቀበት ሪፖርት ነው። በዚሁ ሪፖርት መሠረት በ2012 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት ከመልቲላተራልና ባይላተራል ምንጮች በጠቅላላ ከ39 ቢሊዮን ብር በላይ ብድርና እርዳታ ስለመገኘቱ አስታውቋል። በዚሁ ግማሽ ዓመት ውስጥ ከ54 ቢሊዮን ብር በላይ ለፕሮጀክቶችና ፕሮግራሞች ማስፈፀሚያ ፈሰስ ስለመደረጉም ገልጿል።

ከዚህም ሌላ በግማሽ ዓመቱ የማዕከላዊ መንግሥት ጠቅላላ የአገር ውስጥና የውጭ ብድር መጠን ከ29 ሚሊዮን ዶላር በላይ መድረሱም ተነግሯል።

ከብድር ጫና ጋር በተያያዘ አይኤምኤፍና የዓለም ባንክ በጋራ የ2011 በጀት ዓመት ከነበረው መቀነሱን ማስታወቃቸውን የሚያመለክተው የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ፤ ይህም ኢትዮጵያ የብድር ጫና ሥጋት ከከፍተኛ ወደ መካከለኛ እንድትወርድ ያስችላታል። ወደዚህ ደረጃ መድረሷ እንደ ዋነኛ ምክንያት የሚጠቀሰው፤ የቻይና የንግድ አበዳሪዎች የእዳ ክፍያ ጊዜ ሽግሽግ እንዲራዘም በመደረጉ እንደኾነ ይኸው የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ ይጠቅሳል። (ኢዛ)

የቡራዩ የጸጥታ ዘርፍ ኃላፊ በታጣቂዎች መገደልና የመንግሥት እርምጃ

ከለውጡ ወዲህ እስካሁን ማንነታቸው ባልታወቀ በሚል የተለያየ መልክ ያለው ጥቃት በተደጋጋሚ ስሟ በሚነሣው ቡራዩ ከተማ ውስጥ ባሳለፍነው ሳምንትም በተካሔድ ሌላ ጥቃት የሰው ሕይወት ጠፍቷል። ከፍተኛ የአካል ጉዳት መድረስ መንስኤ ኾኗል። ከሰሞኑ ጥቃት በፊት በጋሞ ተወላጅ የቡራዩ ከተማ ነዋሪዎች ላይ የደረሰው ጥቃት አንዱ ነበር። ዓርብ የካቲት 12 ቀን 2012 ዓ.ም. በታጣቂ ኃይሎች በከፈቱት ተኩስ የከተማውን የጸጥታ ኃላፊ ኮማንደር ሰለሞን ታደሰ ሲገሉ፤ የፊንፊኔ ዙሪያ ልዩ ዞን የልዩ ፖሊስ አዛዥ አቶ ተስፋዬ ድንቁ፣ አንድ ሌላ ፖሊስና አንድ ድምፃዊ ቆስለዋል።

በዚህ በጠራራ ፀሐይ ተኩስ ተከፍቶባቸው የሞቱት የቡራዩ ከተማ የጸጥታ ዘርፍ ኃላፊ ኮማንደር ሰለሞን ታደሰ ወዲያውኑ ሕይወታቸው ሲያልፍ፤ ሦስቱ የቆሰሉት የጥቃቱ ሰለባዎች ደግሞ ሕክምና ላይ ናቸው። ታጣቂዎቹ ተኩስ የከፈቱት ኮማንደር ሰለሞንና ሌሎቹ ሰዎች ምሳ በመብላት ላይ እያሉ ነው።

ይህንን አደጋ የጣሉት ወንጀለኞች ግን እስካሁን ማንነታቸው ያልታወቀ ሲሆን፣ በመንግሥት በኩል ጥቃቱን አድራሾችን ለሕግ ለማቅረብ እየሠራ መኾኑን የገለጸ ሲሆን፣ የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አራርሳ መርደሳ እሁድ የካቲት 15 ቀን ማምሻውን በሠጡት ጋዜጣዊ መግለጫ 17 በጉዳዩ የተጠረጠሩ ግለሰቦች መታሰራቸውን ገልጸዋል።

እንደኮሚሽነሩ ገለጻ ከኾነ ጥቃቱን ያረድረሱት የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች መኾናቸውን ጠቁመው፤ ከተጠርጣሪዎቹ መካከል ይህንን የሚያረጋግጥ መረጃ መገኘቱን አክለው ገልጸዋል። (ኢዛ)

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የቀድሞ ሥራ አስፈፃሚ ሽኝትና አዲሱ ሹመት

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይልን በዋና ሥራ አስፈፃሚነት ሲመሩ በቆዩት ዶ/ር አብርሃም በላይ ምትክ አቶ ሽብር ባልቻ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኾነው የተሰየሙ ሲሆን፣ ለዶ/ር አብርሃም በላይ የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል የሽኝት ፕሮግራም በማዘጋጀትና በመሸለም እንደሸኛቸው የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል አስታውቋል።

ድርጅቱ በዚሁ መረጃው ላይ ጨምሮ እንደገለጸው፤ የሽኝት ፕሮግራሙ ላይ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የቀድሞ የሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ የነበሩት አምባሳደር ግርማ ብሩን ጨምሮ ትልልቅ ስትራቴጂካዊ ውሳኔዎችን በመወሰን ላደረጉት ድጋፍ ከተቋሙ አመራርና ሠራተኞች ሽልማት እንደተበረከተላቸው ድርጅቱ ያስታወቀው በዚህ ሳምንት ነው።

ዶክተር አብርሃም በላይ ከሽልማቱ በኋላ እንደተናገሩት፤ በሌላ መንግሥታዊ ተልዕኮ ሕዝብን የበለጠ በሚያገለግሉበት ቦታ ቢመደቡም፤ ተቋሙን በቅርብ እንደሚያግዙ መናገራቸውን ድርጅቱ አስታውቋል።

አዲስ የተመደቡት ሥራ አስፈፃሚ አቶ አሸብር ባልቻም በተቋሙ የተጀመረውን ለውጥ እንደሚያስቀጥሉና ተቋማዊ አደራቸውን በብቃት እንደሚወጡ ተስፋቸውን በመግለጽ፤ የተቋሙን ዓርማ ወይም ሎጎ አበርክተውላቸዋል። የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የቀድሞ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዶ/ር አብርሃም በጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ ሹመት ወደ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ቢኾኑም፤ ይህ ሹመት ከተሠጣቸው በኋላ በቀናት ልዩነት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የቦርድ ሰብሳቢ ኾነው ተሹመዋል። እርሳቸው ይህንን የቦርድ ሰብሳቢነት እስከተረከቡ ድረስ ለአንድ ዓመት ተኩል የቦርድ ሰብሳቢው አምባሳደር ግርማ ብሩ ነበሩ። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ