Ethiopia Zare (ቅዳሜ ጥቅምት 22 ቀን 2001 ዓ.ም. November 1, 2008)፦ በሕግ ባለሙያዎቹ አቶ ዳንኤል በቀለና አቶ ነፃነት ደምሴ ላይ የሐሰት ምስክር አዘጋጅተው ያቀረቡት፣ በምርጫ 97 ኢህአዴግን ወክለው የተወዳደሩትና የአዲስ አበባ ሴቶች ማኅበር መሪ የሆኑት ወ/ሮ ጥጉ ወልደሰንበት በግምገማ ከሥልጣናቸው ተነሱ።

 

ወ/ሮ ጥጉ ወ/ሰንበት ባለፉት ሰባት ዓመታት ማኅበሩን በመምራት ላይ የነበሩ ቢሆንም፤ ከአባላቱ ተደጋጋሚ ወቀሳ ይደርስባቸው ነበር። 96 ሺህ አባላት ያሉት ይህ ማኅበር ሲቋቋም ለመንግሥት ቀኝ እጅ ሆኖ ሊያገለግል ይችላል የሚል ስጋት የነበረ ሲሆን፣ የማኅበሩ መሪና አንዳንድ አባላት ስጋቱን ሊያራጋግጥ በሚችል ሁኔታ ሲንቀሳቀሱ ነበር።

 

የማኅበሩ ዓላማ ምንም እንኳን ከማንም የፖለቲካ ቡድን ነፃ ሆኖ ለሴቶች የሚጠቅም ሥራ ይሠራል የሚል የነበረ ቢሆንም መሪዋ በምርጫ 97 ኢህአዴግን ወክለው ተወዳድረው ነበር።

 

ወ/ሮ ጥጉ ከምርጫ 97 በኋላ የታሰሩት ሁለቱ የሕግ ባለሙያዎች አቶ ዳንኤል በቀለና አቶ ነፃነት ደምሴ፤ “በምርጫው እንደ ሲቪል ማኅበረሰብ አባልነታቸው ገለልተኛ ነፃ ሆነው መንቀሳቀስ ሲገባቸው ቅንጅትን እንድንመርጥ አግባበውተናል፤ ስብሰባ አድርገው ኢህአዲግ ሌባ ነው፣ ድምፃችሁን ይሰርቃችኋል ብለውናል” የሚሉና እና ሌሎች በርካታ ምስክርነቶችን የሰጡ ሦስት ምስክሮችን ለፍርድ ቤት አመቻችተው አስመስክረውባቸዋል።

 

በወ/ሮ ጥጉ ላይ ከአባላቱ የቀረበባቸውን ክስ እንዲያጣራ የተቋቋመው ኮሚቴ ሪፖርቱን ሲያቀርብ፤ አባላቱ ሴትየዋ ሊወክሉት እንደማይገባ በመግለጹ እንዲነሱ ተወስኖባቸዋል።

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ