Ethiopia Zare (ዓርብ መጋቢት 19 ቀን 2000 ዓ.ም. March 28,2008) ከቅንጅት ለአንድነትና ለዲሞክራሲ አመራሮች ጋር በቃሊቲ እስር ቤት የነበሩት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት አባላት ዳንኤል እና ነፃነት በዛሬው ዕለት ከእስር ቤት የተለቀቁ መሆኑን ከአዲስ አበባ የደረሰን ዘገባ ጠቆመ።

 

አቶ ዳንኤል በቀለ እና አቶ ነፃነት ደምሴ የተባሉት ሁለቱ የሕግ ባለሙያዎች የቅንጅት አመራሮች በምህረት ሲለቀቁ ጉዳያችንን በሕግ እንከታተላን በማለት ሲከራከሩ የነበረ ሲሆን፣ ፍርደ ገምድሉ የኢህአዴግ ፍርድ ቤት ሁለት ዓመት ከስድስት ወር ተፈርዶባቸው እንደነበር አይዘነጋም።

 

ፍርዳቸውን በአመክሮ አጠናቀው መለቀቅ ሲገባቸው የእስር ቤቱ አስተዳደር ሊለቃቸው ፈቃደኛ ያልሆነና ያልቻለ ከመሆኑም በላይ፤ ፍርዳቸውን ጨርሰው ሊለቀቁ ጥቂት ሣምንታት ሲቀራቸው ዓቃቤ ሕግ ፍርዱ አጥጋቢ አይደለምና በዕድሜ ልክ ይቀጡልኝ በማለት ይግባኝ ጠይቆባቸዋል እንደነበር መዘገባችን አይዘነጋም።

 

ፍርዳቸውን ለማጠናቀቅ ጥቂት ቀናት ሲቀራቸው ሽማግሌዎችና ቤተሰቦቻቸው ባሳደሩባቸው ከፍተኛ ጫና እንዲሁም በአገዛዙ በኩል በነበረባቸው ግፊት በፕሮፌሰር ኤፍሬም አማካኝነት ባቀረቡት የይቅርታ ማመልከቻ መሰረት በዛሬው ዕለት በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር ከቀኑ በአስር ሰዓት ከእስር ተፈትዋል።

 

ይህንን የይቅርታ ማመልከቻ ወይንም የይቅርታ መጠየቂያ ደብዳቤ ለጠ/ሚኒስትሩ (አቶ መለስ ዜናዊ) ፈርመው ባያቀርቡ ኑሮ፤ ምናልባትም የዓቃቤ ሕጉ ይግባኝ ተቀባይነት አግኝቶ፤ አቶ ዳንኤል በቀለ እና አቶ ነፃነት ደምሴ በእስር እንዲቆዩ ተደርጎ የፍርድ ቤቱ ሂደት ይቀጥል እንደነበር ጥርጥር እንዳልነበረው ብዙዎች ይስማማሉ። በተለይም የኢህአዴግን የፍትህና የፍርድ ቤቶች ሂደት ጠንቅቀው የሚያውቁና የሚከታተሉት ወገኖች፣ እንዲሁም ካለፈው የምርጫ 97 ሂደት ወዲህ ኢህአዴግን እና እየተከተለ ያለውን መስመር የሚከታተሉ ገለልተኛ ወገኖችን ጨምሮ ብዙዎች እንደሚስማሙበት ከሆነ፤ የይቅርታ ደብዳቤውን ባይፈርሙ ኑሮ ሁለቱ ግለሰቦች የፍርድ ጊዜያቸውን ከጨረሱም በኋላ ቢሆን የፍርድ ሂደቱ እንዲቀጥል ተደርጎ፤ ኢህአዴግ በቀጠሮ ብቻ ፍርድ ቤቱ እያመላለሳቸው የሚቀጥሉትን ቀጣይ ዓመታት በእስር እንዲቆዩ ያደርጋቸው እንደነበር ይስማማሉ።

 

የኢትዮጵያን የፍርድ ሂደት እርቃኑን በማውጣት በተጨባጭ ያረጋገጡትና እውነትን በመጋፈጥ የኢህአዴግን የፍትህ ትርዓት ለዓለም ማኅበረሰብ ያጋለጡት ወጣቶቹ የሕግ ባለሙያዎችና የሲቪክ ተቋም ባልደረቦች ለአቶ ዳንኤል በቀለና ለአቶ ነፃነት ደምሴ ከቤተሰቦቻቸውና ከወገኖቻቸው ጋር በዛሬው ዕለት መቀላቀል ከልብ የተደሰትን መሆናችንን እንገልጻል የኢትዮጵያ ዛሬ ዶክ ኮም አዘጋጆች።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ