Derartu Tulu

አትሌት ደራርቱ ቱሉ

በስፖርቱ ብቻ ሳይኾን በመልካም ምግባርዋ ጭምር ትታወቃለች

ኢዛ (ሰኞ መጋቢት ፳ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. March 29, 2021)፦ ታዋቂዋ አትሌት ደራርቱ ቱሉ በሁሉም ኢትዮጵያዊ ልብ ውስጥ ያለች፤ የብዙዎችን ቀልብ በመልካም ምግባርዋ እና ጀግንነቷ የገዛች ኢትዮጵያዊት ነች።

በአትሌቲክሱ መድረክ የመጀመሪያዋን የኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳልያ ያስገኘች ኢትዮጵያዊ በመኾን የአገሯንም፣ የአህጉሯንም ስም ያስጠራች ባለታሪክ ናት።

በስፖርቱ ዓለም ያለው አበርክቶዋ በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ድረስ ዘልቆ ዛሬም ድረስ እያገለገለች ነው።

ይቺን የአገር ምልክት፣ የስፖርቱ ብቻ ሳይኾን በመልካም ምግባርዋ ጭምር የምትታወቀውና በፍልቅልቅ ገጽታዋ አገር የሚያከብራትና ወደፊትም የሚያስከብራት ደራርቱ ቱሉ፤ ለበዛ አበርክቶዋ ያለ ልዩነት ያስማማ ክብር የተጐናጸፈችበት እውቅና ተበርክቶላታል። ትናንት እሁድ መጋቢት 19 ቀን 2013 ዓ.ም. ለክብሯ ተብሎ በተሰናዳው ፕሮግራም ላይ እቱ ፍልቅልቂቱ ደራርቱ በሽልማት የተንበሸበሸችበትም ኾኗል።

ይህ ለደራርቱ ተብሎ የተበረከተው ሽልማት፤ ደራርቱን የሚመጥን ባይኾንም በዚህ ደረጃ እውቅና ማግኘቷ ይገባታል የተባለበት ኾኗል።

በዕለቱ ለዚህች የአገር ባለውለታና ኢትዮጵያዊነትን በማጉላትና በማቀንቀን የኢትዮጵያውያንን ክብር ለተጐናጸፈችው ጀግኒት እነኾ ይገባሻል ተብሎ ከተበረከተላት ሽልማት ውስጥ፤ የ2021 ሞዴል ሌክሰስ መኪና የዕለቱ ፕሮግራም ኮሚቴ አስተባባሪ ባለሀብቶች የተበረከተላት ይጠቀሳል።

ይህ ብቻ ሳይኾን የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት 5 ሚሊዮን ብር ይገባሻል ብሎ ሸልሟታል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደግሞ ሁለት ሚሊዮን ብር ጨምሮላታል። ይህ ብቻ አይበቃትም ከሁሉም በላይ ግን የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ በኦሎምፒክና በሌሎች የውድድር መድረኮች ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ ላደረገችው አስተዋጽኦ አገር አቀፍ የብር፣ የወርቅ ኒሻን ሽልማት የተበረከተላት መኾኑ ነው። 350 ግራም የሚመዝነውን የወርቅ ኒሻን የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ በአንገቷ አጥልቀውላታል።

ደራርቱ ሌላም ሽልማት ነበራት። ይህም የአዲስ አበባ የሃያት አደባባይን በስሟ እንዲሰየም ኾኗል። የሱሉልታ አካዳሚም በትሁቷ አትሌት ስም እንዲሰየም ተወስኗል።

የደራርቱ የትናንትናውን ሽልማት አስመልክቶ በተለያዩ መገናኛ ብዙኀንና ማኅበራዊ ድረ ገጾች የተላለፉ መረጃዎች በአንድ ድምፅ ብሔራዊ ጀግንነቷን ያመለከቱና የተሰጣት ክብር ይገባታል የሚል ነው። ምናልባትም ያለ ልዩነት አበጀሽ ይገባታል የተባለ እውቅና ኾኗል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ