ቀነኒሳ በቀለ በበርሊን ሁለተኛውን ወርቅ ለማግኘት ማጣሪያውን አለፈ
ኢትዮጵያ በሜዳሊያ 8ኛ፣ በነጥብ 6ኛ ላይ ትገኛለች
Ethiopia Zare (ዓርብ ነሐሴ 15 ቀን 2001 ዓ.ም. August 21, 2009)፦ በጀርመን ዋና ከተማ በርሊን እየተካሄደ ባለው 12ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ባለፈው ሰኞ ነሐሴ 11 ቀን 2001 ዓ.ም. ኮከቡ አትሌት ቀነኒሳ በቀለ በአሥር ሺህ ሜትር ለኢትዮጵያ የወርቅ ሜዳሊያ ካስገኘ በኋላ፤ በ5 ሺህ ሜትር ትናንት ሐሙስ ነሐሴ 14 ቀን በተደረገው የማጣሪያ ውድድር በ13፡19፡77 ደቂቃ በአንደኝነት ውድድሩን አጠናቅቋል።

በሁለት ዙሮች በተደረገው የማጣሪያ ውድድር ላይ የተሳተፉት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ዓሊ አብዶሽ እና በቃና ዳባ ሲሆኑ፣ የፊታችን እሁድ ነሐሴ 17 ቀን 2001 ዓ.ም. በሚደረገው የፍፃሜ ውድድር ላይ ከአትሌት ቀነኒሳ በቀለ ጋር የሚሳተፈው አትሌት ዓሊ አብዶሽ መሆኑ ታውቋል። አትሌት ዓሊ አብዶሽ ለፍፃሜው ውድድር ያለፈው በማጣሪያው ውድድር ላይ አንድ አትሌት ጫማውን ረግጦበት ስለነበርና በዚህም ምክንያት ዘግይቶ ለመግባት ተገድዶ ነበር። ይሁን እንጂ የውድድሩ አዘጋጅ ኮሚቴና ዳኞች የጫማ ረገጣውን በማስተዋል ለፍፃሜው እንዲያልፍ በሰጡት ውሳኔ መሠረት እሁድ በሚደረገው የፍፃሜ ውድድር ላይ አትሌት ዓሊ አብዶሽ ተሳታፊ እንደሚሆን ታውቋል።
በዚህ እሁድ ነሐሴ 17 (ኦገስት 23) ቀን በሚደረገው የ5000 ሜትር ርቀት ውድድር ላይ አትሌት ቀነኒሳን በከፍተኛ ሁኔታ ይፎካከሩታል ተብለው የሚታሰቡት የኬንያ እና የሞሮኮ አትሌቶች ናቸው።
ባለፈው ሰኞ አትሌት ቀነኒሳ በቀለ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናውን ክብረወሰን (ሪከርድ) የሰበረ ሲሆን፣ ውድድሩን 26 ደቂቃ ከ45፡11 ሰከንድ ጨርሷል። እስካሁን ድረስ በ10 ሺህ ሜትር ተሸንፎ የማያውቀው ኮከቡ አትሌት ቀነኒሳ፤ ለአራተኛ ጊዜ በርቀቱ በዓለም ሻምፒዮናነቱን ድል ተቀዳጅቷል። የ10 ሺህ የዓለም ክብረወሰን 26 ደቂቃ ከ17፡53 ሰከንድ ሲሆን፣ ብራስልስ ቤልጅየም ላይ በቀነኒሳ በቀለ የተመዘገበው መሆኑ ይታወቃል።
በዚህ በበርሊኑ 12ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ተሳትፈው ሜዳሊያ ካገኙት 28 ሀገሮች ኢትዮጵያ በአንድ ወርቅ፣ በሁለት የብር እና በአንድ የነኀስ ሜዳሊያ በማግኘት በሐሙሱ የሜዳሊያ ሰንጠረዥ ላይ 8ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። አትሌቶች ቀነኒሳ በቀለ በ10 ሺህ ወንዶች የወርቅ፣ ደረሰ መኮንን በ1500 ሜትር የብር፣ መሰለች መልካሙ በሴቶች የ10 ሺህ ሜትር የብር እና አትሌት ውዴ አያሌው በሴቶች 10 ሺህ ሜትር የነኀስ ሜዳሊያዎቹን አግኝተዋል።
በበርሊኑ ሻምፒዮና ከተሳተፉት 52 ሀገሮች ውስጥ በሐሙሱ የነጥብ ሰንጠረዥ ላይ 44 ነጥብ በማግኘት በ6ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።



