Demeke Mekonen

አቶ ደመቀ መኮንን

ከሃዲ ቡድኑ ማንነት ላይ ያነጣጠረውን ጥቃት ቀጥሏል አሉ

ኢዛ (ረቡዕ ኅዳር ፪ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. November 11, 2020)፦ ዛሬ በይፋ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ሥራቸውን የጀመሩት አቶ ደመቀ መኮንን በምድር ላይ የመጨረሻ የክፋት መገለጫዎችን ከመፈጸም ወደኋላ የማይመለሰው ቡድን፤ በየክልሉ ጽንፈኞችን እያስተባበረ በማንነት ላይ ያነጣጠረ ጭፍጨፋ መፈጸሙን ቀጥሎበታል አሉ።

አቶ ደመቀ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልእክት፤ ይህ ከሃዲ ቡድን ጭፍጨፋውን የሚያካሒደው በተለያዩ ክልሎች ጽንፈኞች እና አሸባሪዎችን እያስተባበረ፤ ስምሪት እየሰጠ እና በፋይናንስ እየደገፈም ነው ብለዋል።

አቶ ደመቀ በዚህ ጉዳይ ላይ ያስተላለፉት ሙሉ መልእከት የሚከተለው ነው። (ኢዛ)

“በምድር ላይ ያሉ የመጨረሻ የክፋት መገለጫዎችን ከመፈጸም ወደ ኋላ የማይመለሰው ይህ ከሃዲ ቡድን፤ በተለያዩ ክልሎች ጽንፈኞች እና አሸባሪዎችን እያስተባበረ፣ ስምሪት እየሰጠ እና በፋይናንስ እየደገፈ በማንነት ላይ ያነጣጠረ ጭፍጨፋ መፈጸሙን ቀጥሎበታል።

በተመሳሳይ በማይካድራ አካባቢ በንጹኀን ዜጎቻችን ላይ የደረሰው እጅግ ልብ ሰባሪ፣ ኢሰብአዊ እና ፍጹም አሳዛኝ ዘር-ተኮር ጭፍጨፋ በከሃዲው ቡድን አስተባባሪነት የተፈጸመ ይቅር የማይባል ወንጀል ነው። ይህ ጭፍጨፋ እጅግ ሰው መኾንን ጥያቄ ውስጥ የሚከት ዘግናኝ ድርጊት ነው።

ሁላችንም እንደታዘብነው ከሃዲው ቡድን ከቀናት በፊት በሰሜን ዕዝ የመከላከያ ሠራዊታችን ላይ የፈጸመው አሳዛኝ ጭፍጨፋ ሳይበቃው፤ አሁንም በንጹኀን ዜጎች ላይ የዘር ማጥፋት እርምጃ መውሰዱን አጠናክሮ ገፍቶበታል።

እኩይ ድርጊቱን የቀጠለበት ዐቢይ ምክንያት የኢትዮጵያውያንን አንድነት እና የአብሮነት ክብር ለማዋረድ ቆርጦ የተነሳበትን ዓላማ እስከመጨሻዋ ሰዓት ድረስ ለማስፈጸም ነው።

ኢትዮጵያ በዘመናት ገጸ-ብዙ ፈተናዎች ያሳለፈች አገር ብትኾንም፤ በታሪኳ እንደ ሕወሓት ዐይነት የወጣለት አረመኔ እና የጭካኔ ጫፍ የተቆናጠጠ ወንጀለኛ ቡድን ገጥሟት አያውቅም ለማለት ይቻላል።

ይህ ቡድኑ ከአፈጣጠሩ ጀምሮ ፀረ-ኢትዮጵያ የኾነ የተግባር ስሪት አራማጅ እንዲሁም ፀረ-አማራ የኾነ የአስተሳሰብ ቅኝት ወላጅ ኾኖ ለበርካታ ዓመታት ሰፊውን ማኅበረሰብ ሲያደናግር ቆይቷል።

በተፈጠረበት ቅኝት እና ባደገበት ስሪት ሁልጊዜ "የበላይ" ኾኖ ለመኖር ካለው የተንጠራራ ምኞት፤ ከሌሎች የአገራችን ሕዝቦች ጋር በእኩልነት መራመድ ውርደት ስለሚመስለው "ጥፋት"ን የሥነ-ልቦና ስብራቱ ማካካሻ አድርጎት ዘልቋል።

በአሁን ሰዓት አገራችን በእጅጉ ፍትሕን ተጠምታለች፤ ሕዝብ እና መንግሥት በጀመሩት የጋራ ርብርብ የከሃዲያኑን ስብስብ በፍጥነት ወደ ሕግ ያቀርቡታል፤ እንዲሁም በማያዳግም ሁኔታ ያስወግዱታል።

አሁንም ከሃዲ ቡድኑ በአንድ በኩል “ሰላም"፤ በሌላ በኩል "ጥፋት" እያጣቀሰ ጊዜ ለመግዛት የሚያደርገው ጥረት ብዙ ርቀት የሚያደርስ ባለመኾኑ፤ ለእውነት እና ለፍትሕ መረጋገጥ ሲባል መንግሥት የጀመረው ሕግና ሥርዓት የማስከበር ኦፐሬሽን እስከመጨረሻው ተጠናክሮ የሚቀጥል ይኾናል።”

ኅዳር 2፣ 2013 ዓ.ም.
አዲስ አበባ

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ