ሶማሌ እና አፋር

የሶማሌና የአፋር አርብቶ አደሮች በግመል ርቢ ይታወቃሉ

የግጭቱ መንሥኤ እስካሁን አልታወቀም

ኢዛ (ሐሙስ ጥቅምት ፲፱ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. October 29, 2020)፦ በሶማሌና አፋር ክልል አዋሳኝ ላይ በተፈጠረ ግጭት የ27 ሰዎች ሕይወት ማለፉ ተነገረ።

ግጭቱን በተመለከተ የሶማሌ ክልል የግጭቱን መንሥኤ ሳይገልጽ ባወጣው መግለጫ፤ በግጭቱ ሕይወታቸው ካለፉት መካከል አሥሩ የሞቱት በትናንትናው ዕለት (ረቡዕ ጥቅምት 18 ቀን 2013 ዓ.ም.) እንደኾነ ታውቋል።

በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ ቦታ ላይ ግጭት ከተቀሰቀሰ ቀናት የተቆጠሩ ስለመኾኑ ከአካባቢው የሚወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ።

የሶማሌ ክልል መግለጫ እንደሚያመለክተው፤ ግጭቱ እያስከተለው ካለው የሰው ሕይወት መጥፋት ባሻገር፤ ለከባድ የንብረት ውድመት መንሥኤ መኾኑን ነው። በመኾኑም ይህንን ችግር ለመፍታት ክልሉ ከፌዴራል መንግሥት ጋር በመኾን ተጎጂዎችን ለመርዳት እየሠራ መኾኑን ገልጾ፤ የተፈጠረው ችግር የሁለቱ ክልሎችን ወንድማማችነት እንዳይጎዳ ይሠራል ብሏል።

በአፋር እና በሶማሌ ክልል አዋሳኝ ቦታዎች ላይ ከዚህም ቀደም ግጭቶች በተደጋጋሚ እየተፈጠሩ ለበርካታ ዜጎች ሕይወት መጥፋት ምክንያት እየኾነ መቆየቱ አይዘነጋም።

በዚህ ግጭት ዙሪያ እስካሁን ከአፋር ክልል የተሰጠ መረጃ ያልተደመጠም። የሶማሌ ክልል ግን የሰሞኑ ግጭት መንሥኤ ባይታወቅም፤ የሶማሌ ክልል የችግሩን መንሥኤ በመመርመር ለመፍትሔው የሚሠራ መኾኑንና ይህንንም ለሕዝብ እንደሚያሳውቅ አመልክቷል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ከትናንት በስቲያ ከትምህርት ሚኒስቴር ወደ አፋር ክልል ለሥራ ተሰማርተው የነበሩ ሁለት ሠራተኞች ባልታወቁ ሰዎች መገደላቸውን ማስታወቁ አይዘነጋም። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ