National Election Board of Ethiopia updated 2020 schedule

ዛሬ የካቲት 6 ቀን 2012 ዓ.ም. ምርጫ ቦርድ ያሻሻለው አዲሱ የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ

የድምፅ መስጫ ቀኑ ነኀሴ 23 ኾኗል

ኢዛ (ዓርብ የካቲት ፮ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. February 14, 2020)፦ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የ2012ን አገር አቀፍ ምርጫ የጊዜ ሰሌዳ በመከለስ ባወጣው አዲስ ፕሮግራም መሠረት የድምፅ መስጫው ቀን ነኀሴ 23 ቀን 2012 ዓ.ም. እንደሚኾን አስታወቀ።

አዲስ የቀረበውን የጊዜ ሰሌዳ ይፋ ያደረጉት የቦርዱ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ናቸው። ከዚህ ቀደም ወጥቶ በነበረው የምርጫው ጊዜ ሰሌዳ መሠረት የድምፅ መስጫው ቀን ተብሎ ተጠቅሶ የነበረው ነኀሴ 10 ቀን 2012 ዓ.ም. ነበር።

ምርጫ ቦርድ የመጀመሪያውን የምርጫ ሰሌዳውን ባስታወቀበት ዕለት፣ ጥር 6 ቀን 2012 ዓ.ም. በተደረገ ውይይት ላይ ነበር ነኀሴ 10 ቀን የድምፅ መስጫ ቀን አድርጎ መምረጡን ገልጾ የነበረው። በዚያው ውይይት ላይ የአገሪቱን የአየር ንብረት ያላገናዘበ መኾኑን አስመልክቶ ትችት እንደቀረበበት መዘገባችን አይዘነጋም። ከእነዚህም ውስጥ የኢዴፓው አቶ ልደቱ አያሌው “ምርጫ ቦርድ ኢትዮጵያን ያውቃታል ወይ?” የሚል ጥያቄ በመሰንዘር አስተያየታቸውን ጀምረው፤ በደጋማ አካባቢዎች የሚኖረው ሕብረተሰብ የዝናብና የብርድ ጊዜ በመኾኑ ከቤቱ የማይወጣበት መኾኑ በመግለጽ፤ ምርጫ ቦርድ የመረጠው ቀን ትክክል አለመኾኑን ገልጸው ነበር።

“ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ”ን የሚመሩት አቶ እስክንድር ነጋም በያዝነው ሳምንት እንዲሁ፤ ነኀሴ 10 የምርጫው ድምፅ መስጫ ቀን ተደርጎ መመረጡ አግባብ አለመኾኑን አስመልክቶ አስተያየት ሠጥተው ነበር።

ጥር 6 ቀን ምርጫ ቦርድ ይፋ አድርጎት የነበረውንና ዛሬ በወሩ የካቲት 6 ቀን 2012 ዓ.ም. አሻሽዬዋለሁ ያለውን የጊዜ ሰሌዳ ለንጽጽር ይመች ዘንድ ከዚህ በታች አቅርበናቸዋል። (ኢዛ)

National Election Board of Ethiopia updated 2020 schedule
ዛሬ የካቲት 6 ቀን 2012 ዓ.ም. የተቀየረው አዲሱ የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ

 

National Election Board of Ethiopia 2020 the first schedule released on January 14, 2020
ምርጫ ቦርድ ለመጀመሪያ ጊዜ አውጥቶት የነበረው የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ፣ ጥር 6 ቀን 2012 ዓ.ም.

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ