L. Tsegaye G/MedhinEthiopia Zare (ኀሙስ ሐምሌ 17 ቀን 2000 ዓ.ም. July 24, 2008)፦ ለታዋቂው ኢትዮጵያዊ የሥነ ጥበብ አባት ለሎሬት ፀጋዬ ገብረመድኅን መታሰቢያ ይሆን ዘንድ በመጀመሪያ ስሙ መጠሪያ ”ፀጋዬ” የተሰኘ ድረ ገጽ መከፈቱንና በይፋ ሥራውን መጀመሩን ድረ ገጹ በዛሬው ዕለት ለኢትዮጵያ ዛሬ በላከው ኢ-ሜይል ገለጸ።

 

”ትውልዳዊ ድርሻችንን እንወጣ!” በሚል መሪ መፈክር መራሂነት ድረ ገጹ ሥራውን መጀመሩንና አሁን በኢትዮጵያ የሚደረገውን የነፃነትና የዲሞክራሲ ትግል በአለው አቅምና ችሎታ ለማገዝ እና የታላቁ የሥነ ጥበብ አባት የሆኑት የብላቴን ጌታ ሎሬት ፀጋዬ ገብረ መድኅን ስም ከመቃብር በላይ አብቦ ይኖር ዘንድ የበኩሉን አስተዋጽኦ ለማድረግ መሰናዳቱን ከላከው ኢ-ሜይል ለመረዳት ችለናል።

 

ድረ ገጹ ”በእውነቱ የአዕምሮም ሆነ የኑሮ አቅማችን ብቁ ሆኖ አይደለም። ነገር ግን የፀጋችንን መክሊት ዘላለማዊነት እንደ አቅማችን ለማለምለም በቅንነት በማሰብ ነው።” ሲል የተቋቋመበትን ዓለማ ገልጿል።

 

አክሎም ለኢትዮጵያውያን ባስተላለፈው መልዕክት፤ አስፈላጊውን የእርምትም ሆነ የማሻሻያ እንዲሁም ገንቢ አስተያየቶች ይለገሰው ዘንድ ጠይቋል። ሁሉም ወገኖች ለድረ ገጹ ዕድገትና የተሟላ አግልግሎት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እና ተሳትፎ የሚያደርጉበት መድረክ እንዲሆን ”ፍፁም በሆነ ኢትየጵያዊ ስሜትና ደስታ እንጋብዛለን” በማለት ጥሪ አስተላልፏል።

 

በመጨረሻም ”ሀገራችን ኢትዮጵያ ሁሉንም ልጆቿን በእኩልነት፣ በነፃነትና በዲሞክራሲ አቅፋና ተንከባክባ ለምትኖርበት የሠላምና የፍቅር ዘመን ያበቃን ዘንድ የቅዱስ እግዚአብሔር መልካም ፈቃድ ይሁንልን!” በማለት የፀጋዬ ድረ ገጽ ዝግጅት ክፍል ያለውን ምኞት ገልጿል። (ድረ ገጹን ለመጎብኘት እዚህ ይጫኑ!)

 

ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድኅን ነኀሴ 11 ቀን 1928 ዓ.ም. (August 17, 1936) "ቦዳ" በተሰኘችውና ለአንቦ ቅርብ በሆነች መንደር ተወልዶ፤ የካቲት 18 ቀን 1998 ዓ.ም. (February 25, 2006) ከዚህ ዓለም የተለየ ሲሆን፣ ገጣሚና ፀሐፊ ተውኔት ነበር። ሎሬት ፀጋዬ በርካታ የኪነጥበብ ሥራዎችን ያበረከተ ሲሆን፣ "የኢትዮጵያውያን ሼክስፒር" እንደሆነ በርካታ ኢትዮጵያውያን ይስማሙበታል።

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ