“የምናውቀውን እንናገራለን፣ ያየነውንም እንመሰክራለን”  ዮሐንስ ም. 3፥11

Ethiopia Zare (እሁድ ግንቦት 3 ቀን 2000 ዓ.ም. May 10, 2008)፦ “የማይገለጥ የተከደነ የማይታወቅም የተሰወረ ምንም የለም” ይላል በስደት የሚገኘው ህጋዊ ሲኖዶስ ዜናችንን አስተባብሎ ባወጣው መግለጫ። ሚያዚያ 24 ቀን በኢትዮጵያ ዛሬ ድረ ገጽ “ስደተኛው ፓትርያርክ ለእርቅ ወደ ኢትዮጵያ ሊሄዱ ነው” በሚል ርዕስ መዘገቡ አይዘነጋም። በጉዳዩ ላይ ያገባናል የሚሉ ወገኖች በተለያዩ ድረ-ገጾች እና ራዲዮኖች የበኩላቸውን አስተያየት በመስጠት ዘገባው “ሐሰት ነው” ሲሉ አስተባብለዋል።

 

ከእነዚህም ውስጥ ለመጥቀስ ያህል፣

1) የስደተኛው ሲኖዶስ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ እና በካናዳ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ኃላፊ ሊቀ ካህናት ምሳሌ በፓልቶክ የኢትዮጵያን ከረንት አፌርስ ዲስከሽን ፎረም፣ (ቃለምልልሱን ለማድመጥ የማጫወቻ ቁልፉን ይጫኑት)

2) “ምኞት ወይስ ቅዠት” በሚል ርዕስ ሚያዝያ 28 ቀን 2000 ዓ.ም. ‘ከሕጋዊው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ’ ማሕተም ያለውና የባለሥልጣን ፊርማ የሌለው መግለጫ በኢንተርኔት ተሰራጭቷል፣ (መግለጫውን በፒ.ዲ.ኤፍ. አስነብበኝ)

3) ብጹዕ አቡነ መልከ ጸዴቅ ደግሞ በፍኖተ-ዴሞክራሲ ራዲዮ ዘገባውን አስመልክተው ቃለምልልስ ሰጥተዋል። (ቃለምልልሱን ለማድመጥ የማጫወቻ ቁልፉን ይጫኑት)

 

ከእነዚህም ሌላ ዜናውን አንብበው በኢሜል አድራሻችን በጉዳዩ ላይ የየራሳቸውን አስተያየት የሰጡ፣ ዘገባው ሐሰት ነው ያሉ፣ እናውቃለን የሚሉትን መረጃ የላኩ፣ ማዘናቸውን የገለጹ፣ በእርቁ የተደሰቱ፣ እኛንም የረገሙ፡ የዘለፉን፣ … በርካቶች ናቸው። በዚህ አጋጣሚ ሁላችሁንም በእርግጥም ሁላችሁንም ልናመሰግን እንወዳለን። ወደ ጋዜጠኝነት ሙያ ስንሰማራ በምናቀርበው ዘገባ የሚመጣውን ሁሉ ለመቀበል ተሰናድተን ነውና አልደነቀንም።

 

ከላይ በተራ ቁጥር አንድ እና ሦስት ላይ ሊቀ ካህናት ምሳሌ እና ብጹዕ አቡነ መልከ ጸዴቅ በድረ ገጻችን የተዘገበውን ሁለቱን ሲኖዶሶች ለማስታረቅ እየተደረገ ያለውን ጥረት አልሸሸጉም። በተራ ቁጥር ሁለት የተቀመጠው መግለጫ ግን ስለእርቁ መኖር ምንም ያለው ነገር የለም። ይልቁንም ብሔራዊ የእርቅ መድረክ ከተከፈተ ሲኖዶሱ ለውይይት በሩን ክፍት አድርጎ የሚጠባበቅ መሆኑን ገልጿል።

 

ሁለቱን የኃይማኖት አባቶች ጨምሮ በተራ ቁጥር ሁለት ላይ የተጠቀሰው መግለጫ በኢትዮጵያ ዛሬ ዘገባ ያልተስማሙትና “ሐሰት ነው!” ያሉት ፓትርያርክ አቡነ መርቆርዮስ ወደ ኢትዮጵያ በመሄዳቸው ጉዳይ ላይ ነው። ሦስቱም ወገኖች “ፓትርያርክ አቡነ መርቆርዮስ ለእርቅ ወደ ኢትዮጵያ አይሄዱም!” ብለዋል። ሰው ወይም ሌላ ሕግ የፈጠረው አካል የሚለው ሐሰት መሆኑ እስኪረጋገጥ ድረስ እሱ ነኝ ብሎ የሚያምነውን አምነን እንቀበላለንና ማስተባበያቸውን ይሁን እንበል።

 

ይሁን እንጂ፤ እስካሁን ድረስ ግን ፓትርያርክ አቡነ መርቆርዮስም ሆኑ የሸምጋዮቹ ቡድን በጉዳዩ ላይ ምንም አይነት አስተያየት ሲሰጡ አልተደመጡም። በዚህ የ“ሽምግልና” ሂደት ዋና ተዋናይ የሆኑት ሸምጋዮች በዚህ አንድ ዓመት ግዜ ውስጥ በሽምግልና ስም በዳዩ ወገን ምንም ዓይነት ነገር ሳይሰጥና ሳያጣ፣ ተበዳዩን ብቻ በጸጥታ የሚያንበረክኩበትና በዳዩን በድል የሚያስፈነጩበት ተሞክሮ አይተናል። ከዚህ አንጻር የዚህ የሽምግልናው ዜና እውነትነት መቶ በመቶ ትክክል እንደሆነ ማስረጃዎች የጠቆሙን ሲሆን፣ በማናቸውም የሽምግልና ሂደት ውስጥም ህዝቡ መሳተፍ እንዳለበት ብለን እናምናለን። በድብቅብቅና በሽፍንፍን የሚደረጉ ሽምግልናዎች የጉዳዩ ባለቤት የሆነውን ህዝብ ይጎዳሉ ብለን ስለምናምንና እኛም ጋዜጠኞች ብቻ ሳንሆን፣ የዴሞክራሲ ለውጥ ፈላጊዎች ስለሆንን ዘገባውን አቅርበነዋል።

 

የሽምግልናውን ሂደት በመምራት ከፍተኛ ሚና የሚጫወቱት ፕ/ር ኤፍሬም ይስኃቅ በቅርቡ ሀገር ቤት ላለ በየሳምንቱ ለሚታተመው እንቢልታ ለተሰኘው ጋዜጣ በቅጽ 1 ቁጥር 014፣ የመጋቢት 19 ቀን 2000 ዓ.ም. ዕትም ስለሽምግልናው ተጠይቀው በሰጡት ቃለምልልስ “… ውይይቱ በተፈለገው ቦታ ሊሆን ይችላል። እዚህም (አዲስ አበባ) ሊመጡ ይችላሉ - አገራቸው ነው፣ ከዚህም ወደዚያ (አሜሪካ)  መሄድ ይቻላል፣ ወይም ደግሞ መካከለኛው ቅዱስ ቦታ ኢየሩሳሌምም አለ - እዚያ ሊገናኙ ይችላሉ። ነገር ግን ሁለት ትልልቅ ወገኖች ለመገናኘት መንገድ የሚጠርግ አካል ያስፈልጋል። …” ብለዋል።

 

በዚህ አጋጣሚ ፓትርያርክ አቡነ መርቆርዮስም ሆኑ ሸምጋዮቹ በኢትዮጵያ ዛሬ ዘገባ ላይ አስተየየት የሚሰጡ ከሆነ ድረ ገጹ ለማስተናገድ ዝግጁ መሆኑን ይገልጻል። ምናልባት በዚህ ረገድ ያሰፈርነውን ዜና እውነተኛነትን ዋጋ ባይቀንሰውም፤ ዜናውን በምንዘግብበት ወቅት ከስደተኛው ሲኖዶስ ወገን ሃሳባቸውን አለመጠየቃችን ስህተት ሆኖ ቢቆጠር እንቀበለዋለን።

 

አቋማችንና ዓላማችን

እኛ በኢትዮጵያ በጋዜጠኝነት ሙያ የበኩላችንን ለማድረግ የጣርንና በዚህም የኢህአዴግን ዱላና መከራ የቀመስን የኢትዮጵያ ዛሬ ሰዎች ዓላማችን ጥርት ያለ ነው። ከኢትዮጵያ ዛሬ ድረ-ገጽ አቋሞች አንዱ “ሕዝብ የማወቅ መብት አለው!” የሚል ሲሆን፣ ዓላማችንም ይህንን የህዝብን የማወቅ መብት ከግብ ማድረስና የመረጃ ጥማቱን ማርካት ነው። በዚህም መሠረት ስደተኛውንና በሀገር ውስጥ ያሉትን ሲኖዶሶች በሽምግልና መያዙንና የደረሰበትን ደረጃ የማሳወቅ ግዴታችንን ለህዝብ ይፋ በማድረግ ተወጥተናል። ከአንድ የመገናኛ ብዙኀን የሚጠበቀውም ይኸው ነው - መረጃን ለህዝብ ማድረስ። በዚህ መረጃ የማሰባሰብ ሂደት ውስጥ ዘወትር የመረጃ ምንጮቻችን አስተማማኝና እውነተኛ እንዲሆኑ ሥራችንም ጥራቱን የጠበቀ እንዲሆን ጥረት የምናደርግ ሲሆን፣ እንደማንኛውም ሰው ሠራሽ ሥራ ግን፣ ሥራችን ፍጹምና ከስህተት የፀዳ ነው ብለን አናምንም።

 

በዚህ ሂደት ግን የህዝቡን አንድነት እንዳይሸረሽሩና ህዝቡን እንዳያስደነግጡት ብለን የተውናቸው ከዚሁ “የሽምግልና” ሂደት ጋር የተያያዙና እንደጋዜጠኛ ልናወጣቸው የሚገቡ እንደጉዳዩ ባለቤት ግን ብዙ ነገሮችን ከግምት በማስገባት የተውናቸው አያሌ ተያያዥ ጉዳዮች አሉ። በጉዳዩ ላይ ያሰባሰብናቸውንና እያሰባሰብናቸው ያሉትን መረጃዎች ጊዜ እና ወቅት ጠብቀን እንደአስፈላጊነቱ ለህዝብ ይፋ እናደርጋለን። ለጊዜው ግን ወቅቱ ስለማይፈቅድልንና ጉዳዩን የበለጠ ለማራገብ ስለማንፈልግ መቆጠብን መርጠናል። ጊዜና ወቅት ሲፈቅዱ እውነቱ እንደሚወጣ እምነታችን የፀና ነው።

 

የጉዳዩ ቀጥተኛ ባለቤት ፓትርያርክ አቡነ መርቆርዮስ አጨቃጫቂ የሆነውና ማስተባበያ የተሰጠበት ጉዳይ የእሳቸውን ወደ ኢትዮጵያ ስለመሄድ ስላለመሄድ አስመልክቶ ነውና ከላይ እንደገለጽነው እሳቸው በቀጥታ ለኢትዮጵያ ዛሬ የሚሉት ነገር ካለ በራችን ክፍት መሆኑን በድጋሚ ልናረጋግጥ እንወዳለን።

 

ጊዜና ወቅቱ ሲፈቅድ እውነቱ ይወጣል። እስከዚያው ግን “የምናውቀውን እንናገራለን፣ ያየነውንም እንመሰክራለን”።

የኢትዮጵያ ዛሬ የህዝብ ግንኙነት ክፍል

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ