ስደተኛው ፓትርያርክ ለእርቅ ኢትዮጵያ ሊሄዱ ነው
ሽማግሌዎቹ እነ ፕ/ር ኤፍሬም ናቸው 
Ethiopia Zare (ዓርብ ሚያዝያ 24 ቀን 2000 ዓ.ም. May 2, 2008)፦ ለ16 ዓመት ውጭ ሀገር በስደት የቆዩት የኢትዮጵያ ፓትርያርክ አቡነ መርቆርዮስ ከአባ ጳውሎስ ጋር ስምምነት ለማድረግ ወደ አዲስ አበባ ሊሄዱ መሆኑን የአዲስ አበባ ምንጮቻችን ገለጹ።
ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች እንደጠቆሙት በፕሮፌሰር ኤፍሬም ይስኃቅ የሚመራው የሽማግሌዎች ሕብረት የቅንጅት አመራሮችን በምህረት እንዲለቀቁ ካደረጉ በኋላ ሀገር ውስጥ በሚገኘው ቅዱስ ሲኖዶስና አሜሪካን ሀገር በሚገኘው ስደተኛው ሲኖዶስ መካከል ያለውን ልዩነት ለመፍታት ቡድኑ ወደ አሜሪካ አገር ሄዶ የተሳካም ባይባል መግባባት ላይ ደርሶ እንደነበር ታውቋል።
የቅርብ ምንጮቻችን እንደገለጹት ግን ሰሞኑን በተደረገ ስምምነት አሜሪካን ሀገር የሚገኙት የስደተኛው ሲኖዶስ ፓትርያርክ አቡነ መርቆርዮስ አዲስ አበባ ገብተው እርቅ ሊፈፅሙ እንደሆነ ታውቋል። አቡነ መልከ ጼዴቅን ጨምሮ ተከታዮቻቸው የሆኑ 17 ስደተኞች ጳጳሳት ወደ ኢትዮጵያ ስለመሄዳቸው የታወቀ ነገር የለም።
አቡነ መርቆርዮስ በ1980 ዓ.ም. በሊቀ ጵጵስና ያገለግሉበት ከነበረው ጎንደር አገር ስብከት ተጠርተው ፓትርያርክ ሆነው የተሾሙ ሲሆን በወቅቱ ለኢትዮጵያ ሦስተኛ ፓትርያርክ የነበሩት አቡነ ተክለኃይማኖት በደርግ መንግሥት ላይ የረሃብ አድማ አድርገውና 23 ኪሎ መዝነው ሕይወታቸው ያለፈበት ወቅት ነበር።
በ1983 ዓ.ም. ኢህአዲግ አዲስ አበባን ከተቆጣጠረ በኋላ፤ አቡነ መርቆርዮስ ከደርግ ጋር ሲሠሩ የነበረ በመሆኑ ከእሳቸው ጋር አብሬ አልሰራም በማለት አቡነ መርቆርዮስ ከቦታቸው እንዲነሱ ከፍተኛ ጫናና ግፊት ያሳድር እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፤ በኋላም በገዛ ፈቃዳቸው "አሞኛል መሥራት አልችልም" ብለው በሐምሌ ወር 1983 ዓ.ም. ለሲኖዶሱ አሳውቀው እንዲለቁ ከተደረገ በኋላ እንጦጦ ኪዳነምህረት አካባቢ የተሰጣቸው መኖሪያ ለደህንነታቸው አስጊ በመሆኑ ብስራተ ገብሬል አካባቢ ዘመዳቸው ቤት ተጠግተው መኖርን መርጠው እንደነበር ይታወቃል።
ከጥቂት ጊዜ በኋላም በደረሰባቸው ወከባና ግፊት አገር ጥለው ወደ ኬንያ ከዛም ወደ አሜሪካ መሰደዳቸው አይዘነጋም።
በወቅቱ ፕትርክናቸውን ጥለው እንዲሰደዱ ከሚመክሯቸው ውጭ እንደ አለቃ አያሌው ያሉ ሌሎች ወገኖች ፖትርያርክ መስዋዕት ይሆናል እንጂ አይሰደድም ሲሉ ይቃወሟቸው ነበር።
ፓትርያርክ ሥራውን ለመሥራት በሚያግደው የጤና እክሎች፣ ካልገጠመውና ካልሞተ በስተቀር ሌላ አይሾምም ዐቃቤ መንበር ይሰይማል እንጂ፤ የሚለውን የቤተክርስቲያኑን ሥርዓት የያዙ ጳጳሳት ጉምገምታ ማሰማት ጀመሩ።
አቡነ መርቆርዮስ እንደተነሱ በአሁኑ ሰዓት ኤርትራ የሚገኙት አቡነ ያዕቆብ ዐቃቤ መንበር ሆኑ፣ እሳቸው እንደወረዱም አቡነ ዜና ማርቆስ ተተኩ።
ብዙም ሳይቆይ አቡነ ዜና ማርቆስ፣ አቡነ መልከ ጼዴቅ፣ አቡነ ኤልያስ እና አቡነ ዮሴፍ አቡነ መርቆሪዮስን ተከትለው አሜሪካ ገቡ።
በስደት ላይ ያሉት እነዚህ ጳጳሳት አገር ውስጥ ያለውን ሲኖዶስ መቃወማቸውን ቀጥለው ባለፈው ዓመት ለስደተኛው ሲኖዶስ ፓትርያርክ መሾም እንደሚፈልጉ እና እሳቸውም የቀድሞው ፓትርያርክ አቡነ መርቆርዮስ መሆናቸውን ገለጹ።
ይህን ተከትሎም አገር ውስጥ ያለው ሲኖዶስ ተቃውሞውን ከመግለጹ ባሻገር ጉዳዩ በእርቅ እንዲፈታ አምስት ጳጳሳትን በልዑክነት ወደ አሜሪካ ልኮ ተቀባይነት በማጣቱ አቡነ መርቆርዮስን ጨምሮ በሌሎችም ጳጳሳት ላይ ቃለ ውግዘት አስተላልፏል። በዚህ ቃለ ውግዘትም እነ አቡነ መርቆርዮስ ከሥልጣነ ክህነታቸው የታገዱ መሆናቸው ነው።
እንደምንጮቻችን ገለፃ የሽማግሌው ቡድን እነ አቡነ መርቆርዮስን እና አቡነ ጳውሎስን ተራ በተራ ሲያነጋግር መቆየቱንና በመጨረሻም ተሳክቶለት አቡነ መርቆርዮስ ኢትዮጵያ ለመግባት መስማማታቸው ታውቋል።



