በኃይሌ ገብረሥላሴ ጡረታ መውጣት አስተያየቶች እየጎረፉ ነው

የኒው ዮርኩን ማራቶን አትሌት ገብሬ ገብረማሪያም አሸነፈ
Ethiopia Zare (ሰኞ ጥቅምት 29 ቀን 2003 ዓ.ም. November 8, 2010)፦ አንጋፋው አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ ትላንትና በተካሄደው የኒው ዮርክ ማራቶን ውድድር ላይ በተሰማው ሕመም ምክንያት አቋርጦ ከወጣ በኋላ በሰጠው መግለጫ ራሱን ከአትሌቲክስ ጎራ ጡረታ እንደሚያወጣ ይፋ አደረገ። በአስደንጋጩ የአትሌት ኃይሌ ውሳኔ የተለያዩ አስተያየቶች እየጎረፉ መሆኑን የኢትዮጵያ ዛሬ ምንጮች ገለጹ።
እ.ኤ.አ. 1992 ጀምሮ የዓለም ክብረ ወሰኖችን በአስደናቂ ሁኔታ በመሰባበር የዓለምን የአትሌቲክስ ተመልካች ያስደመመው ኃይሌ በ1995 የአምስት ሺህ ሜትር ክብረወሰን በ12፡44፡39 ዙሪክ ላይ ድልን በመቀዳጀት ስሙን አንቱ ከተባሉ የስፖርት ሰዎች ተርታ አሰልፏል። ኔዘርላንድ ላይ በተካሄደው የ10 ሺህ ሜትር ውድድር በተቀናቃኙ ኬንያዊ ፖለል ታርጌት ተቆልፎ የነበረውን የዓለም ክብረ ወስን 12፡55፡30 ሰንጥቆ በመግባት የአትሌቲክስ ሙገሳ አቅጣጫዎች ወደ ትውልድ ሀገሩ ኢትዮጵያና ራሱ እንዲሆን አድርጓል።
አትሌት ኃይሌ በተደጋጋሚ የቤት ውስጥ ውድድሮች በመካፈልም የማይነኩ የተባሉ ውጤቶችን ከማስመዝገቡም በላይ፤ የሀገሩን ባንዲራ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ በማድረጉ የሻለቃነት ማዕረግ እና የክብር ዶክተር ለማግኘት አብቅቶታል።
ትላንት ጥቅምት 28 ቀን 2003 ዓ.ም. (Nov.7/2010) በኒው ዮርክ ከተማ የዓለም ታላላቅ የተባሉ ግለሰቦችና ዝነኛ ሰዎች የተሳተፉበት ውድድር ላይ የታላቁ ሯጭ ኃይሌ ገብረሥላሴ መገኘት የመገናኛ ብዙኀኑን አውታር ተቆጣጥሮ የነበረ ቢሆንም፤ ውድድሩን ከ27 ኪሎ ሜትር በኋላ በተሰማው ሕመም ምክንያት ሊያቋርጥ ተገድዷል። ኃይሌ ከውድድሩ በኋላ ለጋዜጠኞች በሰጠው መግለጫ "እዚህ ላይ ይብቃኝ ... እዚህ ላይ አቁሜ ወደ ሌላ ሥራ ብሰማራ ይሻላል" ሲል ተደምጧል።
ምንም እንኳን አትሌት ኃይሌ ውድድሩን አቋርጦ ቢወጣም፤ ኢትዮጵያዊው አትሌት ገብሬ ገብረማሪያም ውድድሩን በ02፡08፡14 ሰዓት በመጨረስ አንደኝነትን ተቀዳጅቷል። ኬንያውያን አትሌቶች ሁለተኛ፣ ሦስተኛ፣ አምስተኛ፣ ዘጠነኛ እና አሥራሁለተኛ ውድድሩን ጨርሰዋል።
ኃይሌ ይህንን ውሳኔ ለመወሰን ማናጀሩንም ሆነ ማንንም እንዳላማከረነና ከራሱ ጋር ተወያይቶ ውሳኔውን እንዳሳለፈ የገለጸ ሲሆን፤ ከአሁን በኋላም ለወጣቶች ቦታ መልቀቅን እንደሚፈልግ አስምሮበታል። በዚህ በኒው ዮርኩ ማራቶን የአትሌት ገብሬ ገብረማሪያም ውድድሩን በአንደኝነት ማጠናቀቅ አትሌት ኃይሌ ተተኪዎች እንዳሉት ተስፋ ሰጪ ውጤት እንደሆነ ይገመታል።
ይህንኑ የኃይሌ ገብረሥላሴን የግል ውሳኔ በሚመለከት የተለያዩ የህዝብ አስተያየቶች እየተንጸባረቁ ሲሆን፤ በተለይ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ አድናቂዎቹን ያስደነገጠ ቢሆንም ሊተኩት የሚችሉ አያሌ አትሌቶች እንዳሉም የሚናገሩ አልጠፉም።
አንዳንዶች እንደሚሉት ኃይሌ ለሀገሩና ለወገኑ በቂ አገልግሎት አበተርክቷል፣ ጡረታ መውጣቱ ለተተኪው ትውልድ ቦታ እንደመልቀቅ መታየት አለበት ሲሉ የተደመጡ ሲሆን፤ ሌሎች ደግሞ በንግዱ ሥራ ዘርፍ ጠልቆ የገባው ኃይሌ የሚሠራው ንግድ ሥራ ለስፖርቱ ትኩረት እንዳያደርግ አስተዋጽዖ አበርክቷል ብለዋል።
በሠራቸው አኩሪ ገድሎች እንደሚያደንቁት የገለጹና በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የ'ሀገር ሽማግሌዎች' ከሚባሉት ከእነ ፕሮፌሠር ኤፍሬም ይስኃቅ ጋር በመሆን ሚዛናዊ ያልሆነ የሽምግልና ሥራ ውስጥ በመግባቱና ባለፈው ወር በተካሄደው የኢህአዴግ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩንና የመንግሥት ባለሥልጣናትን በማሞጋገስ በተናገረው ንግግር ያዘኑ ብዙ ኢትዮጵያዊያን የኃይሌ ጡረታ መውጣትም ሆነ እንደገና መቀጠል ከእንግዲህ ለኢትዮጵያ የሚፈይደው ምንም ነገር የለም ሲሉ ተደምጠዋል። (አትሌት ኃይሌ ጡረታ መውጣቱን የገለጸበትን ንግግር ለመመልከት ከታች የማጫወቻ ቁልፉን ይጫኑ!)



