Artist Sahele Degago's Funeral, 15th March 2010“ሞተዋል” የተባሉት አትሌት ዋሚ ቢራቱ በሌ/ኮሎኔሉ ለቅሶ ላይ ተገኝተዋል

አርቲስት ሌ/ኮሎኔል ሳህሌ ደጋጎ, Sahle DegagoEthiopia Zare (ሰኞ መጋቢት 6 ቀን 2002 ዓ.ም. March 15, 2010)፦ አንጋፋው የሙዚቃ መሣሪያ ተጫዋች፣ ገጣሚ፣ የዜማ ደራሲ እና የሙዚቃ አቀናባሪ ሌተናል ኮሎኔል ሣfህሌ ደጋጎ የቀብር ሥነሥርዓት ዛሬ መጋቢት 6 ቀን 2002 ዓ.ም. ከቀኑ በዘጠኝ ሰዓት በአዲስ አበባ ከተማ ፈረንሣይ ለጋሲዮን በሚገኘው በገነተ-ኢየሱስ ቤተክርስቲያን ዛሬ ተፈፀመ። ሌ/ኮሎኔል ሣህሌ በ79 ዓመቱ በትናንትናው ዕለት ነበር ያረፈው።


ሌ/ኮሎኔል ሣህሌ በሕክምና ስህተት ጤነኛ ጥርሱን ነቅለውበት ለጭንቅላት ነርቭ በሽታ ከተጋለጠ በኋላ ላለፉት ሰባት ዓመታት የአልጋ ቁራኛ ሆኖ ለህልፈተ ሕይወት በቅቷል።

 

ሌ/ኮሎኔል ሣህሌ ደጋጎ ለአንጋፋዎቹ ኢትዮጵያውያን ድምፃውያን ለክቡር ዶ/ር ጥላሁን ገሠሠ፣ ለድምፃዊት ብዙነሽ በቀለ፣ ለድማፃዊት መንበረ በየነ፣ ለድምፃዊት ውብሻው ስለሺ፣ ... ግጥም በመግጠም፣ ዜማ በመድረስ እና ሙዚቃ በማቀናበር ለኢትዮጵያ ሙዚቃ ከፍተኛ አስተዋጽዖ ካበረከቱት አንጋፋና እውቅ የሙዚቃ ባለሙያዎች አንዱ ነበር።

 

የአርቲስት ሌ/ኮሎኔል ሣህሌ ደጋጎ የቀብር ሥነሥርዓት፣ መጋቢት 6 ቀን 2002 ዓ.ም.ከቀብር ሥነ-ሥርዓቱ ፍፃሜ በኋላ የተነበበው የሕይወት ታሪኩ እንደሚያመለክተው፤ መጋቢት 5 ቀን 2002 ዓ.ም ማለዳ ሕይወቱ ያለፈው ኮሎኔል ሣህሌ፤ የተወለዱት በ1923 ዓ.ም በምዕራብ ወለጋ ነጆ በተባለው ሥፍራ ሲሆን፤ በ79ኛ ዕድሜያቸው በኢትዮጵያ ኪነ-ጥበብ መስክ አንቱ ያሰኛቸውንና የዘመናዊ ሙዚቃ ቅመራ ፋና-ወጊ የተሰኙባትን ውድ ሀገራቸውን፣ ወገናቸውንና ቤተሰባቸውን በሞት ተለይተዋል።

 

የሙዚቃው ጠቢብ ሣህሌ ደጋጎ “ዋይ! ዋይ! ዋይ! ሲሉ …” የሚለውን የወገንን የረሃብ ሰቆቃ ገላጭ ሙዚቃ ለጥላሁን ገሠሠ የቀመረው አርቲስት ሌ/ኮሎኔል ሣህሌ፤ ለዓመታት ያህል በሕመም ሲሰቃይ ቆይቶ በወገን ቤተሰቦቹና በአድናቂዎቹ አጀብ “ዋይ! ዋይ! ...” ተሸኝቷል።

 

ከወይዘሮ ደጊቱ ፈይሣ እና ከባላንባራስ ደጋጎ አለቤ አብራክ የተገኘው ሣህሌ፤ በለቀምት አንደኛ ደረጃ እና በአዲስ አበባ ተፈሪ መኮንን ት/ቤት ዘመናዊ ትምህርቱን ከተከታተለ በኋላ በነበረው ልዩ የወትድርና ፍቅር በቀድሞ 1ኛ ክፍለ ጦር በስተኋላም ማዕከላዊ ዕዝ ተብሎ በተጠራው የክ/ዘበኛ የጦር ክፍል ውስጥ በ1942 ዓ.ም. ተቀጥሯል። በነበረው ሙያዊ ብቃትና ወታደራዊ ሥነ-ሥርዓት አክብርነት ከተራ ወታደርነት በአንድ ጊዜ የሃምሳ አለቅነት ማዕረግ ማግኘት የቻለው ሣህሌ፤ በሂደት እስከ ኮሎኔል ደረጃ ደርሷል።

 

ወደ ሙዚቃ ቀማሪነት፣ ዜማና ግጥም ደራሲነት እንደዚሁም ወደ የማዕከላዊ ዕዝ የሙዚቃ ባንድ ኃላፊነት ከመሸጋገሩ በፊት በእግረኛ ባንድ ውስጥ “ክላርኔት” የተሰኘው የሙዚቃ መሣሪያ ተጫዎች የነበረው ሣህሌ ደጋጎ፣ የሙዚቃን ትምህርት የቀሰመው ከፈረንሣዊው መምህሩ ሙሴ ኒኮ መሆኑን የሕይወት ታሪኩ ላይ ተጠቅሷል። ከክላርኔት በተጨማሪ “አኮርዲዮን፣ አልቶ-ሳክስ፣ ፒያኖ” የተሰኙትን የሙዚቃ መሣሪያዎችንም በብቃት ይጫወት ነበር።

 

በጠቅል ራዲዮ ጣቢያ (በተቋቋመ ጊዜ) በአኮርዲዮን ጥዑም ዜማ ለጣቢያው አድማጮች ሲያንቆረቁር ከነበሩት የሙዚቃ ሰዎች መካከል ሣህሌ ደጋጎ የመጀመሪያው ነበር።

 

ከእነ ሻለቃ ግርማ ይህደጎ፣ ሻምበል አፈወርቅ ዮሐንስ እና ከሻለቃ ባሻ ገብረዓብ ተፈሪ ጋር በመሆን የክቡር ዘበኛ ኦኬስትራን ስም እፁብ ድንቅ በማድረጉ በኩል የበኩሉን ሚና ተጫውቷል። ግጥምና ዜማ ደራሲ ከመሆኑም ባሻገር የአጫጭርና ረዣዥም ድራማዎች ፀሐፊ የነበረው ሣህሌ፣ “ሁለገብ የታሪክ ማኅደር” ያሰኘውን ተግባር በሕይወት ዘመኑ አከናውኗል።

 

ክቡር ዶ/ር ጥላሁን ገሠሠ ከተጫወታቸው ሙዚቃዎች ውስጥ “ስቆ መኖር”፣ “እውነት ማሪኝ”፣ ... የሚሉትን ግጥሞች፣ “ዋይ ዋይ ሲሉ”፣ “ውሸት ለመናገር”፣ “ልብሽን ለአፈርሰው”፣ “ኮቱሜ”፣ ... የሚሉትን ዘፈኖች ግጥምና ዜማዎች የደረሰው ሌ/ኮሎኔል ሣህሌ ደጋጎ እንደሆነ ይታወቃል።

 

ከዚህም ሌላ ለድምፃዊት ብዙነሽ በቀለ “አይወጣኝም ክፉ” በሚል የዘፈነችውና በብዙኀን ዘንድ ተወዳጅነት ያለውን (“... ወደመጣሁበት ምድር፣ እስክመለስባት በክብር፣ ሰውን ከማስደሰት በቀር፣ አይወጣኝም ክፉ ነገር፣ ...”) ሙዚቃውን ያቀናበረው ሌ/ኮሎኔል ሣህሌ ነው። ሌ/ኮሎኔል ሣህሌ “ፍላጎቴ”፣ “ምን ነበር”፣ “ምንድነው ትዝታህ”፣ ... የተሰኙትን የብዙነሽ በቀለን ዘፈኖች ያቀናበረ ሲሆን፣ “ከንቱ ሥጋ” የሚለውንና ሌሎችንም ዘፈኖችዋን ግጥም ደርሶላታል። “አታሳየኝ ጭንቁን”፣ “የፍቅር ወጋገን”፣ “ቃልኪዳን”፣ “በብር አይጋዛም”፣ “ፍቅርህ ቀሰቀሰኝ”፣ … የተሰኙትን ዜማና ግጥሞች ያዘጋጀው ሣህሌ ደጋጎ እንደነበረ ይታወቃል።

 

“ሰው ከተሰማራ” በተሰኘው ዘፈኗ ለምትታወቀው ለድምፃዊት መንበረ በየነ ደግሞ “እንዴት ከረማችሁ” የሚለውን ዘፈን ግጥም የደረሰው ሌ/ኮ/ል ሣህሌ ነበር። “የቆራጡ መሪ ፍሬው ጎመራ” የተሰኘውንና ለቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት መንግሥቱ ኃይለማርያም ላቀነቀነችው ለድምፃዊት ውብሻው ስለሺ ደግሞ “ይህ ነው ጌትነት”፣ “የምድር ፈተና” የተሰኙትንና በ1966 ዓ.ም. የታተሙትን ዘፈኖችዋን ያቀናበረላት ሌ/ኮሎኔል ሣህሌ ደጋጎ ነበር።

 

በዕድሜ ዘመን የኪነ-ጥበብ አገልግሎት የክብር ሜዳሊያ እና የ20 ሺህ ብር ተሸላሚ የሆነው ሣህሌ ደጋጎ፤ የ30፣ የ20 እና የ10 ዓመት የረዥም ዘመን አገልግሎት የወርቅ፣ የብርና የነኀስ እንደዚሁም የተዋጊ ወታደርነት የደረት ዓርማ ኒሻን ተሸለሚም ነበር። ሙዚቃ ቀማሪው ሣህሌ ደጋጎ ከባለቤታቸው ከወ/ሮ ወይንሸት ተክሉ 4 ሴትና 3 ወንድ ልጆችን አፍርቶ የ10 ልጆች አያት ለመሆን በቅቷል። በቀብር ሥርዓቱም ላይ ከቤተሰቡ ውጪ በሺ የሚቆጠሩ ወዳጅ ዘመዶቹ፣ የቀድሞ የሥራ ባልደረቦቹ እና አድናቂዎቹ፣ የመኖሪያ አካባቢያው ሰዎች ተገኝተው በዕንባ ሸኝተውታል። የአበባ ጉንጉንም አኑረዋል።

 

ይህ በእንዲህ እንዳለ በቀብር ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ዘግይተው የተገኙት የአርቲስት ጥላሁን ገሠሠ ባለቤት ወ/ሮ ሮማን በዙ፤ “ለሣህሌ ደጋጎ ቤተሰቦች መደጎሚያ ይሁን …” ያሉትንና መጠኑ በውል ያልታወቀ ገንዘብ ማበርከታቸውን በሌተናል ኮሎኔሉ የሕይወት ታሪክ አንባቢዎች በኩል አስነግረዋል።

 

በሌላም በኩል ሌተናል ኮሎኔል ሣህሌ ባረፈበት ቀን “ሞተዋል” ተብሎ የተነገረባቸው የ95 ዓመቱ አዛውንትና ፈር-ቀዳጁ ኢትዮጵያዊ አትሌት ሻለቃ ባሻ ዋሚ ቢራቱ፤ በኮሌኔሉ ለቅሶ ላይ ተገኝተው ኀዘንተኛውን አስደምመዋል። ዋሚ ቢራቱ “ሞተዋል” በመባላቸው የወሬውን እውነትነት ለማረጋገጥ መጋቢት 6 ቀን 2002 ከማለዳ እስከ ቀትር ቤታቸውን የጎበኙ ብዙ ነበሩ። በሁኔታው የተገረሙት ዋሚ ቢራቱም “ይኸው አለሁኝ፣ እግዚአብሔር አልጠራኝምና …” የሚል አስተያየት ሰጥተዋል። አትሌት ዋሚ ቢራቱና ኮሎኔል ሣህሌ ደጋጎ በአዲስ አበባ ከተማ ፈረንሣይ ለጋሲዮን በቀድሞ ከፍተኛ 12 ቀበሌ 07 ነዋሪ ናቸው።

 

ኢህአዲግ ግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም. ኢትዮጵያን ከተቆጣጠረ በኋላ ሌ/ኮሎኔል ሣህሌ ደጋጎ ለሰባት ወራት በጦላይ የጦር ማሠልጠኛ ማዕከል ታስሮ እንደነበር ይታወቃል።

 

በዚህ አጋጣሚ ለመላው የሌተናል ኮሎኔል ሣህሌ ደጋጎ ቤተሰብ አባላት፣ ለወዳጅ ዘመዶቹ እና ለአድናቂዎቹ ፈጣሪ አምላክ ልባዊ መጽናናትን እንዲሰጥ የኢትዮጵያ ዛሬ ዝግጅት ክፍል ይመኛል።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ