በስደት ከኢትዮጵያ መምህራን ማህበር አባላት አስተባባሪ ኮሚቴ

Coordinating Committee of Exiled members of Ethiopian Teachers Association

የተሰጠ መግለጫ

መጋቢት 24 ቀን 2004 ..

 

ስንት ዘንድሮ ያልፍብናል!

የኢትዮጵያ ሕዝብ የግፍ አግዛዙን ከጫንቃው ላይ አውርዶ በሕዝቡ ይሁንታ የሚመሠረት ሥርዓት ለመገንባት ብዙ መልካም አጋጣሚዎች ተከስተው እንደዋዛ አልፈዋል። አንደኛው የሕብረተሰብ ክፍል ላይ አደጋ ደርሶ ጩኸት ሲያሰማ ሌላው እንዳላየ፤ እንዳልሰማ እየሆነ ነግ በኔን ዘንግቷል ማለት ያስደፍራል። በእርግጥ ሕዝባዊ ትግሎች በየአቅጣጫው ተጀምረው ሲፋፋሙ ጠላቶቻችን በመረባረባቸው የሚፈለገው ድል ርቆብናል። ለድሉ መጨናገፍ ግን የጠላቶቻችን ጥንካሬ አልነበረም ወሳኙ። በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የጠላቶቻችን አቅም ያጎለበትን ራሳችን መሆናችንን መካድ ከገሀዱ ዕውነት መሸሽ ይሆናል።

 

ወያኔ ኢትዮጵያን እንዲያፈርስ ውክልና ሰጥተው ባሰማሩት የውጭ ኃይሎች የሞራልና የማቴሪያል እገዛ እየተደረገለት ሲገሰግሥ ለንደን ላይ የተጀመረውን የይስሙላ ድርድር ስናስታውስና የወያኔ አገዛዝ 97 ትን ምርጫ በነማን እገዛ መና እንዳስቀረው ስናስብ የምናመሳክረው ብዙ ጉዳዮች አሉ። ዘረኛው የወያኔ ፓርቲ ዘረኝነትን በአዋጅ ከአረጋገጠ በኋላ የሥልጣን ማሟሻ ያደረገው ለግማሽ ምዕተ ዓመት የዳበረውን የኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት በማፍረስ ነበር። ከዚያም 80ሺህ በላይ የሕንጻ ኮንስትራክሽን ሠራተኞች፣የገጠር መንገድ ሰራተኞችእያለ ማፍረስ ቀጠለ፡፡ከሁሉም በላይ ታሪካዊ የነበረዉ የባሕር ትራንዚት ሰራተኞች በአብዮት (በመስቀል) አደባባይ ከሶስት ወራት በላይ የሌሊት ቁር የቀን ሐሩር እየተፈራረቀባቸው የመብት ጥያቄ እያነሱ ቆይተው በታጣቂ ኃይል በቆመጥ እየተደበደቡ፤ በጫማ እየተረገጡ ሲባረሩ ለምን ብሎ የጮኸላቸው ወገን አልታየም፤ ትብብርም አላገኙም ነበር። ወያኔም የልብ ልብ ስለተሰማው ወኔአችንን በዘንግ እየለካ እንደአስፈላጊነቱ ቅጣት ማውረዱን ቀጥሎ እስካሁን ደርሷል። እንደባህር ትራንስፖርት ሠረተኞች ሁሉ የባንክ ሠራተኞች ባሳዩት ብልህና ቆራጥ ርምጃ መታገዝ ሲገባቸው በምትካቸው ሠራተኛ ለመቅጠር ወያኔ ማስታወቂያ ሲያወጣ ራስ ወዳዶችና ኅሊና ቢሶች ለመቀጠር የባንኩን ቅጥር ግቢና አካባቢውን የድጋፍ ሰልፍ አስመሰሉት አሳፋሪ ድርጊትም ነበር። በሂደቱም የባንኩ ሠረተኞች አድማ ከሸፈ።

 

አንድ ሕዝብ፣ አንድ አገር፣ ፍትህና ነፃነት፣ የሕግ የበላይነት፣ እኩል የትምህርትና የሥራ ዕድል፣ ከዚሁ ጋር ዴሞክራሲያዊና ሰብአዊ መብቶች ይከበሩ የምንል ከሆነ በአንድ የህብረተሰብ አካል ላይ የሚቃጣው ጥቃት የሌላውም ሆኖ ሊሰማን ይገባል። ያንዱ የሙያ /የሥራ መስክ ለሌላው መስተጋብራዊ ጥቅም ያለውን ያህል ችግሩም በዚያው አንጻር ተወራራሽ መሆኑ አያጠያይቅም። በእኛ ዘመን ላይ ጀምሮ እያደገ የመጣ አጉል ባህል ወይም አስተሳሰብ በሌላው መሰዋእትነት መልካም ሥርዓት ግንባታ ዕደገት ብልጽግና ፍትህ ወዘተርፈእንዲፈጠሩ የመፈለግ አዝማሚያ ነው። የበኩሌን ምን ላበርክት ለሚለው ጥያቄ መልስ

 

ለእያንዳንዱ ዜጋ የሚተው ቢሆንም ተጨባጩ ሐቅ ግን እኔን አይመለከተኝም የሚል ይመስላል። ይኸ አመለካከት መቆም አለበት።

 

ኢትዮጵያውያን ሳይቃጠል በቅጠል የሚለውን ቁም ነገር ወደተግባር ለመለወጥ ባንድነት ቆመን ርምጃ ለመውሰድ ዳተኞች እየሆንን ተቸግረናል። ብዙውን ጊዜ የወያኔ ማወናበጃ ፕሮፓጋንዳ አደንዝዞ ወርቃማ አጋጣሚዎች እንዲያልፉን አድርገናል። የጋራችን የሆኑና ልንቆምላቸው በሚገቡ ጉዳዮች ዙሪያ አደጋ ሲያንዣብብ በየግላችን ላይ የማይደርሱ አየመሰለን የጥቃቱ ሰደድ አሳት አገሪቱን በመላ አዳርሶ ዘር፣ሃይማኖት፣ፆታ፣ወጣት፣አረጋዉያን፣አርሶ አደር፣ ሠራተኛ፣ ተማሪ፣ መምህር ወዘተሳይለይ እየለበለበ ይገኛል። ባጠቃላይ የአገሪቱ ሕልዉና አደጋ ላይ ነዉ።

 

የማያጠግብ እንጀራ ከምጣዱ ያስታውቃል እንዲሉ የወያኔን የዘረኛነት ፖሊሲና አምባገነናዊ አካሄድ ከመነሻው የተረዱት ኢመማና መምህራን መራራ ትግል አካሂደው ዙሪያ ገብ መስዋእትነት ከፍለዋል። ወያኔ በማህበራቸው የውስጥ ጉዳይ እየገባ የማተራመስ ተግባሩን እንዲያቆም በኃይማኖት አባቶች፤ ያገር ሽማግሌዎች ሳይቀሩ አበክረው መጠያቃቸውን እናስታውሳለን። በዕውን የታየው ግን አገር በቀል ከሆኑት ድርጅቶችና ግለሰቦች የበለጠ የሞራልና የማቴሪያል ድጋፍ ይገኝ የነበረው ከአገር ውጪ ካሉ ግለሰቦች፣ ከዓለም አቀፍ የትምህርት ድርጅት (Education International- EI) ከአለም አቀፍ ሰራተኖች ማህበር (International labor organization – ILO) ከዓለም አቀፍ የሠራተኞች ኮንፌዴሬሽን (International Confederation of Trade Union- ICFTU) ከሂውማን ራይትስ ዎች (Human Rights Watch) አምነስቲ ኢንተርናሽናል (Amnesty International) ነበር። መምህራን የሙያ ክብራቸውን፤ የትምህርቱን ጥራት፤ የመደራጀት ነፃነታቸውን ለማረጋገጥ በሚያደርጉት ግብግብ በተወሰነ ደረጃ ዜጎች ከጎናቸው መቆማቸው ባይካድም የትምህርት ጥራትና የተተኪው ትውልድ ዕጣ ፋንታ ያለ ሕዝብ ሁለገብ እገዛ ግቡን ይመታል ብሎ መጠበቅ ስህተት ነው። መምህራን የወያኔ የትምህርት ፖሊሲትውልድ ገዳይነው ብለው ሲሟገቱ ሕዝቡ ጩኸታቸውን አዳምጦ፤ ወደትግሉ መቀላቀል በትምህርቱ ላይ የተደቀነውን ደባ አቅጣጪያውን ማስቀየር የሚጠበቅ ነበር። ነገር ግን ይህ አልሆነም።

 

በመምህራንና በሙያ ማህበራቸው በኢመማ ላይ የሚድርሰው ወከባና እንግልት ሳያቋርጥ እስካሁን መዝለቁን ከፍ ብሎ ጠቅሰነዋል። ለዚህም ነው ከቅርብ ወራት ጀምሮ መምህራን በኑሮ ውድነት እጅግ በመደቆሳቸው እርዛቱ፤ ረሃቡና ከዚህ ጋር ተያያዥ የሆኑት የጤንነት፤ የሞራል፤ የመብት ጥያቄ ሊያነሱ የተገደዱት። የኢትዮጵያ መምህራን እንደቀድሞው መከበርና ያለስጋት መኖር የቅንጦት ጥያቄ ያህል እየተረሳ መጥቷል። የትምህርቱ ጉዳይ ዋጋ ማጣት የመምህሩ ሙያና ክብር መርከስና መዋረድ ነፀብራቅ ሊሆን ችሏል። ቢያንስ እንደሌላው የመንግሥት ሠራተኛ ተመጣጣኝ ደመወዝ እየተከፈለን መኖር እንችል ብለው ላነሱት ጥያቄ የካድሬና የወያኔ ባለሥልጣናት መሣለቂያ እየተደረጉ ነው። በጣም የሚያሳዝነው ያለ መምህራን ምርጫ በማህበሩ አመራር ላይ የተቀመጡ ተለጣፊዎች በድሬደዋ ከተማ በተደረገ ጉባዔ ተብዬ ለመምህሩ የቆሙ መስለው ስለደሞዝ ጭማሪ ጥያቄ ለመለስ ዜናዊ አቅርበው ነበር። ምላሹ በመዘግየቱና የመምህራንም የኑሮ ውድነት ከሚችሉት በላይ አሻቅቦ ስለአንገፈገፋቸው ዴሞክራሲያዊና ሠላማዊ የሆነውን መብታቸውን በመጠቀም የሥራ ማቆም አድማ መምታት ተገደዱ። ወያኔም እንደ ልማዱ የሽንገላና የማጭበርበር ሥራውን ጀመረ። ተለጣፊዎችም በበሉበት መጮሀቸውን ቀጠሉ። ለመምህራን የተፈቀደው የደሞዝ ጭማሪ ተገቢ ነው ሲሉም የአይጥ ምስክር ድንቢጥ ሆኑ። ይህ ደግሞ ይበልጥ የመምህራኑን ሆድ አስከፋው። የተቃውሞውንና የሥራ ማቆም አድማሱን እያሰፋው መጣ።ባለፈው

 

በስደት የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር አባላት አስተባባሪ ኮሚቴ ባወጣው መግለጫ ሰለተለጣፊው ማህበር አፈጣጠርና ባህርይ ጥቂት ተብሎ ነበር።መምህራንን አስተባብሮና የነርሱን ፍላጎት አንግቦ ለመራመድ እንደማይችል፤ ይልቁንስ መምህራን በራሳቸው ተነሳሽነት እየተሰበሰቡ ትግሉን እንዲያጠናክሩ አሳስቦ ነበር። ችግሩ በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል ያለ ስለሆነ በክልል፤ በከተማና በገጠር በሚል የሚታጠር ሳይሆን ከዚያም በላይ ሕዝባዊ ተሳትፎ እንዲጎለብት ተደርጎ የትግሉ ወላፈን ቦግ እልም የሚል ሳይሆን እስከድል ድረስ የሚጫጫስ፤ የሚንቀለቀል እንዲሆን ጠቁሞ ነበር። አሁንም መደረግ ያለበት ነው።

 

አዎ አሁን ውቅቱ የሕልውና ጥያቄ ጉዳይ ሆኗል፤ ትውልድ የማዳን ጉዳይ ሆኗል፤ አገር የማዳን ጉዳይ ሆኗል። መምህራን ደግሞ ለዚህ ግምባር ቀደም ሆነው መሰለፍ ይጠበቅባቸዋል። በእርግጥም ምልክቶቹ የቀድሞ ታሪኩን የሚያድሱ ይመስላሉ። የኮከብ ጽባሕ ሁለተኛ ደረጃ /ቤት መምህራን ስብሰባ ተቀምጠው ያወጡት ያቋም መግለጫ የትም ቦታ ያለውን መምህር ሁኔታ የሚያሳይና የሚያኮራ ነው። ለተግባራዊነቱ ከሁሉም መምህራንና የህብረተሰብ ክፍል መተባበርና መታገል ደግሞ ራሱን የቻለ አዎንታዊ ክንዋኔ ይሆናል።

 

በሰሜን ጎንደር በተለያዩ /ቤቶች የታየው የመምህራን እንቅስቃሴ በፈር ቀዳጅነት የትግሉን አዲስ ምዕራፍ የከፈተና የሚደነቅ ከመሆኑም በላይ በአገሪቱ በመላ ሊሸጋገር የሚገባ እንቅስቃሴ ነው።

 

ከላይ አልፎ አልፎ እንደተጠቆመው ያሁኑ የመምህራን ትግል የችግሩ መንስኤ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ነው። በቅርቡ በቴሌኮሙኒኬሽን ሠረተኞች ላይ ወያኔ የወሰደውን የጭካኔ ርምጃ ማስታወስ በራሱ በቂ ነው። የኑሮ ውድነት ያልነካው ቢኖር ወያኔና ግብረ አበሮቹ ብቻ ናቸው። ወያኔ በኢትዮጵያ ሕዝብ ስም ከተለያዩ አገሮች ገንዘብ ተበድሮ ሕዝብን ዕዳ ተሸካሚ ከሚያደርግበት ለመላቀቅ ገበሬዎች ለዘመናት ከኖሩበት ቀዬ እየተወገዱና እየተሰደዱ ይዞታቸው የነበረ መሬት ለውጭ ባለሀብቶች ወያኔ ከሚቸበችብበት ተግባሩ ለመከላከል፤ በቁማችን በኑሮ ውድነት እንድናልቅ ወያኔ ከሚያደርግበት ሁኔታ ለመከላከልና ባጠቃላይ የአገሪቱን ሕልውና አዳክሞ የዜጎችን መብት ከሚረገጥበት ለመከላከል በጋራ እንነሳ። ስንት ይለያል ዘንድሮ ያልፍብናል? አናፈግፍግ።

 

በአሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያ መምህራን እያደረጉ ካሉት የሥራ ማቆም አድማ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ሠራተኛው፤ ገበሬው፤ ታክሲ ነጂው፤ ምሁሩ፤ ተማሪው፤ ነጋዴው፤ ወላጅ ከመምህራን ጎን ቆመው በመተባበርና በመሳተፍ ሕዝባዊ ትግሉን እንዲያቀጣጥሉ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።

 

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ !

 

ድር ቢያብር አንበሳ ያስር!

 

የመምህራን ትግል ግቡን ይመታል!

 

 

ሁሉም ለመብቱ ዘብ ይቁም !

 

በስደት የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር አባላት አስተባባሪ ኮሚቴ

 

መጋቢት 24 ቀን 2004 ..

 

ለበለጠ መረጃ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. በመጻፍ ሊገናኙን ይችላሉ

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ