የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ የተሠጠ መግለጫ
በሀገሪቱ ውስጥ እየደረሰ ያለው የመብት ጥሠት እና የህጋዊ ሥርዓት መናጋት በእጅጉ አሳሳቢ ሆኗል
ከኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) የተሠጠ መግለጫ
ገዢው ፓርቲ አገሪቱን ከተቆጣጠረበት ጊዜ አንስቶ እስከአሁን ባለው ሁኔታ የዜጎች የመብት ጥሰት ከእለት ወደ እለት ከመሻሻል ይልቅ እየባሰ የመቀጠሉን ሁኔታ መድረክ በከፍተኛ ትኩረት እየተከታተለው ነው፡፡ ከነዚህ መረጃዎች በመነሳትም በሀገሪቱ ውስጥ የህግ የበላይነት አለ ለማለት ይቸግራል፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ለመብት ጥሰት ሳይጋለጡ በሠላም ለመኖር የገዢው ፓርቲ አባላት መሆን የግድ እየሆነ የመጣ መሆኑንም ሲገነዘብ ታላቅ ቁጭት ያሳድርበታል፡፡ ምክንያቱም በኢህአዴግ ካድሬዎች ከሕግ አግባብ ውጭ ዜጎች ይታሰራሉ፡፡ ከሥራ ይፈናቀላሉ፡፡ ንብረታቸውን ይነጠቃሉ፤ ባጠ ቃላይ አለአግባብ ግፍና በደል ይደርስባቸዋል፡፡ ይህንን በገዢው ፓርቲ አካላት በዜጎች ላይ የሚፈፀመውን በደል መድረክ ሲመለከተው፣ ህግ የታለ? በወረቀት ላይ የመኖሩ ፋይዳው ምንድነው? እንዲል ያስገድደዋል፡፡ ለዚህ የመድረክ ድምዳሜ ለናሙና ያህል ጥቂት ማስረጃዎችን እንጠቅሳለን፡፡
1. የመድረክ ከአባል ድርጅቶቹ አንዱ የሆነው የአረና ትግራይ አባላት የደረሰባቸውን ግፍና በደል በመዘርዘር ባወጣው መግለጫ እንደተገለፀው በአረና ትግራይ አባላት ላይ እየደረሰ ያለው ግፍና በደል፣ በሀገሪቱ ህገ-መንግሥት የተደነገጉትን የዜጎች መብቶች በእጅጉ የሚፃረር እንደመሆኑ ዜጎች የፈለጉትን የፖለቲካ መስመር ደግፈው ያልፈለጉትን ተቃውመው በሠላም መኖር የማይችሉበት ሁኔታ ላይ መድረሱን ያሳያል የኢህአዴግን የፖለቲካ መስመር የሚቃወም ድርጅት አባል መሆን ለሕገ-ወጥ እስራት፣ ድብደባና ሕይወት ማጣት ድረስ ላለመጉዳት የሚዳርግ ከመሆን በተጨማሪ እንደሙያው ዜጎች ተቀጥረው መስራትና ይህ ለሚያስገኘው ጥቅማ ጥቅም ባለመብት አንዳይሆኑ አድልዎና መገለል የሰፈነበት ሥርዓት በሀገሪቱ መንገሱን ያሳያል፡፡
2. ከመድረክ አባል ድርጅቶች አንዱ የሆነው የኦሮሞ ፌዴራሊስት ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ኦፌዴን) በስፋት በሚንቀሳቀስበት አካባቢ ካገኘው መረጃ መድረክ እንደተረዳው በዜጎች ላይ እየተፈፀመ ያለው በደል እጅግ ዘግናኝ ነው፡፡ ድርጅቱ በሚንቀሳቀስበት በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት በቄለም ወለጋ ዞን በሀዋ ገላንና በሀዋ ወለል ወረዳዎች በሚገኙ ቀበሌዎች ውስጥ ዜጎች ሌቦች ናቸው፣ በማለት በፖሊሲና በሚሊሺያ ያለ ፍርድ ቤት ትእዛዝ ከያዙዋቸው በሁዋላ፣ ፖሊስ ጣቢያ በመውሰድ ከባድ ድብደባ እንደፈፀሙባቸው ተረድተናል፡፡ ለምሳሌ በሀዋ ወለል ወረዳ አውሳ ሰመራ በተባለ ቀበሌ 1ኛ ሰንበቶ ወዬሳ፣ 2ኛ ይልቅ እስራኤል፣ 3ኛ ደገፉ ሲራጋ፣ 4ኛ ወሰኑ ዲሳሳ የተባሉ ሠላማዊ ዜጎች በፖሊስ ጣቢያ ከተፈፀመባቸው ድብደባ በተጨማሪ ሰብአዊ ከብራቸውን በማዋረድ፣ በድንጋይ ዳቦ ዘመኑ በኋላ ቀር የቅጣት መፈፀሚያ ዘይቤ ገበያ ውስጥ እያዞሩ በሕዝብ ፊት የመግረፋቸው ሁኔታ ኢሕአዴግ በ21ኛ ምእተ ዓመት ይችን ሀገር ወደኋላ ቀሩ ጥንታዊ (Primitive) ሥርዓት እየወሰዳት ነው ወይ? እንድንል ያስገድደናል፡፡ እንደዚሁም፣ በዚሁ በሀዋ ወለል ወረዳ ጉራቴ ወለል በተባለ ቀበሌ ነዋሪ የሆነ ረጋሳ ቲቾ የተባለ ሰው በየካቲት ወር በቶጆ ወረዳ ፖሊስ ተይዞ ተደብድቦ ህይወቱ ማለፉን ተረድተናል፡፡ ከዚያም ሬሳውም ወደ ተገቢው ህክምና ተቋም ተልኮ መመርመር ሲገባው፣ የወንጀል ድርጊቱን ለመሸፈን ሲባል ያለምርመራ እንዲቀበር መደረጉ ድርጊቱን ለመሸፈን የተወሰደ እርምጃ መሆኑም ግልጽ ነው፡፡ ይህ መሠረታዊ የሆነ የህግ ጥሰት ዜጎች በኢህአዴግ መንግሥት የፍትሕ ሥርዓት ላይ እምነት ያሳጣ ስለመሆኑ የሟቹ ረጋሳ ቶቹ ባለቤት ወ/ሮ ተመስጌ ለሙ በድርጊቱ ተበሳጭታ ባሏ በሞተ እለት በመኖሪያ ቤቷ እራስዋን በመስቀል ህይወቷ በአሳዛኝ ሁኔታ ማለፉ ጉልህ ማሳያ ነው፡፡ የዜጎች የሰብአዊ መብት ጥሰቱ በእጅጉ የተንሰራፋ ስለመሆኑ ተጨማሪ ማስረጃ የሚሆነው ደግሞ ከሟች ረጋሳ ቱቾ ጋር በወቅቱ በፖሊስ ጣቢያ ውስጥ የነበሩት 1ኛ ሰንበቶ ወዬሳ፣ 2ኛ ገመቹ ፈጠነ፣ 3ኛ አማና ጨዋቃ የተባሉ ንፁሃን ዘጎች ከባድ ድብደባ ተፈጽሞባቸው ሀኪም ቤት ተኝተው እየታከሙ መገኘታቸው ነው፡፡
1. የመንግሥት የፀጥታ ኃይል ሠራተኞች በቄለም ወለጋ ዞን በሀዋ ገላን ወረዳ፣ በየካቲት ወር 2ዐዐ4 ዓም በጎዳና ጨዋቃ ቀበሌ ነዋሪ በሆኑ ሰዎች ላይ ጨለማን ተገን አድርገው ዝርፍያ መፈፀማቸውና ተመሳሳይ ድርጊቶች በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በኢህአዴግ የቀበሌ ባለስልጣን ካድሬዎች በሠላማዊ ዜጎች ላይ እየተፈፀሙ መሆናቸው፣
2. በደቡብ ክልላዊ መንግሥት በሀላባ ልዩ ወረዳ ቀበሌ፣ የቀበሌ ባለስልጣናት የስልጣን መቀራመት ሹክቻ ባስከተለው ግጭት የሰዎች ሕይወት ማለፈና ከፍተኛ ንብረት መውደሙ፡፡
3. በሀዲያ ዞን፣ በምሥራቅ ባደዋቾ ወረዳ በቀበሌዎች አከላለል ጉዳይ ላይ በሕዝቡ መሀከል ስምምነት በመጥፋቱ መንስኤነት በሰው ሕይወትና ንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳይ መድረሱ፣
4. በሱረማና የደዚ፣ ብሔረሰቦች መሀከል ሳይፈታ የቆየው የመሬት ይገባኛል ጥያቄ በኢህአዴግ ሥርዓት መልካም አስተዳደር ድቀት የተነሳ ወቅታዊና ፍትሓዊ ውሳኔ መስጠት ባለመቻሉ ቅራኔው ተባብሶ ወደ ግጭት በመሸጋገሩ የዘጎች ሕይወትና ንብረት በከፍተኛ ደረጃ መጥፋቱና በተለይም የሱርማውን አርብቶ አደር ሕዝብ ከመኖሪያ ቀየው እንዲሰደድ ምክንያት መሆኑ፣
5. ለጋምቤላ ክልል ጎደሬ ወረዳ በንፁሃን ዜጎች ላይ የደረሰው አሳዛኝ የጥቃት እርምጃ ይዚህ አይነቱ እንቅስቃሴዎች እየሰፋ እንዳይሄዱ መድረክን በእጅጉ ያሳስበዋል፡፡ ይኸውም በተለያዩ ፖለቲካዊ ማህበራዊና ኤኮኖሚያዊ ምክንያቶች መብቶቻቸው ያልተከበሩላቸው ወገኖች በሥርዓቱ ላይ ያላቸውን ጥላቻና ተቃውሞ ለማስተላለፍ ሲሉ ንፁሃንና ዜጎችን ጭምር ወደ ሚጎዳ አፍራሽ እርምጃዎች ውስጥ እንዳይገቡ መድረክ ይሰጋል፡፡
6. በቅርቡ በቤንች ማጂ ዞን የተከሰተው ምስኪን አርሶ አደሮችን ከመኖሪያ ቀዬአቸው በማፈናቀል በገፍና በግፍ የማባረሩ እርምጃም በሀገሪቱ የሕግ የበላይነት ከሥም ሥርዓት አልበኝነት የበላይነቱን በመያዘ ሀገሪቱን ቀውሰ ውስጥ እንዳይከታት መድረክ አጥብቆ ይሰጋል፡፡
ስለሆነም፣ የተቃውሞ ፖለቲካን ለማጥፋት ሲባል የዜጎችን ግለሰብና ቡድን መብቶችን እየ ረገጠ ያለው በሀገሪቱ መልካም አስተዳደር በመጥፋት ሕግና ሕጋዉነት የማይከበርበት ደረጃ ላይ የተደረሰበትን ሁኔታ በሠላማዊ ደሞክራሲያዊ አግባብ ለመቀየር መድረክ የሚያደርገውን ትግል በመደገፍ መጠነ ሠፊ ሠላማዊ እንቅስቃሴ ውስጥ እንዲገባ ለመላው ሕዝባችን ጥሪ እናስተላልፋለን፡፡
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ (መድረክ)
መጋቢት 23 ቀን 2ዐዐ4 ዓም
አዲስ አበባ



