ውዥንብር ውስጥ
ተስፋዬ ገብረአብ
ሰሞኑን ግርማ ብሩ አሜሪካ ለሚገኝ ሬድዮ ሰጠውን ቃለመጠይቅ በጥንቃቄ አዳምጬው ነበር። በርግጥ ሰውየው ስነአመንክዮአዊ ክርክር ይችልበታል። የሚጠቀምባቸው ቃላት ምርጥ ናቸው። ቢሆንም መረጃ ይደብቃል። ከእውነታው ይሸሻል።
ኢህአዴግ ውስጥ ስለተከሰተው የስልጣን ሽኩቻ ተጠይቆ ሲመልስ፣ “እውነት አይደለም” ካለ በኋላ፣ “… በአብዛኛው የሚነገሩት ግምት ላይ የተመሰረቱና ተጨባጭነት የሌላቸው ናቸው” ሲል ገለፀ።
ይህ የግርማ አባባል እውነት አይደለም።
“መለስ ሞቶአል ወይስ አልሞተም” ከሚለው የአንድ ሰሞን ክርክር ጋር ተመሳሰለብኝ። በረከት ስምኦን፣ “መለስ ከእንቁጣጣሽ በፊት ይመለሳል” ብሎ በፈገግታ ሲነግረን፣ እኔ በበኩሌ “በረከት አፉን ሞልቶ እንዲህ ካለ እውነቱን ሊሆን ይችላል” ብዬ አምኜው ነበር። በማመኔም፣ ዶክተር ፍሰሃን፣ “ችኩል” ብዬ ጭምር ፃፍኩበት። በዚያው ሰሞን በረከት እንደገና በቴሌቪዥን ብቅ አለና፣ “… መለስ ሊድን ሲል ለጥቂት ሞተ” ብሎ አይኑን በእንባ አጥቦ ነገረን። አስናቀች ወርቁ በዜማዋ፣ “እሱ ካበውና - እሱ ራሱ ናደው” እንደምትለው ነበር የሆነብኝ።
አሁንም ኢህአዴግ በስልጣን ሽኩቻ ውዥንብር ውስጥ መግባቱን እየካደ ነው። ፈንድቶ እስኪወጣ መካዱን ይቀጥልበታል። ኃይሌ የፓርላማውን ስብሰባ አቋርጦ፣ ካቢኔውን ሳያሳውቅ፣ ኡጋንዳ ድግስ ላይ የሚያስኬድ ነገር አልነበረውም። በትክክል መገመት እንደሚቻለው ኃይለማርያም ስራ አልበዛበትም። ሌሎች ከጀርባ እንቅልፍ እና ጊዜ አጥተው የሚሰሩ መኖራቸውን ማሽተት ይቻላል።
ዘመኑ ውዥንብር የበዛበት ዘመን ሆኖአል።
“ኃይለማርያም አሻንጉሊት ለመሆን አይፈቅድ ይሆናል” የሚል ግምታችን የሰሜን ነፋስ የመታው ደመና እየሆነብን ነው። ኃይሌ ስልጣኑን ከያዘበት እለት ጀምሮ ባደረጋቸው ንግግሮች ሁሉ፣ “የታላቁ መሪያችን ራእይ” የተባለችውን ቃል ሳይጨምር አንድም ንግግር ማድረግ አልቻለም። “ስንት ልጆች አሉህ?” ተብሎ ቢጠየቅ፣ “ታላቁ መሪያችን ምስጋና ይግባውና ሶስቱም ልጆቼ …” ብሎ እንዳይመልስ እንሰጋለን። ይህ ሁኔታ ኃይለማርያም በራስ የመተማመን ችግር እንዳለበት ይጠቁማል። የመለስን ስም ያገኘው ቦታ ሁሉ መደንጎሩ፣ ጉዳቱ እንደሚያመዝን እንኳ ማስተዋል አልቻለም።
ኦህዴድ ርግጥ ነው ታምሶአል።
በሚዲያዎች ሲገለፅ እንደሰነበተው “ለሶስት ተከፋፍሎአል” ብዬ ግን አላምንም። በመሰረቱ የአይዲዮሎጂ ልዩነት የላቸውምና በምን ጉዳይ ሊለያዩ ይችላሉ? የስልጣን ሽሚያ ብቻ ነው የሚያምሳቸው። አባዱላ እና ኩማ እሳት እና ጭድ ናቸው። ፀባቸው ግን ስልጣን ነው። በህወሓት ይበልጥ ተቀባይነት ለማግኘት ከመጣር አንፃር ነው የዘመናት ሽኩቻቸው። አንድ ባል የሚጋሩ ሁለት ሚስቶች አይነት። አባዱላ እስረኛ በመፍታትና ጥቂት የልማት ስራዎችን በመስራት ካገኘው ብጫቂ ስም በቀር የኦህዴድ አመራር አባላት ገና በራሳቸው ጭንቅላት ማሰብ አልጀመሩም። በኦነግነት የሚጠረጠረው የኦህዴድ ከፍተኛ ካድሬ በአመራሩ ላይ ያሉትን የመገልበጥ አቅም ይኖረዋል? “ነገም ሌላ ሰኞ አለ” እንዲሉ በቅርቡ የምናየው ይሆናል።
ተስፋዬ ገብረአብ
This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.



