ማርያም Mariamተስፋዬ ገብረአብ

ስብሃት ነጋ፣ በፓልቶክ ክፍል ተጋብዞ ባደረገው ንግግር፣ “ለኦርቶዶክስ ወይም ለአማራ ብቻ ተወስኖ የቆውን የኢትዮጵያ መንገስታዊ ስልጣን ለተጨቆነው ህዝብ አስረከብነው” ማለቱን አንድ ጓደኛዬ ነገረኝ። ይህን የነገረኝ ጓደኛዬ በስብሃት ንግግር በጣም ተገርሞ ስለነበር፣ “አታስብ! ስብሃት አብሻቂ የንግግር ጠባይ አለው።” ስል ጠቆምኩት። ለነገሩ በሚናገረው ባልስማማም፣ ስብሃት ያመነበትን እንደወረደ ስለሚያፈርጠው ከሌሎቹ እሱ ይሻለኛል። “በዚህች አለም ላይ መጥፎም ይሁን ጥሩ ያመንክበትን ፈፅመህና የልብህን ተናግረህ ማረፍን የመሰለ እርካታ የለም” ይል ነበር መለስ ዜናዊ - ነፍሱን ይማረውና።

 

 

ስብሃት ነጋ በርካታ ዝነኛ ያልሆኑ አባባሎች አሉት። ለመጥቀስ ያህል፣ “… ትግሬዎችን ወደመጡበት እንመልሳቸዋለን” የተባለችው የበድሩ አደም ነጠላ ዜማ የተለለቀቀች ሰሞን፣ ስብሃት እንዲህ ሲል መልስ ሰጥቶአል፣ “… እኛ ወደመጣንበት ስንባረር፣ መንዜዎችን ሰሜን ሸዋ አራግፈን ነው የምናልፈው!”

 

ርግጥ ነው፣ አቦይ ስብሃት ከአማራው ኤሊት ጋር አንድ ችግር ያለበት ይመስላል። ከመንዝ ኦርቶዶክስ የፈለቁት መሪዎች፣ የምኒልክን ቤተመንግስት “ለሰፊው ህዝብ” አስረክበው ከስልጣኑ ገለል ካሉ 40 አመታት ሞልቶአቸዋልና ዛሬ ስማቸውን ማንሳት ተገቢ አልነበረም። ዳሩ ግን ከብሽሽቁ እና ከእልሁ በስተጀርባ ያለው ፖለቲካዊ ይዘት ከቶ ምንድነው?

 

ኮሎኔል መንግስቱ በርግጥ በእናቱ የሸዋ አማራ ነው። እንደ ህወሓት ሰዎች አባባል ኮሎኔሉ የአማራው ገዢ መደብ አገልጋይ የነበረ ነው። ይሄ በራሱ አከራካሪ ነው። ኮሎኔል መንግስቱንም ሆነ መለስ ዜናዊን የኦርቶዶክስ ኃይማኖት ተከታዮች ማለትም አይቻልም። ሁለቱም ኢ-አማኒ ነበሩ። እና የስብሃት፣ “ከአማራ እና ከኦርቶዶክስ” አባበል ለምን መጣ?

 

የስብሃትን አባባል ተከትሎ ለኃይለማርያም፣ “ፀረ-ማርያም” እና፣ “ፀረ-አማራ” የተባሉ ቅፅሎች እየተሰጡት ነው። በሶሺያል ሚዲያዎች እና በድረገፆች ጭምር የኃይለማርያም መናፍቅ መሆን እየተሰበከ ይገኛል። በእግረመንገድ ምክትሉ ደመቀ መኮንን እስላም መሆኑ እየተጠቀሰ፣ “የጎንደርን መሬት ለሱዳን የሸጠ” የሚል ካባ ይመረቅለታል። ዋናው የጥቃት ኢላማ ከሆነው ኃይለማርያም ላይ የሚወረወሩት ቦምቦች በአብዛኛው ውሸት ናቸው። ለአብነት ኃይለማርያም ሶስት ጊዜ ኃይማኖት ስለመለዋወጡ የሚፃፈው እውነት አይደለም።

 

ኃይለማርያም በጴንጤነቱ እና በወላይታነቱ ምክንያት በአማሮች የደረሰበት በደል እንደ መወያያ አጀንዳ ሆኖ ጠረጴዛ ላይ ወድቆአል። እንደ ዘገባው ኃይለማርያም የወያኔ አባል ለመሆን ፍላጎት ያደረበት፣ በዘረኛነት ምክንያት እድል የነፈጉትን አማራ ግለሰቦች ለመበቀል ሲል ነበር። ባለቤት አልባው መጣጥፍ እንደሚጠቅመው ኃይለማርያም ወደፊት “በፀረ-አማራነት አቋሙ” ሊገፋበት ይችላል?

 

ለመሆኑ እንዲህ ያሉ ያልተረጋገጡ መረጃዎችን የሚለቀው ማነው?

 

ለምን አላማ?

 

በርግጥ ኃይለማርያም ፀረ-አማራ አቋም አለው?

 

ጽሑፎቹ፣ “ትምክህተኞች” በግዴለሽነት የሚበትኗቸው ናቸው ወይስ ህወሓት ሆን ብሎ ለአላማው የሚያሰራጨው? መረጃ ስለሌለኝ አላውቅም። ይህን በመሰሉ ቅስቀሳዎች ግን ወያኔ ይበልጥ ተጠቃሚ ሊሆን እንደሚችል ማሳመን ይቻላል።

 

የህወሓት ሰዎች ኃይለማርያምን በመሪነት ሲያስቀምጡ፣ ለጊዜው አማራጭ ስለሌላቸው እንጂ፣ ልባቸው ፈቅዶት አይደለም። ብአዴን የተባለውን የስልጣን ተፎካካሪ፣ ገለል ለማድረግ ግን የኃይለማርያምን ሹመት ከማፅደቅ የተሻለ አማራጭ አልነበራቸውም። እንዲህም ሆኖ የብአዴን እና የህወሓት የውስጥ ሽኩቻ ገና መፍትሄ አላገኘም። የብአዴን ሰዎች እንደ መድሃኒት ቤቱ የእባብ አርማ፣ ኃይለማርያም ላይ ተጠምጥመውበታል። ኤልያስ ክፍሌ የጀመረው፣ “ለኃይለማርያም እድል እንስጠው!” ዝንባሌም ለህወሓት አሳሳቢና ራስ ምታት ሊሆን እንደሚችል ማመን ይቻላል። ምክንያቱም ኃይለማርያምን እንደ አባዱላ ጠፍጥፈው እንዳልሰሩት ያውቃሉ። ያነበበ፣ በማንበብ ላይ ያለ እና የተማረ ሰው ነው። የተማረና ያነበበ መሆኑ፣ ብቁ የፖለቲካ መሪ ሊያደርገው ባይችልም፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ቢሮ ሲለማመደው አንጎሉን መጠቀም ሊጀምር ይችላል ብለው ይሰጋሉ። ከኃይለማርያም ሹመት በፊት ተጣድፈው ጄኔራሎቹን መሾማቸው ለዚህ አባባል አንድ ጠቋሚ ምልክት ነው። ኃይለማርያም ከምእራባውያን እና ከህዝብ በሚያገኘው ድጋፍ፣ አሻንጉሊት ላለመሆን ድፍረት ሊሆነውም ይችላል። ኃይለማርያም አንድ ደካማ ግለሰብ ቢሆንም፣ የገባበት ቢሮ ኃይል ሆኖ ሊያበረታው ይችላል። የህወሓት ሰዎች ይህን ያውቃሉ፣ ይህንንም ይገምታሉ።

 

ከኃይለማርያም በኩል ያጋጥመናል ብለው ከሚሰጉት ነገር ዋናው፣ ከብአዴን ወይም ከተቃዋሚዎች፣ (በተለይ ከአማራ ተቃዋሚዎች) ጋር የአላማ አንድነት ከመሰረተ ህወሓትን ማንሳፈፍ የመቻሉ እውነት ነው። ከወዲሁ ኃይለማርያምን ከአማሮችና ከኦርቶዶክሶች ማጋጨት ይህን አደጋ ይቀንሰው ይሆን? በትክክል ይመስላል። ለኃይለማርያም፣ “ፀረ-አማራ” እና “ፀረ-ኦርቶዶክስ” የተባሉ ቅፅሎችን የመለጠፉ ዘመቻ በማን እንደተጀመረ ባይታወቅም፣ አንድ ስሙን ያልጠቀሰ፣ “የኃይለማርያም ተማሪ ነበርኩ” ባይ ግለሰብ ግን መርዝ የተቀቡ ከረሜላዎችን በነፃ ሲያድል ሰንብቶአል። ይህን ጽሑፍ በመቃወም በጎ አስተዋፅኦ ለማድረግ የሞከረው ዶክተር አባቡ ተክለማርያም ምስጋና ያስፈልገዋል። ከምስጋና ይልቅ ግን፣ “አድርባይ” የተባለ ርግማን ሲወርድበት ነበር የሰነበተው።

 

እንግዲህ ብእሮች ኃይለማርያም ላይ ማነጣጠራቸው ግድ ነው። ኃይለማርያምን ከፀረ-ማርያምነት እስከ ፀረ-አማራነት ፈርጀነዋል። ከአሻንጉሊትነት እስከ አምባገነንነት መድበነዋል። ከየዋህነቱ እስከ መሰሪነቱ ልቡን እየቆፈርን ተንትነናል። ከጭንቀታምነቱ እስከ ኮስታራነቱ፣ እንደ ሞተር በትነን ገጥመነዋል። ኃይለማርያም ማን መሆኑ እስኪረጋገጥ፣ ወይም ኤልያስ ክፍሌ አጥብቆ እንደጠየቀው፣ “ኃይለማርያም አቋሙን ግልፅ እስኪያደርግ” ግምታዊ ሙገሳ እና ውንጀላው በዚህ መንገድ ለጥቂት ሳምንታት መቀጠሉ ግድ ነው።


ተስፋዬ ገብረአብ

 

This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

http://www.tgindex.blogspot.com

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ