ኢትዮ-ኤርትራዊነት? አልገባኝም!
ተስፋዬ ገብረአብ
ከ18 ወራት በፊት ፍራንክፈርት ላይ ከአንድ ሃበሻ ቤት ምሳ ተጋብዤ ነበር። በጨዋ ደንብ እያወጋን ሳለ፣ በመካከሉ በወንድምነት እንዲህ ሲል መከረኝ፣ ... “አንተ ኤርትራዊ ነህ። በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ እየገባህ ባትፅፍ ይመረጣል!”
ቁጭ ካልኩበት የምግብ ጠረጴዛ ፊት ለፊት ግድግዳው ላይ ኤርትራን የጠቀለለ ከእንጨት የተሰራ የኢትዮጵያ ካርታ ተሰቅሎ ነበር። በአገጬ ካርታውን ጠቆምኩትና ሳቅሁበት። እንደዋዛ ካርታውን አየት ካደረገው በሁዋላ፣
“ኤርትራ ከመገንጠሏ በፊት የተሰቀለ ነው” አለኝ።
ምክንያቱ አሳማኝ ስለነበር፣
“… እንደሱ ከሆነ በመጋዝ ቆርጠህም ቢሆን ካርታውን ብታስተካክለው ጥሩ ነው” ስል ቀለድኩ።
መቼም ኤርትራ ጣጣ የበዛባት አገር ናት። ለጃንሆይም ሆነ ለመንግስቱ መውደቅ ምክንያት ሆናለች። መለስም በኤርትራ ጦስ እንደሚሰናበት ስለሚጠረጥር ነጋ ጠባ፣ የኤርትራን ስም ካፉ አይለይም። አንዳንድ የኛ ዘመን የጨረቃ ፖለቲከኞችም፣ ኤርትራን እንደ ማስቲካ ማላመጥ ይወዳሉ። በቅርቡ በማላስታውሰው ሚዲያ ላይ አንድ አስቂኝ ጥያቄ ሰምቼ ነበር። “ኤርትራ የኢትዮጵያ ግዛት ናት” የሚሉ አሉ። አያይዘው ደግሞ፣ “…ኢትዮጵያ በቅኝ ግዛት ስር አልነበረችም” ሲሉ ይከራከራሉ። ኤርትራ ግን ቢያንስ 62 አመታት በኢጣልያና በእንግሊዝ አገዛዝ ስር ስትማቅቅ ኖራለች። ፕሮፌሰር መስፍን ግን ለየት ባለ መንገድ ይገልፁታል። “ኢትዮጵያ ከኤርትራ ተገነጠለች ቢባል ወደ እውነት እንቀርባለን” በዚህ አባባል እኔም እስማማለሁ። ኤርትራን የጎበኘ ሁሉም በዚህ ሊስማማ ይችላል …
“ኢትዮጵያዊ አይደለህም” የሚል ክስ ደጋግመው ለሚያቀርቡልኝ አስቂኝ ምላሽ መስጠት እፈልጋለሁ። በርግጥም በዚህ ሰአት ኢትዮጵያዊ አይደለሁም። ኢትዮጵያዊ የሚባለው በህግ ተቀባይነት ያለው የኢትዮጵያዊነት ሰነድ ያለው ሰው ነው። እኔ ምንም የኢትዮጵያዊነት ሰነድ እጄ ላይ የለኝም። ስለዚህ በህግ ኢትዮጵያዊ አይደለሁም። ወያኔ በካልቾ ተጠልዛ ስትባረር እና እኔ አዲስአበባ ተገኝቼ፣ ኢሚግሬሽን ቢሮ ገብቼ “ኢትዮጵያዊነቴ ይመለስልኝ” ብዬ ስጠይቅ ያን ጊዜ ተቃውሞ ማቅረብ ይቻላል። ለነገሩ ውስጥ ውስጡን እንደሚወራው ቀጣዩ የኢትዮጵያ መሪ "ስዬ አብርሃ" የሚሆን ከሆነ እዚያም አንደርስም። ሆላንዳዊ ሆኜ ለመቀጠል እገደዳለሁ። በተቀረ ስደተኛ ነን። በአገሩ የሌለ - የትም የለም።
“ኢትዮጵያዊ ስላልሆንክ ስለ ኢትዮጵያ አያገባህም” የሚል ደብዳቤ አልፎ አልፎ ይደርሰኛል። እንዴት አይነት አስተሳሰብ ነው? እነዚህ ከሳሾቼ በምእራቡ አለም ረጅም ህይወት ኖረው ስለ ግለሰቦች መብት አለማወቃቸው ቢያሳዝንም ምን ይደረጋል? መልህቅ ከአሳ ጋር ባህር ውስጥ እየኖረ ዋና አይችልም። መዘጋጃ ቤት እንደማያውቃቸው የጨረቃ ቤቶች፣ የጨረቃ ፖለቲከኞችም እንደ ሙጃ የትም በቅለው ይታያሉ። የመናገር እንጂ የማዳመጥ ችሎታ ያንሳቸዋል። አሳብን በአሳብ መመከት አያውቁበትም። የስድብ ችሎታቸው እንደ እንቧይ አበባ አብቧል። ኢትዮጵያዊ ባልሆንስ ስለኢትዮጵያ መፃፍ አልችልም? ለመሆኑ እስከዛሬ ያለው የኢትዮጵያ ታሪክ በማን ተፃፈ? በርግጥ እንዲህ የሚፅፉት እነማን እንደሆኑ መገመት እችላላሁ? ቀደም ሲል የወያኔ ሰዎች ነበሩ። አሁን ደግሞ የኢህአፓ ታንከኞች ተጨምረዋል። መለስ ዜናዊ በጣም ብልህ ሰው ነው። የኢህአፓን ስም በክፉ አንስቶ አያውቅም። እውነቱን ነው። ጠንክረው እየሰሩለት ነውና ለምን በክፉ ያንሳቸው? በተቀረ አማርኛ ቋንቋን ለፅሁፍ አገልግሎት መጠቀም መብቴ ነው። ቋንቋ እንደ ዶማና ዲጂኖ የመጠቀሚያ መሳሪያ እንጂ ሌላ ምንም ማለት አይደለም። የአማርኛ ቋንቋ ተናጋሪ የሆንኩት መርጬ አይደለም። የሚወለድበትን ቦታና የሚናገረውን ቋንቋ የመረጠ ህፃን ስለመኖሩ አላውቅም።
“ስለ ኢሳይያስ አፍወርቂ አምባገነንነት ለምንድነው የማትፅፈው?” ብለው ደጋግመው የሚጠይቁኝ አሉ። እኔ ስለማን እና ስለምን መፃፍ እንዳለብኝ የመምከር መብት ያለው ከቶ ማነው? አንባቢ ፈለገውን ብቻ መርጦ የማንበብ መብት እንዳለው ሁሉ፣ እኔም የምፅፍበትን ርእስ መምረጥ የኔ ጉዳይ ነው። በመሰረቱ ስለ ፃፍኩት እንጂ ስላልፃፍኩት ልጠየቅ አልችልም። በጣም የሚጠሉኝ ሰዎች የፃፍኩትን እያነበቡ ሲበሳጩ አያለሁ። እስከዛሬ ስላነበቡኝ አመሰግናለሁ። መበሳጨት ካልፈለጉ ግን ወደፊት እኔ የምፅፈውን ከማንበብ እንዲቆጠቡ እመክራለሁ።
አንድ ብእረኛ ህዝብን የማሳሳት ብቃት ሊኖረው አይችልም። ህዝብ የሚጥመውንና የማይጥመውን ራሱ ያውቃል። መመዘን ይችላል። የሚጠቅመውን ወስዶ የማይጠቅመውን ይጥላል። የተፃፈ ሁሉ ታሪክ አይደለም። የታተመ ሁሉ ሰነድ አይደለም። የውሸት ድሪቶ ተንገዋሉ በራሱ ጊዜ ከሰነድነት ውጭ ይሆናል። ስለዚህ ማንም ቢሆን ሌላውን ሊጠመዝዝ ወይም ሊያታልል አይቻለውም። “የቡርቃ ዝምታ” ተነባቢ የሆነው እውነት ስለሆነ ብቻ ነው። ውሸት ቢሆን ኖሮ፣ 12 አመታት ቀርቶ፣ 12 ቀናትም ቢሆን አጀንዳ መሆን ባልቻለ ነበር። የበረከት ስምኦን “የሁለት ምርጫዎች ወግ” ገና ከመወለዱ ሞቷል። አንድ ወር እንኳ አላነጋገረም። ምክንያት - በረከት ስምኦን እራሱም ያላመነበትን ነው የፃፈው። መራራ ቢሆንም እንኳ እውነትን መጨለጥ መለማመድ ይገባናል። ከተነሳ ላይቀር ግን ኤርትራን በተመለከተ ፅፌያለሁ። የከረዩ ዘመዶቼ “ኦብሳቱ አናን ጎረምሳ ዱጋ” ይላሉ ...
በተቀረ የጨረቃ ፖለቲከኞችን ማሸነፍ ከባድ አይደለም። አብላጫ አይደሉም። እንደ ምፅዋ ቁራዎች ድምፃቸው ቀበሌ ቢያናውጥም፣ አይጓዱም። ቢንቢ ጆሮ ላይ ሲያምም በርግጥ ይረብሻል። እንደሱ ናቸው። እና የብእር ሰው ነኝ:: እፅፋለሁ። የሚፈልጉ ያነቡኛል። የሚያነበኝ ባይኖርም እፅፋለሁ። መፃፍ ካቆምኩ እንደሞትኩ ጠርጥሩ። እንዲህ ያለ ተቃውሞ በገጠመው ጊዜ ጎርኪይ ምን ነበር ያለው? “… በፀጥታ ቆሞ በዝንቦች ንክሻ እንደተቸገረ ፈረስ ሆኛለሁ …”
ተስፋዬ ገብረአብ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.



