“ካርቱም ሄዶ ቀረ” እንዲሁም “ካምፓላ ሄዶ ተቀረቀረ”
ክፍሉ ሁሴን
ስደት ለወሬ ያመቻል እንዲሉ በ1999 ዓ.ም ስደት ከገባሁ ጀምሮ መጽሐፍ እጽፋለሁ እያልኩ እንደፎከርሁ አለሁ። ሳልሞክር ግን አልቀረሁም። በተለያየ ጊዜና በተደጋጋሚ እያነሳሁ ከጣልኩ በኋላ ለስንፍናዬ መጽናኛ ያደረኩት በቅርቡ እስተወዲያኛው ያሸለበው ስብሃት ገብረእግዚያብሄር በአንድ ወቅት በራዲዮ ቃለምልልስ “ከመጻፍ መኖር ይበልጣል፤ የምንጽፈው ከኑሮ ነውና” ያለውን በመውሰድ ‘መች ኖርኩና ለመጻፍ እጋበዛለሁ’ ብዬ ራሴን ቀስ በቀስ በቁመና እየገዘገዝኩት እገኛለሁ።
ስብሃት ስለኑሮ ሲያነሳ እድሜን በራሱ ብቻ ወስዶ ‘ዘለግ ያለ እድሜ የኖረ የበሰለ ስለሆነም ለመጻፍ የታደለ’ማለቱ እንዳልሆነ ከራሱ በወጣትነት ከተጀመረው የተዋጣ ጸሃፊነት መገንዘብ ይቻላል። አሊያማ በምድሪቱ ላይ መኖርን በተመለከተ ስንት ጉድ እያየሁና በራሴ ላይም ጉዱ እየፈላብኝ ስኖር አምስት አስርተ አመታትን ልደፍን ሶስት ፈሪሃ ብቻ ናት የቀረችኝ። ዝም ብሎ መኖር ሳይሆን መኖርን በማስተዋል ማጀብ፤ ያስተዋሉትንም ወደ ቋሚ ቅርስ ከሚቀይር ተሰጥኦ ጋር ተሰጥኦውን ወደ አደባባይ ሊያወጣ የሚችል ወኔ መታጠቅም እንደሚያስፈልግ ከገባኝ ቆየ። ወዴት ወዴት ጠጋ ካልተባልኩ ከፊሉ የስብሃት ታሪክ በሆነው ደራሲው በተሰኘ መጽሃፉ በአሉ ግርማም ይህንኑ ሲያስረግጥ “እውነተኛ ችሎታ አይናፋር ናት። አደባባይ መውጣት ያቅታታል።
”የእኔን መጽሐፍ ለመጻፍ የሚያበቃ ችሎታ እንተወውና በጋዜጣና መጽሄት በማናቸውም ርእስ ጥልቅ የሆኑ ጽሁፎችን የሚያሳትሙ ግን መጽሐፍ ለመጻፍ ቀርቶ እስከዛሬ በየጋዜጣው የጻፉትን እንኳ እንደ ኒዮርክ ታይምስ ጋዜጣ እውቅ አምደኛ ቶማስ ፍሪድማን በመጽሐፍ ጥራዝ ለማውጣት ዳገት የሚሆንባቸው በርካታ አፍሪካዊያን ጸሃፊዎችን ዩጋንዳ ስደት ከገባሁ ጀምሮ ለማየት ችያለሁ።
የዩጋንዳ ስደተኝነቴን ካነሳሁ ዘንዳ ወደተነሳሁበት ርእስ ልምጣ። ምኞት ብቻ ሳይሆን ከአገሬ ውጪ የተለያዩ ጥቂት የአፍሪካ፣የመካከለኛውና ምናልባትም የሩቅ ምስራቅ አገሮችን አይቀሬ ከሆነው አውሮፓና ሰሜን አሜሪካ ጋር አንድ ቀን ለመጎብኘት እንደምችል ባውቅም ጭራሹኑ ዩጋንዳ ተሰድጄ ከዚያም በአገሬ ፓስፖርት ሳይሆን ለስደተኛ በሚሰጥ የጉዞ ሰነድ እምጓዝበት ጊዜ ሊመጣ እንደሚችል አስቤበት አላውቅም።
ይልቁንስ የጊዜ ጉዳይ እንጂ ወያኔ በዚያም ሆነ በዚህ አንድ ቀን ሊያስረኝ እንደሚችል ገና በማለዳ ግምት ወስጄ ስለነበር ጥቅምት 18,1998 በሌሊት ከቤቴ ጎትቶ ከወሰደኝ በኋላ በሙስና ከሶ ዋስትና በመንፈግ ለአንድ አመት ከማእከላዊ እስከ ቃሊቲ ሲያግተኝ አለመደነቅ ብቻ ሳይሆን የመንፈስ ዝግጅቱ ስለነበረኝ ፈረንጆች በፈጣሪ የተረሳ/god forsaken/ከሚሉት የግፍና የሰቆቃ ካምፕ በጽናት እንድወጣ አስችሎኛል። የመንፈስ ዝግጅቱ ነበረኝ እያልኩ ግን ዳግመኛ በወያኔ ላለመታሰር በተፈታሁ ሶስተኛው ወር ተሰደድኩ። የፖሊቲካ ባላንጣን ሙስናን በመዋጋት ስም እንዲያኮላሹ ቀሪውም በሌብነት ከመከሰስ ውርደት ራሱን ለማዳን ፈርቶ ዝም እንዲል ማድረግ የሚችሉ እንደአቡሃይ ጓዴ የመሳሰሉ ወራዳ ህሊና ቢስ የህግ ባለሙያ ተብዬዎችን በመጠቀም የሚያሳድደው ቢሮ ሊያሳድደኝ ከመነሳቱ አንድ አመት በፊት በገዛ ፈቃዴ የለቀኩትን የኢትዮጵያ መድን ድርጅት በህግ ባለሙያነት ስሰራ ክስ ልመሰርትባቸው የሚገቡኝን ጉዳዮች የማይገባ ጥቅም ለማግኘት ሆነ ብዬ ይርጋ በማሳለፍ፤ እንዲሁም ፍርድ ቤት ሳልቀርብና ክስ ሳልመሰርት የሃሰት ሪፖርት በማቅረቤ በደርግ ጊዜ የወጣውን ልዩ የወንጀለኛ መቅጫ ህግ ጨምሮ ሰማያዊውንም ወያኔያዊውንም ድንጋጌ በመተላለፍ አገር ያሸነፍኩ ሙሰኛ ስለሆንኩ እስተወዲያኛው ዘብጥያ እንዲዘጋብኝ ጠየቀ።
ክሱ ጅል እንደነበረ ህግ ጠቅሼ ማስረጃ መዝዤ አላደክሞትም። ሆኖም እኔን ፍርድ ቤት ሳትቀርብና ክስ ሳትመሰርት እንደቀረብክና እንደከሰስክ አስመስለህ ሪፖርት አቅርብሃል--ያውም የንግድ ድርጅትን በሚመለከት የፍትሃብሄር ጉዳይ ላይ--ተብዬ ከቃሊቲ ማጎሪያ ካምፕ እየተጋዝኩ የምቆምበት የወያኔ ፍርድ ቤት ዳኛ ተብዬዎች ከእኔ በፊት ከአምስት አመታት በላይ ከየባንክ ቤቱና ንግዱ ማህበረሰብ ተለቃቅመው ከታሰሩ በኋላ ዋስትና የተነፈጉትን “ጉዳያችሁን መርምረን ብይን ሰጥተን ነበር ሆኖም የፋይል ካቢኔት ቁልፍ ስለረሳን ተለዋጭ ቀጠሮ እንሰጣለን”እያለ ፍጹም ንቀት የተሞላበት ውሸት ጋር ፍርድ የሚያዛባው ተቋም እኔን በሃሰት ሪፖርት አቅራቢነት ይዳኛል።
ከዚህም የባሰ ወያኔ የኢትዮጵያውያኖችን ደም ለከንቱ ጦርነት በከንቱ ካስፈሰሰ በኋላ ባድሜ ሳትፈረድለት ተፈርዶልኛል ብሎ በትልቅ አገራዊ ጉዳይ ላይ ትልቅ የመንግስት ወንበር ላይ ቁጭ ብለው ከመለስ ዜናዊ ጀምሮ ህዝብን የዋሹትንና በውሸት ጉዳይ ህዝቡን አስገድደው ሰልፍ ያስወጡት ባልተጠየቁበት አገር የአቡሃይ ጓዴ ቢሮ አንድ ተራ ነገረፈጅ ላይ በመናኛ የፍትሃብሄር ጉዳይ ሙስናን የሚያህል የካባ ድንጋይ ይጭንበታል። እንዳልኩዎ ክሱ ጅል ስለነበር ቢያንስ ሙሉ ለሙሉ ህሊናቸውን ያላሟጠጡት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ህግ ፋክልቲ የተመረቁት ሁለቱ “የሙስና ዳኞች”ብቻዬን ያለአባሪ የተከሰስኩበትን በስልጣን አለግባብ መጠቀም፣ሙስና ገለመሌ የሚለውን ክስ ጥለውና የአቡሃይ ቢሮ እኔን ለመክሰስ ስልጣን እንደሌለው ጠቅሰው የካባ ድንጋዩን ሊያነሱልኝ ፈራ ተባ እያሉ ሞከሩ።
“ጊዜ የሰጠው ቅል ድንጋይ ይሰብራል” የሚለውን እንደኔው ሲሰሙ ያደጉ እንደመሆናቸው ምንም እንኳ በሙያ ክህሎት እግራቸው እጣቢ ባይደርስም ከጎሳው በተጨማሪ ጫካ በነበረ ጊዜ ለነመለስ ሻይ ቡና በማቅረብ ይካድም ነበር የሚባለውንና ለውለታው ዋና “የሙስና ሰብሳቢ ዳኝነት”የተሰጠውን መድህኔ ኪሮስን ወያኔዊ ቁጣ ለማብረድ ሲሉ ሙሉ ለሙሉ በነጻ ከመልቀቅ ታቅበው አንዱን ክስ በመያዣነት አንጠልጥለው “በአፋጣኝ ፍትህ”ከአንድ አመት በኋላ በዋስ ወጥቼ በቀሪው ክስ ላይ እንድከላከል መልካም ፈቃዳቸው ሆነ። ዳሩ ግን በሚቀጥለው ቀጠሮ መከላከያ ምስክሮቼን ይዤ ስቀርብ ዳኛ ተብዬዎቹ በከፊል የተቀያየሩ ከመሆኑም በላይ በተለይም ድንክዬ ሰብእናውን የሚያካክስለት እየመሰለው ከሚለብሰው ካባ በላይ በመኮፈስ ምስክሮችን ሳይቀር የሚሳደበው ኑሩ ሰይድ መከላከያዬ እንደማይሰማና የአቡሃይ ጓዴ ቢሮ ባቀረበው ዝባዝንኬ ብቻ በተለዋጩ ቀጠሮ እንደሚፈረድብኝ ቁርጡን ነገረኝ።
ኑሩ በዚያን ጊዜ በብቸኛ የህግ ሊቅነት በደርግ ባለስልጣኖች ላይ ለቀረበው ክስ ቤት ዘግቶ ፍርድ እንዲጽፍ ተብሎ ከሙስና ዳኝነት ገለል ብሎ ነበር። እናም ያንን ግዳጁን አጠናቆ ከፍ ባለ “የፍትህ ስሜት”በእኔ ላይ እንደሚፈረድ አስታወቀኝ። ደግነቱ ሙስና የተባለው ጨዋታ የታለመው ስዬንና ተከታዮቹን ለማስተንፈስ ስለነበር ያም ግቡን ስለመታ የወያኔም አብዮት እንደደርግ አብዮት ሰክኖ ሰው የመቀርጠፍ ሃራራው ለጊዜው በመጠኑ ጋብ ስላለለት በሙስና ሰበብ የሚያግታቸውን ሁሉ ዋስትና መንፈግና የጉዞ ማእቀብ መጣል አቁሞ ነበር። እናም ኑሩና መድህኔም በኔ ላይ የጉዞ ማእቀብ ከማስተላለፍ ተዘናጉ።
እንኳን እኔን የለየለት ወንጀለኛንም ለመዳኘት የሞራል ብቃቱ የሌላቸው ሰዎች በኔ ላይ ፍርድ ሊያስተላልፉ ነው ከሚለው ጭንቀት በተጨማሪ ልዩ ትኩረት የሚሻ አዲስ የቤተሰብ ሁኔታ ለመጀመሪያ ጊዜ ስደትን እንዳሰላስል አደረገኝ። ለስደት ተስፋ ከፈነጠቀችልኝ አገሮች አንዷ ቤልጂየም ብትሆንም በኢሚግሬሽን ቢሮክራሲያዊ ዳተኝነቷ የተነሳ እህል ውሃዬ ወደዩጋንዳ ሆነና ወደዚሁ እንዳቀና ከባለቤቴ እና ጥቂት የቅርብ ወዳጆቻችን ጋር ተመካክረን ወሰን። አጨቃጫቂ የነበረው ጉዳይ ጉዞ በአየር ይሁን ወይስ በመኪና ድንበር ተሻግሮ የሚል ነበር። ስሜ በውስጠ ታዋቂ ለኢሚግሬሽን ተላልፎ ሊሆን ይችላል የሚል ፍርሃት ቢኖርም በበኩሌ የመጣው ቢመጣም በአየር ካልሆነ በመሬት በኬንያ በኩል እንደማላልፍ ወሰንኩ።
ደግነቱ ወያኔ አንዴ ከከረቸመኝ በኋላ ረስቶኛል ወይም የትም ቢሄድ ምንም ከማያመጡት የውጪ አገር ጯሂዎች አንዱ ይሆናል ብሎ ንቆኛል። ያም ሆነ ይህ ዩጋንዳ የቪዛ ጥያቄዬን ወዲያው ስለተቀበለች ኑሩ በአሳዳሪው መድህኔ ኪሮስ ወያኔያዊ የዛር ፈረስ ሊፈርድብኝ እንደነገ እኔ እንደዛሬው በኢትዮጵያ አየርመንገድ ቦይንግ 767 በካፕቴን አረፋይኔ አብራሪነት እብስ አልኩ። እናም ከአንድ ሰዓት አርባ ደቂቃ በረራ በኋላ ኢንቴቤ አረፍኩ። በመሆኑም እንደአቅሚቲ እኔም በዘውዴ ረታ በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግስት የኤርትራ ጉዳይ በሚለው መጽሐፍ ላይ “የተከበሩ ስደተኛ”ተብለው እንደተገለጹት ወልደአብ ወልደማሪያም ፓስፖርት ተሰጥቶኝ በአውሮፕላን እየተንፈላሰስኩ መጥቼ ስደተኛ ለመሆን በቃሁ። ልዩነቱ እኔ እንደወልደአብ ወልደማሪያም የኢትዮጵያ አይደለም ይገንጠል የምለው አገር የለኝም። ተወልጄ ያደኩባት አዲስ አበባ መሃል ከመሆኗም በላይ የገዛ አያቶቼንና ወላጆቼን ከኢትዮጵያ ዋና ዋና ማእዘናት በማምጣት እኔን ከፈጠረች በኋላ ፍጹም ኮስሞፖሊታን ብቻ ሳይሆን አገር ወዳድ አድርጋኛለች--አገር ወዳድነት ዛሬ የፋራ ታሪክ ቢመስልም።
እህል ውሃ በዩጋንዳ
እንዳልክዎት የውጪ አገሮችን የመጎብኘት እቅድ ቢኖረኝም ዩጋንዳ በህልሜም በውኔም መጥታ አታውቅም። ያውም እሸሸግበት ጥግ በመፈለግ አንድያዬን ተፈጥሜ ልኖርባት?እንዴት አድርጌ ላስበው እችላለሁ?የሆነው ግን እንዲያ ነው ተስፋዬ ገብረአብ ማለት እንደሚወደው። እናም የውጭ አገር ልጎበኝ እንደምችል የሚያሳየው የመጀመሪያው መርገጭ/ብሩህ አእምሮ ያለው ያልተማረው ጎጃሜ አጎቴ ቪዛን የመሳሰሉ ማህተሞችን መርገጭ ይላቸዋል/በፓስፖርቴ ላይ የተመታው አዲስ አበባ በሚገኘው የዩጋንዳ ኤምባሲ ሆነ። በወቅቱ ከወያኔ ፍርደገምድልነት ማምለጤን እንጂ በፓስፖርቴ ላይ የተመታውን የመጀመሪያ የሆነውን የመርገጩን ጉዳይ እምብዛም አላጤንኩትም። ምንም እንኳን ከዚያ በኋላ የተለያዩ የአፍሪካ አገሮችን የመጎብኘት እድል ቢያጋጥመኝም በኢትዮጵያዊነቴ ያገኘሁት ፓስፖርት ላይ በዩጋንዳ መንግስት የተመታው መርገጭ ግን የመጀመሪያውም የመጨረሻውም ሆነ።
ለስደተኛ አለማቀፍ መጓጓዣ አገልግሎት እንዲሆን የሚሰጠውን ሰነድ ስወስድ በወያኔ ኢሚግሬሽን የተሰጠኝን ፓስፖርት መመለስ ቢጠበቅብኝም በዚህ ፓስፖርት ዩጋንዳ ከመምጣቴ ጋር የተያያዙ አንዳንድ አስገራሚ መገጣጠሞችን ያጫወትኳቸው ዩጋንዳውያን ባለስልጣን ወዳጆቼ ፓስፖርቱን በታሪካዊ ሰነድነት እንድይዘው ፈቀዱልኝ። በነገራችን ላይ ይህ በወያኔ አገዛዝ ሙስና ሆኖ በትላቁ ሊያስከስስ ይችላል። ይህን ያነበበ አፍቃሪ ወያኔም ለአሳዳሪዎቹ ነግሮ በዩጋንዳ ባለስልጣናት ሊያሳቅለኝ አይሞክርም አይባልም። ከሆነ ከዩጋንዳዊያን ወዳጆቼ ጋር ሆነን እንደአፍሪካን አሜሪካኑ ተዋናይ ኤዲ መርፊ ሆዳችንን ይዘን እንስቃለን። አሁን ወደመገጣጠሞቹ ልውሰዶት።
ነፍስ ካወቅሁ ለመጀመሪያ ጊዜ በአይኔ ያየሁት የውጭ አገር መሪ ዩጋንዳዊውን ኢዲ አሚንን ነው። በ1967 ሰኔ ወር አካባቢ ይመስለኛል ከታናሼ ታናሽ ጋር ከሆነ ቦታ ቦሌ ሩዋንዳ ኤምባሲ ወደሚገኘው መኖሪያ ቤታችን ለመመለስ በወሎ ሰፈር በኩል ስናቋርጥ ከቦሌ ማተሚያ ቤት ጀርባ/ማተሚያ ቤቱ በዚያን ዘመን አልነበረም/ወደሚገኘው ዩጋንዳ ኤምባሲ አካባቢ ስንቃረብ የሰው ግርግርና በርካታ የታጠቁ ወታደሮች አየን። የታጠቁ ወታደሮች ቢኖሩም ክፉው 1969 ገና ስላልባተ ሲቪሉ ህዝብ ያለምንም መሸበር አንድ ቦታ ተክሎ ወደአንድ አቅጣጫ አተኩሯል።
ሁኔታው የኛንም ትኩረት ስለሳበው በእድሜ እኩዮቻችን የሆኑ የአስር የአስራ አንድ አመት ልጆች ፈልጌ ምን እንደተፈጠረ ጠየቅሁ። ከልጆቹ ቀድሞ አንድ ጎልማሳ ኢዲ አሚን ከጀኔራል ተፈሪ ባንቲ ጋር ኤምባሲውን ለመጎብኘት እንደመጣ ነገረን። ገና በማለዳ ኢዲ አሚን ከአካሉ ግዝፈት በተጨማሪ የዩጋንዳ ንግስናው ታሪኩን አግዝፎት ስለነበር እኔም ወንድሜም ሳንነጋገር በጨረፍታም ቢሆን ሳናየው እንደማንነቃነቅ ተስማማን። አመርቂ ባይሆንም ከነአጃቢዎቻቸው ከኤምባሲው ሲወጡ ጀኔራል ተፈሪንና አሚንን ለማየት ቻልን።
ከአመታት በኋላ የቪዲዮ ቴክኖሎጂ ሲመጣ ቴክኖሎጂውን በማስገባት ግምባር ቀደም ከሆኑ የቦሌ ዲታዎች ቤት በአንዱ በልጃቸው አማካኝነት Raise & fall of Idi Amin Dada የተሰኘው ፊልም በመጀመሪያ በቪዲዮ ያየሁት ለመሆን በቃ። ይባስ ብሎ በኢንግሊዚኛ ንባብ ከልብወለድ ኢልብወለድ መጽሐፍ ስሸጋገር እጄ የገባው የመጀመሪያ መጽሐፍ በአሚን ዘመነመንግስት የጤና ጥበቃ ሚኒስትር የነበረው ሄንሪ ኪምባ የተባለው ሰው ስለአሚን አገዛዝ ጨካኝነት ከተሰደደ በኋላ የጻፈው A State of Blood ሆነ። እንደነገርኩዎ መሰደዴ ሐቅ ሲሆን ለውጭ አገር ጉዞ በመጀመሪያ መርገጭ ያስመታሁባት ዩጋንዳ እህል ውሃዬ ከመሆን አልፋ በአጋጣሚ ከህይወቴ ጋር የሚገጣጠመው ታሪኳ እየመሰጠኝ ይሄድ ገባ።
ከሁሉም በላይ እስከዛሬ የሚያስደምምኝ ዩጋንዳ ከመምጣቴ በፊት በቅኝ ስለተገዙ አገሮች የነበረኝ ግምት እዚህ ከመጣሁ በኋላ እጅጉን ሲፋለስ ልጽፍበት ይገባል ብዬ አንዳንድ መረጃዎች ሳሰባስብ በፊት ያላጤንኩት ሌላ አጋጣሚ ከዩጋንዳ አመጣጤ ጋር መገጣጠሙ ነው። ዩጋንዳ ከመምጣቴ በፊት ሁሉም ባይሆንም አብዛኞቹ በቅኝ የነበሩ አገሮች ከእኛ በተሻለ ዘመናዊነት ላይ ይገኛሉ የሚል ግምት ነበረኝ። በሚያሳዝን ሁኔታ ኢንቴቤ አርፌ ወደካምፓላ ጉዞ የጀመርኩ የመጀመሪያውኑ ቀን ይህ ግምቴ ያላንዳች የችሮታ ዘመን ወዲያውኑ ተንኮታኮተ። አንዳችም የዘመናዊ ከተማ እቅድ አይታ የማታውቅ የምትመስለው ካምፓላ ካፒቴን አረፋይኔን ሁሉ እንድጠረጥር አደረገችኝ።
አንጋፋው ካፒቴን በናቪጌሺን ስህተት አርባ ምንጭ ጥሎኝ የሄደ እስኪመስለኝ ድረስ እንግሊዝ ያቀናው አገር መሆኔን ተጠራጠርኩት። መንገዳቸው ሁሉም ቦታ እንደክፉ ገላ የፈራረሰ ቀኑን ሙሉ የሚቆየው የትራፊክ ጭንቅንቅ በየቦታው ከሚወጣው ልክየለሽ ሙዚቃና የሽያጭ ማስታወቂያ ጋር ተዳምሮ ከፍተኛ የአእምሮ ጭንቀት የምትፈጥር ከተማ ነው የጠበቀችኝ። ሳይደግስ አይጣላም እንዲሉ ዩጋንዳውያንን ግን ቄጠማ/ከተስፋዬ ገ/አብ የኮረጅኩት ሌላ ቃል መሆኑ ነው/ሆነው ነው ያገኘኋቸው። እናም በገዛ አገራቸው ሳይጠሩኝ ልሸሸግ መጥቼባቸው አገራቸውን ሳማርርና ስነጫነጭባቸው እኔኑ መልሰው ከማጽናናትና በሆደሰፊነት የምለውን ሁሉ በቅንልቦና ከማዳመጥ ውጪ ‘አገርህ አይደለም ስትሮጥ መጥተህ ምን ታላዝናለህ’በሚል ስደተኝነቴን ሊያስታውሰኝ የሚሞክር ዩጋንዳዊ አጋጥሞኝ አያውቅም። በተቃራኒው በአገራቸው ፖሊቲካዊ ማህበራዊና ኢኮኖሚ ነክ ጉዳዮች ሁሉ የሚመስለኝን በአደባባይ በፈለኩት የመገናኛ ብዙሃን እንድተች በየጊዜው የሚጋብዙኝ ከመሆኑም ባሻገር ትንሽ ፍራንክም ካለኝ መሬት ገዝቼ ኑሮዬን እዚሁ እንዳደላድል ይመክሩኛል። እግረመንገዳቸውንም ስለእኛ በቅኝ አለመገዛትና ኮሎኒያሊዝምን አፈርድሜ ስላስጋጥንበት ታሪክ የተማሩት ዛሬ ከሚያዩን አሜሪካና ካናዳ ናፋቂ ኢትዮጵያዊያኖች ጋር እንደሚጋጭባቸው ሳያለዝቡ ይነግሩኛል።
ይህኛው ራሱን የቻለ ታሪክ ስለሚወጣው በይደር አቆይቼ ዩጋንዳ እያደር እየሰነበትኩ በሄድኩ መጠን በአስተናጋጄ አገር ህዝብ ላይ እንዲሁም ዩጋንዳ ኗሪ በሆኑ የገዛ ራሴ ወገኖች ላይ የማየው በፍጹም ተቃርኖ የተሞላ ህይወት ይበልጥ እንድጽፍበት ይጎነትለኝ ገባ። በዩጋንዳውያኑ መመሰጥና መደመም ሲበዛብኝ ጉንተላውንም ለማስታገስ ዩጋንዳ በገባሁ በሁለተኛው አመት የሆነ ነገር በፈረንጅኛ ልጽፍ ተነሳሁ። ለጽሁፌ የሚሆኑ አንዳንድ መረጃዎች ሳሰባስብ ታዲያ ኢዲ አሚን በመፈንቅለ መንግስት ስልጣን የያዘው እ.ኤ.አ ጃኑዋሪ 25,1971 እንደነበር ተረዳሁ። ይገርምዎታል እኔም ዩጋንዳ እግሬ የረገጠው በዚያኑ ቀን አሚን ከእሱ በፊት የነበረውን ሚልተን ኦቦቴን በገለበጠበት ሰላሳ ስድስተኛ አመት እ.ኤ.አ በ2007 ነው።
ዩጋንዳ በገባሁ ሁለተኛው አመት ማለትም እ.ኤ.አ በ2009 ከምኖረው ኑሮ ከማየውና ከምታዘበው ጋር ተጨማምሮ በዚያን ጊዜ አርባ ሰባተኛ የነጻነት በአሏን ለማክበር በዝግጅት ላይ በነበረችው ዩጋንዳ ላይ “Two years in a nation only two years older than me” በሚል ርእስ የሆነ ስንክሳር ጀምሬ ከስንፍናዬ ጋር አንድ ፋታ የማይሰጥ የኑሮ ጣጣ ሲያጋጥመኝ ተውኩት። ፌሎውሺፕ በሚሉት ስታይል እንድጽፍ ብቻ እዚሁ ዩጋንዳ ኑሮ የሚባለውን ጣጣ የሚሸክፍልኝ ባገኝ ማን ያውቃል ያኔ ከጀመርኩት በበለጠ ልጽፈው እችላለሁ። ተተመኙ አይቀር እንዲህ ነው። ገሃዱ አለም ለምኞት ብዙም በር ስለማይከፍት ምኞቱን ትቼ በአምስት አመት የስደት ኑሮ ውስጥ አምስት የመኖሪያ ሰፈር የቀያየርኩባት ዩጋንዳ ሃምሳኛ የወርቅ ኢዮቤልዩ የነጻነት በአሏን ለማክበር በዝግጅት ላይ ስለሆነች ጀምሬ ከተውኩት ስንክሳር የበለጠ የማውጣት እድል እንደመጣልኝ ይሰማኛል። ደበበ ሰይፉ “አንቺ ልጅ ኩሪባቸው፤በእንግሊዝ አናግሪያቸው”በሚል ዘፈን የዘፈነውንና ያዘፈነውን ትውልድ “ረግረጋማ”ሲል በብርሃን ፍቅር ቅጽ 1 መግቢያ ላይ የዠለጠበት ሊመለከተኝ ቢችልም የምጽፈው ከሆነ እየጎለደፍኩም ቢሆን በእንግሊዝ አፍ ይሆናል። ስለምን ዩጋንዳውያንም እንዲያነቡኝ።
ይሁንና ዩጋንዳንና ዩጋንዳውያንን ያስተዋወቀኝ ስደት ግን ከመጀመሪያው ጀምሮ ቀናኢ ስለነበር ይበልጥ በስደት በራሴ ስደተኝነትና በኔ ቢጤ ስደተኞች ላይ ብቻ እንደቆዝም አስገደደኝ። ሃ ብዬ ቁዘማውን ስጀምር ታዲያ ትዝ ያለኝ በልጅነቴ ያነበብኩት በቅርቡ ህይወታቸው ባለፈው ማሞ ውድነህ የተደረሰው “ካርቱም ሄዶ ቀረና ዲግሪ ያሳበደው”በሚል የተለያየ ርእስ ሁለት አጫጭር ታሪኮችን በአንድ ላይ ያሳተሙበት መጽሐፍ ነው። ያነበብኩት የአራተኛ ወይም የአምስተኛ ክፍል ተማሪ በነበርኩበት 1966 ወይም 1967 ስለነበር በአብዛኛው ተረስቶኛል። የሁለቱም አጫጭር ልብወለዶች ጭብጥ ግን በድንግዝግዝም ቢሆን ይታወሰኛል።
ከኔ ጋር የሚያያዘው “ካርቱም ሄዶ ቀረ”ታሪክ የሚያጠነጥነው በኤርትራ ፌዴሬሽን መፍረስ ወይም በመሃል አገር አገዛዝ ቅሬታ የተሰማቸው የኤርትራ ተወላጆች በመናኛ ብስጭት አኩርፈው ወደ ሱዳን ከተሰደዱ በኋላ ኑሮ ሳይመቻቸው ቀርቶ ለመመለስ እየፈለጉ ካፈርኩ አይመልሰኝ አባዜ የተነሳ እዚያው ካርቱም እየማቀቁ እንደቀሩ የሚያሳይ ነበር። በነገራችን ላይ መጽሀፉ የታተመው በሃምሳዎቹ መጀመሪያ ገደማ ነበር። እና እኔንም ስደት ካምፓላ ጎትቶ ካመጣኝ በኋላ በዚያን ጊዜ በጥጋብ መልክ የተጀመረው የኤርትራዊያን ክህደትና ስደት እንዴት ከአስር እጅ እጥፍ በላይ አድጎ አሁን የሚያሰድድ ተጨባጭ ምክንያት ኖረም አልኖረ እንዴት የኑሮ መላ እንደሆነ ሳይና ይህንኑም በሽታ እንዴት ወደኛ እንዳጋቡብን ስመለከት እኔስ ለምን “ካምፓላ ሄዶ ተቀረቀረ”በሚል አልጽፍም ብዬ ብዙ ጊዜ ተነስቼ ነበር። ከመጻፌ በፊት ግን “ካርቱም ሄዶ ቀረ”ን መከለስ እንዳለብኝ ተገንዝቤ እስከዛሬ በይደር አቆይቼዋለሁ። ነፍሳቸውን ይማርና የማሞ ውድነህን ይህን መጽሐፍ የት አገኝ ይመስልዎታል?ለመሆኑ እኔ Literary vintage ብዬ የምጠራቸውን እንዲህ ያሉ የቆዩ የጥበብ ስራ በድጋሚ ለማሳተም የሚያስብ ተቋም ወይም በጎአድራጊ ግለሰብ ሰምተው ያውቃሉ?
አስተያየት ሊሰጡኝ ቢሹ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.



