ግርማ ካሣ - ቺካጎ (This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.) እሁድ ነኀሴ 18 ቀን 2000 ዓ.ም.

Tirunesh Dibaba, Beijing Olympic, 20080822Kenenisa Bekele, Beijing Olympic, 20080823

“ድሮ መች ነበረ ዘር መርጦ ጎሮቤት

በጠዋቱ በጥንቱ በነአባብዬ ቤት

እድር መቃብሩ ሲያሰባስባቸው

መች ይጠየቅ ነበር የዘር ሃረጋቸው” 1

በቤጂንግ አትሌቶቻችን በወርቅ፣ በብር እና በነኀስ የተሰሩ ሜዳሊያዎች ብቻ አልነበረም ያስገኙት። የኦሎምፒክ ኮሚቴ ከሚሰጠው ሜዳሊያዎች ያለፈ፣ የኦሎምፒክ ባለሥልጣናት የማያወቁት፣ እጅግ በጣም የከበረ የሜዳሊያዎች ሁሉ ሜዳሊያ ይዘውልን መጥተዋል። … አሲዮ ቤሌማ!!!

 

ይህንን የከበረ “ሜዳሊያ” ያስገኙት ቀነኒሳ በቀለ፣ ጥሩነሽ ዲባባ፣ መሰረት ደፋር፣ ስለሺ ስኅን እና ፀጋዬ ከበደ ብቻ ሳይሆኑ ከኦሎምፒክ ኮሚቴ ሜዳሊያ ያላገኙ እነ እጅጋየሁ ዲባባ፣ ኃይለ ገብረሥላሴ፣ ዘምዘም አሕመድ፣ መስታወት ቱፋ፣ ያዕቆብ ጃርሶ፣ ገለቴ ቡርቃ እና ዲኔ ጡኔን ጨምሮ በቤጂንግ ኦሎምፒኩ ኢትዮጵያን ወክለው የተሳተፉ ወገኖቻችን በሙሉ ናቸው። (በዚህ አጋጣሚ ለአትሌቶቻችን በሙሉ ያለኝን ፍቅር፣ አክብሮትና አድናቆት እየገለጽኩኝ፣ ላደረጉት ለሠሩትና ላባረከቱት ሁሉ የኢትዮጵያ አምላክ እግዚአብሔር ይባርካቸው! እላለሁኝ።)

 

ይህ የሜዳሊይዎች ሁሉ ሜዳሊያ “ኢትዮጵያዊነት” ነው። ይህ ሜዳሊያ የኢትዮጵያውያን በአንድ ላይ መምጣት፤ ይህ ሜዳሊያ የኢትዮጵያውያንን አንድን ነገር የመፈለግና የመመኘት ነገር፤ ይህ ሜዳሊያ ከዚህ በፊት ተሰውሮብን የነበረውን አንድነታችንን የሚያሳይ ነው።

 

ኢትዮጵያን ሪቪው፣ ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል፣ አይጋ ፎረም፣ ኢትዮጵያ ፊርስት፣ ኢትዮሜዲያ፣ ኢትዮፓለቲክስ፣ አቡጊዳ፣ ኢትዮ ላየን፣ ኢትዮጵያ ዛሬ፣ ናዝሬት፣ አባይ ሚዲያ፣ ማኅደር፣ … እንዲሁም በርካታ ኢትዮጵያዊ ድረ-ገጾች ልዩነት ሳያደርጉ አትሌቶቻችን በቤጂንግ የሠሩትን አኩሪ ታሪክ በኩራትና ፕሮፌሽናሊዝም በሞላበት መልኩ ሲዘግቡልን እንደነበረ ሁላችንም የምናወቀው ነው። እነዚህ ድረ ገጾች በአንድ ላይና ለአንድ ዓላማ ሲሠሩ አይተናል። እነዚህ ድረ ገጾች “አንድ ሆነው” አይተናል።

 

ዳግማዊያን ምሩጽ ይፈጠሮች፣ ጥሩነሽ ዲባባ እና ቀነኒሳ በቀለ ደውል ሲደወል በመጨረሻ ዙር ላይ አፈትልከው ሲወጡ፣ ስለሺ ስኅን እና መሰረት ደፋር ሲከተሏቸው፣ ፀጋዬ ከበደ በማራቶን ለመቅደም ሲጣጣር … በቴሌቭዥንና በኢንተርኔት የተከታተልን ሁሉ ግማሾቻችን ዓይኖቻችን አፍጠው፣ ግማሾቻችን ቆመን ወገባችንን በእጆቻችን ይዘን፣ ግማሾቻችን ሰውነታችንን ሲነዝረን እንደነበረ አስባለሁ።

 

ሁለት ሦስት ሆነን በቡድን ሩጫዎቹን የተከታተልን ደግሞ በደስታ የተቃቀፍንና የተሳሳምን ይመስለኛል። ሁላችንም በኢትዮጵያዊነታቻን ከመደሰት አልፎም ትልቅ ኩራት ተሰምቶናል። ሁላችንም ኢትዮጵያዊ በመሆናችን ቀና ብለናል። ሁላችንም በአንድነት በጋራ ኀሴት አድርገናል። በዚህ ወቅት አትሌቶቻችን እግዚአብሔር ይስጣቸውና አንድ አድርገውናል። ይህም ለኢትዮጵያም ሆነ ለዘመናት በጉስቁልና ሲኖር ለነበረው ህዝቧ እጅግ በጣም ትልቅ ገጸ በረከትና ከወርቅ የበለጠ ትልቅ ሜዳሊያ ነው።

 

ኢትዮጵያ አራት ወርቅ፣ አንድ ብር፣ ሁለት ነኀስ በማግኘት በኦሎምፒኩ ውድድር አሥራ ስምንተኛ ወጥታለች። ሕንድን፣ ካናዳን፣ ኢንዶኔዚያን፣ ሳውዲ ዐረቢያን፣ ግብጽን፣ … ከመሳሰሉት ሀገሮች ሁሉ ቀዳሚ ስትሆን የሀገራችን ስም በተለያዩ መገናኛ ብዙኀን በቀዳሚነት ለመጠራት በቅቷል። የሀገራችንን ባንዲራ ለብሰው አትሌቶቻችንን ፎቶግራፋቸው በየታዋቂ ዓለም አቀፍ ድረ-ገጾች ላይ ሲወጣ ነው ያለፉት አሥራ አምስት ቀናት የሰነበቱት። በርግጥ እነዚህ ያለፉት አስራ አምስት ቀናት ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያ ህዝብ እጅግ በጣም ታሪካዊና የሚያኮሩ አሥራ አምስት ቀናት ነበሩ ማለት እችላለሁ።

 

ይህ ለአሥራ አምስት ቀናት በመካከላችን ሲመላስ የነበረው የአንድነትና የደስታ መንፈስ ሰፈራችንና ደመናችንን ለቆ እንዳይሄድና በኛው ዘንድ እንዲዘልቅ ለማድረግ የሚያስፈልገውን ሁሉ ማድረግ ይጠበቅብናል። አትሌቶቻችን ያስገኙልንን የአንድነት መንፈስ እንደ ከበረ እንቁ አጥብቀን ልንይዘውና በእኛው ዘንድ ለዘለቄታው እንዲቆይ ማድረግ ያስፈልጋል። እንዲህ አይነቱ ዕድል ብዙ ጊዜ አይገኝም። ከዚህ በፊት የምናየውና የምንሰማው የሚያጣላ፣ የሚያሳዝን፣ አንገት የሚያስደፋ፣ ሀገር ለቆ የሚያስኮበልል ብቻ ነበር። እርስ በርስ ያለመተማመንና በዓይነ ቁራኛ የመተያየት ነገር ነበር።

 

ይህ ያለፉት አሥራ አምስት ቀናት ግን በሚያስደንቅ ሁኔታ አቀራርቦናል። ወደ አንድነት አምጥቶናል። ይህን አጋጣሚ ለዘለቀታዊ መፍትሔ እንጠቀምበት።

 

ሊያራርቀን የሚፈልግ ሠይጣን አለ። ሊያራርቁን የሚፈልጉ የኢትዮጵያ ታሪካዊ የውጭ ጠላቶች አሉ። ምኞታቸውን አናሳካላቸው። “እኛ ኢትዮጵያውያን አንድ ነን! ችግሮቻችንን በጋራና በውይይት መፍታት እንችላለን። እንደ ቀድሞ በእብደት የተለከፍን ይመስል እናደርገው እንደነበረ እርስ በርስ አንገዳደልም!” ብለን መቁረጥና መወሰን አለብን። “በጋራ ሀገራችንን ማንሳት እንችላለን!” ብለን ለመያያዝ እጆቻችንን የምንዘረጋበት ጊዜ አሁን ነው።

 

ኢትዮጵያ በድህነት በጣም ወደኋላ ከቀሩት ሀገሮች መካከል ትገኛለች። በቤጂንግ ኦሎምፒክ አስራ ስምንተኛ ብትሆንም በብልጽግና ግን አሥራ ስምንተኛ ልትሆን የምትችለው በድህነታቸው ከመጨረሻዎቹ ሀገሮች አንድ ተብሎ መቁጠር ከተጀመረ ነው። ይህ በጣም የሚያሳፍርና የሚያሳዝን ከመሆኑም ባሻገር እያንዳንዱን ኢትዮጵያዊ ውስጡን ሊያደማ የሚገባ ጉዳይ ነው።

 

ሰባ፣ ሰማኒያ ሚሊዮን ደርሰናል። እንደ ዓባይ፣ ሸበሌ የመሳሰሉ ለሌሎች ሀገራትም ሳይቀር የተረፉ አንጋፋ ወንዞች ሞልተውናል። በሚገባ አልተያዘም እንጂ መሬታችን ገራገርና ለምለም ነው። በሁሉም መስክ በሠለጠነና በተማረ ኢትዮጵያዊ የሰው ኃይል ተንበሽብሸናል። በኦሎምፒክ እንዳገኘችው ደረጃ (ድንገትም ከዚያም በላይ) በብልጽግናም ሚዛን በርግጥ ኢትዮጵያን ከዓለም አሥራ ስምንተኛ ማድረግ እንችላለን።

 

“ኦሎምፒክ - ኢትዮጵያ - አንድነት” በተሰኘው፣ የኦሎምፒኩ ውድድር እንደተጀመረ ሰሞን “አውደ ኢትዮጵያ” ዕትም 12 ካወጣው ጥቂቱን መጥቀስ እፈልጋለሁኝ። (አውደ ኢትዮጵያ የሰሜን አሜሪካ የአንድነት ድጋፍ ድርጅት ስር ያለ ጋዜጣ ነው)

 

“አትሌቶቻችን ለአገራቸው ክብር በቤጂንግ ይገኛሉ። እግዚአብሔር ብርታቱን ይስጣቸው። ለሚያደርጉትም መስዋዕትነት እግዚአብሔር ያክብርልን። መልካም ውጤት እንዲያገኙ እጅጉን ምኞታችን ነው። እግዚአብሔር ይርዳቸው! ይከተላቸውም! እነርሱ ለሀገራቸው እንደተሰለፉ፣ እኛ ደግሞ የነርሱን ድል ከመመኘትና ከመናፈቅ ጎን ለጎን እራሳችንን ጥያቄ መጠይቅ ይኖርብናል። ለአገራችን ኢትዮጵያ እኛስ ምንድን ነው የምናደርገው? መቼ ነው በሩጫ ሳይሆን ባለንና በምንችለው ሁሉ የ”የወርቅ ሜዳሊያዎችን” ለኢትዮጵያ የምናመጣው? መቼ ነው ኢትዮጵያን አንድ እርምጃ ወደፊት የምናራምደው? ኢትዮጵያውያን በአራት ዓመት አንዴ ብቻ አይደለም በአንድ ላይ መምጣት የደስታ ባህል ማድረግ ያለባቸው። አሁን! ነገ! … ሁልጊዜ በአንድ ላይ መሆን አለብን። አንድነት ኃይል ነው። መከፋፈል የሕልውና ፀር ነው።” 2

 

አውደ ኢትዮጵያ እንደጠየቀችው እያንዳንዳችን እራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል። እያንዳንዳችን የድርሻችንን ለማድረግ መወሰንና መነሳት የግድ ነው። ኢትዮጵያ የጋራ ሀገራችን ናት። ጥቂቶች መስዋዕትነቱን እንዲከፍሉ፣ ጥቂቶች እንዲደክሙ መጠበቅ የለብንም። እያንዳንዱ በየፊናው ሲሰማራ፣ ‘አምሳ ሎሚ ለአንድ ሰው ከባድ ነው ለአምሳ ሰው ግን ቀሊል ነው’ እንደሚባለው ትልቅ የተባለውን የሀገራችን ችግር መገርሰስ እንችላለን! አንድነት ሁልጊዜም ኃይል ነው!!!

 

እንግዲህ እያንዳንዳችን ለ”ኦሎምፒኩ” ውድድር የምንዘጋጅበት ጊዜ ነው። ከአራት ዓመት በኋላ ሎንዶን የሚደረገው ኦሎምፒክ ሳይሆን ከአሁን ጀምሮ በአዲስ አበባ፣ በጎንደር፣ በአዋሣ፣ በያቤሎ፣ በከረን፣ በምጽዋ፣ በጨርጨር፣ በጊሞቢ፣ በውቁሮ፣ በወልዳይ፣ በደጀን በጭናቅሰን፣ … ወዘተ የሚደረግ “ኦሎምፒክ” ነው። ይህ “ኦሎምፒክ” ኢትዮጵያን በዓለም ደረጃ በዲሞክራሲያዊ ሂደት፣ በሠላም፣ በኢኮኖሚ፣ በትምህርት፣ በጤና፣ በቴክኖሎጂ፣ … ቀዳሚ ለማድረግ የሚደረግ ውድድር ነው።

 

ሁላችንም ንስኀ ገብተን፣ ያለፈውን ምዕራፍ ዘግተን፣ በአዲስ መንፈስና በአዲስ ጅማሬ እንደገና መነሳት፣ በጥላቻ፣ በፍርሃት፣ ባለመተማመን፣ በጭካኔ፣ በአጭበርባሪነት፣ በሙስና፣ በዘረኝነት፣ በቂም በቀል የተሞላውንና የደነደነውን ድንጋዩን ልባችንን አውጥተን በፍቅር፣ በደግነት፣ በመቻቻል፣ በይቅርታና በምህረት እንዲሁም በፈሪሃ እግዚአብሔር የተሞላውን ልብ እንያዝ። የአዕምሮና የአመለካክት ተኀድሶ እናድርግ። ኢትዮጵያ ሀገራችንም አሁን የደረበችውን የውርደት ካባ እንግፈፍላት። እነ ጥሩዬና ቀነኒሳ ጀምረውታል። እኛም እንከተላቸው!

 

“አንድ አርገን!” ከሚለው የአስቴር አወቀ የአንድነት ዜማ በወሰድኳችው ጥቂት ሀረጎች ጽሑፌን እንደጀመርኩት “ሞፈሩን ያዙና ይቅር ተባባሉ” እያለ ቴዎድሮስ ካሣሁን ባቀነቀነው እዘጋለሁኝ።

 

“ዘጸዓት ለኢትዮጵያ ወደ ተስፋ ጉዞ

ባህር የሚያሻግር አንድ ሙሴን ይዞ

ቅርብ ነው አይርቅም የኢትዮጵያ ትንሣዔ

በአንድነት ከገባን የፍቅር ሱባዔ

 

ፍቅር አጥተን እንጂ በረሃብ የተቀጣን

አፈሩ ገራገር ምድሩ መች አሳጣን

ኦሲሳ ኦሲሳ ኦሲሳ ማንዴላ

ይቅር አባብሎ እንዳስጣለ ዱላ

በተስፋው ምድር እንዲፈጸም ቃሉ

ሞፈሩን ያዙና ይቀር ተባባሉ” 3

 

እግዚአብሔር በአትሌቶቻችን በኩል ስለከፈተለን በር ስሙ የተመሰገነ ይሁን! ልቦና ሰጥቶን እኛም እንደነርሱ የአንድነትና የፍቅር፣ የመቀራረብና የመደጋገፍ አምባሣደሮች ሁላችንንም ያድርገን! - አሜን!!!


 

1 http://www.youtube.com/watch?v=C6nnCFKyIXM&feature=related

2 http://www.abugidainfo.com/wp-content/uploads/2008/08/awde_12_final.pdf

3 http://www.youtube.com/watch?v=oUIl6JKqqz4 


 

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ