ይገረም አለሙ

አልተገናኝቶም

የፖለቲካ ትግል የሥልጣን ትግል መሆኑ እሙን ቢሆንም ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን መሆን በመታገል በህዝብ ድምጽ ተመርጦ ሥልጣን መያዝን ዓላማ ካላደረጉ የቤተ መንግሥቱ ወንበር የሚሆነው ለአንድ ሰው ብቻ በመሆኑ ትግሉ የመጠላለፍ ጨዋታው የጥሎ ማለፍ ይሆንና ሥልጣን ላይ ያለውን ኃይል ዕድሜ በማራዘም ሁሉም የሚመኙትን ወንበር ሳያገኙ ዘመናት ይቆጠራሉ።

ደርግን ለማስወገድ በተደረገው ትግል የሁሉም ዓላማና ግብ በደርግ ወንበር ራስን ማስቀመጥ እንጂ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መመስረትን ያስቀደመ አልነበረምና የእርስ በርሱ ትግል ደርግን በመታገል ከተከፈለው ያልተናነሰ መስዋዕትነት አስከፍሏል። መጨረሻም መስዋዕትነቱ ሁሉ መክኖ ሀገሪቱን ለወያኔ አገዛዝ ዳርጓታል።

ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት የታየውም ከዛ ብዙም ያልተለየ በመሆኑ ነው መስዋዕትነት እንጂ ድል ለመታየት አለመቻሉ። በዚህ የተማረረውና በፖለቲከኞቹ ተስፋ የቆርጠው ህዝብ አሁን የነጻነት ትግሉን ራሱ በራሱ ተያይዞታል። ፖለቲከኞቹ ግን የአርባ ዓመቶቹም ሆኑ የአስርና የሀያ ዓመቶቹ (የትግል ዕድሜአቸው ነው) ትናንት ካሳለፉትም ሆነ ዛሬ ከሚኖሩት ተምረውና ተመክረው ዓላማቸውን ከራስ ሥልጣን መሻት ወደ ዴሞክራሲያው ሥርዓት መቀየር ባለመቻላቸው የህዝቡን ትግል ሊመሩት ሊያስተባብሩት ቀርቶ እሱ በራሱ መንገድ ትግሉን ሲያቀጣጥል ወደ እነርሱ መንገድ ሊመልሱት ይዳዳቸዋል።

በ2001 ዓ.ም. አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ እንደተመሰረተ የመጀመሪያዋ ሊቀመንበር ብርቱካን ሚደቅሳ አንድነት የሚታገለው ለሥልጣን ሳይሆን ለዴሞክራሲ ሥርዓት ነው በማለቷ፤ ፖለቲከኞቹ ብቻ ሳይሆኑ አንዳንድ ጋዜጠኞች ጉድ በሉ ለሥልጣን የማይታገል ፓርቲ ተፈጠረ በማለት ሲሳለቁም ሲተቹም ሰምተንም አንብበንም ነበር። ለዴሞክራሲ መታገልና ለሥልጣን መታገል ያላቸውን አንድነትና ልዩነት ተቺዎቹ መረዳት ተስኖአቸው ሳይሆን በሀገራችን የተለመደውና ጡረታ ሊወጣ ያልቻለው የተለየ አስተሳሰብ ይዞ ብቅ የሚልን ተረባርቦ ከመድረኩ የማጥፋት በሽታ ተጠቂዎች መሆናቸው ነበር ብርቱካን በተናገረችው ላይ ያዘመታቸው።

ከዛ ወዲህ ከአርበኞች ግንቦት 7 ሰፈር የሚጻፉትም ሆኑ የሚነገሩት በ2001 ዓ.ም. ወ/ት ብርቱካን ይዛው ከነበረውና የውስጡም የውጪውም በትብብር በአጭር ካስቀረው አስተሳሰብ ጋር አንድ አይነት ነው። ጠብመንጃ አንስተው ዱር ቤቴ ብለው እየሞቱና እየገደሉ የሚታገሉት ለሥልጣን ሳይሆን ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መሆኑን ግባቸውም ወያኔን አሸንፎ ሥልጣን መያዝ ሳሆን የሽግግር መንግሥት እንዲመሰረት ማብቃት እንደሆነ ነው የሚገልጹት። በእውነቱ በዚህ መስመር ከተሰለፈ ኃይል ይህ መሰማቱ በእውነቱ ቅዱስ ዓላማ ነው።

በሰላማዊ መንገድም ሆነ በትጥቅ እንታገላለን ከሚሉ መኖሪያቸውን በሀገር ውስጥም በውጪም ካደረጉ ሌሎች ድርጅቶች እንዲህ አይነት ቃል ተሰምቶ አያውቅም። የምንታገለው ወያኔን አስወግደን ሥልጣን በመያዝ ዓላማችንን ተግባራዊ ለማድረግ ነው ነው የሚሉት። ማለታቸው ባልከፋ ግን በመረጡት የትግል ስልት ተንቀሳቅሰው ለሚያልሙት ሥልጣን የሚያበቃቸው ድርጅታዊ አቅምና የትግል ብቃት ሊፈጥሩ አልቻሉም። ሁሉም ለሥልጣን የሚታገሉና በህልማቸውም በእውናቸውም ምኒልክ ቤተ መንግሥትን የሚያልሙ በመሆናቸው ተባብረው አንድ ጠንካራ ኃይል ሊፈጥሩ አልቻሉም። በዚህም ቢያበቃ ደግ ነበር። ከመካከላቸው አንድ ሁለቱ ትንሽ መንቀሳቀስ ሲጀምሩ ወያኔ ገና ምኑም ሳይነካ በተቀደምን እኩይ መንፈስ ጎትተው ለማስቀረት አደናቅፈው ለመጣል ይሠራሉ። ያሴራሉ።

ለሥልጣን መታገል ምን እንደሆነ ወያኔ በቂ ገላጭ ነው። የትግሉ ፍጻሜ ራስን ለሥልጣን ማብቃት ነው። ሥልጣንኑ ከያዘ በኋላም በትግል የተገኘ ሥልጣን በትግል ይጠበቃል ብሎ እኔ ታግየ ባመጣሁት እያሉ ለሌሎች እንደሚገባቸው ሳይሆን እንደሱ ችሮታ ሥልጣን እየሰጠ፣ የህዝብን የሥልጣን ባለቤትነት የሚያረጋግጥ ሳይሆን የሱን ዕድሜ የሚያራዝም ስመ ምርጫ እያካሄደ፣ ጥያቄንም ተቃውሞንም በኃይል እየጨፈለቀ ከዴሞክራሲ ጋር ሆድና ጀርባ ሆኖ የሚኖር ነው።

በአንጻሩ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን መሆን የሚታገል ኃይል፤ በሰላምም ይሁን በጠብመንጃ ታግሎ ለድል ሲበቃ በትግል ያገኘሁት ሥልጣን ሳይል የህዝብን የሥልጣን ባለቤትነት የሚያረጋግጥና ሀገሪቱን ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚያሸጋግር ነጻ ምርጫ እንዲካሄድ ያደርጋል። ለራሱም የህዝብን አመኔታ አግኝቶ ለመመረጥ የሚያበቃውን ጥንካሬ ይገነባል፣ ተወዳድሮ ካሸነፈ ሥልጣን ይረከባል፤ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ከመነሻው የታገለለት ነውና መሰረቱ የጸና ግድግዳና ጣራው የጠነከረ ዴሞክራሲ ለመገንባት ይሠራል፣ የህዝብን የሥልጣን ባለቤትነት በተግባር ያረጋግጣል፤ ለመመረጥ የቀሰቀሰበትን ሲመረጥም የገባውን ቃል ገቢራዊ ለማድረግ ይተጋል። ከተሸነፈ አሸናፊውን እንኳን ደስ አለህ በማለት ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የበኩሉን አስተዋጽኦ እያበረከተ ለቀጣይ ምርጫ ራሱን ያዘጋጃል።

መነሻ ዓላማውም ሆነ መድረሻ ግቡ ሥልጣን ሳይሆን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ነውና ሥልጣኔን ላጣ እችላለሁ በሚል ስጋት በምርጫ ላይ ፊቱን አያዞርም። እንደውም አስተማማኝ በማንምና በምንም ምክንያት ሊሸረሸር የማይችል የምርጫ ሥርዓትና ተቋም እንዲኖር ያደርጋል። እናም ወንበር እስከ መቃብር ሳይል ነጻና ፍትሐዊ ምርጫ አካሂዶ ቢሸነፍ አሸናፊውን እንኳን ደስ አለህ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓታችንን ይበልጥ ለማጠናከር በርትተህ እንደምትሠራ ጽኑ እምነት አለን እኛም አጋርነታችን አይለይህም በማለት ሥልጣኑን ያስረክባል።

የአብዛኛዎች ፖለቲከኞችም ሆኑ የግል ተንቀሳቃሾች ህልምና ፍላጎት ሥልጣን በመሆኑ በርስ በርስ ፍትጊያ የወያኔን ሥልጣን እያራዘሙ አንዳቸውም የሚመኙትን ሥልጣን ከማጣታቸው በላይ ህዝቡ ከአገዛዝ ተላቆ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዳይበቃ አድርገውት ሃያ አምስት ዓመታት ተቆጠሩ። አሁንም የተማሩ አይመስሉም።

ወያኔ የሚስተካከል ተቀዋሚውም ከራስ በላይ ህዝብ ብሎ የሚታገል አለመሆኑ ተስፋ ያስቆረጠው፣ ግፉ ያንገፈገፈውና መስቃ የመረረው ህዝብ ራሱን እየደራጀ ከሞት ጋር በመጋፈጥ የነጻነት ትግሉን በደም ሲያቀልመው፣ የመለያየቱን የበርሊን ግንብ ደርምሶ አንድነቱን በመስዋዕትነት ሲያደምቀው፣ እጅ ለእጅ ተያይዞ የወያኔን እሳትና ጭድ ሴራ ሲያከሽፈው፡ አብዛኛዎቹን ፖለቲከኞቹ በዚህ መስመር ማየት አልተቻለም። እንደውም የቆረቡበት ከሚመስለው አስተሳሰባቸው ባለመላቀቅ ትግሉን ከደረሰበት ከፍታ በማውረድና የህዝቡን አንድነት በመሸርሸር በእነርሱ ቁመትና ፍላጎት መጠን ለማድረግ መድከማቸው እነርሱም አንደ ወያኔ ከዴሞክራሲ ጋር ሆድና ጀርባ መሆናቸውን ነው የሚያሳየው።

ወያኔ ሃያ አምስት ዓመት ምኒልክ ቤተ መንግሥት ተቀምጦ አለመማሩ፣ ከወዳጅም ጠላቶቼ ከሚላቸውም የሚሰነዘርለትን ምክር ትችት አስተያየት ወዘተ ባለመቀበል አለመሻሻሉ ችግሩ ከተፈጥሮው እንደመሆኑ እነዚህም ሥልጣን ብቻ የሚያልሙ ፖለቲከኞች ሌላው ሁሉ በቀር ከሰሞኑ የህዝብ ትግል አንድትና መስዋዕትነት ለመማር አለመቻላቸው ችግራቸው ከአፈጣጠራቸው በመሆኑ ነው ለማለት ያስችላል።

በተፈጥሮአቸው ከዴሞክራሲ ጋር ያልተጣሉ ወይንም በሥልጣን ጥም ያልናወዙ ዓላማቸው ግልጽ ነው። በሚሰሩትና በሚናገሩት መካከል ልዩነት አይታይም፣ ጭብጨባም ሆነ ውዳሴ የወያኔ መሰሪነትም ሆነ የህዝብ ትግል መፋፋም፣ የአስመሳዮች ሴራም ሆነ የትግሉ እልህ አስጨራሽ መሆን እዛና እዚህ አንዲረግጡ እንደ እስስት እንዲለዋወጡ አያደርጋቸውም።

እባካችሁ፤ ተቃዋሚ ነን ባዮች ብዙ ናችሁ፤ ወንበሩ ደግሞ ካለ አንድ ሰው እንደማያስተናግድ ታውቃላችሁ፣ ስለሆነም መመኘት መፈለጋችሁ እንዳለ ሆኖ ወንበሩን ማግኘት የሚቻለው በሀገሪቱ ነጻ የምርጫ ሥርዓት ተፈጥሮ እኔም ተወዳድሮ ለማሸነፍ የሚያበቃ አቅም ሲኖረኝ ነው ብላችሁ ነጻ የምርጫ ሥርዓት ለመፍጠር የሚያስችል የሽግግር ግዜ ለማምጣት ለመታገል ወስኑ። በያዛችሁት መንገድ የህዝቡን የነጻነት ትግል በመጉዳት የወያኔን ዕድሜ ታራዝሙ ካልሆነ በስተቀር የምትመኙትን ወንበር እንደማታገኙት ሃያ አምስት ዓመት በበቂ አይታችኋል። አሁን ደግሞ የነጻነት ትግሉ በህዝብ እጅ ገብቷልና እንኳን በእናንተ በወያኔም የሚደናቀፍ አይመስልም። እናም ለማታገኙት ሥልጣን የታሪክና የትውልድ ተጠያቂ ከመሆን የምትችሉትን ትንሽ ትንሽ አዎንታዊ አስተዋጽኦ በማድረግ የአኩሪ ታሪክ ተካፋይ ብትሆን ይበጃል።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ