ሥህተቶችን ሳንደግም የተሻለች ኢትዮጵያን ወደ መገንባት
ገለታው ዘለቀ
በሚመጣው ህዳር ወር ላይ የኢትዮጵያ ልጆች የኦሮሞ ብሔር ልሂቃን ተሰብስበው በከፍተኛ ጉዳዮች ላይ ይመክራሉ ሲባል ምክክሩን ወድጄው በስብሰባው ላይ ቢነሳ ጥሩ ነበር ብየ ባሰብኩት ላይ ለመወያየት ነው አነሳሴ። የውይይቱ አሳብ ለሁሉ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ነው በርግጥ። እነዚህ የኦሮሞ ወገኖቼ ከዚህ ስብሰባ በሁዋላ የሚያወጡት የአቋም መግለጫ የኢትዮጵያን ማኅበረ ፖለቲካ ለመለወጥ ትልቅ ድርሻ ያለው የትብብር፣ የአንድነት አሳብ እንደሚሆን አምናለሁ።
በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያችን በከፍተኛ ህዝባዊ ንቅናቄ እየተናጠች ነው። ምን አልባትም ይህ ዓይነቱ ህዝብ መራሽ የሆነ ሰፊ ትግል በታሪካችን አልታየም። የህዝባዊ አመፁ በከፍተኛ ሁኔታ እየገፋ ባለበት በአሁኑ ወቅት የፖለቲካ ኃይላት ሲቪክ ድርጅቶችና የኃይማኖትና የባህል መሪዎች ሁሉ ሁለት ትላልቅ የምክክር አጀንዳዎች ከፊታቸው ተደቅነዋል። በተናጠልም በጋራም በነዚህ ጉዳዮች ላይ መወያየት አለብን። አንደኛው ወቅታዊ ጉዳይ ይህ የህዝብ ትግል እንዴት ነው የሚቋጨው? እንዴት ነው የሚያልቀው? የሚለው አስቸኳይ ጉዳይ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በሽግግሩ ጊዜ ሊሰሩ የሚገባቸው ስራዎች ላይና የሽግግሩ ጊዜ ምን መምሰል እንዳለበት በመምከሩ ላይ ያተኮረ ነው።
በነዚህ ሁለት ነጥቦች ላይ ኢትዮጵያውያን ባሉን አጋጣሚዎች ብንወያይ መልካም ነው። ከፍ ሲል እንዳልኩት ትግሉ ሰፊና አስደናቂ ሲሆን በአብዛኛው አካባቢያዊ ጥያቄን እያሳየ አጠቃላይ የሥርዓት ለውጥን ፈላጊ ሆኖ ይታያል። የትግሉን ባህርይ ስናይ በኦሮምያ አካባቢ በአመዛኙ ሰላማዊ ህዝባዊ አመፅ ሲሆን በአማራ አካባቢ ደግሞ በሰላምም በትጥቅም የመታገል ባርይ አለው። በአሁኑ ሰአት ትግሉን የደቡብ ህዝብም የተቀላቀለው ሲሆን ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል። እንግዲህ ታዲያ ይህ ትግል ሄዶ ሄዶ በምን መንገድ ይጠናቀቃል? እንዴት ነው የሚያልቀው? ህዝብ የትግሉን ድል እንዴት አድርጎ ነው የሚያየው የሚለውን ማጥናት ተገቢ ነው። ይህን እንድንጠይቅ የሚያደርገን የትግሉ ባህርይ ነው። ባለቤቱና የሚመራው ህዝቡ በመሆኑ (ይህንን ጽሁፍ ሳዘጋጅ አንዳንድ ኃይሎች እኛ ነን ትግሉን ያቀጣጠልነው ቢሉም) እንዴት ይህ ትግል ወጥ የሆነ አመራር አግኝቶ መንግሥት ይለውጣል? የሚል ጥያቄ ያስነሳል። መቼም የህዝቡ ትግል ሲያይል ሊከሰት ይችላል ተብሎ ከሚጠበቀው መሃል አንዱ መፈንቅለ መንግሥት ነበር። ነገር ግን በኢትዮጵያ ሁኔታ ይህ ነገር የሚከሰትበትን እድል ማየት ተገቢ ነው። ማን በማንስ ላይ ነው መፈንቅለ መንግሥት የሚያደርገው። ተደረገ ቢባልስ ራሱ ሰራዊቱ ህወሓትን አይደለም ወይ የሚጠብቀው? ምን ለውጥ ይመጣል? የሚል ነው። ሌላው የዚህ የህዝብ ተቃውሞ ግፊት መንግሥትን ወደ ብሔራዊ እርቅና መግባባት የመወስድ ኃይል ነበረው። ይሁን እንጂ መንግሥት ለዚህ ልቡ ተሰብሯል ወይ? ስንል አይመስልም። እስካሁን ምልክቶች አይታዩም። በብሔራዊ እርቅ ዙሪያ የሚሰሩ አሉና እስቲ እነሱ እየገፉ ይሂዱና ለውጥ ካለ እናያለን። እነዚህ ጉዳዮች ካልሰሩ ታዲያ ይህ የህዝብ አመጽ እንዴት ነው ድሉን የሚጨብጠው? ብለን እንጠይቃለን። መቼም መንግሥት ህዝቡ በየከተማው አምፆብኛልና ጥይት የለኝም ብሎ ወታደር አሰናብቶ የአራት ኪሎን ቤተመንግሥት ነቅሎ አይሄድም። በመሆኑም ይህ የህዝብ ትግል በድል እንዲጠናቀቅ የግድ የታጠቀ ኃይል ወጥ የሆነ እዝ ያለውን ኃይል ይሻል። ይህ የታጠቀ ኃይል ህዝብ ያደከመውን መንግሥት በትጥቅ ጥሎ የሚመካበትን ኃይል በቁጥጥር ስር አውሎ ሲያበቃ ነው ይህ ትግል የሚቋጨው። ይህ የታጠቀ ኃይል የሚያስፈልገው ቋፍ ላይ ያለውን መንግሥት ለመናድ ብቻ ሳይሆን የሽግግር ጊዜውን ለማድረግ በመላ ሀገሪቱ የሰላም ማስከበር አገልግሎት መስጠት ስላለበት ነው። በርግጥ ይህ ኃይል ሲያሸንፍ አሁን ያለውን መከላከያና ፓሊስ በሙሉ ይበትናል ሳይሆን እነዚህን ኃይሎች በአዲስ መንፈስ አንፆ መሄድ ይኖርበታል። ትግሉ ሊቋጭ የሚችለው እንግዲህ በታጠቀና የህዝቡን ጥያቄ ባነገበ ብሔራዊ ኃይል በመሆኑ አሁን በየአካባቢው ያለውን ኃይል ወደ ወጥ እዝ በማሰባሰብ የመጨረሻውን ትግል ማድረግ ያሻልና የመጨረሻውን ትግል ለመምራት ዝግጁ ነን ኃይል አለን የሚሉ ኃይሎች ይህን ጉዳይ ማሰብ ይኖርባቸዋል። የአካባቢ ትግሎች በበቂ የተደረጉ ሲሆን አሁን ህብረብሔራዊ የሆነ ኃይል ባስቸኳይ መውጣት አለበት። በመሆኑም የታጠቁ ኃይሎች ወደ ህብረት መጥተው ህብረቱን ለህዝብ መግለፅ ይጠበቅባቸዋል። በተግባርም የኦፐሬሽን ስራዎች መጀመር አለባቸው። የኦሮሞ ለሂቃንም ሆኑ የአማራ ወዘተ. በጋራ በመነጋገር የህዝቡን ትግል በድል እንዲቋጭ እዚያም እዚያም የተበታተነውን ኃይል በአንድ ወጥ እዝ ስር አድርገው ትግሉን መምራት ካልቻሉ ኦሮሞ ለብቻው አማራ ለብቻው ወዘተ ሰራዊት ለመገንባት ከጣሩ ይህ ትግል ወደ ብዙ አቅጣጫ የመውደቅ እድል ይኖረዋል። የአንድ ብሔር የታጠቀ ኃይል ድል ቢያደርግም እንኳን ለኢትዮጵያ ጥሩ አይሆንም። ህወሓት 25 ዓመት ሙሉ የሚለው አብላጫ ታግያለሁና አብላጫ ይገባኛል አይነት ነው። በመሆኑም በተናጠል የነበረው ትግል አሁን ይጠናቀቅ ዘንድ ህብረትን ፈልጓል። ትግሉ ብሔራዊ ንቅናቄን የሚሻበት የመጨረሻ ምእራፍ ላይ ነውና መነጋገር ያስፈልጋል ነው የምላችሁ።
ሁለተኛው ወቅታዊ ጥያቄ ደግሞ ያለፈ ስህተት እንዳይደገም የሽግግር ጊዜው ምን መምሰል አለበት? በዚህ የሽግግር ጊዜ ምን ልንሰራበት ነው? የሚለው ጥያቄ ነው።
ኢትዮጵያችን ከዘውዳዊ አገዛዝ ወደ ዘመናዊ አስተዳደር መሻገር ሲያምራት የሽግግር ጊዜን የፅሞና ጊዜ አድርጋ አልወሰደችም። ወታደር ሥልጣኑን ነጥቆ ወስዶ ለስሙ የሽግግር ጊዜ ቢልም በተግባር ግን የሽግግር ጊዜ አላየንም። ራሳቸው መንግሥቱ “በውኑ ደርግ አለን” ብለው የኢትዮጵያን ህዝብ ቢጠይቁት እስካሁን በዚህ ጥያቄ ይሳለቃል። በህወሓት ኢህአዴግ ጊዜም እንዲሁ የሽግግር ጊዜ ሲጠበቅ ሰፊ ማኅበረሰብ ያገለለ የሽግግር ጊዜ የማይባል አሳልፈን ቀረን። የኢትዮጵያን ህዝብ መሰረታዊ ጥያቄ በሚገባ የምናጤንበት ጊዜ ሳይኖረን ቀረ። ለሶስተኛ ጊዜ ተመሳሳይ ችግር ውስጥ እንዳንገባ በዚህኛው ለውጥ ጊዜ ስለ ሽግግር ዛሬ ላይ ሆነን ማሰብ አለብን። በተለይ የኢትዮጵያ ፖለቲካ አሰላለፍ ወዲያና ወዲህ በሆነበት በዚህ ልዩ ጊዜ የሽግግር ጊዜ የጽሞናና የእቅድ ጊዜ የግድ ያስፈልገናል። በዚህ የሽግግር ጊዜ የሚያስፈልገው ዋና ነገር ምንድን ነው? ካልን የስምምነት አሳብ ነው። ይህ አሳብ ኢትዮጵያውያንን ወደ አንድ የተሻለ አዲስ ኪዳን የሚወስዳቸው መሆን አለበት። በዚህ የሽግግር ሰአት ኢትዮጵያውያን ባህላዊ ኢኮኖሚያዊ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ጉዳዮቻቸውን እንዴት አድርገው ማስተዳደር እንደሚገባቸው በዘላቂ ጉዳይ ላይ አቋም የሚይዙበት ሰአት ነው። ኢትዮጵያውያን ብዙህ ሆነው ግን ደግሞ አንድ ሀገር እንዲኖራቸው ይሻሉ። ይህ ማለት እንግዲህ ይህ የፈለጉት አንድነት የሚጠይቃቸውን የመስዋዕት ጥያቄ አይፈሩም ማለት ነው። ስለሆነም የስምምነቱ አጀንዳ መሆን ያለበት እንዴት አድርግን አንድ ትልቅ አገራዊ የፖለቲካ ጠገግ እንፍጠር የሚል እና በሌላ በኩል ደግሞ ባህላዊ እኩልነትን የምናሳይበትን ሲስተምና ጠገግ መፍጠር ነው። የስምምነቱ አሳብ ይህን ያዘለ ሆኖ ነገር ግን መስዋእቱን የሚያቀርበውና አሳቡን የሚያፀድቀው ህዝብ፣ ዜጎች ሁሉ መሆን አለባቸው። በዚህ በሽግግር ወቅት ሊነሳ የሚገባው አንድ ጉልህ ጉዳይ የአንድነት ትርጉም ነው። የአንድነት መገለጫዎች ምን ምን እንደሆኑ መታወቅና ስምምነት መያዝ አለበት። ይህ ጉዳይ የፖለቲካ ዶክትሪን ሳይሆን ዘመን ተሻጋሪ የሆነ መሰረታዊ የሆነ ሀገርን እንደገና የማነፅ ጉዳይ ነው።
እንደሰማነው የኦሮሞ ብሔር ተወላጆች የኦሮሞን ህዝብ ህልም የሚገልፅና ኦሮሞ ምን አይነት ሀገር በአዲሲቷ ኢትዮጵያ እንደሚፈልግ ሊወያዩ ነው። መወያየት አሳብ ማምጣት ደግ ነገር ነው። ሌሎች ቡድኖችም እንዲሁ በየቡድኑ ምክክር እያሰቡ እንደሆነ አላውቅም። ነገር ግን ያም አለ ይህ ለአዲሲቱ ኢትዮጵያ የሚያስፈልገውን መስዋእቶች ሁሉ እንዳንረሳ ያስፈልጋል። የኦሮሞ ህዝብ ጥያቄ የፍትህ የነፃነት የእኩልነት ጥያቄ በመሆኑ ይህንን የሚያስከብር ሥርዓት አብሮ መምከር እንጂ የኢትዮጵያን መስዋእቶች የሚበላ ወይም የሚቀራመት መሆን የለበትም። አማራ፣ ሲዳማ ወዘተ ለየብቻ ስለመጪው ጊዜ ስለሽግግር ጊዜው የስምምነት አሳቦች መወያየት ሲያምራቸው ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት የሚሆነውን መስዋዕት ካላሰቡ የተሻለች ሀገር አንገነባም። የሽግግሩ ጊዜ ሊያነሳው የሚገባው የስምምነት አሳብ አንድ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማኅበረሰብ መፍጠርና ባህላዊ ማንነትን ራሱን በቻለ ነፃ አስተዳደርና የባህል ፌደሬሽን ማስተዳደር ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ የብሔር ትግል አድራሽ መሆን ይኖርበታል። እስከ ሽግግሩ ጊዜ ቆይቶ ከዚያ በሁዋላ ሊሟሟ ይገባል። የብሔር ፓለተካንም አንድነትንም ይዘን ብሔራዊ ምርጫ አድርገን ወደተሻለች ኢትዮጵያ መሻገር አንችልም።መወሰን አለብን። በአዲሲቱ ኢትዮጵያም የብሔር ፖለቲካን ካልጎተትን ካልን ሀገሪቱ ብዙ ግልፅነት በሚጎድላቸው የባህል የአኮኖሚ የማህበራዊና የፖለቲካ ሥርዓት ውስጥ መውደቋ ይቀጥላል። ግልፅ ያልሆነ ስምምነት ይዘን ያልቆረጠና የሰሰተ ስምምነት ይዘን አዲስ ሥርዓት መመስረት አንችልም። ይህን የምንልበት ብዙ ምክንያቶች አሉ። ዘውግ ለአዲሲቱ ኢትዮጵያ የሥልጣን ምንጭ ይሁን የሚሉ ኃይሎች ሊመልሷቸው ከሚገቡ ጥያቄዎች መሃል
1. የብሔር ፖለቲካ በኢትዮጵያ ብሔሮች፣ በኦሮሞ፣ በአማራ፣ በትግሬ ወዘተ. ባህልና እምነት እሴቶች ውስጥ አለ ወይ? በነዚህ ብሔሮች እሴቶች ልብና መንፈስ ውስጥ ይገኛል ወይ? ብለን ልንመረምረው ይገባል። የኢትዮጵያ ብሔሮች በኃይማኖቶቻቸውም ሆነ በባህሎቻቸው እኔ … እኔ … እኔ … የሚል ነገር አያበረታቱም። አብረው በሚኖሩበት ሀገር ውስጥ የኔ … የኔ … የኔ … የሚል እሴት የላቸውም።
ለምሳሌ የኦሮሞን የገዳ ሥርዓትና ሌሎች ባህሎቹን ብናይ አንድ ከኦሮሞ ብሔር ውጭ ያለ ሰው ወደ ኦሮሞ ማኅበረሰብ ከሄደና አብሮ ከኖረ እንደ ኦሮሞ ነው የሚታየው። የኦሮሞ ማኅበረሰብ ባህል ይህንን ሰው እንዲለይ አይፈልግም። ከገዳ ስርኣትና ከአጠቃላይ የኦሮሞ ባህል መርሆዎች የሚቀዳው የፖለቲካ እምነት የብሔር ፖለቲካ ሳይሆን ሁሉን አቀፍ የሆነ በዜግነት ላይ የተመሰረተ ፖለቲካ ነው። የኦሮሞ ህዝብ መሪዎች ነን የሚሉ ኃይሎች በዘውግ ላይ የሚመሰረት ፖለቲካ የሚያራምዱ ከሆነ የኦሮሞን ባህል እሴቶች እየሰበሩ መሆናቸውን ማጤን አለባቸው። የገዳ ሥርኣት የኦሮሞ ባህል ብቻ ሳይሆን ጌዲኦም ይህን ባህል ይከተላል። የጌዲኦ ህዝብም እንዲሁ ለባህሉ እሴቶች ይጠነቀቃል። በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ብሔሮች አብረው በአንድ ገበታ ይበላሉ። አንተ ትብስ … አንተ ትብስ … ይባባላሉ። አይሰስቱም። ይሉኝታ አላቸው። የብሔር ፖለቲካን እሴቶች ስናይ ደግሞ ከራስ በላይ ነፋስ አይነት ልብ አለው። ራስን በራስ … የራስን እድል በራስ … የራስ ባህል … የራስ መሬት … ራስ … ራስ … ራስ … ነው ጨዋታው። የብሔር ፖለቲካ ከሶሻሊስት አብዮት የተቀዳ የእኛን ባህልና ኃይማኖት የሚፃረር በመሆኑ ነው በህብረተሰቡ ዘንድ ምስቅልቅልን እንዲያመጣ ያደረገው። ይህን የሚሸከም ባህላዊም ኃይማኖታዊም መሰረት የለንም። በመሆኑም ይሄን የሀገራችንን ባህልና ኃይማኖት የሰበረ ስስታም የፖለቲካ ዶክትሪን ልንከተለው አይገባም። ራስ … ራስ … ራስ … ከሚለው ወጥተን እኛ … እኛ … እኛ … ወደሚል የፖለቲካ አስተሳሰብ ስንገባ ነው የአማራን ወይም የኦሮሞን ወይም የሌሎችን ብሔሮች እሴቶች የምናከብረው።
2. የዴሞክራሲ ጉዳይ። ዘውግን ለአደሲቷ ኢትዮጵያ የሥልጣን ምንጭ ማድረግ ከፈለግን የዴሞክራሲ መርሆዎችን ልንረማመድባቸው ነው። ምርጫን የዜግነት መብትን ሁሉ ይጋፋብናል። ስለዚህ እንምረጥ። ዴሞክራሲን ከነሙሉ ክብሩ ለአዲሲቱ ኢትዮጵያ ከተመኘን ከዘውግ ፖለቲካ መላቀቅ አለብን።
3. የብሔር ፖለቲካ ግብ ምንድን ነው? ብለን እንጠይቅ። ኢትዮጵያን የሚያክል ጠገግ እንደ ኮንትራት አድርገን ብሔርን ዘላለማዊ ጠገግ አድርገን ሀገር መመስረት ካማረን ከስረናል። የብሔር ፖለቲካ ችግር ይህ ነው። አካባቢያዊ ማንነትን እያጎላ ብሔራዊ ማንነትን ያኮስስና ሀገርን ያናጋል። ዘላቂ ግብም የለውም።
4. የአባቶች ደምና አጥንት ጉዳይ። ኦሮሞው ሲዋጋ የኖረው አሁን ወያኔ ለፈጠረው የኦሮምያ ካርታ አይደለም። ትግራይ ሄዶ ነው የሞተው። አማራው ጉራጌው ትግሬው ሁሉም ዘብ ሆኖ ሲጠብቅ የኖረው ኢትዮጵያን ነውና የአባቶች ህብረት በዚህ ትውልድ መከበር አለበት። በደምና አጥንታቸው ላይ የምንረማመድ ትውልድ እንዳንሆን።
5. የብሔር ፖለቲካ ህዝባዊ ጥያቄ አለው ወይ? ብለን እንጠይቅ። ከጥቂት ሰዎች በላይ ህዝባዊ መሰረት የለውም። ይህንን ማጥናት ይቻላል። የሁሉም ህዝብ ጥያቄ አንድ አይነት ነው። ፍትህ ነፃነት። በርግጥ ነው ቡድንን ነጥሎ የሚያጠቃ ሲመጣ መመከት ተገቢ ነው ይሁን እንጂ በተረጋጋ መንግሥት ጊዜ ዘውግ የፖለቲካ መሰላል እንዲሆን የሚሻ ኢትዮጵያዊ በጣም ጥቂት ነው።
6. የብሔር ፖለቲካ አሁን ካለችው አለም ጋር ይሄዳል ወይ? ይህን ጥያቄ መመለስ ተገቢ ነው። አለም ወዴት እያመራች ነው? ሚለውን ወጣ ብሎ ማየት ያሻል። የብሔር ፖለቲካ ፊውቸር የለውም።
7. የጋራ ሃብትና የክልል ሃብት ላይ ትልቅ ንትርክ ያመጣል። አነሰም በዛም የጋራ ሃብቶች አሉን። እነዚህን ሃብቶች በኢትዮጵያዊነት ልንወርሳቸው ነው የሚገባው። የኔ የኔ ከመጣ ሁል ጊዜም ለአገሪቱ የግጭት ኃይል መቅበራችን ነው።
8. የማንነት እሽቅድምድም። ፖለቲካ ሁል ጊዜም የፍላጎት ማእከል (center of interest) አለው። ይህን ማእከል ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ሳንሰዋ ከቀረንና የዝንባሌና ፍላጎታችን ማእከል ብሔር ከሆነ በፍትህ ላይ ልንረማመድ እንችላለን። ፍትህ እኩልነት የሚታየን ከላይ ሆነን ስናይ ነው። ከላይ ከኢትዮጵያዊነት ላይ ሆነን …። ከስር ከየብሔራችን የምናየው እይታ የሁሉን እኩልነት አያሳየንም። ከሁሉ በላይ ችግር ጎልቶ የሚታየን የኛ የምንለው ቡድን ይሆንና የሀገርን ለዛ ያጠፋብናል። ከዚህ የተነሳ እኔ መጀመሪያ ወላይታ ነኝ ሁለተኛ ቅብጥርሴ እያልን የማንነት እሽቅድምድም ውስጥ ይከተንና ፍትህን ምስጥ ሆኖ ይበላብናል።
9. ከብሔር ፖለቲካ ተምረን ተምረን ያፈራነው እውቀት ይህ ነው ወይ? ኢትዮጵያ ጥሟታል ወይ? ብለን መጠየቅ ተገቢ ነው። እንደ ኢትዮጵያውያን ስለዚህ ስለብሔር ፖለቲካ የተማረ የለምና እናስብበት። የብሔር ፖለቲካ በማኅበረሰብ ህይወት ውስጥ ምን አይነት ኃይል (energy) እንደሚፈጥር ከሌላው አለም በተሻለ ተምረናልና እናስተውል።
10. የብሔር ፖለቲካ ፓሊሲዎችን ለማውጣት ምርምር ስናደርግ ልንቆጣጠራቸው የማንችላቸው ብዙ ተለዋዋጮች (variables) አሉት። ብዙ ጥያቄ ለማኝ የሆኑ ጉዳዮችን በውስጡ የያዘ ነው።
11. የብሔር ፖለቲካ ፍትህን ዴሞክራሲን ለማምጣት እንዴት ዋስትና ሆኖ ታየን? ሆሞ ጂኒየስ ሆኖ ጭቆና አለና። በአለም ላይ በብሔር ላይ እየተደራጁ ለሥልጣን መሮጥ ለብሔሮች ቢጠቅም አለም ይህን ፍልስፍና በተከተለው። አለም እንደ ጦር የሚፈራውን ፖለቲካ ልንከተል አይገባም።
12. ቅይጡን ዜጋና ኢትዮጵያዊነትን እንደ ብሔር የወሰደውን ዜጋ ምን እናድርገው? ህወሓት ስታትስቲክስ ሲሰራ ብሔሮች ሲቆጠሩ ይህ ቅይጡ ቦታ የለውም። ገማቾች እንደሚሉት ይህ ቅይጥ ከሁለትና ሶስት ብሔር የተወለደው ዜጋ በቁጥሩ ከብዙ ብሔሮች ይበልጣል። ወደፊትም ቁጥሩ እየጨመረ ይሄዳል። የብሔር ፖለቲካ ሲመጣ ይህን ማኅበረሰብ ለዘብተኛ ያደረገው ሲሆን ትልቁ ችግር ይህ ህዝብ በህሊናው የተሳለ ካርታ የለውም። ከቦታ ውጭ ይጥለዋል የብሔር ፖለቲካ። የፖለቲካና የዜግነት መብቱ በጣም ይሸራረፋል። በመሆኑም በዚህች ሀገር የብሔርን ፖለቲካ ለማስፈን የሚጥሩ ኃይሎች ይህን ሰፊ ማኅበረሰብ ያስቡለት ዘንድ ይገባል።
ለማጠቃለል ያህል በፊዚክስ ትምህርት ውስጥ አንድ ጽንሰ ሃሳብ አለ ሲባል እንሰማለን። የስበትና የግፍትሪያ ሕግ (laws of attraction and repulsion) ማለት ነው። ይህ ትምህርት የሚለው ግፍትሪያም ሆነ መሳሳብ የሚኖረው በዚያ በማግኔቲክ ፊልዱ ውስጥ ብቻ ነው። ከፊልዱ ውጭ ይህ ሕግ አይሰራምና ግፍትሪያውም ስበቱም አይሰራም። ምን አልባት ይህ ተዛምዶ (Analogy) ምን ያህል አሳቤን እንደሚያሳይ ባላውቅም ነገር ግን የብሔር ፖለቲካ ሲስተም ዘርግተን ከዚያ በሁዋላ ችግር የለውም ለጋራው ቤታችን በገለልተኝነት አብረን እንሰራለን ማለት ከተፈጥሮ ሕግ ጋር መታገል ነው። የሀገራችን ሰው ዘር ከልጓም ይስባል ይላል። በርግጥ በዘርና በደም ፖለቲካ ሲስተም ውስጥ ገብተን ብሔራዊ ተቋማት እንገነባለን ገለልተኝነት ያብባል ማለት ዘበት ነው። ከዚህ የብሔር ፖለቲካ የስበት ፊልድ ወይም የፖለቲካ መጫወቻ ሜዳ ወጥተን የተሻለች ለሁሉ የምትሆን ኢትዮጵያን መፍጠር የምንችለው የብሔር ፖለቲካ ሲስተም ውስጥ ሆነን ሳይሆን ከዚህ ሲስተም ወጥተን በመርህ ላይ ስንቆም ነው።
እዚህ ላይ አንድ መታየት የሚገባው እውነት አለ በርግጥ። ለራሴ የተማርኩት ነገር ቢኖር በብሔር መደራጀትን በተመለከተ በሁለት መንገድ አየዋለሁ። አንዱ ማንነትን እያነጣጠረ የሚያጠቃ ኃይል ሲመጣ በርግጥ ራስን መከላከል ያሻልና ቡድኖች ማንነታችንን አታጥፉ ብለው ሊደራጁና ለነፃነት ሊታገሉ ይችላሉ። ይህ ፍትሃዊ ነው። አንድ ቡድን ተለይቶ ሲጠቃ ቢደራጅ አይደንቅም። ሁለተኛው መደራጀት በተረጋጋ ሀገር በመድብለ ፓርቲ ሥርአት ውስጥ በዘውግ ላይ ያተኮረ የብሔር ፓርቲ መመስረት ነው። ይህንን ነው አጥብቄ የምቃወመው። ስስታም፣ ሙሰኛ፣ አድልዎኛ የሆነ ልብ ያለው በመሆኑ ለሀገር አንድነት የማይጠቅም በመሆኑ ሁላችን ልናወግዘው ይገባል። ጎረቤት ኬንያን ጨምሮ ስዊዘርላንድን ጨምሮ በብዙ አገሮች ይህ ፖለቲካ ወንጀል የሚያስቀጣ ተደርጎ የሚወሰድ የፖለቲካ ዶክትሪን ነው። የዘር ፖለቲካ በሕግ የሚያስቀጣ የሆነበት ምክንያት እነዚህ ሀገራት የዚህ ፖለቲካ ፍላጎት (motive) ወንጀል መሆኑ ስለገባቸው ነው።
በአጠቃላይ ኢትዮጵያን ወደተሻለ ሥርዓት ለመምራት በሽግግሩ ጊዜ ኢትዮጵያውያን አንድ ከፍ ያለ ዘመን ተሻጋሪ ስምምነት ሊያደርጉ የሚገባበት ጊዜ በመሆኑ ኃላፊነት ይሰማኛል የሚሉ ኃይላት ስምምነቱን እጅግ በሰከነ ሁኔታ ማድረግ ያሻል። አዲስ የሆነ ኪዳን ዜጎች ሁሉ ገብተው የምንቀጥልበት ሁኔታ እንዲፈጠር በስምምነት ላይ የተመሰረተ አንድነት እንድንፈጥር መጣር የሚጠበቅብን ወሳኝ ምእራፍ ላይ ነን። በመሆኑም አንደኛ ትግሉ ቶሎ እንዲጠናቀቅና ተፈላጊ ለውጥ እንዲመጣ ወጥ ንቅናቄ ማቋቋም ሁለተኛ የሽግግሩን ጊዜ ኢትዮጵያ አዲስ ኪዳን የምትገባባት ጊዜ እንዲሆን ሁላችን እንትጋ። በቅርቡ ስብሰባ የጠራው የኦሮሞ ማኅበረሰብም ሆነ ሌሎች በብሔር ላይ የተመሰረተ ድርጅት ያቆሙ ኃይሎች ሁሉ ደግመው እንዲወያዩበት የሚያስፈልገው ነገር ለኢትዮጵያ ምን መስዋዕት እናድርግ? በሚለው ላይ ነው። ሀገር የሚመሰረትባቸውን አለባዎች ሁሉ ተቀራምተን ለህብረት ዝግጁ ነን ማለት ባዶ ነገር ነው። ኢትዮጵያ የማትጨበጥ አይደለችም። የቡድኖችና የዜጎች መስዋዕት ዋልታና ማገር ሆነውላት የምትኖር ሀገር ናት።
እግዚአብሔር የኢትዮጵያን ይባርክ።



