ጋዜጠኛ ርዕዮት አለሙጋዜጠኛ ርዕዮት አለሙ እና ልናገረው የከበደኝ ሮሮ

ነቢዩ ሲራክ

በግልም ቢሆን አዲሱን ዓመት በሠላም እና በደስታ መቀበሌ እውነት ነው! መስከረም ጠብቶ ብዙ ቀናት ሳንቆጥር ከተለያዩ አቅጣጫዎች የሚደርሱኝ የስደተኛ ወገን መከራ ግን ከአዲሱ ዓመት ዋዜማ ጀምሮ እስከ መባቻው አላባራም። እያንዳንዱን የወገን ስደት ሰቆቃ መከራ ጨክኜ ከመናገር ለመቆጥብ ያደረግኩት ትግል ላንዲት ቀን ቢሳካም፤ ህሊናዬ ግን እረፍት አላገኘም። በተለይ በአዲሱ ዓመት ዋዜማ "ብሪማን" ተብሎ በሚጠራው የጅዳው ትልቅ ማረሚያ ቤት የደረሰኝ መረጃ ያማል ...

 

ያሳለፍነው ሮመዳን ወር እንደገባ ጅዳ ውስጥ የትዳር ጓደኛውን በአሰቃቂ ሁኔታ ገድሎ፤ በአሳር በመከራ ከተያዘ በኋላ ዘብጥያ የወረደው አዕምሮውን የሳተ ኢትዮጵያዊ ከጤነኛ ታሳሪ ሐበሾች ጋር ነብሰ ገዳይን ከተራ ወንጀለኛ ጋር ደባልቀው በማሰራቸው ደም እንዲፈስ ምክንያት ሆኗል በማለት ታሳሪዎች እያነቡ ገልጸውልኛል። ይህ ነፍሰ ገዳይ ከአንድ ፍርዱን ጨርሶ በተወካይ ጉትጎታ እጦት ከአምስት ወራት በላይ እስር ይንገላታ የነበረና በእስር ቤቱ ተደብቆ ሲጋራ የሚሸጥን ወጣት ኢትዮጵያዊን ታሳሪ "አንዲት ሲጋራ ለምን አልሰጠኸኝም?" በሚል ቂም በብረት ዘንግ ዓይኑን አፍስሶ የመደብደቡ ወንጀል ሊናገሩት የሚከብድ አሰቃቂ እንደነበር "ተደብዳቢው ከሞት አይተርፍም" ያሉኝ እማኝ ታሳሪዎች በኀዘን ገልጸውልኛል - በአዲሱ ዓመት ዋዜማ።

 

በአዲስ ዓመት መባቻ ዛሬ ምሽት ... ጋዜጠኛ ርዕዮት አለሙ እና ፍትህ
ሀገር ቤት የጋዜጠኛ ርዕዮት አለሙ የርሃብ አድማ መምታት ዜና ከአሜሪካ ራዲዮ የግማሽ ሌሊት የሳተላይት ስርጭት እያዳመጥኩ፤ በወጣቷ ጋዜጠኛ የእስር እንግልት ዙሪያ እንደ ዜጋ የሚሰማኝን ለማለት በሃሳብ ላይ ነኝ። ከኮምፒውተሬ ጋር ተፋጥጨ በሃሳብ ከርዕዮት አለሙን አልፌ ከእስክንድር፣ ከውብሸት እና ከአንዷለም የእስር ፈተና ርቄ ፍትህን ፍለጋ ሄጃለሁ ... "አሸባሪዎች!" አልኩ ለራሴ ውስጤ እየተቆጣ፤ ግን ዝም አልኩ ... ጭጭ ... ዝም! ምን ይባላል?!

 

ጋዜጠኛ ርዕዮት አለሙ Journalist Reyot Alemuወጣቷ ጉብል ትፈታ! ግን እላለሁ
ከምሳ የተረፈችንን ራት አድርገን ከባለቤቴ ጋር እየቀማመስኩም ርዕዮትን አስታውሸ፤ ፍትህን ፍለጋ በሃሳብ ነጉጃለሁ። ምሽት ላይ አብረውኝ ሲጫወቱ ያመሹትን ሁለት ታዳጊ ጎረምሳ ልጆችን በዓመት በዓል ተጠራርተን በዓሉን ያደመቁ ዘመድ፣ ጓደኛ፣ ጎረቤቶችን አንዳፍታ ከእነርዕዮት ጋር አዛምጀ ሳያቸው አመመኝ። በአውደ ዓመት ከልጅ ወላጅ ወዳጅ ዘመድ ተራርቀው የከረሙ እና እንዲከርሙ የተፈረደባቸው ወንድም እህቶች ጉዳይ በእርግጥም ያሳስባል ያማል! የሰረቀ፣ የገደለ በምህረት በሚፈታበት ሀገር፤ የህዝብን ብሶት በተነናገረ መቀመቅ መውረድ አግባብ አይደለም ማለቱ በዘመኑ ባያዋጣም። ይቅርታ ምህረት ጠይቆ መነፈግ ልብ የሚሰብረውን ያህ ስብራት አጣሁለት! የእነ ርዕዮትን ስቅይት፣ እስራት፣ የፖለቲካ እስረኞች ይፈቱ! ሰላማዊ እርቅ ይበጀናል! እላለሁ።

 

መንገድ ላይ ተጥላ የተገኘችው የኮንትራት ሠራተኛ ...

ብዙ ርቄ ስጓዝ ስልኬ አቃጭሎ ከነጎድኩበት ሃሳብ ተመለስኩ ... ከአንድ ወዳጄ የደረሰኝ የስልክ ጥሪ አዲሱን ዓመት ዳግም በአሳዛኝ መረጃ ቅበላ እንድጀምር አስገደደኝ፤ እየተኮላተፈ አማርኛ የሚናገር ወዳጁ መንገድ ላይ አንዲት አትዮጵያዊት በአሰሪዎቿ ተጥላ እንዳገኘና ሐበሻ የሚያውቅ እሱን በመሆኑ እንዲረዳት መረጃ አቀብሎት፤ ይህችን እህት እንዴት መርዳት እንደሚቻል፤ የተሻለ መረጃ ካለህ? ብሎ ሊያማክረኝ መደወሉን አጫወተኝ። እኔም ከሁሉ አስቀድሞ የጅዳ ቆንስል ኃላፊዎችን እንዲያነጋግር በመምከር አድራሻ ጭምር አቀበልኩት እና በጉዳዩ ዙሪያ አማክሬው ስልኩን ዘጋን ...

ወዳጀ በደረቁ ሌሊት መልሶ ደውሎ የደረሰበትን መረጃ አቀበለኝ። ወደ ጅዳ ቆንስል ኃላፊዎች ደውሎ ቆንስል ሙንትሃን በማግኘት ችግሩን አስረድቶ መፍትሔ ጠየቀ። ከዚያም ቆንስል ሙንትሃ ልጅቱን ወደ ቆንስሉ መጠለያ በመውሰድ ለመጠለያው ኃላፊ ለወ/ሮ አዜብ እንዲያስረክባት መክረውት ወደ ጅዳ ቆንስል መጠለያ መሄዱን ገለጸልኝ። በቆንስላው ሲደርስ የተባሉት የመጠለያ ኃላፊም ሆኑ የሚመለከታቸው በቦታው አለማግኘቱን ወዳጀ በአግራሞትና በብስጭት የሆነውን ሁሉ ገልጾልኛል። ለመጠለያውና ለኮሚኒቲው ጠባቂዎች ጉዳዩን በማስረዳት ይህች መንገድ ላይ ተጥላ ያገኟት እህት የቀሩትን ከ140 የዘለቁ ተፈናቃዮች ለመቀላቀል ይቻላት ዘንድ የቆንስል ኃላፊዋን መልዕክትና ቃል ቢገልጹም ከጠባቂዎች ጋር መግባባት አልተቻለም።

ይህች ምስኪን እህት ለሀገር ምድሩ ባዳ በሆነችበት ሰማይ ስር መንገድ እንደመጣሏ ወገኖቿ የደረሱላት መሆኑ ቢያስደስትም ወደ መጠለያው ለመግባት ፈቃድ አለማግኘቷ የተበሳጨው መረጃውን ያቀበለኝ ወንድም እልህ እና ቁጭት እየተናነቀው ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት ስልክ ደውሎ እንዲህ ነበር ያለኝ፤ "አቶ ነቢዩ ዘበኞች አትገባም አሉን፣ ወደ ጅዳው ቆንስላው ኃላፊ አቶ ዘነበ ደወልን፤ ስልካቸው ዝግ ነው! መልሰን ለቆንስል ሙንትሃ ደወልን፣ ቅድም ውሰዷት እና ለወ/ሮ አዜብ አስረክቧት ያሉኝ እመቤት ደጋግመን ብንደውልም ስልካቸውን አያነሱም፣ ምን ማድረግ ይቻላል? ግን ... ወገናችን ይህን መከራ ላለማየት እህታችን ሜዳ ላይ አይተን እንዳላየን በጭካኔ ጥለን መሄድ ነበረብን?"

ብዙ ተነጋግረን ስልኩ ተዘጋ። እንደምንም በግል አስጠግቶ አሳድሮ በማግስቱ የሚሆነውን ለማድረግ ተስማምተን ከተሰነባበትን በኋላ መልሸ አሁንም የደረሰበትን ሁኔታ ለመረዳት ስደውልለት መልካም የምስራች አበሰረኝ። እንዲህ ሲል "አዎ ተሳካ! የቆንስል ኃላፊዎች ስልካቸውን ማንሳት ባይችሉና የምናደርገው ጠፍቶን ብንንገላታም በፍቃድ ማግኘት ያልቻሉትን ወደ መጠለያ የማስጠጋት ሙከራ ሰው በሰው (በዋስጣ) ይህች አንጀት የምትበላ እህት ወደ ቆንስሉ መጠለያ ልትገባ ችላለች!" ብሎኛል።

በየሜዳው እየተጣሉ ያሉ የኮንትራት ሠራተኛ እህቶቻችን ከችግር ብዛት እስከ ማበድ፣ ራሳቸውን እስከ ማጥፋት እንዳደረሳቸው እያየን ነው። ሰብዕናው ቢገደን ገጽታችን እንዳያጠፉት እህቶቻችን ወደ መጠለያ በመሰብሰቡ ረገድ የጅዳ ቆንስል ኃላፊዎች ዛሬም ድምፃችንን ሰምተው ሳይሆን ግፉአኑን ከደጃቸው ተመልክተው አንድ ቢሉን መልካም ነው!

የአዲሱ ዓመት የማለዳ ወግ በመራራው ሮሮ ጀመርኩት፤ በአዲስ ዓመትም ያላባራው ሰቆቃ እና ልናገረው የከበደኝ ሮሮ አልኩት ... ልተንፍሰው በሚል ከብዙ ጥቂቱን ነካክቼ ነው፤ ምን ላድርግ? የዐረብ ሀገር ስደት ኑሯችን እንዲያ ሆኗል።

ቸር ያሰማን!

ነቢዩ ሲራክ
መስከረም 2 ቀን 2006 ዓ.ም.

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ