ታረቀኝ ሙጬ

እንዴት የመሰለ ግሩም መጣጥፍ ልጥፍ ከጧቱ አንድ ሰዓት ላይ ሌባ ጣቴን አነጣጥሬ ኮምፒውተሬ ላይ ጉብ ከማለቴ አለወትሮው የሞባይሉን ኤፍ ኤም የከፈተው ልጄ የመለስ ሞት መታወጁን አረዳኝ። ምቀኝነት ነው። ሃሳቤ ሁሉ ተዘበራረቀ።

 

የተሰማኝ አዲስና በጣም የተለዬ ነገር የለም - በነኢሣት ወሬ ተለማምጄው ስለነበር አልደነገጥኩም። ግን ይህችን መጣጥፍ እስክጨርስ ባልሰማ ኖሮ ምን ነበረበት? አሁን ማን ያነብልኛል? በደስታ ወይም በሀዘን ምክንያት በዛሬዋ ዕለት መቼም ይህችን ደብዳቤ የሚያነብልኝ ሰው አይኖርም። የቆዬ ቆይቷል። ምቀኞች። ነገ ቢያረዱንስ? ስጨነቅለት እንቅልፍ ያጣሁበት መጣጥፍ ነበር እኮ። እግዜር ይይላቸው። በመለስ ሞት መታወጅ ቤተሰቤ ራሱ ተረበሸ። ባለቤቴ ዐይኗ ዕንባ እያቀረረ ‹ሃያ አንድ ዓመት እኮ የማውቀው ነው› እያለች በሌላ ነገር እስክጠራጠራት ድረስ ክፉኛ አዘነች፤ የሚያለቃቅሳት ብታገኝ ኖሮማ ታስነካው ነበር - እኔም ያኔ ቆርጦልኝ ሰማንያየን እፊቷ ቦጫጭቄ በጣልኩ።

 

ኧረ ምን አስዋሸኝ፣ እኔንም የሆነ ስሜት ወርሮኛል። የእፎይታ ይሁን የምን አላውቅም። ለማንኛውም ባለቤቴን በክፉ ዓይን መልከት ብዬ በሁኔታዋ እንዳልተደሰትኩ በዐይነ ውኃየ በመጠቆም ወደምጸፍበት ክፍል አመራሁ። ከዚያ በፊት ግን በቁም የመንትያ ያህል እንደሚዋደዱ ሁሉ - አንዱ የሥጋ ሌላኛው የነፍስ - ሁለቱ አባቶቻችን መንገዳቸውን አንድ አድርገዋልና እየሸከከኝም ቢሆን እግዜር ነፍሳቸውን ይማር ብዬ ልለፍ። ለዚህ የበቁንን ወገኖች እግዜሩ ወሮታቸውን አይንፈጋቸው፤ የሥራቸውን ያግኙ።

 

ነገር ግና በረከት ይህን ሊነግረን ኖሯል ከመስከረም አንድ በፊት ቢሮ ይገባል ያለን? የሞተውም ትናንት ማታ ከምሽቱ 5፡40 ላይ እንደነበር አሁን የሚኒስትሮች ምክር ቤት ተብዬው በሰጠው መግለጫ እየተነገረ ነው። አንድ ታሪክ ተዘጋ፤ ለሃያ አንድ ዓመታት ውሸት ሲያቅመኝ የነበረው ሬዲዮውም ለጊዜው ይዘጋና በብዕር ጨዋታየን ልቀጥል። እንዲያው ግን አንድ ሰው በጎም ሆነ ክፉ ልክ እንደ አንዱ የቤተሰባችን አካል ሆኖ በየዕለቱ ኑሯችን አብሮ ከዘለቀ ለካንስ ሲጎድል አንዳች ስሜት ይሰማናል? ያን አሁን በቅጡ ተረዳሁ። እኔም እኮ እውነቴን ነው ሰውነቴን እንዳንዳች እያደረገኝ ነው፤ ልገልታ የማይቻለኝ ስሜት። የዘፈን ዳር ዳሩ እስክስታ ነው።

 

ልጽፍበት የነበረው ጉዳይ ርዕሱ እንዲህ ነበር፦ በሞት አይቀለድም

ዝርዝሩ እንዲህ ይቀጥላል፦ ትናንት ማታ ከካናዳ ሀንጎቨር ይሁን ቫንኩቨር ከተባለ ቦታ አትክልት አሰፋ በሚባል ወጣት የተጻፈ ስለኢትዮጵያውያን የወቅቱ ለሚሞት ሰው የሀዘን … አይ ስሜቴ ተዘበራርቆብኛል። አሁን መጻፌን ላቁምና የዚህ መርዘኛ ሰውዬ በሞት መለየት የሚያስከትለውን ማኅበረሰብኣዊ ድባብ ወጣ ብዬ ላጢንና ነገ ወይም ሰሞኑን ልመለስበት። ከጎረቤት ሬዲዮ የምሰማው ስለመለስ አፍሪካዊና ዴሞክራሲያዊ ስብዕና፣ ስለሀገር ወዳድነቱና ስለልማታዊ ተፈጥሮው የሚነገረው በጆሮ እየገባ እየረበሸኝ ነው፤ በዚህ መሃልም የሀገሬ ቁስቁልና አብሮ እየተሸረጠብኝ ከመለስም ከሀገሬም የማልሆንበት ድባብ ተፈጥሯልና ጽሑፌን ገታሁ። ነሐሴ 15 ቀን 2004ዓ.ም ከጧቱ 2 ሰዓት ከ7 ደቂቃ።

 

(በተመሳሳይ ቀን ከሁለት ሰዓት በኋላ) በኦፊሴል ከወያኔ መንግሥት በተነገረው መሠረት አባትና ልጅ ያረፉበት ጊዜ ከአንድ ሣምንት አይበላለጥም። እንደወያኔዎች ቀላጤ በሣምንት ውስጥ ተከታተሉ። አስከሬናቸው በአሁኑ ቅጽበት የቀብር ሥነ ሥርዓት ብቻ እየጠበቀ ያለ ሁለቱም ሬሣዎች በቁማቸው ሳሉ በቀበሯት ሀገርና በቀበሩት ሕዝብ መካከል ተጋድመው ይገኛሉ። ግን አሁንስ ቢሆን መሞቱ እውነት ይሆን? እኔ ግን አላምንም። እንዴ፣ እሱ እንዴት ይሞታል? ራሱ መልአከ ሞት አልነበረምን? ያቺ ሚሚ ስብሃቱ ምን ይውጣት ይሆን? እነዚያ ስሙ በክፉ ሲነሳ መንታ መንታ የሚያለቅሱ የመለስ አምላኪዎች ምን ይውጣቸው ይሆን? ሞቱን መቼም አያምኑም - እንደ ኤልያስ ዐረገ እንዳይሉ ሃይማኖት የለውም …

 

(ተመሳሳይ ቀን ከቀኑ 6 ሰዓት ላይ)

የብዙ ሰው ሰሜት ለማጤን ሞከርኩ። ሰው የተደበላለቀ ስሜት ነው ያለው። የወደፊቱን ከመፍራም ይሁን ሰውዬው በየሰው ላይ ባሳደረው ተፅዕኖ አላውቅም ግን ጥቂት የማይባል ሰው ቅጭም የማለት ሁኔታ ይታይበታል። የማታውን ሁኔታ ገና እየተዘዋወርኩ የማየው ይሆናል። ሰሞኑን ግን መከራችን መብዛቱ። የሀዘን መግለጫ የማይልክ እኮ የለም። እጅ እጅ እስኪለን ጆሮኣችንን በተላከም ባልተላከም(በተፈበረከ ለማለት ነው) የሀዘን መግለጫ ስንጥለቀለቅ መክረማችን ነው ቢያንስ እስከ መንፈቁ - እስከዚያን ጊዜ ከቆየን።

 

‹እያነቡ እስክስታ›፦

የገደለው ባልሽ የሞተው ወንድምሽ፤

አዘንሽ ቅጥ አጣ ከቤትሽም አልወጣ።

 

የሚባል ባህላዊ ሥነ ቃል አለን። ጥሩ ገላጭ ነው። ችግራን ቤት ሠራሽ በመሆኑ ግራ ተጋባን። እንዳንደሰት የሚሞቱት የኛው ናቸው - በክፉ ሥራቸው ጠላናቸው እንጂ የአንዲት ኢትዮጵያ ልጆች በመሆናቸው እንዲሞቱ የምንሳልለላቸው አልነበሩም፤ አይደሉምም። እንዳናዝን የሠሩት ሥራ ከፊት ለፊታችን እየተደቀነ ልቅሶዋችንን አርቲፊሻል ያደርግብናል - ዲያብሎሳዊ ተግባራቸው ዕንባችንን ያደርቀዋል - በዚያም ሳቢያ ልቅሶኣችን ይበላሻል። የጨነቀ ነገር ነው የገጠመን።

 

ያቺ ምሥኪን ድሃ ሴት ለከበርቴው ወንድሟ ስታለቅስ፦

"አንት ሳላይሰጥ ሥጋ ዘወር በል ከፊቴ፤

ባሏ ሞቶባታል ላላቅሳት አይቴ።"

ብላ በማልቀስ መሪር ስሜቷን የገለጸችው እንደኛው ያለ አስቸጋሪ ነገር ቢገጥማት መሆን አለበት።

 

አንድ ጸሐፊ ቀደም ሲል ወደ ሱዳን ሊሄዱ ሲሉ ራያ ቆቦ ውስጥ ባለቁ የትግራይ ኪነት ቡዳን አሟሟትና የልቅሶ ሁኔታ አስመልክቶ በጻፈው አንድ መጣጥፍ ላይ የማይረሳኝ መልእክት ማንበቤ ትዝ ይለኛል። ይነጋል በላቸው በሚባል ጸሐፊ የተጻፈ ይመስለኛልና ያን ጽሑፍ ያወጣችሁ ድረገፆች ከዚህች ደብዳቤ ጋር ሊንክ ብታደርጉት ወቅታዊ ነው እላለሁ። ጭብጡ እነዚህ ወያኔዎች እጅጉን ስለከፋፈሉን በደስታው ብቻም ሳይሆን በሀዘኑም ‹የእነእገሌ ሀዘን፣ የእነእገሌ ልቅሶ› በሚል መከፋፈላችንና በዚያን ጊዜው ብሔራዊ ሊሆን የሚገባው ሀዘን የክልል ብቻ እንዲሆን የተደረገውን ጥረት የሚዳስስ ነበር።

 

አትክልት አሰፋ የተባለው ወጣት ሰሞኑን እንደጠቆመው ባህላችን ክፉኛ እየተበከለ መጥቶ በሰው ሞት መደሰት መጀመራችንን የተለያዩ ሰዎችን ስሜት ለማወቅ ባደረገው ጥረት መረዳቱን ነግሮናል። የፓትርያርኩን ሞት በመመርኮዝ ያነጋገራቸው ሰዎች ሁሉም የጳጳሱን ሞት እንደሚፈልጉና ምክንያታቸውም ተመሳሳይ እንደሆነ ገልጾኣል። ሰዎች ግፍና በደል የፈጸመባቸውን ሰው በፈጣሪ ሲሞትላቸው ብቻ አይደለም ራሳቸውም ሊገድሉት አሳቻ ጊዜና ምቹ ሁኔታ እንደሚጠባበቁለት የታወቀ ነው። አትክልት እንዳነጋገራቸው ያሉ በሕይወታቸው የሰውን መከፋት በጭራሽ የማይፈልጉ ዓይነት ሰዎችም ቢሆኑ ያው ሰው ናቸውና በጠላትነትና በሰይጣንነት የፈረጁት ሰው ሲጎዳ ወይም በሞት ሲለይ መደሰታቸው ያለ ነው፤ ነውርነትን የለውም።

 

መጽሐፉ ጠላትህን ውደድ አለ እንጂ የለየለትን ሰይጣን አፍቅር ለርሱም ራራለት እጀ ጠባብህን እንዲወስድ ቀኝ ጉንጭህንም በጥፊ እንዲያቀረናህ ስጠው አላለም። እንደመጽሐፉማ አንድ ሰው ሲበድልህ አንዴ አንተ ራስህ ምከረው፤ ሁለተኛም በሰው አስመክረው፣ እነኚህን እምቢ ካለህ በሦስተኛ ደረጃ ለቤተ ክርስቲያን ንገር ነው ያለው። እኛስ ምን አጠፋን? እነዚህን ዋልጌ የቤተ ክህነትና የመንግሥት ሰዎቻችንን አካሄዳቸውን አይተን ከጧቱ መከርናቸው፤ አስመከርናቸውም፤ ግን ናቁን - ተዛበቱብን፤ በላያችን ላይ ለዘመናት ዶለቱ፤ በቁማችንም እንጦርጦስ ከተቱን። እነሱ ራሳቸው የቀደዱልንን በር ሁሉ እንደገና ቆጭቷቸው ሲጠረቅሙብንና ልቅሶና ዋይታችንን፣ ልመናና ምህላችንን እምቢ ሲሉን ተዋረዱን ጠብቀን ለየአምላካችን ዕንባችንን በልቅሶ ከጎደጎደው ዐይናችንና ደማችንን እነሱው ከሚያዘሩት ዕልቂታችን እየቀዳን ወደላይ ላክነው። መልሱም ከዚህ ዓመት ጀምሮ መከሰት ያዘ። ይሄውናም እየተከታተሉ መንጎድ ጀመሩ።

 

ትናንት እንዳነበብኩት በዚህ የሞት ሠልፍ የተሰደሩ በርካታ የወያኔ ቁጫጭና ቱባ ባለሥልጣናት መኖራቸውን ተገንዝቤያለሁ። [በነገራችን ላይ መለስ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ሊሳለቅና ሀገሪቱን ሊያዋርድ በሚመስል የዕቃቃ ጨዋታ ታችኛውን ቤተ መንግሥት በእንፉቅቂትና በምርኩዝ እየተዘዋወሩ እንዲጠብቁ ያደረጋቸው የኢትዮጵያው ኤርየል ሻሮል፣ አቶ መቶ አለቃ ፕሬዚደንት ግርማ ወ.ጊዮርጊስ አሁን በሚዲያ ስለመለስ እየተናገሩ ነው። አንደበታቸው ይንቀጠቀጣል። አይ እርጅናና በሽታ! እንዴት መጥፎ ናቸው? እኚህ ሰው አራዳ ናቸው ይባላል። በዚያን ሰሞን እጅ ሆነው ነበር ግን በዳይቨርት ወደሌሎቹ አዞሩት እየተባሉ ይታማሉ። ሰው ቀልድ ጨምሯልና ጃል!]

 

በነገራችን ላይ ለአንድ ወያኔያዊ የህክምና ዶክተር የአንድ ወዳጄ ወዳጅ ላስተላልፈው የምፈልገው መልእክት አለኝ። ምንድነው የሚለው ይሄ ዶክተር - “የወያኔ ቱባ ባለሥልጣናት እያለቁ ያሉት በደም ካንሰር ነው። ከአሁን በፊት በርካቶች ሞተዋል። ብዙዎቹ ሲመረመሩ ይሄው ህመም አለባቸው። ምክንያቱን ስናጤነው ቀደም ሲል በረሃ እያሉ በተመገቡት እህል ተመርዘው ነው። ያ እህል ብዙ ጊዜ እንዲቆይ በኬሚካል ታክሞ ነበርና ያ ኬሚካ ነው ለዚህ የዳረጋቸው። የበለጠ ለማጥናት እየሞከርኩ ነው።” ነው። ብዙ ሳልርቅ - አባ ጳውሎስ በረሃ ውስጥ ገብተው ታግለዋል እንዴ? ያን ምግብ ከየት አገኙት ታዲያ? ምክንያቱ ይሄ አይደለም - ማንም እንዳይሳሳት! ይህ የዕንባ ቅጣት ነው። ከእንግዲህ ማቄን ጨርቄን የለም። ጦርነቱን ገጥመዋል - ከገጠሙት ጋር። ከነዚህ አንድኛቸው በሰው ቢሞት ኖሮ አዲስ አበባ ትተርፍ ነበር? እንኳን ከሰማይ ሆነ። ሁሉም ለበጎ ነው። የኢትዮጵያ አምላክ ማንነቱን እያስመሰከረ ነውና የህመማቸው መንስዔ የደም ካንሰርም ይሁን ኤድስ ዋናው የየመክሊታቸውን ማግኘታቸው ነው፤ እንጂ ጌታ ከፈቀደ በገዛ ምራቃችን ትንታ ወይም ሃያና ሠላሣ ግራም ሥጋ አንቆንም እንሞታለን አይደለም እንዴ?

 

የጳጳሱ ጊዜ ሬዲያና ቲቪው እስከዚህም አላሞቀላቸውም ነበር - ጥረቱ የመለስን ለመሸፋፈን መሆን አለበት። ነገር ግን ሁሉም በጊዜው ተገለጠ። የመለስ ሞት ሰኞ አካባቢ እንደሚገለጥ ከዐርብ ጀምሮ ውስጥ ውስጡን ሲናፈስ ሰምቻለሁ። ግን የውሸታቸው ወሸት ትናነት ማታ እኩለ ሌሊት ገደማ እንደሞተ አስመስለው በሞተ ሰው ሳይቀር ድራማ ይሠራሉ። እነሱ በተራቸው ሲሄዱ መለስ ትዝብቱን እንዴት ይነግራቸው? ለነገሩ የውሸት አሰልጣኛቸው አንዱ እርሱ አልነበር? የዋሾች በረት እየተደረማመሰ ነው።

 

እንግዲህ የክት የነበረው የመለስ ዜና(ዊ) ዕረፍት ከወር በላይ ተንቆራጠው ተንቆራጠው ሲያበቁ ሸፍኖ ማቆየቱ እንደማያዋጣ ሲረዱ በመጨረሻው አወጡት። ብዙ መደሰት አይገባም። እግዜር እንደፍጥርጥሩ ያድርግ። ለመማር አንጎሉ ክፍት የሆነለት ማንኛውም የየትኛውም ጎራ ወገን ይማር። መማር የማይችልም እንደእሳት ራት እዬገባ ይለቅ። እኛም በዕድላችን እያዘንን ከመኖርና በዳያችንን በዱኣና በኪሪያላይሶናችን ከማጋፈጥ ወደ ኋላ አንልም።

 

በሞት መቀለድ መጥፎ ባይሆንም - ማንም ስለማይቀር - ‹ፓትርያርኩ የሞቱት የመለስን ሞት በፊቸሪንግ ለማጀብ ነው› እያላችሁ የምትቀልዱ ሰዎች ዕረፉ። እርሳቸው ራሳቸው ሌላ በፊቸሪንግ የሚሠራላቸው ካስት ስላላቸው የመለስ አጃቢ አይሆኑም። ምን በወጣቸው? ለመለስ ፊቸሪንግ የተዘጋጁ ብዙ ተከታይ ኳየሮችና ካስቶች ስላሉ አትጨነቁ። ቀልድ ጥሩ አይደለም። ይህን በመሰለ የመከራ ወቅት መተዛዘንና አንዱ ሌላውን ማስተዛዘን ይገባል እንጂ ባንዱ ቁስል ሌላው እንጨት መስደድ የለበትም። ይልቁናም አንድ የትልቅ ሰው ሞት የሁሉም ሰው ሀዘን እንዲሆን የጋራ ቤት ለማግኘት በርትተን እንታገል። የወያኔ አነሳስና አወዳደቅ መቼም ትልቅ ዩኒቨርስቲ ነው። ወያኔ ጭንቅላቱ ከተመታ በኋላ አልወደቀም ማለት ግንቦት 13/83ዓ.ም መንግሥቱ ኃ/ማርያም ዝምባብዌ ገብቶ ሳለ አዲስ አበባ ላይ ደርግ አልወደቀም ብሎ እንደመቀለድ ነው።

 

ምኞት በተፈጥሮው ለማንም የማይከለከል እስከሆነ ድረስ “በአጠቃላይ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታዮችና ለሕወሓት/ኢሕአዴግ አባላት፣ ለሟቾች ቤተሰቦች እንዲሁም ለአፍሪካ ሕዝቦችና መሪዎች እኚህን የመሰሉ ለ22 ዓመታት አንዲትን ሀገር በሰላምና በፍቅር ያስተዳደሩ ወጣት ዴሞክራትና የቅዱስነታቸው በረከት ለዓለም የበቃ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ በመነጠቃቸው መጽናናትን እመኛለሁ።”

 

ለመሆኑ በረከት - ቅድም አካባቢና ጧትም “የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን ቀብር እስኪፈጸም ባንዴራው ዝቅ ብሎ የሚውለበለብበት ሁኔታ ይፈጠራል።” ምን ዓይነት አማርኛ ነው?” (የተሰመረበትን እዩልኝ) “… ባንዴራ ዝቅ ብሎ እንዲውለበለብ መንግሥት በመወሰኑ በዚሁ አጋጣሚ ይህ መመሪያ ተግባራዊ እንዲሆን ለሚመለከተው ሁሉ አስታውቃለሁ” ለምን አይልም። በሁሉም ድኃ!

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ