አባ ጳውሎስ፣ መተዛዘንና ኢትዮጵያዊነት
አትክልት አሰፋ-ቫንኩቨር (ካናዳ)
አባ ጳውሎስን ፊት ለፊት የማየት እድል ያጋጠመኝ ግሸን ማሪያም ነበር። ግሸንን የሚያውቅና ግሸን ማሪያምን ያየ ሰው ሁል ጊዜ በትዝታ ሲቀዝፍ እንዲኖር የተፈረደበት ፍጡር ነው። የግሸን ማሪያሙን አስደንጋጭ ትዝታ በኋላ ልመለስበት፦ ሰሞኑን የኢትዮጵያ ሁኔታ እንደ ፈሪ ሸምጣጭ አቋራጭ እየፈለገ በፍጥነት ማምለጥን ተያይዞታል። ዛሬ አዲስ ሆነው ነገ በሌላ እየተተካ… እየተተካካ… መጓዝን መለማመድ ጀምረናል።
የዘመነኛው ጉዳችን ጠቅላይ ሚኒስትራችን ብቻ አልሁኑም የአባ ጳውሎሰን ዱብ እዳ አምጣብን ወይንም አመጣልን እንጅ። እንደኔ እንደኔ ኢትዮጵያዊነት ትልቅ ፈተና ውስጥ የወደቀበት ጊዜ እንደዛሬው፤ ልክ እንዳሁኑ ዘመን ያለ ለመፈልግ ብንቧጥጥ የምናገኝ አይመስለኝም።
ዘመኑን የክፋት ዘመን እንዳልለው ዘመኑ እስክንድር ነጋን አንዷለም አራጌን፣ ብርቱካንንም ሆነ የእስርቤት አርበኛዋን ርዮት አለሙን… አለያም ጃስ እያሉ ሚያስፈራሩትን ተመስገን የተፈጠሩበትና ሀገሬ ብለው ትንቅንቅ የተያያዙበት ነውና ስድብ ይሆንብኛል።
አዎ እነዚያ በቅንጅት ዘመን ሆ ብለው የተነሱና ለመከላከያ የሚሆን ጥይት ሳይሆን የድምጽ ካርድ አንግበው ለሀገር አንድነትና እኩልነት ብሎም ለፍትህ ነጻነትና ለዲሞክራሲ መገንባት የቆረጡ ወጣቶች ዘመን ነውና የክፋት ዘመን ለማለት ያሸማቅቃል።
ወያኔን ያህል ደም ናፋቂ ቡድን መትረጌስና ታንክ ይዞ ሲመጣባቸው እስኪርቢቷቸውን ያነሱ ጸሀፊያንም ብቅ ያሉበትና ለሀገራቸው ለወገናቸው የሚበጀውን (በስመ ነጻ ሚድያ ቢሆንም) ሲታሰሩና ሲፈቱ፤ ሲደበደቡ እና ሲሳደዱ የሚኖሩበት ብቻ ሳይሆን በሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ወያኔ መራሹን የኢህአዴግ መንግስት በራሱ ሜዳ ድራሹን ለማጥፋት ቀና ደፋ ያሉ የዚህ ዘመን ወጣቶች ጊዜ ነውና ዘመኑን ክፉ ማለት ያስፈራል።
በሌላ በኩል ደግሞ ሰው የተባለ ፍጥረት… ህይወት ያለውን የአምላክ ምሳሌ… ሞተ ወይንም ታመመ ሲባል በደስታ ጮቤ የሚረገጥበት መሆኑን ለሚያይ ሰው ምን ያህል ኢትዮጵያዊነት ፈተና ውስጥ እንደወደቀ ያስተውሏል።
ድሮና ዘንድሮ
ድሮ ስላችሁ ያንን የድንጋይ ዳቦ ዘመኑን አይደለም። ድሮ ስላችሁ እነኛ ኩሩ አባቶቻችን ከልባቸው ተከባብረው የኖሩበትን አለያም የእድሜ እኩያዎቹ እንኳን አንቱ… እርሶ… እየተባባሉ ቁጭ ብድግ የሚሉበትን አላልኩም። ድሮ ስላችሁ በሀይማኖት ክብር ሰጥተው አብረው በልተውና ጠጥተው ልጆቻቸውን በአንድ ገበታ አስቀምጠው የክብርን ምንነት ውስጣውስጣችን እንዲገባ ያደረጉበትን ያንን የደጋጎቹን የአባቶቻችንን ዘመን ለማለት አይደለም። ድሮ ድሮ የምላችሁ ትላንትናን ነው እኔ ብላቴና እያለሁ ድሮ ልጅ እየነበርኩ ያኔ…
አንድ አቶ ማሞ የሚባሉ ድድ የምናሰጣበት አካባቢ የማይጠፉ ክፉ ሚባሉ ሰው ነበሩ። ውሪው ሁሉ ይጠላቸዋል። ማንም የሚወዳቸው የለም። ድድ ማስጫው ያደረግነውን ለቤተሰቦቻችን ስለሚናገሩ ብቻ ሳይሆን ወይ ኳሳችንን ይቀሙናል አለያም ያባርሩናል ብቻ የልጆች ሁሉ ጠላት ናቸው። ታዲያ አንድ ቀን በድንገት መሞታቸውን እዚያው ድድ ማስጫ አካባቢ ተሰምቶ ልጁ ሁሉ አንገቱን ደፍቶ… በሀዘን ልቡ ተሰብሮ… በዝምታ ተውጦ ሰነበተ። ታዲያ ማንም ማንንም ሳያስተባብር ሁሉም የሚያወራው ስለ ሰውየው ደግነት፣ ለኛ ለህጻናቱ በማሰብ ቤተሰብ ጋር እንደሚነጋገሩ… ብቻ ቅዱስነታቸው ብቻ ሲዘከር ሰነበተ… በሚገርም ሁኔታ ሌት ተቀን ይንቀላቸው ስንል የነበሩት እኒያ አባት ከአባቶቻችን ሁሉ ልቀው ደግነታቸውን ስናወራ ከመሰንበታችንም በላይ ያለጊዜያችን ቀብር ካልሄድን ብለን መሟገታችል ይታወሰኛል።
ይህ የማወራችሁ እውነት የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪ እያለሁ የሆነውን ነው። ሀዘን ምን ማለት እንደሆነ ሁላችንም ኢትዮጵያዊያኖች የምናውቀው፣ አብሮን የኖረ… አልያም ከጎናችን ያደገ ነው ማለት ይቻላል። ሀዘን ካለ ሁሉም አብሮ ያዝናል። ለዚህ ጽሁፍ መነሻየ የአቡነ ጳውሎስ ረፍት ነው። ረፍት ብዬ የጻፍኩት ሞት ላለማለት አስተዳደጌ ወጥሮኝ ነው።
ስለ አባ ጳውሎስ ህልፈት የተሰማቸውን ለመፈተሽ ፈልጌ ከብዙ ወዳጆቼ ጋር አውርቻለሁ… እዚህ የማነሳላችሁ ግን የመረጥኳቸውን ሶስቱን ወዳጆቼን ምልከታ ነው።
መጀመሪያ ስለ አባጳውሎስ ሞት በስልክ ያወራሁት ከአንድ ሩህሩህ፣ ደግና ቸር ከሆነ ወዳጄ ጋር ነበር። ይህንን ስላችሁ ከልቤና ከእውነቴ ነው። የልጁን መጥፎ መሆን አለመቻል ለመግለጽ ቃላቶች ያጥራሉ… እናም በወሬያችን መሀል ደስ ያለህ ትመስላለህ? አልኩት። አያይዠም እንዴት በሰው ልጅ ሞት የደስታ ስሜት ሊሰማህ ቻለ? አልኩና ለመፈታተን ሞከርኩ።
እሱም መለሰልኝ… ያ በኬንያ ምድር በሰው ጭንቀት ሲታመም የማውቀው፣ አንዱ እንዲህ ሆነ ሲባል የራሱን እየሰጠ መኖርን የለመደ ሰው… በቁንጫ ሞት ሲሳቀቅ የማውቀው ወዳጄ መለሰልኝ “እኔ እኮ አሁን የማየው የአንድ ሰውን መሞት አይደለም በአንድ ሰው ሞት ጀርባ ያሉትን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ህይወት ነው የማየው አለኝ”
ይሄንኑ መፈታተኔን በተለያዩ ወዳጆቼ ላይ ለማድረግ ፈለኩና ሌላ ወዳጆቼ ጋርም ሞከርኩት ሁሉም ራሳቸውን የሚገልጹበት የተለዬ ዘዬ ነበራቸው።
ሌላው እንዲህ አሉኝ። ትልቅ ሰው ናቸው… እርሶም በሰው ሞት ይደሰታሉን? አልኳቸው። በወሬያችን መሀል… መልሳቸው እንዲህ ነበር “አንተ እኔኮ ኢትዮጵያዊ ነኝ። አሉ ጥብቅ አድርገው። …ኢትዮጵያዊ ነኝ! ኦርቶዶክስ ተዋህዶ የተባለውን የኢትዮጵያ ህይወት መሰረት እኮ ነው ይሄ ሰውየ ተራ መጫዎቻ ያደረገው እንዴት ልዘን? እንዴትስ ብዮ ሀገሬን ለማፈራረስ ለቆመ ሰው ልቤ ይራራ…? ብለው ፊት ለፊቴ አይናቸው በውሃ ሊሞላ መሆኑን ሳይ ቀላልጀ አረገብኳቸው። ደግሜ ወደ ሌላው አመራሁ…
ይህ ሰው ህይወቱን ለራሱ ኖሮ ስለማወቁ እጠራጠራለሁ። ደግ፣ መልካም፣ ቅን የሚሉት ቃላት አይገልጹትም የምሬን ነው ለሰው ለመኖር የተፈጠረ እንበለው የአባ ጳውሎስን ሞት እንዴት አየኸው አልኩት ለማፋጠጥ፤ መልሱ አጭር ነበር። …እነኝህ ሰዎች እኮ የምትተዛዘንበትን ልብ ቀምተው ወስደውታል አለኝ።
እነዚህ ሰዎች ድንቅ ናቸው ከምላቸው፣ ከተፈታተንኳቸውና ምላሻቸውን ለናንተ ለመንገር የወሰንኳቸው ናቸው። እነሱ እንዲህ ገለጹት እናንተም የራሳችሁ አላችሁ።
እኒህ ሰው ማለትም ወዳጄ እንደሚጠራቸው አባታቸው አቡነ ጳውሎስ ወደድንም ጠላንም በእድሜ የጠኑ አባት ናቸው። ሰው ናቸውና በህመማቸውም ሆነ በህልፈታቸው ልናዝን በተገባ ነበር። ልክ እንደ አቶ ማሞ በተንሰፈሰፍን ነበር። ኢትዮጵያዊ በራሱ፣ በግሉ የሚመጣበትን ነገር በሞት በህመምም ሆነ በድግስ ጊዜ ይቅር ብሎ መኖርን የለመደ ህዝብ ነው።
አባ ጳውሎስም ሆኑ መለስ ግን በሀገር ነው የመጡበት እና ማዘን አቃተው። እነኝህ ሰዎች በህዝቡ ውስጥ ያሳደጉት የአባትነትን ጸጋ ሳይሆን የመጥፎነትን መገለጫ ጠባሳ ነው። ሰውየው በቤተ አማኙም ሆነ በመላ ህዝቡ ውስጣ ውስጥ ያኖሩት ክብርንና ሞገስን ሳይሆን ውርደትንና ቅሌትን ነው። ደግነትንና ዝቅ ማለትን ሳይሆን እልህንና ባልኩህ ተጓዝን ነው።
ለዚህም ነው ኢትዮጵያዊነት ታላቅ እጅግ ታላቅ ፈተና ውስጥ ወድቆ የሚታየው። ኢትዮጵያዊነት ጨዋነት፣ ሩህሩህነት፣ ደግነት ነበር…
በ1985ዓ.ም አካባቢ ይመስለኛል ያኔ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ማጠናቀቂያ ወቅት ነበር። ወደ ግሸን ማሪያም የመጡት አቡነ ጳውሎስ ለየት ያለ ነገር ይዣለሁ ብለው ነበር። እሱም የግሸን ማሪያም ታቦተ ጽላት ተሰርቆ አዲስ አበባ ላይ ሌባውን ይዠ ተቀብዬ ልመልስ ነው የመጣሁት የሚል ስለነበር በርካታ የደሴና አካባቢዋ ሰዎች እጅግ ብዙ የሚባሉ ምእመናንም በአውቶቡስ ከአዲስ አበባ… ሁሉም መንገድ ወደ ግሸን ብለው ነበር።
ታዲያ ግሸን ማሪያም አንድና አንድ ብቻ በር ያላት በመስቀል ተራራ ላይ የተመሰረተች ቤተ ክርስቲያን በመሆኗ የሰው ብዛት ከወትሮው ለየት ያለ ነበር። እዚያ ተራራ ላይ ለመውጣት እራሱ ሌላ ሶስት ቀልልት የሆኑ ሽንጣም ተራሮችን መውጣት የግድ ይላል። ብቻ መስቀል ተራራው ላይ ሆኖ ወደታች ለሚመለከት ሰው በርካታ ነጫች የለበሱ ምእመናን በዝግታ ዳገቱን ሲወጡ ማየትና የአርባ ቀን ህጻን ይኮንበታል የሚባልለትንና ጌታ የተሰቀለበትን ግማደ መስቀል የተሸከመውን መስቀል ያለበትን ቦታ ለመሳለም ተራራን ሲወጡ ማየት ምንኛ ደስ እንደሚል ሄዶ ከማየት ሌላ በጽሁፍ አይጨለፍም።
ወደ አባጳውሎስ ልመለስ
አዎ አቡኑ በተራራው ላይ ባለው የምእመናን መሰብሰቢያ ቦታ መሀል ባለ ማማ ነገር ላይ ወጥተው ንግግር ጀመሩ… የተናገሩት ነገር በግርድፉ… ተሰርቆ ነበር ስላሉት የግሸን ታቦት እና ስለመመለሱ ነው። ይሄንን የሰማው ሀገሬው ሰው ማጉረምረም ብቻ አልበቃውም አዎ የያዘውን ቁመህ ጠብቀኝ መሳሪያ ማቀባበል ጀመረ። ያኔ ሰውየውን ሊያጅቡ የመጡ የጦር ሰራዊትም መሳሪያቸውን ማቀባበል ያዙ። ቅድስቲቱ ቦታ የጦር አውድማ ልትሆን ነው… ጩኸት ይሰማል… ፉከራም አለ… ብቻ ቀውጢ ሆነች… ፍከራውም ቀጠለ… የአምላክ እጅ ያረፈበት የግማደ መስቀል ማረፊያ ድብልቅልቁ ወጣ።
ነገሩ ወዲህ ነው የሀገሬው ሰው የታቦቷን መሰረቅ በፍጹም አላመነም፤ ጭራሽ በፍጹም አልተቀበለውም። የሚሉት ደግሞ የቤተክርስቲያናችን በር አንድ ነው ያንን በር የሚጠብቁትም ልጆቻችን ናቸው። በምንም አይነት ተአምር ታቦታችን ልትሰረቅ አትችልም ነው ነገሩ። ለዚህም ነበር የጦር መሳሪያ የተንኳኳው… ባንድ ወገን ሀገሬው… በሌላ ው ደግሞ የአቡኑ ጠባቂ ወታደሮች።
ያገሬው ሰው ይባስ ብሎም የመጣችሁት ዋናዋን ታቦት ወስዳችሁ ሌላ ተመሳሳይ ልትሰጡን ነው እንጂ ታቦታችን ሊሰረቅ አይችልም ብለው አረፉት። ይህ ውዝግብ ለሰአታት ዘለቀ… ከዚያም አሁን ድረስ የማከብራቸውና በትህትና አባትነታቸውን ያስመሰከሩት የደቡብ ወሎው ሊቀ ጳጳስ አቡነ ናትናቲዮስ ተነስተው ልጆቼ አታዋርዱኝ… ሳከብራችሁ? ምነው ምነው አባታችሁ አይደለሁምን? ይህማ እኔ ባለሁበት አይሆንም… ብለው በአደባባይ የህዝቡን ቁጣ መለሱት። እናም ህዝቡ ጋብ አለ። በሳቸው ሽምግልና አቡነ ጳውሎስ መቅደስ ሳያዩ በኤሊኮፕተር ይመስለኛል እ…ብ…ስ አሉ።
ታዲያ ሊቀ ጳጳሱን የሰማ ህዝብ ለምን ፓትሪያርኩን? ብዬ ስጠይቅ ይሄው ድሮ የምላችሁ ድሮ አልፎ ዛሬ መጣ እናም አባታቸው ብጹዕ አቡነ ጳውሎስ ክብርን ቢያሳዩ በተከበሩ ነበር። እሳቸው ያሳዩን ታላቁን የሲኖዶስ ጉባኤ ሲያንጓጥጡ፣ የሾማቸውን መለስ ማስፈራሪያ አድርገው ብጹአን አባቶችን ሲያዋርዱ፣ የቤተክርስቲያንን ህግ ሲጥሱ… ቤተ ክርስቲያን የተጠለሉ ተማሪዎችን ሲያሳፍሱ… ሲኖዶስ የተባለውን ያንን ታላቅ የአባቶች ጉባኤ ውሳኔ ሲደመስሱ፤ በጉባኤ የተቃወሟቸውን ብጹአን አባቶች መኖሪያ ቤት በወጠምሻ እያስበረገዱ ብጹዕ የተባሉ የሀይማኖት መሪዎችን ለማለት ይቀፋል… ግን ማለት ስላለብኝ ልበለው በኩ… ር…ኩ…ም ሲያስመቱ የሰማ፣ ያዬ የተመለከተ ሰው ራሱን በምን መመዘኛ አስቀምጦ ሀዘን ውስጡ እንደሚገባለት አላውቅም።
ለዚህም ነው ኢትዮጵያዊነት ታላቅ… እጅግ ታላቅ ፈተና ውስጥ ወድቆ የምናየው። እንደኔ እንደኔ ከጠየቃችሁኝ እጅግ በጣም… በጣም… እጅግ አዝኛለሁ፣ አንጀታችሁ ተላውሶ ውስጠ ውስጣችሁ ገብቶ የሚያውቅ ሀዘን፤ ትካዜ ካለ ያ ዛሬ በኔ ውስጥ አለ። ያዘንኩት ይህች በደም ማህተም የተገነባች ሀገሬና ህዝቧ ላይ መተዛዘንን በጣጥሰው በጣሉ ሰዎች ሞት አይደለም፤ በራሱ የኢትዮጵያዊነት ጥያቄ ውስጥ መተዛዘን ጠፍፎ በማየቴ እንጂ…
አበቃሁ
ቸሩ ቸር ያሰማችሁ።



