ያሬድ አይቼህ

የአገራችን ፓለቲካ ውጤታማነትና ፍሬያማነት ነው ሚፈልገው። ወሬ ብቻውን እንደውጤት እንደማይቆጠር ያለፉት 20 ዓመታት ምስክር ናቸው። የሚያወሩ ሳይሆኑ፥ በተግባር ውጤት የሚያሳዩ የፓለቲካ ብድኖች ተደማጭነትና አለምአቀፋዊ ድጋፍ ማግኘት ይችላሉ። በጄኔራል ከማል ገልቹ ሚመራው ኦነግ የወሰደው የአቋም ለውጥ በእውነቱ አስደናቂ ሆኖ አግኝቼዋለሁ።

 

 

በተለይ ግንቦት7 ከተመሰረተ ገና 4 ዓመቱ የሆነ ድርጅት ሆኖ ሳለ፥ ከኦነግ ጋር ያደረገው ውይይት ፍሬያማ መሆኑ አመራሩ ቆራጥና የፓለቲካን ምንነት በአግባቡ የተረዳ መሆኑን የሚያንጸባርቅ ነው ብዬ አምናለሁ። በፓለቲካ ውስጥ ሰቶ-መቀበልን መለማድ በእርግጥ የበሰለና አርቆ የሚያስብ የፓለቲካ ባህል ነው። ግን የግንቦት 7/ኦነግ ውጤት ወዴት ነው ሚያመራን? አገራችንን ከፓለቲካ አጣብቂኝ ሊታደጋት የሚችል ውጤት ነውን? ወይንስ ሌላ የተሻለ ውጤት ማግኘት እንችላለን?

 

ፍጹም አመኔታ የለሽ

ባለፈው አመት “መጪዎቹ የኢትዮጵያ አደጋዎች”[1] በሚል በጻፍኩት አጭር ጽሁፍ ላይ እነዳመለከትኩት፥ በኢትዮጵያ ውስጥ ህዝባዊ ፍንዳታ ሲከስት ተጠቃሚዎቹ ዳር ላይ አሰፍስፈው የሚጠብቁ ሃይሎች እንደሆኑ ነው። ኦነግ ከሚያንዣብቡት አሞራዎች አንዱ ነው። ከግንቦት7 ጋርም ያደረገው ዝምድና እና የአቋም ለውጥ የሚያመለክተኝ፥ የኦነግን መቋመጥ እንጂ፥ ለ40 ዓመት ያነገበውን የመገንጠል አላማ በቀላሉ እንደ አቧራ ከላዩ ላይ አራግፎ መጣል የሚችል እንደሆነ አይደለም።

 

ከሁሉም በላይ ግን የግንቦት7 እና የኦነግ አሞራዎች የሰፈሩበት ዛፍ ሻዕብያ መሆኑ፥ በኦነግ አቋም ለውጡ ላይ ፍጹም አመኔታ አሳጥቶብኛል። ሻዕብያ እንኳን ለኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊነት ሊያስብ ቀርቶ፥ ዴ-ሞ-ክ-ራ-ሲ ብሎ መጻፍ የማይችል የፋሽስቶች ቡድን ነው። ሻዕብያ የራሱን ታጋዮች የሚያስር፥ ድራሻቸውን የሚያጠፋ፥ ከደርግ የባሰ፥ ኤርትራውያንን በጦርነት ስነልቦና ሸብቦ የያዘ የደረግ ሰለባ ነው። ከሻዕብያ ለኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊነት ይገኛል ብዬ ማሰብ በፍጹም አልችልም። በፍጹም! በጭራሽ!

 

“ነጻነት የማያውቅ ነጻ አውጪ”

የአገራችን ታሪክ በተደጋጋሚ እንደሚጠቁመው ነጻነትን የማያቁ፥ የዜጎችን ስብዕና የሚያዋርዱ መንግስታት የተፈራረቁብን አንዱ ምክንያት፥ የገዢዎች ተፈጥሮ ጭምር ነው። የግንቦት7 ፀሃፊ የሆኑት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በጻፉት “ነጻነት የማያውቅ ነጻ አውጪ” በሚባለው መጽሃቸው በግልጽ እንዳሰፈሩት፥ ኢህአዴግ ነጻነትን ሳያውቅ ነጻ አወጣሁዋችሁ ብሎን ይሄው አሁን ለ20 ዓመታት በአምባገነን ስርዓት ውስጥ ተዘፍቀናል። ለመሆኑ ግንቦት7 እና ኦነግ ‘ነጻነትን የ-ሚ-ያ-ውቁ ነጻ አውጪ’ ናቸውን? እንዴት ተደርጎ? የት የተማሩት ነጻነት? ከሻዕብያ? አይመስለኝም። የግንቦት7 እና ኦነግ ዝምድና የሚሰጠን ሌላ አምባገነንነት እንጂ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት አይሆንም።

 

ይህን ማለቴ ግን ግንቦት7/ኦነግ የቋመጡትን ማግኘት አይችሉም ማለቴ አይደለም። በፓለቲካ ውስጥ የአቋም ትክክለኝነት ሳይሆን የስትራቴጂና የስልት የበላይነት ነው ውጤት ሚያስገኘው። ለዚህም ነው የግንቦት7/ኦነግ ዝምድናና የኦነግ የአቋም ለውጥ ለገዢው ፓርቲ ትልቅ ስጋት ሚሆነው። ኢህአዴግ አጣብቂኝ ወደሚያስገባ ወጥመድ እየተገፉ ነው።

 

ለምሳሌ ከዚህ በኋላ ኢህአዴግ ድርድር ላድርግ ቢል፥ ግንቦት7/ኦነግ ያንን የድርድር ጥሪ እንደ ኢህአዴግ መዳከም እንደሚያዩት ጥርጥር የለኝም። ያ ብቻ ሳይሆን ማን ነው ኢህአዴግን የሚያምነው? ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ናቸው ወይስ ጄኔራል ከማል ገልቹ ናቸው? የኢህአዴግ የፓለቲካ ካፒታል ባዶ ነው። ከ99.6% የምርጫ ውጤት በኋላ ኢህአዴግን ማመን ሞኝነት ነው።

 

የስትራቴጂና የስልት የበላይነት

ግንቦት7፥ ኦነግና ሻዕቢያ የጠነሰሱት የስትራቴጂና የስልት የበላይነት ለኢትዮጵያ እንኳንስ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ማምጣት ቀርቶ፥ እንዲያውም ኢትዮጵያን ለኦነግ አፈሙዝ አሳልፎ የሚሰጥ እጅግ ተላላ የሆነ፥ ተስፋ ቢስነት የወለደው፥ አጥፊና መርዛማ አማራጭ ነው። ኦነግ በኢትዮጵያ የበላይ የሆነ የፓለቲካ ሃይል እንዲሆን ሊያስችለው የሚችለው መንገድ አሁን እነ ጄኔራል ከማል የወሰዱት ጎዳና ብቻ ነው።

 

ምንም እንኳን ሌሎች ኦነጎች እነ ጄኔራል ከማልን አሁን በጥብቅ ቢያወግዙም፥ እነ ጄኔራል ከማል በኢትዮጵያ አንደ አቶ መለስ የስልጣን ቁንጮ ሲሆኑ፥ ከሰፊው የኦነግ ደጋፊ የሚነሳው ያው የዱሮው የመገንጠል ጥያቄ እንጂ ሌላ ነገር አይሆንም። ኦነግን ኦነግ ሚያሰኘው ተገንጣይነቱ ነውና። ያለዚያ እንደ አህዴድና ሌሎች መሆን ነው እጣ ፈንታው። ያንን እጣ ከ40 አመት በኋላ መላው የኦነግ ደጋፊ ይቀበላል ብሎ ማሰብ የኦነግን ባህሪ መዘንጋት ነው። የማይሆን ነገር ነው።

 

የዶ/ር መሳይ ከበደ ሃሳብ

ኢህአዴግ አጣብቂኝ ውስጥ ከመግባቱ በፊት ማድረግ የሚችለው ነገር ቢኖር ሰፊ የፓለቲካ እድሳት ነው። ያለዚያ ደርግ የገጠመው አይነት አጣብቂኝ ውስጥ ቀስበቀስ እየገባና፥ መጨረሻው እየጨለመበት ነው። አንዱ ሚዛናዊና በሳል የፓለቲካ እድሳት ሃሳብ የቀረበው ከዶ/ር መሳይ ከበደ ነው[2]። የኢህአዴግ መሪዎች የዶ/ር መሳይን ሃሳብ አንብበውታል ብዬ እገምታለሁ። “በጭራሽ አይሆንም! የምን እድሳት ነው እቴ?!” ከሆነ ግን መልሳቸው፥ እንደነ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋና እንደነ ጄኔራል ከማል ገልቹ ያሉ የፓለቲካ ጨዋታውን በአግባቡ ያብላሉ ወገኖች ብዙ ግብ ማስገባታቸው አይቀሬ ነው። ግብ ሚያስገባ ተጫዋችን ማን ይጠላል?!

 

አዲሱ አመት ለአገራችን የፓለቲካ እንድሳት ይሁን!

መልካም 2012!

ያሬድ አይቼህ - ጃንዋሪ 4, 2012

1. http://www.abugidainfo.com/amharic/index.php/6672

2. http://www.abugidainfo.com/index.php/18194/

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ