እንረዳቸዋለን ወይስ እናርዳቸዋለን?

ግሩም ተክለኃይማኖት

የመን መንግሥት ይውረድ በሚሉ ተቃዋሚዎች ከተናወጠች ጀምሮ የኢትዮጵያ ኤምባሲ እና የወያኔ መንግሥት ያላሰለሰ ጥረት የሚያደርጉት ቅጥፈታቸውን ለማስተጋባት ነው። አንዳንዴ በመጠኑ መዋሸትም ጥሩ ነው። ባለፈው ረቡዕ ዕለት በዶቼቬሌ ቃላቸውን የሰጡት የኢትዮጵያ ኤምባሲ ቃል አቀባይ አቶ አምደሚካኤል አሳፈሩኝ። አሳፈሩን። ”ኢትዮጵያዊያኑን እንረዳቸዋለን ... ከአይ.ኦ.ኤም. ጋር በመተባበር ወደ ሀገር መመለስ የሚፈልጉትን እንመልሳለን” ብለዋል።

 

 

የመን ያለን ኢትዮጵያዊያንን በአባባላቸው ግራ መጋባት ብቻ ሳይሆን የተለያየ መላምት እንድንሰጥ አድርጎናል። አንዳንዶች ”አዎ! ይረዳሉ፤ ግን ኤምባሲ ውስጥ ላሉ ሠራተኞች ነው። ነገር ግን ከውጭ ላሉ አጨብጫቢዎቻቸው እና ወሬ አቀባዮቻቸው እንኳን ሲረዱ አናውቅም” ሲሉ ተደምጠዋል። ሌሎች ደግሞ ”... እንረዳለን ማለት ፈልገው ሳይሆን እናርዳቸዋለን ማለታቸው ነው። ሲያርዱ እንጂ ሲረዱ መቼ ታይተው ነው?” ሲሉ ተደምጠዋል።

 

በባህር ሲመጡ ተይዘው በየመን መንግሥት፣ በሳዑዲ ዓረቢያ እና በአይ.ኦ.ኤም. ትብብር እና ወጪ ወደ ሀገራቸው እንዲገቡ የሚደረጉትን ነው እንረዳለን ያሉት? ለዛውም ፎቶግራፍ አንስተው ወረቀት ላዘጋጁበት ክፍያ መጠየቃቸውን ትብብር ያደረጉት ሀገሮችም ሆኑ ድርጅቶች እያወቁ ይህን ማለታቸው ያሳፈራል። በቴሌቪዥንም ሆነ ራዲዮ ከየመን በጦርነቱ ምክንያት በፍቃደኝነት የተመለሱ ሲሉ የውሸት ዜናቸውን ማቅረባቸው የመን ያለ ስደተኛን አንገት አስደፍቷል።

 

በኮንትራት የመጣችን ኢትዮጵያዊ የቤት ሠራተኛ ”… አሰሪዎቼ በዱላ ደበደቡኝ፣ በሰውነቴም ላይ ጉዳት ደረሰ …” ብላ አምልጣ ወደ ኤምባሲ ሄደች። አሰሪዋ የመናዊት ሴት ኤምባሲ ስትሄድ አሳልፈው ሰጡዋት። ተበደልኩ ያለችን፣ እግርዋ ላይ አደጋ ደርሶባት ኤምባሲ አለኝ ብላ የሸሸችን ዜጋ አሳልፎ ለዓረብ መስጠት እና ስትጠፈጠፍ ማየትን የመሰለ ምን እርዳታ አለ? ይህች ጉዳት የደረሰባትን ልጅ ከኤምባሲ ግቢ ሰብለወርቅ ታደሰ የምትባል ሴት ይዛት ሾልካ ዩኒዶም የሚባል ለአፍሪካ ስደተኞች መብት እና የሴቶችን ጥቃት የሚከላከል አንድ ድርጅት ጋር አገናኘቻት። ይህ ድርጅት ኩሩቤል በሚባል ስደተኛ የተቋቋመ ነበር። በዚሁ ድርጅት ተመዝግቦ ያለ ታሪክ ነው። አሰሪዋ የፈላ ውሀ ደፍታባት ወደ ኤምባሲ ያመለጠችን ሴት ”... እኛ ለገረድ አልመጣንም” ብለው አሰናብተዋት ወደ ኩሩቤል ጋር ዩኒዶም ሄዳ እርዳታ ማግኘቱዋን የማያውቅ ሐበሻ ይኖር ይሆን? ይሄ መርዳት ነው ማረድ? ብራቮ!!!! የኢትዮጵያ ኤምባሲና ኃላፊዎቹ ትክክለኛ የወያኔን ምግባር እያሳያችሁን ነው።

 

መርዳት ማለት እንዴት ነው? ሀገር ውስጥ ያለው ብልሹ የፖለቲካ ሥርዓት ለስደት የዳረጋቸውን ምስኪኖች ገንዘብ መብላት ይሆን? የኢኮኖሚ ስደተኛ ናቸው እያላችሁ ታብጠለጥላላችሁ። የኢኮኖሚ ድቀት፣ ድሽቀት ሆነ የኢኮኖሚ ስደት የሚመጣው ከብልሹ የፖለቲካ ሥርዓት መሆኑን ዘንግታችሁት ይሆን? ሽቶ የተባለች ልጅ በኮንትራት መጥታ ሁለት ዓመት አሠርተዋት የሁለት ዓመቱን መኖሪያ ፍቃድ ሳያሰሩላት፤ ሁለት ዓመት የሠራችበትን ሳይሰጡዋት፣ ፓስፖርቷ ላይ ቀይ አስመትተው አባረርዋት። ለስሞታ ኤምባሲ ሄደች። ”ይሄ ... ይሄ በደል ደረሰብኝ ሁለት ዓመት ሠርቼ ገንዘቤን ከለከሉኝ፣ ፓስፖርቴ ላይ ቀይ አስመትተው ወደ ሀገሬም አላሳፈሩኝ፣ ለዕለት የማርፍበትም ሆነ የምበላው የለኝም” ስትል የተሰጣት መልስ ”የኮሚኒቲ አባል ነሽ? መጀመሪያ ተመዝገቢና ሁለት ሺህ ከፍለሽ መታወቂያ ውሰጂ” የሚል ነበር። ይሄ ነው መርዳት? ጣር ላይ ሲሆኑ አንቆ መግደል?

 

በተናጠል ያለውን እንተውና ሌላውን እንይ …

 

እንደ አለመታደል ሆኖ የመን ካለን ስደተኞች ስደት የወለደው ስደት ላይ ያለን በዝተናል። በስደት የመን ውስጥ ከምንኖርበት አካባቢ በጦርነት እየተፈናቀልን ነው። የምንሰራበትም ሆነ መኖሪያ ቤታችንን ትተን ከተሰደድን አስራ አምስት ቀናቶች ተቆጥረዋል። ቤታችንን ጥለን ከተሰደድነው ውስጥ በርካታዎቹ በፓስፖርት ያሉ ናቸው። ሥራም ሆነ መጠለያ ያጣነው ሰዎች ቁጥር ትንሽ አይደለንም። ኤምባሲው ግን ያደረገላቸው እርዳታ የለም። UNHCR ቢሆን በስሩ ላለነው ከፌዝ የዘለለ አጥጋቢ ምላሽ ሊሰጠን አልወደደም። ባለፈው እሁድ በ25/9/2011 አንድ ትውልደ ሐበሻ ለኢትዮጵያ ኤምባሲ 8 ኢትዮጵያዊያን መሞታቸው ተነገረ አለኝ። ሬሳውን ግን ሊወስዱ አልፈቀዱም አለኝ። እውነታውን ለማጣራት ስሞክር በትክክል መሞታቸውን እና ሬሳቸውም ጀማዕተል ኢማን የሚባል (የእስልምና ኃይማኖት ተከታዮች ቁርዓን የሚማሩበት ቦታ) እንዳለ ሰማሁ። ለመሄድም ሞከርኩ። የኤምባሲ ወረቀት ካላሳየህ መሄድ አትችልም። ብትሄድ እና አደጋ ቢደርስብህ አይመለከተንም ተባልኩ። ጦርነቱ የሚጋሽርበት ሮኬቱ፣ መድፉ፣ መትረየሱ፣ ... የሚንዷዷበት መንግሥት የተቃዋሚዎች ማዕከል ብሎ ዶጋ አመድ ያደረገው ቦታ በመሆኑ ፈራሁ። ቢሆንም ግን 8 ኢትዮጵያዊያን፣ 3 ሶማሊያዊያን አስከሬኖች መኖራቸው እውነት ነው።

 

በማግስቱ ሰኞ ዕለት ኪንታኪ የሚባለው ቦታ ቤት ተከራይተው በችግሩ ሰዓት ሸሽተው ቆይተው ቤታቸው መዘረፉን ሰምተው ሊያዩ ሄዱ። ዮናስ እና መኪ ይባላሉ። በመንግሥት ወታደሮች ተያዙ። ቤታችን እዚህ ነው፣ መዘረፉን ሰምተን ነው፤ አሁን ቦታው በመንግሥት ይዞታ ስለሆነ ልናይ ነው ቢሉ ማን ሊሰማ? ማን እሺ ሊል? ታሰሩ። መንግሥት ለደህንነት ጥበቃ ሲል ከኤምባሲ ወረቀት አምጡ ተባለ። ለዜጋው ፈጥኖ ደራሽ የሆነው ኢትዮጵያ ኤምባሲ ንብረታቸውን ተዘርፈው በእስር ላይ የሆኑትን ልጆች ለማስፈታት የሚሯሯጡትን ቅዳሜ ተመለሱ ሲል በቀጠሮ አሰናበተ። ዜጎችን መርዳት ማለት ይሄ ነው አይደል?! በነገራችን ላይ በተመሳሳይ ሁኔታ ሌሎች 8 ኢትዮጵያዊያን ታሰረዋል። መሀመድ ኑር፣ አሊ ...፣ አማና ቱፋ፣ ቃሲም ... የሚባሉት ይገኙበታል።

 

ቀይ መስቀል ማኅበር ቤት ለቤት ባደረገው ፍተሻ ማክሰኞ ዕለት ብቻ 60 አስከሬኖች አባብጠው፣ ሸትተው እና ተበላሽተው እንዳገኘ መግለጫ አወጣ። በየቦታው ተሸርቁጦ፣ በየህንጻ ውስጥ የተለቀመ ነው እንጂ በሆስፒታል እና የዛኑ ሰሞን የተቆጠረውን ያልጨመረ ነው ይህ አኀዝ። ከዚህ ውስጥ አንድ ሰው ቤት ሠራተኛ የነበረች ኢትዮጵያዊ ሞታ አስከሬኗ ሸቶ ተገኝታለች። አስከሬኗን ግን የሚረከብ አልተገኘም። ጦርነቱን ፍራቻ መውጣት ያልቻለ ሁሉ በየቤቱ ከቶ በረሃብ ተጠብሷል። ይህን ረሃብ መቋቋም ያቃታቸው ሁለት ልጆች ኩበዝ (ቂጣ) ሊገዙ ወጥተው ደብዛቸው ጠፈቷል። ሁለት አፋሮችም እስካሁን የገቡበት አልታወቀም። ፋልማታ በሚል ቅጽል ስም የሚታወቅ መሀመድ እንድሪስ የተባለ ልጅ በህክምና ቢረዳም ሊድን አልቻለም። በመጨረሻም አረፈ።

 

ይህ እንግዲህ በሞት ያለፉትን እና የጠፉትን ነው የሚያመላክተው። የቆሰሉትን ሁለት አውቃለሁ። መሀመድ አልዬ እና ከዲጃ አማን፤ ... የኢትዮጵያ ኤምባሲ ግን ማንኛቸውንም ሲረዳቸው አላየሁም። ሌላው ቀርቶ በኤች.አይ.ቪ. ሰበብ ሞታ አስከሬንዋን አውጥቶ ለመቅበርም ሆነ ለቤተሰብ ለመላክ ኤምባሲው ምንም ነገር ሊተባበር ባለመቻሉ ከ3 ወር በላይ አስከሬኗ ጁሜሪ የተባለ ሆስፒታል ፍሪጅ ውስጥ የቀረች ልጅ አለች።

 

ለሚረዱት ዜጋቸው የሚደርጉትን ትብብር መሰል ብር ተኮር እንቅስቃሴ እና ኢትዮጵያዊያኑ ያሉበትን የመኖሪያ ፍቃድ ማጣት፣ ሀገር መመለሻ ማጣት፣ ... መሰል የስቃይ ሕይወት እንይ፦ …

 

የመን ያለ ኢትዮጵያዊ በሙሉ አገባቡ ሕጋዊ አይደለም። በአየርም ሆነ በባህር የሚገባው አገባብ ሕጋዊ እንዳልሆነ ኤምባሲው ጠንቅቆ ያውቃል። በተለይ በአየር የሚያስገቡ ሕገ ወጦቹን ደላሎች ኮሚኒቲ እና ኮሚቴ እያለ ሲያሽሞነሙን ነው የሚታወቀው። ፓስፖርት ስለተያዘ ሕጋዊ የተሆነ የሚመስላቸው ሴት እህቶቻችን ለደላላ ከፍለው ወደ የመን የሚገቡት በአንድ ወር የጉብኝት ቪዛ ነው። ደሞዝ ሲከለከሉ በደል ሲደርስባቸው መጠየቅ አይችሉም። እስር ቤት ገቢ ናቸው። በጉብኝት ገብተው መሥራት አይቻልም እና ተጎጂ ናቸው። ይህን ኤምባሲው ያውቃል። ወ/ሮ እጅጋየሁ የተባለች ሴት ሳሪስ አካባቢ ያለች የመን ካለ ወኪሏ ጋር ሁና ሴት እህቶቻችንን ከሚደርስባቸው በደል በተጨማሪ ለወንዶች እየሸጡ መጫወቻ ሲያደርጉዋቸው ኤምባሲው ምን እርምጃ ወሰደ? ሴትዮዋ ዘዴዋን እየቀያየረች አሁንም ሥራዋን ቀጥላለች። አሽጣል የሚባለውን ኤምባሲው ከሰስኩ ቢልም አንድ ግለሰብ ሊያገኝ የሚችለውን ያህል ፍትህ ሊያገኝ ያልቻለ ሽባ እንቅስቃሴ አድርጎ ሰውየው ነፃ ሆነ። አንድ ትውልደ ሐበሻ የሚባል በኮንትራት የወሰዳት እና ሊያስቀጥራት የነበረችን ልጅ ደብድቦ፣ ደፈሮ ምስጢር እንዳታወጣ ገሎ ማን ይጠይቀው፤ በነፃ ወጣ። ለዜጎቼ ቆሜያለሁ ያለው ኤምባሲ አልሰማም አይባል ጉዳዩን ጀምሮ ጉርሻ ይሁን ልምሻ ያሽመደምደዋል።

 

ለሀገሩ ዜጎች ኤምባሲው ባያስብም ኢትዮጵያዊያኑ ሕጋዊ ሆነው መኖር ያለባቸው መሆኑን የየመን መንግሥት አምኖበት በጣም በዝቅተኛ ሣንቲም መኖሪያ ፍቃድ እንዲያሠሩ ፈቀደ። ኤምባሲው ግን በኮሚኒቲ በኩል ተባለና እየአንዳንዱ 25,000 ሪያል እንዲከፍል ተደረገ። የየመን መንግሥት ስጦታውን ሰረዘ። በነፃ የተፈቀደውን ዜጋው ላይ ንግድ በማሰቡ ዕድሉ ታጣ። ይህም ለዜጋ ማሰብ ነው? አንድ በሉ።

 

የመን ያለ ኢትዮጵያዊ የመኖሪያ ፍቃዱን ለማሠራት ችግር ውስጥ በመሆኑ ለበላተኛ ተጋለጠ። ጀብሃ የተባለ የኤርትራ ተቃዋሚ የየመን መንግሥትን አስፈቅዶ የኢትዮጵያዊያንን የመኖሪያ ፍቃድ ያሠራ ጀመር። በ18,000 የየመን ሪያል ለሚሠራ መኖሪያ ፍቃድ 52,000 ሲያስከፍሉ ኤምባሲው ዜጎቼ ሰው ቤት፤ ለፍተው ያገኙትን ለበላተኛ ተዳረጉ ብሎ ያደረገው እንቅስቃሴ የለም። እንዲያውም በሰበብ አስባቡ ተጨማሪ ገንዘባቸውን የሚያቆረቁዝበት መንገድ ያመቻቻል። እውነት ለሀገር ተቆርቋሪ ቢሆኑ የዜጎች ውጪ የሚቀንስበትን መንገድ ቢያመቻቹ የተረፋቸውን ወደ ሀገር ስለሚልኩ ምንዛሪም ተገኘ ማለት ነበር። ለዜጋችን እያገለገልን ነው የሚል መግለጫ ሲያወጡ አለማፈረቸው ያሳፍራል።

 

ይህም ሆኖ ገንዘቡም ተከፍሎ መኖሪያ ፍቃዱ ቢሠራ ጥሩ ወደ 5,000 በላይ ፓስፖርት እና ቅድመ ክፍያ እያንዳንዱ 200 ዶላር ሰጥተው ሁለት እና ሦሰት ዓመት ጠብቀው ብራቸው ተበልቶ፣ የመኖሪያ ፍቃዱም ዕዳ ጨምሮ፣ ሁሉ ሰው ዕዳ ውስጥ ሲዘፈቅ ለዜጋቸው ያረጉት ምንድን ነው? አሁን ለአንድ ወር የሚቆይ የዕዳ ቅነሳ ከየመን መንግሥት ጋር ተነጋገረናል ተባለ እና ዙሪያ ጥምዝ ሐበሻውን ለእንግልት የሚዳርግ ሥራ ሠሩ። ከ30 ያልበለጠ ሰው አሰራ። በ42,000 የየመን ሪያል ያልቃል ብለው አስጀምረው በ105 ሺህ የየመን ሪያል የጨረሰ አንድ ሰው ነው። እስከ 120 እና 130 ሺህ ጨርሰዋል። ሌላው ችግር እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ኃላፊ የሚሆን የየመን ዜጋ ያቅርብ ተባለ። ኤምባሲው ለዜጎቹ ኃላፊነት መውሰድ አቅቶት ማለት ነው። አንድ በሉ። መቶ ዶላር ድረስ እየከፈሉ የመኒ ፈልገው ያስፈረሙ፤ ምን ይገጥማቸዋል? ትንሽ ቀን ቆይቶ ወይ ብር ወይ ሴትነትሽን ያለበለዚያ የመኖሪያ ፍቃድሽን አሰርዘዋለሁ ይባላል። ሌላ ዕዳ … ምኑ ነው ለኢትዮጵያዊያን የሠሩት?

 

ቢያስረዱን ቢዘረዘሩት ጥሩ ነበር ...

 

ቅጥፈት መሰረቱን፣ ማገሩን … ሰው ውንጀላ ማሰር መግደል ሥራው ከሆን መንግሥት ኤምባሲ ከዚህ የበለጠ አውሬነት ቢታይ ምን ሊደንቅ? ግን በቃ!!!! ቅጥፈቱ ይቁም! ህዝቡ እንዲሁ የቆሰለው መቼ አነሰው?


ግሩም ተክለኃይማኖት

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ