ሞገደኛው መለስና፤ የሰላማዊ ትግል ተስፋና እውነታ (ክፍል - 1)
ሉሉ ከበደ
ከአበቃቀላቸው አስከ አስተዳደጋቸው፤ ከቤተሰብ አስተሳሰባቸው እስከ አካባቢ እምነታቸው፤ ከጫካ ልምዳቸውና ከተፈጥሮ እውቀታቸው እስከ መናኛ ትምህርታቸው፤ ከግለሰብ እስከ ቡድን እምነታቸው፤ ከጠባብ የዘረኝነት አስተሳሰብ በቀር፤ ከቶም ከቶ ብሄራዊና ኢትዮጵያዊ መንፈስ ያልተፈጠረባቸው፤ የፈጣሪ ስህተቶች፤ እነሆ ኢትዮጵያ ህዝብ ጀርባ ላይ ተፈናጠው ተሸክመናቸው ስንኖር ሀያ ዓመታት ተቆጠሩ።
ለቡድን ግብና ጥቅም ቆርጠው የታገሉና የኢትዮጵያን ህዝብ እንደማንኛውም የባእድ አገር ጠላት እየተመለከቱ ያደጉ፤ እጅግ የመረረ ጥላቻና በቀል በውስጣቸው እያመረቀዘ የሚኖሩ፤ ቢቻላቸው የኢትዮጵያን ህዝብ አጥፍተው፤ ሀገሪቱን በታትነው፤ ሰላም ካገኙ፤ የኛ በሚሉት ክልል ላይ የበላይነታቸውን አረጋግጠው ለመኖር የሚፈልጉ የመጨረሻ ክፉ ሰዎች ኢትዮጵያን የተቆጣጠሩበት ዘመን አሁን አሁን አሁን ነው።
ዛሬ ለዚህ ያበቃቸው፤ በሀሰት ፕሮፓጋንዳቸውና በአዞ እንባቸው አውረውት ወደስልጣን መወጣጫ እርካብ ያደረጉት የትግራይ ህዝብ፤ በተለይም አርሶ አደሩ ለነርሱ መሳሪያ ሊሆን የቻለበት የራሱ የሆነ ኢኮኖሚያዊና አስተዳደራዊ ችግሮች ቢኖሩትም፤ እነመለስ ዜናዊ ከውስጡ ፈልቅቀው ሊያወጡ የታገሉትን ኢትዮጵያዊነት መንፈስ በውስጡ ማጠናከርና ጸረ ኢትዮጵያዊነት አካሄዳቸውን ቀድሞ እየተረዳ እንዳይከተላቸው ለማድረግ በራሳቸው ቋንቋ ለማስተማር ያለመታከት መስራት ያስፈልግ ነበር። ግና እንደዘገየን ቀረ፤ ቀረ። በአንባ ገነኑ ደርግ የተገፋ ህዝብ፤ ለሌላ አንባገነን ክንድ ሆኖ እዚያው የአፈና አዙሪት ውስጥ ተሽከርክረን ተመልሰን አረፍነው።
እርግጥ አንድ ህዝብ በድርጅት የተጠናከረ ቡድን በቁጥጥር ስር ካዋለው፤ በተለይም ያ ቡድን በጦር መሳሪያ የተጠናከረና ጭካኔ የተሞላበት አመራር መስጠት የሚችሉ ግለሰቦች ጥርቅም ከሆነ፤ የተቃወማቸውን ሁሉ ስለሚገሉ፤ ስለሚያሰቃዩ፤ ያ ህብረተሰብ ከዚያ ቡድን ሊከላከለው የሚችል የአካልም ሆነ የህግ ጥበቃ የሚያደርግለት መንግስት ከሌለ ህብረተሰቡ በግድም ሆነ በውድ ያንን ቡድን ለመከተል ይገደዳል።
ለዚህ ሁኔታ አስረጅ የሚሆን አንድ እውነት እነሆ። እንደ ኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር በ1983 መጨረሻ አካባቢ ወያኔ መላ አገሪቱን በመቆጣጠር ላይ እንዳለ ደርግ ከወደቀ በኋላ ለተወሰነ ጊዜ ህዝቡ ያለመንግስት ራሱን አስተዳድሮ ነበር። በዚያን ጊዜ ሀረርጌ ውስጥ ኦነጎች በጫካና በከተማ መካከል ብቅ ጥልቅ እያሉ፤ ወያኔንም አላመኑ እየፈሩ፤ ደፈር ሲሉም አብረን ነው ተዋግትን የመጣነው እያሉ፤ አንዳንድ ትንንሽ ከተሞች እኛ ነን አስተዳዳሪዎች ብለው በየቢሮው ገባ ገባ ብለው ነበር። ከፊሉ ገጠር እንዳለ ነበር። ታዲያ እነዚያ ገጠር ያሉት የኦነግ ካድሬዎች ጫካ ተደብቀው የከተማውን ነጋዴዎች “ለነጻነት ትግሉ ገንዘብ አዋጡ” እያሉ በጨለማ ሰው እየላኩ ያዛሉ። የኦሮሞ ተወላጅ የሆኑ ነጋዴዎች ያለፍላጎታቸው ገንዘብ እያዋጡ ከጫካ ለተወከለው ሰው ይሰጣሉ። ይህንን ያወቀው የወያኔ ቡድን ገንዘብ ያዋጣሉ ብሎ የጠረጠራቸውን አረጋውያን እያሰረ ለኦነግ ተዋጊዎች ለምን ገንዘብ እንዳዋጡ ይጠይቃል። አረጋውያኑም ለማስረዳት ሲሞክሩ “እናንተ እዚህ አጠገባችን የላችሁም ። ከኛ ጋር አትቆዩም። ሰዎቹ ጨለማ ለብሰው ነው የሚመጡት። ጠመንጃ ይዘው ነው የሚመጡት። የታዘዝነውን ካልተቀበልን የተጠየቅነውን ካልሰጠን የነጻነት ትግላችንን አትደግፉም ለመንግስት ተሰልላላችሁ። ወሬ ታቀብላላችሁ። ብለው ይገሉናል። መኖር ስላለብን የሚሉንን እንቀበላለን። የተጠየቅነውን እንሰጣለን። እነሱ በራሳቸው መንግስት ስለሆኑ ጠመንጃ በጃቸው ስላለ እጣፈንታችን በጃቸው ነው ። ምርጫችን መኖር አለመኖር ነው።” ነበር ያሉት።
በመለስ ዜናዊ የሚመራው የወያኔ ቡድን በትግራይ ውስጥ ትግል ሲጀምር፤ ህዝቡን በስሩ ማሰባሰብ ሲጀምር ከዚህ የተለየ መንገድ ተከትሎ ነው ማለት አዳጋች ነው።
ይህ በንዲህ እንዳለ ሆኖ እንደማንኛውም በትምህርት ወደኋላ የቀረ ህብረተሰብ የኢትዮጵያም ህዝብ በተለይ አርሶ አደሩ በተለያየ ወቅትና አጋጣሚ መሰረት ለሌለው የሀሰት ታሪክና ፕሮፓጋንዳ ሰለባ መሆኑ የማይታበል እውነታ ነው። ህውሀት ይህንን ደካማ ጎን በትግራይ ህዝብ ላይ በሚገባ ተጠቅሞበታል። እየተጠቀመበትም ነው። ነፃ አውጭ ነን የሚሉ ጠባብ ቡድኖች ሁሉ ጥሬ ሀብታቸው አርሶ አደሩና በትምህርትና በንቃት ዝቅ ያለው ወጣት የህብረተሰብ ክፍል ነው።
በሀገራችን ዘመነ መሳፍንት ተብሎ በሚታወቀው ስርዓት ውስጥ የነበረው የአካባቢ መሳፍንትና ነገስታት ጦርነትና ትርምስ፤ ሀገሪቱን በታትኖ ተቃርጦ ለመቀመጥ ሳይሆን፤ አንዱ አንዱን አሸንፎ ግዛቱን እያሰፋ ኢትዮጵያን አንድ አድርጎ ለመግዛት እንደነበር ታሪክ ያስረዳል። አጼ ሚኒሊክ በበላይነት እስከወጡበት ጊዜ ድረስ የነበው የኢትዮጵያ ታሪክ ደም መፋሰስ የበዛበት በአማራውም በትግሬውም በኦሮሞውም በሌላውም በኩል የተነሱ ገዢዎችና ባላባቶች አንዱ ሌላውን ለማስገበር የጨፈጨፉበት የተጨፈጨፉበት በጥፋቱም በልማቱም ሁሉም የተሳተፉበት ዘመን እንደበረ ታሪክ ያስተምረናል። መቸም በማንኛውም ትግል ላይ አንድ ይወድቃል አንድ ይነሳልና የኋላኋላ አጼ ሚኒሊክ በበላይነት ወጡ። ክፋ አጋጣሚ ሆነና እሳቸውም አማራ ሆኑ።
ወያኔም ሆነ በዘር ላይ የተመሰረተ ፖለቲካ የሚየቀነቅኑ ብሄረተኛ ቡድኖች ሁሉ እንወክለዋለን የሚሉትን የህብረተሰብ ክፍል በስራቸው ለማሰባሰብ አፍ የሚፈቱበት የፖለቲካ ቋንቋ “ሚኒሊክ አርዶህ፤ ሚኒሊክ ቆርጦህ፤ አማራ አርዶህ፤አማራ ቆርጦህ ፈልጦህ’’ ብቻ ሆነ። ህዝቡን የሚያውሩበት ቁንጽል የፈጠራ ታሪክና ወሬ ሌሎቹን ጨፍልቆ ኢትዮጵያን አማራ በጉልበቱ አንድ እንዳደረጋት የሚተርክ ብቻ ሆነ። አያት ቅድም አያቶቻችን አማራውም ኦሮሞውም ትግሬውም ሌላውም ሁሉ ቢሳካላቸውም ባይሳካላቸውም የበላይ ሆኖ ለመግዛት የተቻላቸውን ያደረጉበትን ሁሉም የተሳተፉበትን ጦርነት፤ ነፍጠኛው ተነስቶ (አማራው) ሌሎቹን በግፍ እንደጨረ በማስመሰል፤ ለሁሉም ድህነትና ኋላ ቀርነት ተጠያቂ እሱ እንደሆነ በማስመሰል ኢትዮጵያንም የፈጠራት እሱ ስለሆነ የሱ አንጂ የሌሎች ኢትዮጵያውያን እንዳልሆነች አድርጎ ማቅረብ የዘረኛ ቡድኖች ፕሮፓጋንዳ መነሻ ምዕራፍ ሆነ።
እዚሁ አጠገባችሁ አንድን ጽንፈኛ የኦነግ ደጋፊ ከየት መጣህ ብትሉት ከኢትዮጵያ አይደለም የሚላችሁ። ከኦሮሚያ እንጂ። “ድሮ ድሮ ጊዜ አሉ። ኦሮሚያ የምትባል ሉአላዊት አገር ነበረች አሉ። ሚኒሊክ ጡት ቆረጠ አሉ። ኢትዮጵያ ቅኝ ገዛቻት።” በቃ ይህ ነው ተረቱ። እህ ብላችሁ ካደመጣችሁ። ኢትዮጵያ በነመለስ ዜናዊና በመሰሎቹ ዘረኞች አስተሳሰብ ሚኒሊክ ከመቶ አመት ወዲህ የፈጠራት ያልነበረች አገር ናት። ያልነበረች አገር መፍጠርም አንድ ትልቅ ገድል ነው። ለምሆኑ ጥንት አባቶቻችን የርስ በርስ ውጊያቸውና ጥላቸው እንዳለ ሆኖ ለውጭ ወራሪዎች ቢመቹ ኖሮ፤ እንደሌላው ያፍሪካ ሕዝብ በቀላሉ ባውሮፓውያን ቅኝ ገዢዎች እጅ ላይ ቢወድቁ ኖሮ፤ ዛሬ ስንት ትንንሽ የባእድ ቋንቋ የሚናገሩ የኦሮሞ አገሮች እንደሚኖሩ መገመት ያዳግታል ? ስንት የባእድ ቋንቋ የሚናገሩ ትንንሽ የአማራ መንግስታት እንደሚኖሩ መገመት ያዳግታል? ከጃችን ያመለጠው ትግሬ ጣሊያን፤ በወዲህ የቀረው ኢትዮጵያ ሆኖ ለዘመናት የኖረው ከተደጋጋሚ ሙከራ በኋላ ጣሊያን በለስ ቢቀናው አይደለም? እና ታዲያ በግድም ሆነ በውድ አሰባስበው ባንድነት ላቆዩን አባቶቻችን ምስጋናና ክብር መቸር እንጂ፤ ከዘመናዊው ዓለም ጋር እኩል ሰልጥነን መራመድ ያቃተን እራሳችንን መመርመር ትተን አነሱን ማማር ለምን ቅኝ ገዢዎች ተቃርጠውን አልቀረን ከማለት በቀር ሌላ ትርጉም ያለው አስተሳሰብ አይደለም።
የዚህ ትውልድ ሀላፊነት፤ ተፈጸሙ የሚባሉ ስህተቶች ካሉ አርሞ፤ አንባገነንነትንና አንባገነኖችን አስወግዶ፤ የመቻቻልና የመፈቃቀርን ባህል አዳብሮ፤ አገር በቀል ዲሞክራሲያዊ አስተዳደርን (የ ኦሮሞ ገዳ) ከዘመናዊ የዲሞክራሲ ያስተዳደር ብልሀት ጋር በማዋሀድ፤ ኢትዮጵያ ዜጎቿ በሙሉ በእኮልነት የሚበለጽጉባት የሚያበለጽጓት ሀገር፤ ለልጆቻችን የተሻለች የመኖሪያ ቦታ የምትሆን ምድር ማድረግ እንጂ፤ በግል ጥቅም በራስ ፍቅር ከተመረዘ ሰብእና በሚመነጭ ሰንካላ አስተሳሰብ፤ መቶ አመት ወደ ኋላ ተጉዘው መቃብር እየማሱ፤ የጥፋት ታሪክ እየቃረሙ፤ የገዢ ቡድን የሚፈጽመውን ስህተትና ወንጀል ያ ገዢ ከወጣበት ህዝብ ጋር እያቆራኙ፤ ህዝብን በመጥላት በሽታ ትውልድን እየመረዙ፤ በጠብና በጦርነት እየተተራመሰ ህይወቱን የሚያጨልም ዜጋ መፍጠር መለስ ዜናዊና መሰል ዘረኞች ተሸክመው የሚዞሩት እነሱኑ የሚያጠፋቸውን በሽታ ማስፋፋት ነው።
እርግጥ በአሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያ ህዝብ አጠቃላይ የፖለቲካ ንቃቱና የመልካም አስተዳደር ግንዛቤው እንመራሀለን ወይም ነጻ እናወጣሀለን እያሉ ከሚያደናቁሩት ጠባብ ቡድኖች እጅግ የቀደመበት ደረጃ ላይ ነው ያለው። ለፈጠራ ታሪክና ለውሸት ፕሮፓጋንዳ ሰለባ የሚሆንበት ዘመን እያለፈ ያለ ይመስላል።
ምርጫ 97 ላይ ፍጹም የሆነ የፖለቲካ ሽንፈት የደረሰበትና በወታደራዊ ሀይል እስከመጨረሻው ስልጣን ላይ ለመቆየት ቆርጦ የተነሳው የመለስ ዜናዊ ቡድን፤ ህዝቡ በዚያ ምርጫ ላይ የሳየው “የይበቃችኋል” አቋም ከላይ ባለው አንቀጽ የተጠቀሰውን እውነታ አስረድቷቸዋል።
መለስ ዜናዊ የኢትዮጵያን ህዝብ ሰላማዊ አብዮት፤ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር፤ ከ200 ሰው በላይ ገሎ ከ 800 በላይ አቁስሎ ከ30,000 በላይ ወህኒ አጉሮ በጦር ሀይል ከቀለበሰ በኋላ ሕዝቡ በድምጹ መርጧቸው በዝረራ ያሸነፉትን ተቃዋሚዎች በሀሰት ሲወነጅል፤ የኢትዮጵያን ህዝብ ድጋፍ ታርዞ፤ እርቃኑን ቆሞ፤ እራሱን አውላላ ሜዳ ላይ ሲያገኘው፤ የትግራይን ህዝብ (እራሱም ያልመረጠውን ሕዝብ) ከቀረው ህዝብ ሊያያይዝ፤ ሌብነትና ውሸት የማያልቅበት ሞገደኛ ሰው፡ ቅንጅቶች እንደጻፉት አድርጎ እራሱ ወረቀት ጽፎ እየበተነ ተቃዋሚዎች የዘር ማጽዳት ዘመቻ ሊያካሂዱብን ነው፤ እያለ ማስወራትና መወንጀል ጀመረ። የዘር ማጽዳቱ ዘመቻ እንደመጡ አካባቢ እራሳቸው በአማሮች ላይ ሊያንቀሳቅሱት ሞክረው አርሲ አርባጉጉ ላይ የኢትዮጵያ ህዝብ በታላቅ ጨዋነትና ትግስት በመቻቻል በመስዋእትነት አሳልፎታል። ኢትዮጵያ ውስጥ የሚጸዳ ዘር የለም። የሚጸዳ ቡድን አንጂ።
ህዝቡ በከፍተኛ ድምጽ ተቃዋሚዎችን በመምረጥ ለመለስ ዜናዊና ላስተሳሰቡ ያለውን ከፍተኛ ጥላቻ ከገለጸ በኋላ ከተቃዊሚዎች ጋር እያገናኘ ደጋግሞ የሚያነሳው የሩዋንዳው የዘር ፍጅት ዋነኛ ተዋናይ የነበረው ኢንተርሀምዌ የሚባለው ጦር፤ ከተቃዋሚዎች ጋር ሳይሆን ከራሱ ከመለስ ጋር ሊነሳ የሚገባው የጥፋት መልክተኛ ሰራዊት ነው። እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1994 ሩዋንዳ ውስጥ ሁቱ መራሹ ገዢ ቡድን አራት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ አንድ ሚሊዮን የሚሆኑ ቱትሲዎችንና ለዘብተኛ ሁቱዎችን በግፍ ያስጨፈጨፈው “ኢንተርሀምዌ“ የተባለውን ጦር አሰማርቶ ነበር። ይህ ጦር ወዶዘማቾች የሚበዙበት ባጭር ጊዜ የሬዲዮ ፕሮፓጋንዳ ዘመቻ የተቋቋመ ዓላማው በሁቱ መራሹ ገዢ ቡድን ላይ የተነሳውን ተቃውሞ ማፈን ነበር። መለስ ዜናዊ “አግአዚ” ብሎ ያሰማራው የህዝቡን ድምጽ ለማፈን ጭፍጨፋ ካካሄደው ጦር ጋር የሚመሳሰል ተልእኮ ያለው ነው። ልዩነታቸው አግአዚ መለስ ለዚሁ ዓላማ አስቀድሞ ተዘጋጅቶ ተደራጅቶ የተቀመጠ መሆኑና ኢንተርሀምዌ ባጭር ጊዜ በዘመቻ መልክ መደራጀቱ ነው።
እንደ አውሮፓውያኑ ዘመን አቆጣጠር በ1916 ዓ.ም. የበልጅግ ቅኝ ገዢዎች ወደ ሩዋንዳ ሲመጡ በመጀመሪያ ያደረጉት ነገር ሕዝቡ በዘሩ ተለይቶ መታወቂያ እንዲሰራለት ነበር። መለስ ዜናዊ በልጅግ ምን አንዳደረገች አንብቦ ይሆን መጀመሪያ ወደስልጣን እንደመጣ የኢትዮጵያ ህዝብ በየዘሩ መታወቂያ እንዲሰራለት ያደረገው? ባለፉት ሀያ ዓመታት በኢትዮጵያ ውስጥ ዜግነት የሚል መታወቂያ የለም። ብሄር ነው የሚለው መታወቂያ። በልጅግ ሀገሪቱን ታስተዳድር በነበረበት ዘመን ህዳጣኑን የቱትሲ ጎሳዎች በመምረጥ፤ የበላይ በማድረግ፤ ባገዛዙ እንዲሳተፉና ሌሎቹን ወገኖቻቸውን ወደታች በመርገጡ አንዲረዷት የዘመናዊ ትምህርቱን፤ የስልጣኑን፤ የስራውን አድል ሁሉ ለነሱ አድርጋ፤ እነሱም ተጠቃሚ በመሆናቸው ከቅኝ ገዢዎች ጋር ወርቅና ሰም ሆነው ወንድሞቻቸውን በመግፋትና በመበደል እያገዙ ራሳቸውን የበላይ አድርገው ሲኖሩ በወንድማማቾቹ ብዙሀን ሁቱዎችና ቱትሲዎች መካከል ቂምና ቁርሾ ስር ሰዶ ቀርቶ ኖሯል ።እናም በቱትሲዎች ሁኔታ የተናደዱት ሁቱዎች እኤአ በ1959 ላይ በቁጣ ገንፍለው በተፈጠረ ትርምስና ብጥብጥ ከ 15 ሺህ በላይ ቱትሲዎች አለቁ። ከ1962 ከነጻነት በኋላ ደግሞ ሁቱዎች በተራቸው ስልጣኑን ተቆጣጠሩት። ብድራቸውን ሊመልሱ እነሱም በተራቸው ቱትሲዎችን ይገፉ ይጨቁኑ ጀመር። ከዚያ በኋላ በዚሁ ምክንያት ከ200.000 በላይ ቱትሲዎች ወደየጎረቤት አገር ተሰደው ለመኖር ተገደዱ። ኋላ ላይ የሩዋንዳ አርበኞች ግንባር ብለው ተደራጁና በትጥቅ ትግል ወደ ሀገራችን እንመለሳለን ብለው ትግል ጀመሩ። ይሁንና ሁቱዎቹ ያኔም ለቱትሲዎች ስልጣን ለማጋራትም ሆነ ለማካፈል ፍቃደኛ ሳይሆኑ ቀሩና ውጊያ ቀጠለ። አሁን በኢትዮጵያ ስልጣኑንም ሆነ የሀገሪቱን ሀብት የተቆጣጠሩት ምልምል የመለስ ዜናዊ ዘሮች ሀብትም ስልጣንም የማጋራት ፍላጎት ምልክት ይታይባቸዋል?
በሩዋንዳውያኑ የርስ በርስ ጦርነት መካከል አፕሪል 6/94 የሩዋንዳው ፕሬዚዳንት ሀቢያ ሪማና ታንዛኒያ ውስጥ ከአማጽያኑ ተወካዮች ጋር ተነጋግረው ሲመለሱ ይበሩበት የነበረውን አውሮፕላን አማጽያኑ ካየር ላይ የመቱትና ሰውየው ይሞታሉ። ከዚያ ነበር የሁቱ ጽንፈኞች በበቀልና በቁጣ ተነሳስተው ለዘብተኛ ሁቱዎችንና ቱትሲዎችን ከምድር ገጽ ሊያጠፉ ጭፍጨፋ የጀመሩት። መለስ ዜናዊ ተመሳሳይ ሁኔታ ቢገጥመው ተከታዮቹ ምን ያደርጉ ይሆን ? ኢንተርሀምዌ የሚል ስያሜ የተሰጠው ሰራዊት ነበር የፍጅቱን ዘመቻ የመራው። አግአዚ የተባለው የመለስ ዜናዊ ገዳይ ሰራዊት በመለስ ላይ አንድ ነገር ቢፈጸም ምን ታሪክ ይሰራ ይሆን?
እዚህ ላይ ልብ ልንል የሚገባን ነገር የችግሩ ቁልፍ ስልጣንን ለማጋራት አለመፈለግ ወይም አለመዘጋጀት ነው። ያ የቱትሲዎች አቋም አሁን ወያኔ የያዘው አቋም አይነት ነው። ያ ቅኝ ገዢዎች ያደረጉት ህዳጣኑን ቱትሲዎች የበላይ ማድረግ አሁን መለስ ዜናዊ የተያያዘው ትግሬዎችን በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ የበላይ አድርጎ የማስቀመጥ ሙከራ አይነት ነው።
(ይቀጥላል ...)



