ለህዝብ መሞት ክብር ነው!
ዛሬ፣ ማክሰኞ፣ ሐምሌ ዐ5 2ዐዐ3 አዲስ አበባ ውስጥ ከሚታተመው አዲስ ወሬ ጋዜጣ ጋር አጭር ቃለምልልስ አድርጌያለኹ። የጋዜጣው ማኔጂንግ ኤዲተር፣ ዳንኤል ኃይሉ፣ ባለፈው ሰሞን ከመንገድ ላይ ታፍኖ ተደብድቧል፣ ቢሮው ተፈትሿል።
በጋዜጦች ላይ ያለው አደጋ እየተባባሰ ነው። ፅናታችን ግን ዝንፍ አትልም። ይሄ ነው የቃለምልልሱ ጭብጥ።
ድምፃችንን ለዴሞክራሲ ማሰማቱን እንቀጥላለን!!
ቃለ ምልልሱ እነሆ፡-
አዲስ ወሬ፡- ሰሞኑን በጋዜጠኝቱ ሥራ ላይ የተሰማሩ ወጣቶች ከፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጋር በጋራ በሽብርተኝነት ተጠርጥረው ተይዘዋል። ይህ ሁኔታ በነጻው ፕሬስ ላይ ድንጋጤን እንዲፈጠር የሚናገሩ በርካታ ወገኖች አሉ ያንተ ሀሳብ ምንድነው?
መልስ፡- ከዚህ በፊት የሆነውን ልንገርህ። ፀረ-ፕሬስ ዘመቻው በማሸማቀቅ ጀመረ። ማሸማቀቁ ወደ ክስ አደገ። ክሱ ወደ ጥፊና ቦክስ አደገ። ጥፊውና ቦክሱ ገልብጦ ወደ መግረፍ አደገ። ገልብጦ መግረፉ ወደ ጋዜጦች መዝጋት አደገ። ጋዜጦች መዝጋት ወደ ጋዜጦች ፍቃድ መከልከል አደገ። እዚህ ላይ ነው አሁን ያለነው፡፡ እርቃኑን የቀረ ጭቆና ላይ ደርሰናል፡፡
አሁን ደግሞ፣ ሁለት ጋዜጠኞችን በማሰር የተጀመረው ዘመቻ፤ የአዲስ ወሬን ሥራ አስኪያጅ ከመንገድ ላይ አፍኖ ወደ መደብደብ አድጓል፡፡ ይቀጥላል፡፡ በፕሬሱ ላይ ያለው ተፅእኖ የሀገር አቀፍ ጭቆና አንድ መገለጫ ነው፡፡ ፕሬስ ላይ ያለውን ችግር በአጠቃላይ ካለው የሥርዓት ችግር ነጥለን ልንመለከተው አንችልም፡፡ ፕሬሱ የነጻነት ደሴት መሆን አይችልም፡፡ የፕሬሱ ችግር መፍትሔ የሚያገኘው የዲሞክራሲ ጥያቄው ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ምላሽ ሲያገኝ ነው፡፡ እስከዚያው ድረስ መስዋዕትነት እየከፈልን መቀጠል አለብን፡፡ ታሪካችን የመስዋዕትነትና የጽናት ነው፡፡ አዲስ ነገር የለም፡፡ እስከመጨረሻው የመቀጠል ታሪካዊ አደራ አለብን፡፡ ከዚህ ድቅድቅ ካለ ጨለማ በኋላ ያለውን ንጋት ሁላችንም ላናየው እንችላለን፡፡ መንገድ ላይ መውደቅ አለ፡፡ የቆምነው ለተቀደሰ ዓላማ ስለሆነ ግን ይሄ ሊያስፈራን አይገባም፡፡ ከዚህ በኋላ መታሰር እድል ሊሆን ይችላል፡፡ ከእስር የባሰም ነገር ሊያጋጥመን ይችላል፡፡ ብዕራችን ግን መታጠፍ የለባትም፡፡ የአካል ሞት ፈርተን በመንፈስ መሞት የለብንም፡፡ ለእውነትና ለሕዝብ መሞት ትልቅ ክብር ነው፡፡ ፀጋ ነው፡፡ ጻዲቅነት ነው፡፡
አዲስ ወሬ፡- የአሸባሪነት ሕጉ በፕሬሱ ላይ የፈጠረው ተፅእኖ አለ? ካለ ብትገልፁልን?
መልስ፡- የፀረ-ሽብሩ ሕጉ ሆን ተብሎ ሰላማዊ ተቃዋሚዎችንም ጭምር ለመጨፍለቅ ታስቦ የወጣ ነው፡፡ ከቢንላደን በላይ ማን ነው አሸባሪ? በየትኛው ሀገር ነው የቢንላደንን መልዕክት ማስተላለፍ ወንጀል የሆነበት? ቢንላደንን መደገፍና ስለቢንላደን መዘገብ የተለዩ ነገሮች ናቸው፡፡ የኢትዮጵያው ፀረ-ሽብር ሕግ በዚህ ልዩነት ላይ በሩን የዘጋ ነው፡፡ ለዚህ ነው በዓለም አቀፉ ደረጃ የተወገዘው፡፡ አሁን እኮ ስለ ኦነግ፣ ግንቦት 7፣ ኦብነግ መጻፍ አይቻልም፡፡ በአደባባይ መወያየት አይቻልም፡፡ ይህ ማለት ግን ሕዝቡ ስለእነዚህ ድርጅቶች መወያየትና መነጋገር አቁሟል ማለት እንዳልሆነ አስረጂ አያስፈልግም፡፡ ስለድርጅቶቹ መጻፍና መወያየት ስላልተቻለ ተነው ይጠፋሉ ማለት አይደለም፡፡ በተቃራኒው የሀገሪቱ ችግሮች የሚባባሱበት ሁኔታ ነው የተፈጠረው፡፡ ወደ መፍትሔ እየሄድን አይደለም፡፡ ስለሽብር ተግባራት የመጻፍና የመወያየት ነፃነት ሊኖር ይገባል፡፡ በጽሑፍና በውይይት ላይ ምንም ዓይነት ገደብ ሊጣል አይገባም፡፡ ይሄ ነጻነት በፈረንጆቹ ሀገሮች ብቻ አይደለም ተከብሮ የሚገኘው፡፡ ባለፈው ሰሞን ሂላሪ ክሊንተን እዚህ አዲስ አበባ ውስጥ ባሰሙት ንግግር እንደገለጹት፣ በአብዛኛው የአፍሪካ ሀገራት ተከብሯል፡፡ እነዚህ የአፍሪካ ሀገራት እኛ ለነጻነት ያበቃናቸው ናቸው፡፡ ከኋላ ተነስተው ቀድመውናል፡፡ ይሄ ሊቆጨንም ሊያሳፍረንም ይገባል፡፡ በምንም መለኪያ ከአፍሪካ ሀገራት አናንስም፡፡ እኛ ጋር የጎደለው የገዢዎቻችን ቅንነት ብቻ ነው፡፡ የመከራችን ምንጭ ራስ ወዳድነታቸው ነው፡፡
አዲስ ወሬ፡- ኢትዮጵያ ወደሱዳን የሰላም አስከባሪ ሠራዊት ከላኩት አገራት ተርታ ተሰልፋለች፡፡ በሁለቱ አገራት መካከል ለሚኖረው ግንኙነትም ሆነ አገሪቱ በዓለም አቀፍ መልኳ ምን ውጤት ያስገኝላታል?
መልስ፡- ሠራዊት ለመላክ እየቀረበ ያለውን ምክንያት አስተውል፡፡ «ሱዳን ውስጥ ጦርነት ከተነሳ ወደ ኢትዮጵያ ሊዛመት ይችላል» ነው የመንግስት ስጋት፡፡ ኬኒያ ከሱዳን ጋር ትደናበራለች፡፡ ይሄ ሥጋት ግን የላትም፡፡ ለምን? ለጦርነት የሚዳርግ ፖለቲካ ስለሌለ፡፡ ሌላ ምስጢር የለውም፡፡ በኬኒያ ዲሞክራሲ አለ፡፡ ስለዚህ፤ አይሰጉም፡፡ በኢትዮጵያ ግን የእርስ በእርስ ጦርነት እንዳይለኮስ ኢሕአዴግ አንድ ጊዜ ወደ ሶማሊያ ሌላ ጊዜ ወደ ሱዳን ይሮጣል፡ ምንጩን ማድረቅ የሚቻለው ግን እዚሁ ኢትዮጵያ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ጭቆና እስከሌለ ድረስ የጎረቤት ሀገር እርስ በእርስ ጦርነት ወደሀገራችን ሊዛመት አይችልም፡፡ ቢበዛ የሚያሰጋን ስደተኛ ነው፡፡ እሱ ደግሞ የዓለም አቀፉ ሕብረተሰብ ሸክም ነው የሚሆነው፡፡ ስደተኞች የእኛን ወጪ አይፈልጉም፡፡ የኢትዮጵያን ፀጥታ ወታደር ወደ ጎረቤት ሀገሮች በማዝመት ዋስትና መስጠት አይቻልም፡፡ ዋስትናው ዲሞክራሲ ነው፡፡ ዋስትናው ጭቆናንና አፈናን ማጥፋት ነው፡ ይሄ ነው እውነተኛ ሰላም የሚመጣው፡፡ እስከዚያው የዛፍ ላይ እንቅልፍ ነው የሚሆነው፡፡ ዛፍ ላይ ሆነህ እንቅልፍን ትታገለዋለህ፤ መጨረሻ ላይ ግን ያሸንፍሃል፡፡ ያኔ መውደቅ ይመጣል፡፡
ፀሐፊውን ለማግኘት This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.



