ግርማ ካሣ

ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ልትፍታ እንደምትችል ከአንዳንድ ምንጮች አንዳንድ ፍንጮች ያገነሁት ከአንድ ሳምንት በፊት ነበር። እንደዚያም ሆኖ ግን ያለፈው ዓመት አዲስ ዓመት መግቢያ አካባቢ ትፈታለች የሚል ወሬ ተወርቶ ስላልተፈታች፣ በዚህ ዓመትም ሙሉ ለሙሉ ትፈታለች የሚል ተስፋ በልቤ አልነበረም። በእርግጠኝነት እንደምትፈታ ድረ ገጾች ማክሰኞ መስከረም 26 ቀን 2002 ዓ.ም ዘገባ እስኪያወጡ ድረስ፣ በአይምሮዬ ውስጥ ጥያቄው ”መቼ ይሆን ነው የምትፈታው? ” የሚለው ነበር።

 

ማክሰኞ ማታ አቡጊዳ፣ ኢትዮጵያ ሪቪው ወ/ት ብርቱካን ረቡዕ እንደምትፈታ ለአንባቢያናቸው አሳወቁ። ”የሰማነው ወሬ ብቻ ሆኖ አልቀረም ማለት ነው” በሚል ውስጤ ተደሰተ። ጥያቄዬም ተለወጠ። ”መቼ ይሆናል የምትፈታው?” ከሚለው ”ስትወጣ ጤናዋ እንዴት ይሆን?” ወደሚለው ዞረ።

 

በሀገራችን በርካታ ታስረው የተፈቱ የፖለቲካ እስረኞችን እናውቃለን። ዶ/ር ታዬ ወልደሰማያት፣ አቶ ታምራት ላይኔ፣ አቶ ስየ አብርሃ የመሳሰሉ … እነዚህ እስረኞች በርከት ላሉ ዓመታት ቢታሰሩም፣ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ በሁለት ዓመት እሥራቷ የደረሰባት አይነት ግፍና ጭካኔ ግን ብዙ፣ ባልሳሳት ብዙ ያዩ አይመስለኝም።

 

ወ/ት ብርቱካን ግን ለስድስት ወራት ያህል ሁለት ሜትር በሁለት ሜትር ባለ፣ ጨለማ ቤት ለብቻዋ እንድትቀመጥ ተደርጋለች። ፍርድ ቤት ውሳኔ ወስኖላትም እንኳን በወዳጅ ዘመድ፣ በጠበቃ፣ በመንፈሳዊ አባት እንዳትጎበኝ የአቶ መለስ አገዛዝ አግዶ ነበር። በሳምንት አንድ ቀን የዕድሜ ባለጠጋ እናቷ ለ15 ደቂቃ ሲጎበኟት፣ እናትና ልጅ የሚነጋገሩትን ሙሉ በሙሉ በዚያ የምትቆም ከፍተኛ የደህንነት ጠባቂ ታዳምጣለች። ካስፈለገም ንግግራቸውን ታስቆማለች። በዚህ አይነት ሁኔታ ነው እንግዲህ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ከውጭው ዓለም ፍጹም እንድትነጠል ተደርጋ የነበረው።

 

የብርቱካን ወዳጅ ዘመዶች እንዳይጎበኟት ተከልክለው ባለበት ሁኔታ እነ ፓስተር (ካድሬ) ዳንዔል ግን በየጊዜው ይጎበኟት ነበር። እነዚህ የሀገር ሽማግሌ ተብዬዎች ከመጀመሪያውኑ እውነትን ቢናገሩ ኖሮ ይሄ ሁሉ ችግር አይመጣም ነበር። ነገር ግን የመለስ አገዛዝ መልእክተኛ ሆነው ”ደጋፊ የለሽም። ታግሎ ከመለስ እጅ የሚያስወጣሽ የለም። የውጭ ሀገር ሰዎች አያስፈቱሽም። ደጋፊዎችሽም ረስተውሻል። ድርጅትሽም ተከፋፍሏል። እናትሽና ልጅሽ እየተሰቃዩ ናቸው። ዝም ብለሽ መለስ የሚለውን አድርጊና ተፈቼ … ወዘተረፈ …” እያሉ በተዘዋዋሪ መንገድ የአቶ መለስ ግራ እጅ በመሆን፣ አይምሮዋን ሲሰብሩ፣ ልቧን ሲያሟሽሹ ነበር የከረሙት።

 

በአጠቃላይ ታይቶ በማይታወቅና ማንም ኢትዮጵያዊ ሊረሳው በፍጹም በማይችል ሁኔታ ወይዘሪት ብርቱካን ከፍተኛ የሆነ የስነ-ልቦና ቶርቸር ለሁለት ዓመታት በመለስ አምባገነን አገዛዝ የተፈጸመባት ሴት ናት። ታዲያ በዚህ ሁኔታ ጤነኛ ሆና ትወጣለች ብሎ ማን ሊጠብቅ ይችላል? ለዚህ ም ነው እኔም ሆነ አብዛኞቻችን ትልቅ ጭንቀት ላይ የነበርነው።

 

የመፈቻዋ ሰዓት ደረሰና መፈታቷን ሰማን። ሄደው የጎበኟት ወገኖች ደህና እንደሆነች ደውለው ነገሩን። ጥቂት ሰዓታት እንደቆየን የጀርመን ድምጽ ራዲዮ ላይ ድምጿን ሰማሁ። ፎቶግራፎቿንም በድረ ገጾች አየሁ። ፈገግታ ይታይባታል። ድምጿ የጠራ ነው። ደህና ትመስላለች። እጆቼን ወደ ሰማይ አነሳሁኝና ተዓምረኛውን እግዚአብሔር አመሰገንኩት። በማንም ሌላ እስረኛ ላይ ያልደረሰ ግፍ ደርሶባትም የምታመልከው አምላክ ስለጠበቃት ደህና ሆና ወጣች።

 

”እግዚአብሔር ከኛ ጋር ባይሆን ሰዎች(ክፉ ሰዎች) በተነሱብን ጊዜ፣ ሕያዋን ሳለን በዋጡን ነበር። ውሃም ባሰጠመን ነበር ..ለጠላቶቻችን ንክሻ ያላደረገን እግዚአብሔር ይመስገን” ተብሎ በመዝሙረ ዳዊት እንደተጻፈ፣ በርግጥ እግዚአብሔር ከክፉዎች ንክሻ ጠብቆ በጤና እህታችን አውጥቷታል።

 

ሌላው የሚያስገርመውና የሚያሳዝነው የአቶ መለስ ዜናዊ ቴሌቭዥን ከወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ጋር አደረኩት ስላለው ቃለ መጠይቅ ነው። ብርቱካን ፈረመች ስለተባለውም ወረቅት ከኢቲቪ ሪፖርተር ሰማን። እነ አቶ መለስ እርሷን እንደ ወንጀለኛ እነርሱን ደግሞ እንደ ጻድቅ አድርገው ለማሳየት ሞክረዋል። እነርሱ ደጎች፣ እነርሱ ቸሮች፣ እነርሱ እውነተኞች፣ እነርሱ መሃሪዎች፣ እነርሱ ለሕግ ተቆርቋሪዎች፣ ወ/ት ብርቱካን ደግሞ ወንጀለኛ፣ ይቅርታ የተደረገላት፣ ያጠፋች፣ የዋሸች፣ ያጭበረበረች እንደሆነች ሊነግሩን ይሞክራሉ።

 

ከአራት ኪሎ ቤተመንግስት ጓዳ ውጭ፣ይህ አይነቱን ርካሽ የመለስ ቴሌቭዥንን ዘገባ ቦታ ሰጥቶት የሚያወራውም ሆነ የሚያስበው ኢትዮጵያዊ ይኖራል ብዬ አላስብም። ”ስንተዋወቅ አንተናናቅ” እንደተባለው፣ እንደው የኢትዮጵያ ህዝብ እያወቃቸው፣ እራሳቸውን ይልቅ ባያስገምቱ ይሻላቸው ነበር።

 

ወ/ት ብርቱካን በነጻነት መናገር የምትችልበት ጊዜም ይመጣል። ያኔ ላለፉት ሁለት ዓመታት የተደረገባትን ግፍ በሙሉ ትገልጸዋለች። (አሁንም በመጠኑ መግለጽ ጀምራለች። ለምሳሌ ለቢቢሲ ጋዜጠኛ ስለ እሥሯ ስትናገር “Horrible” ነበር ያላችው) በርሷም ላይ ኢሰብዓዊና ኢፍትሃዊ ጭካኔ ሲፈጽሙ የነበሩ ሁሉ በርግጥ ተጠያቂ የሚሆኑበት ጊዜ ይመጣል።

 

ለማጠቃለል ያህል በኔም ሆነ በአብዛኛው ኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ አሉ ብዬ የማምናቸው ጥቂት ትላልቅ ቁም ነገሮችን ልዘርዝ።

 

አንደኛው ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ በእሥር ቤት በቶርቸር ውስጥ ሆና ለተናገረችውም ሆነ ለፈረመችው ማናቸውም ነገር፣ አሁን ያለው ትውልድ ብቻ ሳይሆን የወደፊቱ ትውልድ ይጠይቃታል ብዬ አላስብም። ቶርቸር የተደረገ ሰው በዚያን ወቅት እርሱ አይደለም። በየትኛውም የሰለጠነ ዓለም በቶርቸር የተገኘ መረጃ ተቀባይነት የለውም።

 

ሁለተኛ በየትም መንገድ ይሁን በየትም መፈታቷ ለልጇ፣ ለቤተሰቧም ሆነ ለሀገር ትልቅ ጥቅም አለው። አሜሪካኖች ለነጻነታቸው ሲዋጉ በወቅቱ ጠንካራ በነበረው የእንግሊዝ ጦር ክፉኛ ጉዳት ደረሰባቸው። የአሜሪካን ጦር መሪ ጆርጅ ዋሺንግተን ወታደሮቹ እንዲያሸገሽጉ አዘዘ። (ፈረንጆች tactical retreat ይሉታል) ብዙም አልቆየም እንግሊዞች ተሸነፉ። አሜሪካም ነጻ ወጣች።

 

የወ/ት ብርቱካን ውሳኔም እንደ ጆርጅ ዋሺንግተን ብስለትና ማስተዋል ያለበት ውሳኔ ነው ብዬ አስባለሁ። እርሷ ተጎዳች እንጂ በመታሰሯ ሊገኝ የሚችለው የፖለቲካ ጥቅም ተገኝቷል። ብቻዋን በቃሊቲ ታስራ፣ የመለስን አገዛዝ አጋልጣለች። አቶ መለስ በሄደበት ቦታ ሁሉ እንዲያቀረቅር አድርገዋለች። በዓለም አቀፍ ደረጃ እርሱ ከነኪሚል ሱንግና ካስትሮ ምድብ ሲገባ፣ ሲዋረድ፣ እርሷ ከነአንሳን ሱንኪና ማንዴላ ጋር ተመድባለች። (በቅርቡ ለሳካሮቭ ሽልማት እጩ መሆኗ እራሱ አንድ ትልቅ ምስክርነት ነው) በሚሊዮን የሚቆጠሩ ታጋዮችን አፍርታለች።

 

ነገር ግን እስከአሁን መታሰሯ ያገኘው የፖለቲካ ጥቅም እንደተጠበቀ ሆኖ ከአሁን በኋላ ግን አሁን ከተገኘው የበለጠ ሌላ ጥቅም ይገኛል ብዬ አላስብም። በመሆኑም ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ የወሰደችው እርምጃ ጊዜው የሚጠይቀው፣ ከአንድ መሪ የሚጠበቅ ጠቃሚ እርምጃ ነው ብዬ ነው የምወስደው።

 

እንግዲህ በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ የምትኖር ኢትዮጵያዊ ሁሉ እግዚአብሔር ቆራጥ፣ ጀግና ዳግማዊት ጣይቱ ቡጥል የሆነች መሪ ሰጥቶሃል። ካወቅክበት ይሄንን ጊዜ ተጠቀም። መሪዎችህን ተከትለህ ነጻ ውጣ። የኢትዮጵያ ህዝብ ሆይ እንሆ መሪህ!!!!!

 

አንዲት ሴት ይህን ያህል አምባገነኖችን ብቻዋን ካነቃነቀች፣ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ኩራቱን ውጦ፣ ከፍርሃትና ከተስፋ መቁረጥ ተላቆ፣ የድርሻውን ቢያበረክት ለኢትዮጵያ አይደለም፣ ለአፍሪካ ሁሉ መብቃት የምንችል ታላቅ ህዝብ መሆን የምንችል ነን። ብርቱካን ሚደቅሳ አንዲት ሴት ናት። ብቻዋን ሀገር መለወጥ አትችልም። ሰው ናትና ገደብ አላት። ከኛ ጋር ሆና ግን፣ አብራን ብዙ መሄድ ትችላለች።


ግርማ ካሣ

This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.  

መስከረም 28 ቀን 2003 ዓ.ም.

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ