ጯኺ መፈክሮች እና ውጤቶቻቸው
ታደሰ ብሩ
መግቢያ
“የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የግብርናም የኢንዱስትሪም ሳይሆን የመፈክር ኢኮኖሚ” ነው እያልኩ ስቀልድ ኖሬአለሁ። አሁን አሁን ግን ምፀቱና ቀልዱ ቀርቶ የምር “የመፈክር ኢኮኖሚ የሚባል ነገር ይኖር ይሆን?” እያልኩ ማሰላሰል ጀምሬአለሁ። ይኸ ጉዳይ በአንድ ጋዜጣ በቀልድ መልክ መነሳቱ ነገሩ ሌሎችንም ሰዎች እያሳሰበ መሆኑን ተረድቻለሁ።
የመፈክር ኢኮኖሚ የሚባል ነገር ካለ መሠረታዊ መርኁ - መፈክሮች ከሚገባ በላይ ጮኸው ካልተሳኩ ተቃራኒው ይፈጸማል - የሚል መሆን ይኖርበታል።
በጥሩ ሁኔታ የተከሸነ መፈክር ለአጭር ጊዜ ይጠቅም ይሆናል፤ ያነቃቃል፤ ያሟሙቃል። ሆኖም ግን የተጠበቀው ውጤት ሳይገኝ መፈክሩ “መወየብ” ከጀመረ ፌዝ ይከተላል። አንሰራርቶ የነበረው ተስፋ ያሽቆለቁላል። የተስፋ መቁረጥ እና የአቅመ ቢስነት ስሜት ይነግሳሉ። ስለሆነም መፈክር የአጭር ጊዜ ጠቀሜታ ቢኖረውም፤ ስኬታማ ካልሆነ የረዥም ጊዜ ጉዳቱ ከፍተኛ ነው።
ዕቅድም ቢሆን እንደዚሁ ነው። ጥሩ ዕቅድ ቢያንስ ሦስት ነገሮችን ማሟላት ይኖርበታል።
1ኛ) አስቸጋሪ ቢሆንም እንኳን ጥረት ከተደረገ ሊሳካ የሚችል መሆን ይኖርበታል፣
2ኛ) ዕቅዱ ተፈፃሚ ለሚሆንበት ማኅበረሰብም ሆነ ተፈጥሮ ተስማሚ መሆን ይገባዋል፤ እና
3ኛ) ዕቅዱ በአብዛኛው አስፈፃሚ ዘንድ ተቀባይነት ያገኘ ሊሆን ይገባዋል። አለበዚያ ዕቅድም ሆነ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ለጊዜው ሞቅ ሞቅ ቢያደርጉም በረዥም ጊዜ ግን ጉዳት አላቸው።
አንዳንድ በግል ያስተዋልኳቸውን ትናንሽ ምሳሌዎችን ላንሳ። ትላልቆቹን እናንተ ጨምሩልኝ።
አረንጓዴው ምንጣፍ
ተወልጄ ያደግሁባት የገጠር መንደር ውስጥ አቧራማ ገደል አለ። በደርግ ጊዜ የወረዳችን አስተዳዳሪ “ኢትዮጵያን አረንጓዴ ምንጣፍ እናለብሳለን!” የሚለውን አብዮታዊ መፈክር በወረዳ ደረጃ ተግባራዊ ለማድረግ ከመረጣቸው ቦታዎች አንዱ የትውልድ መንደሬን ነበር። በዚህም ምክንያት የእኛ የተማሪዎች ብቻ ሳይሆን የመምህሮቻችንና የወላጆቻችንም የበርካታ ቀናት ጉልበት እዚያ ገደል ላይ ፈሰሰ። ያ ቦታ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ጥቅጥቅ ያለ ደን እንደሚሆን አስተዳዳሪያችንም አንዳንድ መምህሮቻችንም በእርግጠኝነት ነግረውን ነበር።
ይኽ ከሆነ ከሃያ ዓመታት በኋላ፤ የዛሬ ሁለት ዓመት ተኩል አካባቢ፤ በአፈር ጥበቃ ሥራ ላይ የተሠማራ የበጎ አድራጎት ድርጅት ባለሙያ ጋር በዚያ በኩል ስናልፍ፤ ይኽ ቦታ በሱ ፕሮጀክት ውስጥ ለምን እንዳልተካተተ እንደዋዛ ጠየቅሁት። የሥራውን አስቸጋሪነት፣ የገደሉን በፍጥነት እየሰፋ መምጣት እና በአካባቢው መንደሮች ላይ ስላንዣበበው አደጋ በሰፊው ተረከልኝ። ሌላው ቀርቶ ቀላል የጎርፍ ክትሮችን በመገንባት የአፈሩን መሸርሸር ለመቀነስ አስቦ እንዳልተሳካለት አወጋኝ። ለምን? “ድሮ እዚህ ቦታ ላይ እጅግ ብዙ ጉልበት ፈሷል፤ ስለዚህ ቦታ ሲነሳ የሰፈሩ ሰው ሁሉ ያንገሸግሸዋል። ይህ ሥራ የማኅበረሰቡ ሙሉ ድጋፍ ሳይኖረው ከተሠራ ነገ ተመልሶ ያው ነው” አለኝ። እዚህ ቦታ የኔም የልጅነት ጉልበት መፍሰሱን ሳወጋው የመገረም ተራው የሱ ሆነ። “ከዚያ ሁሉ ችግኝ አንድ እንኳን አለመጽደቁን እያየህ እንዴት ተስፋ ሊኖርህ ቻለ?” ሲል ጠየቀኝ። “ለችግኝ” ተከላ መሬቱ መቆፋፈሩ የአፈሩን መሸርሸር እንዳፋጠነው ነገረኝ። “ከሁሉም የከፋው ጉዳት ግን ሰውን ተስፋ ማስቆረጡ ነው” አለኝ።
በቀን ሦስቴ ስለመመገብ አቶ መለስ ዜናዊ በለስ ቀንቷቸው አናታችን ላይ ከተቀመጠበት ጊዜ ጀምሮ ሀገሪቷን የሚመራት በመፈክር እና በጉራ ነው። “በአምስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ኢትዮጵያዊያን በቀን ሦስት ጊዜ ይበላሉ” ካለ በኋላ በነበሩት ጥቂት ዓመታት የነበረው መነቃቃት የሚያበረታታ ነበር። እንዲያውም በአንድ የአዝመራ ወቅት ጥሩ የበቆሎ ምርት ተመረተና የምግብ እህልን ኤክስፖርት ማድረጋችን ተነገረን። ግን ጥቂት ቆይቶ መፈክሩ ወየበና ፈጣን የቁልቁለት ጉዞ ተጀመረ።
ያ የተስፋ መፈክር ከተነገረ ሃያ ዓመት ሊደፍን ቢቃረብም ዛሬም እውነት አልሆነም። ዛሬ የምንገኘው መፈክሩ ሲነገር ከነበርንበት ሁኔታ በባሰ ሁኔታ ላይ መሆኑ እጅግ አሳዛኝ ነው። ይህ ፉከራ ያሸማቀቃቸው ጠንቃቃ የሆኑ ምሁራን ዛሬ ኢትዮጵያዊያን ሦስቴ መቼ መመገብ እንደሚችሉ ለመገመት እንኳን አይደፍሩም። እንዲያውም “ተዓምር ካልተፈጠረ በስተቀር በእኔ ዕድሜ እዚህ ደረጃ ላይ አንደርስም” ያሉኝ ሰዎች አጋጥመውኛል።
ኢትዮጵያ ለዓለም ዋንጫ
የዛሬ ስምንት ዓመት አካባቢ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአራት ዓመት ጊዜ ውስጥ ለአፍሪቃ ዋንጫ፤ በሰባት ዓመት ውስጥ ደግሞ ለዓለም ዋንጫ ውድድር ይሰለፋል ተብሎ ነበር። በእርግጥ የዚያን ሰሞን ትንሽ መነቃቃት ነገር ነበር። ትንሽ ቆይቶ 4 ለባዶ እና 5 ለዜሮ መሸነፍ ለመደበት። አሁን አሁንማ የመሸነፍን “ዕድል” እንኳን ማግኘት ትልቅ ነገር ሆኗል።
የጥይት ድምፅ
አቶ መለስ ከ15 ዓመት በፊት “ከእንግዲህ ከሰሜኑ የሀገራችን ክፍል የጥይት ድምፅ የሚሰማው ለደስታ ብቻ ነው” ብለው ነበር ይባላል። ስለሰሜኑ ክፍል ለይተው የተናገሩት ሌላው የሀገሪቱ ክፍል ድሮም ሠላም ነበር ብለው ስለሚያምኑ ይሆናል። ያኔ በጦርነት የተጎዳው የሰሜኑ ክፍል ነው የሚል ትንታኔም ይሰጥ ነበር። መፈክሩ በእርግጥ ለጥቂት ዓመታት ሠራ። ኢትዮጵያ ከዘመናት ጦርነት ትንሽ እፎይታን አገኘት። ከዚያ በኋላ የሆነውን የምናውቀው ነው። አሁን ሰሜን ኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ የአፍሪካ ቀንድ እሳት ውስጥ የተወረወረ ቋንጣ ሁናለች።
ሻማ ለልደት
ግልገል ጊቤ በተመረቀ ሰሞን “ከአሁን በኋላ ሻማ የሚበራው ለልደት ነው” አሉ - “አቶ እንደልቡ”። ለጥቂት ቀናት መብራት በሽ ሆነ። ቀጥሎ ግን የመብራት መጥፋት ከቀድሞው የባሰ ሆነ። ቀድሞ ቢያንስ መብራት የሚጠፋበት ቀን በቅድሚያ ይታወቅ ነበር፤ ኋላ ላይ ግን ያም ቅንጦት ሆነ። አዲስ አበባ ውስጥ ሥራው መብራትና ስልክ የሚያሻው ሰው ወይ ጄኔሬተር መግዛት አሊያም በከተማው አራት የተለያዩ ቦታዎች ቢሮ ማዘጋጀት ነበረበት - አንደኛው ሰፈር መብራት ሲጠፋ እሌላኛው ቢሮ ለመሄድ።
የመረጃ መረብ ሽፋን
ስለስኩል ኔት፣ ወረዳ ኔት እና ኮኦፕሬቲቭ ኔት ያልተወራ የለም። በአንድ ወቅት በትምህርት ቤቶች መምህራንን “በቴክኖሎጂ” ስለመተካት ሁሉ ተወርቷል። ስለሞባይል እና ኢንተርኔት ሽፋንም ብዙ ጉራ ሰምተናል።
እየሆነ ያለው ግን የተባለውን ተቃራኒ ነው። ትምህርት ቤቶች እንኳንስ ኔትዎርክ፤ ቾክ እንኳን በወጉ ማግኘት አልቻሉም። ወረዳዎች ለወረቀትና እስክሪብቶ እንኳን የእርዳታ ድርጅቶችን ድጋፍ ይሻሉ። በተንቀሳቃች ስልክና ኢንተርኔት አቅርቦት የዓለም ጭራ ነን።
አከርካሪ ስለመስበር
ሼህ ሸሪፍ አህመድ መቋዲሾ ውስጥ ሆኖ ዝናር አንገቱና ወገቡ ላይ ጠምጥሞ ኢትዮጵያ ላይ ሲዝት፤ አቶ መለስ የኢትዮጵያውያንንና የአሜሪካ መንግሥትን ትኩረት የሚስብ መልካም አጋጣሚ አገኙ። በሼህ ሸሪፍ አህመድ ላይ ለመዝመት የፓርላማውን ሙሉ ድጋፍ ለማግኘት የጣረ ቢሆንም፤ የተሳካላቸው የእነ ልደቱን ድጋፍ ማግኘት ብቻ ነበር። በዚህም ምክንያት ተቃዋሚዎች “ታሪካዊ ስህተት” መፈጸማቸውን እልህ እየተናነቃቸው ተናገሩ። አቶ መለስ ጦራቸውን አዘመቱ። በሣምንት ጊዜ ውስጥ ሼህ ሸሪፍን ከሞቃዲሾ አባረው መላውን ሶማሊያ ተቆጣጠሩ። “ድል አድራጊው” አቶ መለስ በሁለተኛው ሣምንት ፓርላማ ሲገኙ በፓርቲው አባላት የጀግና አቀባበል ተደረገላቸው። ቀጥሎም “ግዳጃችንን በድል አጠናቀቅን! የአክራሪዎችን አከርካሪ ሰበርን” አሉ። አያይዘውም ለኤርትራ መንግሥትና ለኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች ጥብቅ ማስጠንቀቂያ ሰጡ። መልዕክቱም “እኛ እንዲህ ነህ!!!” የሚል ነበር። ወታደሮቹም “የተራረፉ ቃርሚያዎችን ለቃቅመው” በቅርቡ እንደሚመለሱ በልበ ሙሉነት ተናገሩ።
ሆኖም የአቶ መለስ ወታደሮች ሳይለመሱ ቀናት፣ ሣምንታት፣ ወራት፣ አለፉ። ዓመት ሞላው። ሞቃዲሾ ውስጥ አፍንጫው ስር ከሼህ ሸሪፍ አህመድ የባሱ አክራሪዎች ተፈጠሩና ከእነሱ አንፃር ሲታይ ሼህ ሸሪፍ ለስላሳ ሆኖ ተገኘ። አሁን ሼህ ሸሪፍ “ለዘብተኛ ኃይል” ተብሎ በመለስና አሜሪካ እርዳታ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሆነ። ክፋቱ የኃያላን ሁሉ ድጋፍ ቢጎርፍለትም መንግሥቱ ገና አልጠናም። አቶ መለስ፣ ጦራቸው የማንን አከርካሪ እንደሰበረ እስካሁን የደረሰበት ያለ አይመስለኝም።
አጠቃላይ ግንዛቤ
የወያኔ ዕቅዶች መፈክሮች ናቸው - ለዚያውም ተመልሰው የሚባርቁ መፈክሮች።
“ድህነትን ተረት እናደርጋለን!!!” የሚለው ዝነኛ መፈክር ለብዙ ሰው አስቂኝ እንደሆነ እገምታለሁ። ለእኔ ግን አስደንጋጭና አደገኛም ነው። ለመጀመሪያ ጊዜ ይህን መፈክር ያየሁት ካዛንቺስ ዑራሄል ቤተክርስቲያን አጠገብ ነበር። ያ ሰፈር ደግሞ ከድህነት ጋር ታርቀውና ተስማምተው የሚኖሩ “የኔ ብጤዎች” የበዙበት ቦታ ነው። እኔ እንደታዘብኩት እዚያ ያሉ “የኔ ብጤዎች” በልመና “ጥበብ” ለመካን ጥረት ያደርጋሉ። ከመካከላቸው ነቃ ያሉት የውጭ ሀገር ሰው ሲያጋጥማቸው በእንግሊዝኛ ይለምናሉ፤ የበረቱት ፈረሳይኛም ይሞካክራሉ።
አዲሱ መፈክር በድሆቹ ውስጥ ያሉትን ጥቂት “ኢንተርፕሪነሮችን” ያነሳሳ ይሆናል። ምናልባትም መፈክሩ በተራቀቀ ልመና “ድህነትን ተረት” ስለማድረግ ያሳስባቸው ይሆናል። መፍክሩ “ልማታዊነትን ያሳስባል” ብለን ድርቅ ብንል እንኳን የተለየ ነገር አናገኝም። መፈክሩ የተሰቀለላቸው ሰዎች መፈክሩ እሚጠይቀው እርቀት ድረስ የመጓዝ አቅም የላቸውም። የተፍጨረጨሩት ወድቀው ከመነሳታቸው በፊት መፈክሩ ይወይባል፤ እናም የወየበው መፈክር ይስቅባቸዋል። እነሱን ያዩ ሌሎች ድሆች “ይችንም አታሳጣኝ” ይላሉ።
እንዴት ተግባራዊ እንደሚሆን በሚገባን ቋንቋ ሳይነገረን “ድህነትን ተረት እናደርጋለን” የሚለውን መፈክር ማጮህ ድህነትን የማባባስ አደጋ አለው።
በተመሳሳይም ሰሞኑን የኢትዮጵያ ራዲዮና ቴሌቪዥን የተለቀቁበት “የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን” ፉከራ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ የባሰ ግትር ያደርገው ይሆን? ብዬ እፈራለሁ። የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከሚታወቅባቸው አስር ያህል ባህሪያት ውስጥ አንዱ መዋቅራዊ ግትርነት (structural rigidity) ነው። በአለፉት አምሳ ዓመታት ውስጥ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ያመጣው መሠረታዊ ለውጥ የለም። አንድ አረጋዊ ኢኮኖሚስት “የልጅ ልጄ Ethiopian Economy የተባለውን ኮርስ በኔ ደብተር አጥንታ ተፈትና ’A’ አመጣች” ብለዋል። የተናገሩት ሊሆን የሚችል ነገር ነው። የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ጥናት ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ዋና ዋና የማክሮኢኮኖሚ ምጣኔዎች አልተቀየሩም። “የኢኮኖሚው ግማሽ ግብርና፤ ኢንዱስትሪው ከ15 በመቶ በታች፤ 85 በመቶ የሚሆነው ህዝብ የሚተዳደረው በግብርና ነው፣ ...” መባል ከጀመረ ስንት ዓመቱ ነው?! እናም አረጋዊው ኢኮኖሚስት ያሉት ሊሆን የሚችል ነገር ነው። በእሳቸውና በልጅ ልጃቸው ጊዜ የተቀየረ ነገር ቢኖር የህዝብ ብዛት ብቻ ነው።
እንዲያው ለነገሩ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥ ማምጣቱ ስንቴ ነበር የተነገረን? የንጉሡ የመጨረሻው የአምስት ዓመት ዕቅድ ዋነኛ ግቡ መዋቅራዊ ለውጥ ማምጣት ነበር፤ ”አምጥቷል” ተባለ ግን ውሸት ነበር። የደርግ የአስር ዓመት ዕቅድ ዋነኛ ግቡ መዋቅራዊ ለውጥ ነበር፤ ”አምጥቷል!” ተባለ። እንዲያውም ያኔ ኢኮኖሚው ወደ ሶሻሊስታዊ ኢኮኖሚ መቀየሩ በመቶኛ አኀዝ ሳይቀር ተሰልቶ ተነግሮናል፤ ግን ውሸት ነበር። ወያኔ PASDEP እያለ በሚጠራቸው ተከታታይ ዕቅዶች አንዴ ’ግብርና-መር’ ሌላ ጊዜ ደግሞ ’ገበያ-መር’ እያለ ኢኮኖሚው መዋቅራዊ ለውጥ ማምጣቱን ነግሮናል፤ ግን ይህም ውሸት ነበር። ከላይ የተዘረዘሩት ለውጦች ከንብረት ባለቤትነት ውጭ ያመጡት መዋቅራዊ ለውጥ የለም። ያልታደለው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ መፈክሮች ይቀያየሩበታል እንጂ እሱ ፍንክችም አይላት። ለመፎከርና ለመፎገር ካልሆነ በስተቀር የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ለመቀየር የተነሳሳ መንግሥት እስካሁን አልተገኘም። እንዲያውም ከእያንዳንዱ ፉከራ በኋላ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እየባሰበት መጥቷል።
እናም ያሁኑ “ትራስፎርሜሽን” በድል ከተጠናቀቀ የሚሆነውን መገመት አያቅትም። ግብርናው የኢኮኖሚው ግማሽ ይሆናል፤ ሆኖም ባለመሬቶቹና ባለምርቶቹ የቻይና መንግሥትና ህንዳዊያን ይሆናሉ። የኢንዱስትሪው ድርሻ ያው እንደድሮው ከ15 በመቶ ያነሰ ይሆናል፤ ባለንብረቶቹም “ልማታዊ ቤተሰቦች” ይሆናሉ። ሰማንያ አምስት በመቶው የኢትዮጵያ ህዝብ በግብርና የቀን ሥራ የሚተዳደር ይሆናል።
ምን ቢደረግ ይበጃል?
ከዚህ ጥያቄ በፊት መመለስ የሚኖርበት ሌላ ዓብይ ጥያቄ አለ። እኛ ራሳችን ማን ነንና ነው ይህን ጥያቄ የምናነሳው? በእርግጥ ሀገራችን የኛ ናትን? ይህ ጥያቄ ሳንመለስ ምን እንደሚበጀን መነጋገር ተግባራዊ ፋይዳ የለውም። በመጀመሪያ ሀገራችንን እናስመልስ። ከዚያ በኋላ ምን ማድረግ እንዳለብን እንመካከራለን። First things first ይባላል። የትራስፎርሜሽን መዝሙር ሳያዘናጋን ትኩረታችን ራሳችንን የሀገራችን ሙሉ ዜጎች በማድረግ ሥራ ላይ ይሁን እላለሁ።
ቸር እንሰብት!
ታደሰ ብሩ
(መስከረም 2003)



